ሦስተኛው ‹ዙር› ጦርነትና መደገም የሌለባቸው ስህተቶች!

0
1709

ብሰላም አብዝታ ስትፈለግ አብዝታ እየሸሸች እስኪመስል፤ ለሰላምና ድርድር የተሰጡ ተስፋዎች ሁሉ ዳመና ለብሰዋል። የሰላም ሚኒስቴር መቋቋሙ፣ አገር ሽማግሌዎች መለመናቸው፣ እናቶች በእንባ መማጸናቸው፣ የሕጻናት ለቅሶና መከራ ሰላምን ሊያመጣ አልቻለም። ይልቁንም አሁንም በሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል ለአምስት ወራት አረፍ ብሎ የነበረው ጦርነት አገርሽቷል። ዜጎች አንድም ችግሩ ቀርቧቸው አንድም በስጋት የተነሳ ቀደም ብለው ከየመኖሪያቸው እየተፈናቀሉ ነው። ንብረት እየተዘረፈ፣ ሴቶችና ሕጻናትም ከባዱን መከራ ከፊታቸው እየጠበቁ በጭንቀት ውስጥ ይገኛሉ።

መንግሥት ለዜጎቹ ደኅንነት ቅድሚያ በመስጠት እሳቤ፣ ከዚህ ቀደም ከነበሩ እንቅስቃሴዎች በመነሳት አሁን ምን እርማቶችን ሊያደርግ ይችላል? የአዲስ ማለዳዋ ሊድያ ተስፋዬ ይህን ጥያቄ በማንሳት ባለሞያ በማናገር፣ እንዲሁም የቀደሙ ዘገባዎችን በማገላበጥ ጉዳዩን የሐተታ ዘ ማለዳ ርዕሰ ጉዳይ አድርጋዋለች።

ለመግቢያ

የሰላም ያለህ ቢባልም ሰላም ደጅ እያስጠና ይገኛል። ኢትዮጵያ አብዝታ ተስፋ ያደረገችው የሰላም መንገድ ጥርጊያ የሆነው ድርድር ከቀናት በፊት ለሦስተኛ ጊዜ በተጀመረው ጦርነት የተነሳ አመድ ለብሷል። ‹ታሪካችን ሁሉ የጦርነት ነው› ብለው የቀደመውን ዘመን ይኮንኑ የነበሩ ሁሉ አዲስ የጦርነት ታሪክን በወጣቶች ደምና አጥንት እየጻፉ ይገኛሉ። በዚህም ዳፋው የማይደርሰው አንድም እንኳ ኢትዮጵያዊ እንደሌለ እሙን ነው።

በሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎችን ሕይወት የቀጠፈው በሚሊዮን የሚቆጠሩትን ደግሞ ለመፈናቀልና ለእንግልት የዳረገው የሰሜኑ ጦርነት ለሦስተኛ ጊዜ አገርሽቷል። የፈረሱት ሳይጠገኑ፣ በአካልም በአእምሮም በብዙ የታመሙት ሳይድኑ ነው ጦርነቱ የተነሳው። ብዙዎችም የሰላም ድርድር ደጋግመው የሚሰሙት ጉዳይ መሆኑን ተከትሎ ሰላም ይመጣል ብለው በጉጉት ሲጠብቁ የነበሩ ናቸው።

ነገር ግን አልሆነም። እንዳይመለስ የተፈራው ጦርነት የተከሰተ ሲሆን፣ ብዙዎችም ይህን ሽሽትና እያንሰራራ የነበረውን ተስፋቸውን ለመጠበቅ ቀደም ብለው ከየቀዬአቸው ለቅቆ መውጣቱን የመረጡ ይመስላል። ‹ሰላም ወደየት ትገኛለች?› ብለው እየጠየቁም ሰላምን ፍለጋ የወጡ ብዙዎች ናቸው።

ምልሰት

ጥቅምት 24/2013 ፤ ማምሻው ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በኢትዮጵያ ቴሌቭዥን መስኮት ብቅ ብለው አስደንጋጭ የሆነ መረጃን ለሕዝብ አደረሱ። በዛን እለቱ ማምሻውን በሠሜን ዕዝ የሚገኘው የአገር መከላከያ ሠራዊት ከመቀሌ ጀምሮ በበርካታ ስፍራዎች ጥቃት እንደተፈፀመበት አስታወቁ።

በዛም መግለጫቸው ላይ ‹‹ጥቃቱ በአገራችን እስካሁን ከደረሱ ጥቃቶች እጅግ አስነዋሪ ነው። ሰላም ለማስከበር በተለያየ አገር የተሰማራው የመከላከያ ሠራዊት በውጭ ኃይሎች እንኳን ያልደረሰበት ጥቃት በገዛ ወገኖቹ ከጀርባው እንዲመታ ተደርጓል›› አሉ። በተፈጸመው ጥቃትም ብዙዎች የሠራዊቱ አባላት መሰዋታቸውን፣ መቁሰላቸውን፣ ንብረቶች መውደማቸውን ገለጹ።

ጥቅምት 25/2013 ፤ የሚኒስትሮች ምክር ቤት በትግራይ ክልል የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አወጀ። ይህም አዋጅ ለስድስት ወራት ተፈጻሚ ይሆናል ተባለ። ይህን የሚያስፈፅም ተጠሪነቱ ለኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር የሆነ፣ ‹የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ግብረኃይል› ተብሎ የሚጠራ ኃይል ተቋቋመ።

በዚሁ እለት የሃይማኖት አባቶች የእርስ በእርስ ግጭቱ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ እንዲቆም ጠይቀዋል። እንዲሁም ከጥቅምት 26/2013 ጀምሮ ለአንድ ሳምንት የሚቆይ ጸሎት እና ምህላ በሁሉም እምነት ተቋማት እንደየ እምነት ስርዓቱ ይከናወን ተባለ።

ጥቅምት 27/2013 ፤ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በትዊተር ገጻቸው ባስተላለፉት መልዕክት የሕገ መንግሥቱን አንቀጽ 51 በመጥቀስ የፌዴራል መንግሥት ሕገመንግሥቱን ያስከብራል። እንዲሁም መከላከያ ሠራዊቱ ላይ ጥቃት በፈጸመው ቡድን ላይ የሕግ የበላይነትን ለማስከበር እርምጃዎችን ይወስዳል አሉ። ይህም ‹የሕግ ማስከበር› ዘመቻ መጀመሩን አሳወቀ።

ኅዳር 19/2013 ፤ በትግራይ ክልል ሲካሄድ የነበረው የሕግ ማስከበር ዘመቻ መጠናቀቁ ተገለጸ። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለፓርላማው በትግራይ የሚካሄደው የሕግ ማስበር ዘመቻ መጠናቀቁንና መቀሌ በቁጥጥር ስር መሆኗን ገለጹ።

ሰኔ 28/2013 ፤ የፌዴራል መንግሥት በሰብዓዊነት ላይ የተመሠረተ የተናጠል ተኩስ አቁም አዋጅ ማወጁን አሳወቀ። የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ከመቀለ ለቅቆ መውጣቱ ተገለጸ። የሕወሓት ከፍተኛ አመራር ጌታቸው ረዳም ‹የትግራይ ዋና ከተማ መቀሌ በቁጥጥራችን ስር ነች› ሲሉ ለሮይተርስ ተናገሩ።

ሐምሌ 6/2014 ፤ በአማራ እና ትግራይ ክልል አዋሳኝ አካባቢዎች ላይ ከባድ ውጥረት እንዳለ ሲገለጽ፣ ከሳምንት በኋላ የአማራ ክልል መንግሥት ወረራ ነው ያለውን ጥቃት ለመቀልበስ ከመከላከል ወደ ማጥቃት መሸጋገሩን አሳወቀ። ሕወሓትም በአማራ እና አፋር ክልሎች ወረራ ማድረግ ቀጠለ።

ጥቅምት 4/2014 ፤ ሕወሓት በአማራና አፋር ክልል ያደረሳቸውን ጥፋቶችና ጥቃቶች ተከትሎ መከላከያ ሠራዊት ጥቃቱን የመመከት ውጊያ እያካሄደ መሆኑን ገልጾ፥ መመከት ብቻ ሳይሆን እየደመሰሰ የኢትዮጵያን ደኅንነት እና ህልውና የማስከበር ታሪካዊ ኃላፊነቱን እየተወጣ ነው ሲል በመግለጫ አስታወቀ። ጠቅላይ ሚስትሩም ይህን ዘመቻ የተቀላቀሉ ሲሆን፣ ‹የሕልውና ዘመቻ› በዚህ ጊዜ ጀመረ ተባለ።

መጋቢት 15/2014 ፤ የኢትዮጵያ መንግሥት በድጋሚ ለሰብዓዊነት ሲባል ግጭት ለማቆም ውሳኔ ማሳለፉን አሳወቀ። በወቅቱ በሺዎች የሚቆጠሩ የትግራይ ክልል ነዋሪዎች የሰብዓዊ እርዳታን ፍለጋ ወደ አጎራባች ክልሎች እየተጓዙ መሆኑን አመላክቶ፣ ‹እነዚህ ዜጎች የሰብዓዊ እርዳታው ከቀያቸው ሳይፈናቀሉ ባሉበት እንዲደርሳቸው ቢደረግ እንግልታቸውን እንደሚቀንስ በጽኑ አምናለሁ› ሲል ነው የተናጠል የተኩስ አቁሙን ያወጀው።

ሰኔ 7/2014 ፤ በይፋ የታወቀ አጥኚ ኮሚቴ ተቋቁሞ በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ አማካኝነት እየተመራ እንደሆነና የሚደራደረው ኮሚቴም ይኸው እንደሆነ ይፋ ተደረገ።

ነሐሴ 18/2014 ፤ ሕወሓት በምሥራቅ ግንባር በቢሶበር፣ ዞብል እና ተኩለሽ በኩል ከሌሊት 11 ሰዓት አንስቶ ጥቃት መፈጸሙ ተገለጸ።

ከሕግ ማስከበር እስከ ሕልውና ዘመቻ

ሕወሓት እና የፌዴራል መንግሥት በቃላት መወራወር የጀመሩት፣ በኋላም በሽምግልና እና በሰላም ጥሪ ያልዳኙት ግጭት ዛሬ ላይ ደርሶ ኹለት የሚጠጉ ዓመታት እድሜን አስቆጥሯል። መንግሥት ከጅምሩ በሕግ ማስከበር ዘመቻው ተፈላጊ የሕወሓት ‹ባለሥልጣናትን› ይዞ በጥቂት ቀናት የሚቋጨው ዘመቻ እንደሆነ ጠቅሶ ነበር። ሆኖም ያንን አልፎ የሕልውና ዘመቻ እና አሁንም ለሦስተኛ ጊዜ ውጊያው ሊከሰት ችሏል።

ይህን በሚመለከት ሐሳባቸውን ያካፈሉን የቀድሞ የኢትዮጵያ ሠራዊት የድጋፍና የልማት ማኅበር ሥራ አስኪያጅና የወታደራዊ ደኅንነት ባለሙያ ሻለቃ ታመነ አባተ ናቸው። ‹‹ሕወሓት በምንም መልኩ ከስህተቱ የሚማር ድርጅት አይደለም›› ሲሉ ነው ንግግራቸውን የጀመሩት። ይህንንም በሕግ ማስከበሩ እንዲሁም በሕልውና ዘመቻው ላይ ማየት ተችሏል ብለዋል። እንደውም መንግሥት ብዙውን ጊዜ ሆደ ሰፊ ሆኖ፣ ወደኋላ በመመለስ ሰላም ይወርዳል በሚል ብዙ ጥረቶችን አድርጓል ባይ ናቸው።

‹‹ነገር ግን ሕወሓት ከአሁን በፊት ለ17 ዓመት ያህል ስንዋጋ ጸባዩን ጠንቅቀን እናውቃለን። ሁልጊዜ ሽንፈት ሲደርስበት ሽንፈቱን ማካካሻ የሚሆን ምክንያት ይፈጥርና የሚደራጅበት፣ የሚዘጋጅበትና ኃይሉን የሚያጠናክርበትን ጊዜ ይገዛል።›› ሲሉ ገልጸዉታል።

ይህን ሲያነሱም ከላይ በምልሰት ያወሳናቸውን መንግሥት በተናጠል ኹለት ጊዜ ያደረጋቸውን የተናጥል ተኩስ የማቆም ውሳኔን ጠቅሰው ነው። ይህም ምንም ውጤት ያመጣ እንዳልሆነና እንደውም ሕወሓት ይህን የተኩስ ማቆም ስምምነት እና ሰላም ድርድሩን አጣምሮ በመያዝ ለራሱ የሚዘጋጅበት ጊዜ አደረገው ይላሉ። ‹‹እንጂ [ሕወሓት] በምንም መስፈርት ሰላም ለመፈለግ፣ ለኢትዮጵያ እድገትና ሰላም እንዲመጣ አስቦና አቅዶ የተዘጋጀ አይደለም›› ብለዋል።

ከዚህ ቀደምም ከአዲስ ማለዳ የአንደበት አምድ ጋር ቆይታ ያደረጉት ሻለቃ ታመነ፣ ጥንቃቄዎች ካልተደረጉ ለሦስተኛ ጊዜ ጦርነቱ ሊነሳ እንደሚችል ስጋታቸውን ሲገልጹና ሲያሳስቡ ነበር።

‹‹ለዚህ [ሕወሓት ለዝግጅት ጊዜ ሲገዛ እንደነበር] እቅድ ማረጋገጫ የሚሆው መንግሥት የሰላም ተደራዳሪዎች በግልጽ ሲያሳውቅ፣ ሕወሓት ግን ተደራዳሪዎቼን ለማሳወቅ ፈቃደኛ አይደለሁም ማለቱ ነው። ይህ ማለት ድርድሩን እንደማይፈልግ መቶ በመቶ የሚሳይ ፍንጭ ነው። ይህን መንግሥት የሚያጣው አይመስለኝም።›› ሲሉም ዕይታቸውን አጋርተዋል።

ተጠባቂ እርማቶች!

ሻለቃ ታመነ ሲናገሩ፣ መንግሥት በሕግ ማስከበሩ እንዲሁም ከሕልውና ዘመቻው ትምህርት ወስዷል ብለው እንደሚያምኑ ጠቅሰዋል። አሁን ያለውን ሁኔታም አውስተው፤ ከብዙ የሰላም ጥሪ እና መለማመን በኋላም ሕወሓት በየአቅጣጫው ትንኮሳ ካደረገ በኋላ ውጊያ መክፈቱን ጠቅሰዋል። ‹‹እንደ ወታደር አባልነቴ እንዲሁም እንደ ወታደር ሳይንሱ በመንግሥት በኩል ከአሁን በኋላ ነካ መለስ የሚባል ነገር ሊኖር አይገባም የሚል አቋም ነው ያለኝ።›› ብለዋል።

ይህን ያሉት ከትግራይ ክልል ወይም በትግራይ ሕዝብ ላይ አለመሆኑን አጥብቀው ያስረዱት ሻለቃ ታመነ፣ የትግራይ ሕዝብ ራሱ በመሣሪያ ስር ሆኖ መተንፈስ ያቃተውና ባገኘው ቀዳዳ ለመተንፈስ ሲሞከር እየሞተ ያለ ነው ብለዋል። ‹‹ስለዚህ እነዚህን በቁጥር 20 እና 30 የማይበልጡ የሕወሓት አመራሮች፤ አንድም ተደምስሰው አልያም ተይዘው ለሕዝብ መታየት መቻል አለበት።›› ሲሉ አሳስበዋል።

ይህ ሳይሆን ግን ነካ መለስ የሚደረግ የውጊያ ስልት ጉዳት ከማስከተሉ ባለፈ ያመጣው ውጤት እንደሌለም ነው የገለጹት። በዚህም ሁሉም የበኩሉን ድርሻ እንዲወጣ ጥሪ አስተላልፈዋል። በበኩላቸውም፣ የኢትዮጵያ ሠራዊት የድጋፍና የልማት ማኅበር ከአሁን ቀደም ሲያደርግ እንደነበረውና ከዛም በላይ፣ በማሠልጠን፣ በግንባር በመሳተፍ ብሎም በገንዘብም አስተዋጽኦ ለማድረግ ዝግጁ መሆኑን አስታውቀዋል።

‹‹መንግሥት መለስ ቀለስ የማለት ነገሩን ትቶ ሙሉ የማጥቃት ኃይሉን ተጠቅሞ ወታደራዊ ሂደቱን አጠናክሮ እነዚህን ሰዎች ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ከትግራይና ከኢትዮጵያ ትከሻ ሊያወርዳቸው ይገባል የሚል እምነት ነው ያለኝ።›› ሲሉም ሐሳባቸውን አካፍለዋል።

በበኩላቸው መታረም አለበት ያሉት በመንግሥት በኩል የሚታየውን አካሄድ ነው። በዚህም ሄድ መለስ ማለት ተገቢ እንዳልሆነ ሻለቃ አሳስበዋል። ‹‹ወታደራዊ ኃይሉ አንዳንድ ሁኔታዎች ላይ እኛ እንደምናስበው አይደለም የሚወስነው። ለምሳሌ መከላከያ ሠራዊት ቆቦ ላይ ነበር። በቆቦ መቆየቱ ጉዳት የሚያመጣ ሆኖ ስትራቴጂክ ቦታዎች ቀይሮ መያዝ አስፈላጊ ሆኖ ከተገኘና ውጤት የሚመጣ ከሆነ፣ ያንን መጠቀም ይችላል።›› አሉ።

ይልቁንም ‹ሄድ መለስ› ያሉት፤ መንግሥት ለሕዝብ ጥቅም ሲል፣ የትግራይ ሕዝብ አደጋ እንዳይደርስበትና ገበሬም እንዲያርስ ሲባል ከዚህ በፊት የተከፈለውን መስዋዕትነት በማንሳት ነው። ይህን መነሻ በማድረግ የተደረገ የተናጠል ተኩስ አቁም ለሕወሓት የመዘጋጃ ጊዜ የሰጠ መሆኑን አንስተው፣ ‹‹የዛን ዓይነት ተመሳሳይ ነገር አሁን ሊደገም አይገባም›› ብለዋል።

‹‹ውጊያ ተከፍቷል፤ የሰላሙን መንገድ  አጥፍተዋል። ሰላሙን እንደ ፍርሀት ቆጥረውታል። የትግራይ ሕዝብም ለራሱ ሲል እነዚህን ሰዎች ከትከሻው ላይ ማውረድ አለበት። ቁጭ ብሎ እህሉን፣ ነዳጁን እየቀሙት ነው። ቁጭ ብሎ ሞትን መጠበቅ የለበትም። ተፋልሞ ከራሱ ላይ ማውረድ አለበት።›› ሲሉ መክረዋል።

ሥማቸው እንዲጠቀስ ያልፈቀዱ የደኅንነት ባለሞያ ለአዲስ ማለዳ እንደገለጹት፣ የመረጃ ልውውጥና ለሕዝብ የሚደርስ መረጃ ላይ ከወዲሁ ጥንቃቄ ሊደረግ እንደሚገባ አሳስበዋል። ከዚህ ቀደም በነበረው የሕግ ማስከበርም ሆነ የሕልውና ዘመቻ የነበረውን ክፍተት በማውሳት፣ ዓለም ዐቀፍ የሆነውን ጫና ለመቋቋምናነ የሚወጡ መረጃዎች በማጥራት መንግሥት ፈጣን እርምጃዎችን ሊወስድ እንደሚገባ አሳስበዋል።

አሁን ላይ በመንግሥት ኮምዩኒኬሽን በየጊዜው የሚሰጠው መግለጫ ከቀደመው በተሻለ ለጉዳዩ ትኩረት እንደተሰጠ ማሳያ መሆኑን አንስተው፤ ነገር ግን አሁንም ብዙ መሠራት እንደሚጠበቅ ነው የገለጹት። ‹‹ይህ ከተማ ተለቀቀ፣ እዚህ ከተማ የወገን ጦር ገባ፤ እዛኛው አካባቢ የሕወሓት ኃይል ያዘ› የሚሉ መረጃዎች ሲወጡ እንሰማለን። መደበኛ መገናኛ ብዙኀኑ ለእነዚህ ፈጣን ምላሽ ካልሰጠ ማኅበራዊ ሚድያው ላይ የሚወጣው መረጃ ሁሉ እውነት ስለሚመስል ሕዝብን ሊያሳስት ይችላል።›› ብለዋል።

በወልድያ እና በሌሎችም ከተሞች በነዋሪዎችና ባንኮችን ጨምሮ በንግድ ቤቶች ቀድመው የተወሰዱ እርምጃዎችን ጠቅሰውም፤ ይህ ችግሩን እንደሚያባብስና ክፍተትን እንደሚፈጥር ገልጸዋል። እናም በመንግሥት በኩል በሕዝብ መታወቃቸው ለውጥ ከማያመጡና ምስጢራዊ ከሆኑ ጉዳዮች ውጪ ያለውን ሁኔታ በግልጽ ማሳወቁ ላይ እንደሚያተኩር ሲሉ የደኅንነት ባለሞያው ምክረ ሐሳባቸውን ሰጥተዋል።

በመንግሥት በኩል ብቻ ሳይሆን ሕዝብም የሚወጣውን መረጃ በስሜታዊነት ከመቀባበልና በፍጥነት ከማመን በፊት ሊያገናዝብና ሊያመዛዝን እንደሚገባ ተናግረዋል። ‹‹ይህ መረጃ ለማን ይጠቅማል? እውነተኛ ነው ወይ? እውነተኛ ሆነም አልሆነ፣ ጥቅሙ ምንድን ነው? የመረጃ ምንጬስ ማን ነው? የሚሉ ጥያቄዎችን ማንሳት ከማኅበረሰቡ ይጠበቃል።›› ብለዋል።

የተገኘ ሁሉ ወደ አፍ እንደማይላከው ሁሉ፣ ሰዎች የሰሙትን መረጃ ለራሳቸው ከመውሰዳቸውም ሆነ ለሌሎች ከማስተላለፋቸው በፊት ማስተዋልና ደጋግመው መጠየቅ አለባቸው ብለዋል። በሕዝቡ ዘንድ መረጃን ማጣራት ሲኖርና በመንግሥትም በኩል ትክክለኛ መረጃዎችን የማድረስ ልምድ ሲኖር፤ በመንግሥትና በሕዝብ መካከል በጉዳዩ ላይ መተማመን ሲያኖር፤ መንግሥትም ከተጨማሪ የቤት ሥራ ይድናል ሲሉ ዕይታቸውን አካፍለዋል።

ሻለቃ ታመነም በዚህ ሐሳብ ይስማማሉ። መስተካከል አለበት፣ እርማት ሊወሰድበት ይገባል፣ መፍትሄም ለማግኘት ያግዛል ያሉት ከመረጃ ስርጭት ጋር በተያያዘ ያለውን ጉዳይ ነው።

‹‹በመጀመሪያ ደረጃ መንግሥት እንደ መንግሥት ወቅታዊ መረጃዎችን ቶሎ ለሕዝብ ማሳወቅ አለበት። ኹለተኛ በፍጥነት ማሳወቅ ባይችል እንኳ የውስጥና የውጪ ሚድያዎች ያልሆነ ነገር ሲናገሩ ወዲያውኑ ማፍረሻን ማቅረብ መቻል አለበት።›› ብለዋል።

አያይዘውም፣ ‹‹ማኅበረሰባችን የዋህነቱን ማቆም አለበት። ከፌስቡክ ጋር የሚያደርገውን ወዳጅነት ሊያቆም ይገባል። ይህ የአገር ሉዓላዊነትና የሕዝብ ደኅንነት ጉዳይ ነው። እየሞትን ፌስቡክ የምናነብ ከሆነ እየሞትን እያለ የሚናፈሰውን ሁሉ እውነት ነው ብለን የምናስተጋባና ምዕራባዊያን የሚያወሩትን ዜና ተቀብለን የምናባዛ ከሆነ፣ በራሳችንና በሕልውናችን ላይ እየተጫወትን መሆናችን ማወቅ አለብን።›› ሲሉም መልዕክታቸውን ለሕዝብ አድርሰዋል።

ነባራዊ ሁኔታ

የሕግ ማስከበር እንዲሁም የሕልውና ዘመቻው አንደኛ እና ኹለተኛ ተብለው፤ አሁን የተቀሰቀሰው ጦርነት ሦስተኛ ዙር እየተባለ ይገኛል። ታድያ በዚህ ነሐሴ 18/2014 በጀመረውና ከአንድ ሳምንት የራቀ እድሜ ባላስቆጠረው ሦስተኛው ዙር ጦርነት፣ በየእለቱ አዳዲስ ዜናዎች እየወጡ ይሰማል።

አዲስ ማለዳ ይህን የሐተታ ዘ ማለዳ ጥንቅር በምታዘጋጅበት ሰዓት ወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ከፌዴራል መንግሥት መግለጫ ወጥቷል። በዚህም ነሐሴ 26/2014 ሕወሐት ወረራውን እያስፋፋ መሆኑ ተጠቅሶ፣ በዚህም ንጹሐን እየተገደሉ፣ ሕዝብ እየተፈናቀለ፣ ንብረትም እየወደመ ነው ተብሏል።

በተያያዘም፣ መንግሥት ቅሬታውን ያቀረበ ሲሆን፣ ‹‹በሕወሓት ቡድን እየደረሱ የሚገኙ ጥፋቶችን ለማስቆም ለሰላማዊ  አማራጭ እየተደረጉ ያሉ ጥረቶች ሁሉ እየመከኑ ባሉበት ሁኔታ፣ ሕወሓትን መጫን ሲገባቸው ‹ኹለቱም ወገኖች› በሚል የሚወጡ መግለጫዎች ከእውነታው ያፈነገጡ ስለሆነ ተቀባይነት የላቸውም›› ብሏል።

በተጓዳኝ የኢትዮጵያ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን አሁንም የሰላም በሮች ክፍት መሆናቸውን አሳውቀዋል። ነገር ግን ከዛው ጎን ለጎን መንግሥት የአገሪቱን ሉዓላዊነት ለማስከበር በሕወሓት ላይ የትኛውንም ዓይነት እርምጃ ለመውሰድ እንደሚገደድ አስታውቀዋል። ይህንንም የገለጹት ለአምባሳደሮችና የዓለም ዐቀፍ ተቋማት መሪዎች በሰጡት ማብራሪያ ነው።


ቅጽ 4 ቁጥር 200 ነሐሴ 28 2014

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here