የኖቤል ሽልማቱ የለውጥ ማንቂያ ደወል ይሁን!

0
717

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ወደ ሥልጣን በመጡበት ሰሞን ሲደራረብ የነበረው የፈንጠዚያ ዶፍ ለተወሰነ ጊዜ በተለያዩ የሃገሪቱ ክፍሎች በተከሰቱ ግጭቶች እና በልዩ ልዩ የፖለቲካ ጡዘቶች ተቀዛቅዞ ቢቆይም ከሰሞኑ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ባገኙት የኖቤል ሽልማት ተመልሶ የመጣ ይመስላል።

ጠቅላይ ሚኒሰትሩ የሚመሩት ቡድን ወደ ፊት ከመጣ ወዲህ በተለይም በዐቢይ ጥረት የተመለሰው የኢትዮ ኤርትራ የሰላም ስምምነት አንዱ የፈንጠዚ ምክንያት ነበር። የኹለቱ መሪዎች ተግባር ኹለቱን ወንድማማች ሕዝቦች ከማስደሰት አልፎ ሃገራቱን በዓለም ዐቀፉ ማህበረሰብ ዐይን የከተተ ሂደትም ነበር።

ይህንንም የሰላም ሂደት ምክንያት በማድረግ ጅምላ ጨራሽ የሆነውን እና በተለያዩ የጦር አውድማዎች ብዙዎችን የጨረሰውን ድማሚት ፈንጂ በመፍጠሩ በመፀፀት ሙሉ ሃብቱን የኖቤል ሽልማት ማቋቋሚያ ያደረገው አልፍሬድ ኖቤል የቀረፀውን የሰላም ሽልማት የኢትዮጵያው መሪ ዐቢይ አሕመድ እንዲወስዱ ምክንያት ሆኗል።

እርግጥ የኹለቱ ጎረቤት ሃገራት መሪዎች ለፈጠሩት ሰላም እውቅና ይገባቸዋል። በተጨማሪም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በሱዳን ወታደራዊ መሪዎች እና የሲቪል ፖለቲከኞች መካከል የተፈጠረውን ክፍተት በመሙላት ጥምር ሽግግር መንግሥት እንዲቋቋም በማድረግ በሱዳናዊያን ጭምር ከፍተኛ ምስጋና እንዲቸራቸው ምክንያት ሆኗል። እንዲሁም በጅቡቲ እና በኤርትራ መካከል ለዘመናት የነበረው ቁርሾ እንዲፈታ በማድረግ፣ ኬንያ እና ሶማሊያ መካከል የነበረውን ግጭት በማርገብ ጊዜአዊ ሰላም እንዲፈጠር ባደረጉት ሙከራም ለቀጠናው መረጋጋት ከፍተና ሚና ተጫውተዋል።

በሃገር ውስጥም ቢሆን ከፓርቲ አጋሮቻቸው ጋር በመሆን የፖለቲካ እስረኞች፣ ጋዜጠኞች እና የሰብአዊ መብት ተሟጋቾችም ከእስር እንዲፈቱ በማድረግ የራሳቸውን ሚና ተጫውተዋል። የሚዲያ ሳንሱር እንዲቆም፣ ሥልጣንን ያለ አግባባብ በመጠቀም ሕገ ወጥ ተግባራትን ሲፈጽሙ የነበሩ አካላት ወደ ፍርድ እንዲቀርቡ እና ሴቶችም ቢያንስ በከፍተኛ የአመራር ቦታዎች ከግማሽ በላይ የሥልጣን ወንበር እንዲይዙ ያደረጓቸው ተግባራትም የሚታወሱ ናቸው።

ታዲያ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያመጧቸው መልካም ጅምሮች ማለቂያ በሌላቸው ችግሮች ታጅበው እየታዩ ነው። ከእነዚህም መካከል ሽልማቱን ያገኙበት የኢትዮ ኤርትራ ጉዳይ የሚጠቀስ ነው። በኹሎቱ ሃገራት መካከል ሰላም እንዲሰፍን አንዱ ምክንያት የሆኑት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሥልጣን ከያዙ በኋላ የአልጀርስ ስምምነትን እንደሚያከብሩ እና እንደሚያስፈጽሙ ቃል ቢገቡም ተፈፃሚ ግን አልሆነም።

የተባበሩት መንግሥታት ገለልተኛ ኮሚሽን በ1994 ያወጣውን ድንበር ማካለል ሪፖርት ኢትዮጵያ ብትቀበልም፤ ይቅርና የድንበር ማካለል ሥራውን መተግበር ለተወሰነ ጊዜ ክፍት ተደርገው የነበሩ አራቱ የአገራቱ ድንበሮች ተዘግተው ስምምነቱም ባለበት ቦታ ቆሞ ይገኛል። ለድንበሩ መዘጋትም፣ በአገራቱ መካከል ስላለው ንግድ ወይም ኹለትዮሽ ግንኙነት ግልፅ ማብራሪያ ከኹለቱም ወገን ሳይሰጥ በዝምታ ላይ ይገኛል።

በሑለቱ ሃገራት መካከል ያለውን የመንገድ፣ የትራንስፖርት እና የውጪ ምንዛሬ ጉዳይ ስምምነት ለማካሄድ የኢትዮጵያ መንግሥት ዝርዝር ጥናት በማካሄድ በውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር በኩል ምክረ ሃሳቡን ቢልክም እስከ አሁን መልስ አልተገኘለትም።

ሌላው ለስምምነቱ መሻከር ዋነኛ ማሳያ ከሚባሉ ምልክቶች መካከል ከመላው ዓለም የእንኳን ደስ አላችሁ መልእክት ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ቢላክም ሽልማቱ የሚመለከተው የኤርትራ መንግሥት እስከ አሁን ይፋዊ መግለጫ ከማውጣት ተቆጥቧል።

በሃገር ውስጥ ጉዳይም የተለያዩ የሕግ ማሻሻያዎችን፣ ፖለቲካ ምህዳሩን ማስፋት እና የሰብአዊ መብት ማክበር ላይ የተለያዩ ለውጦች ቢታዩም ማንነትን መሰረት ያደረጉ ግጭቶች ተባብሰዋል። በክልላዊ መንግሥታት መካከል ያለው አለመስማማት፣ አለመተማመን እና መተነኳኮስ ተቀጣጥሏል።

ሕዝብ መንግሥት ላይ ያለው እምነት ተሸርሽሮ በተለይም ከመንግሥት በቀዳሚነት የሚጠብቀውን የሕግ የበላይነትን ባለማግኘት እብሪተኝነት እና ማን አለብኝነት የእለት ተእለት ትዕይንት ሆኗል። ሰበብ እየደፈለጉ በመጋጨት፣ መሰረተ ልማት ላይ ጉዳት ማድረስ፣ የእምነት ተቋማትን ማውደም፣ ሴቶችን እና አቅመ ደካሞችን እንኳን ሳይለዩ የደቦ ፍርዶችን መስጠት እና የመንቀሳቀስ መብትን ጨምሮ የተለያዩ መብቶች በግለሰቦች ሲነፈጉ መመልከት እና የፀጥታ ተቋሙም የዚህ ተባባሪ አንዳንዴም አስተባባሪ መሆኑ ዜጎችን ስጋት ውስጥ የጣለ አድርጎታል።

ይህ ብቻ ሳይሆን በክልልች መካከል የጋራ መስማማት ያለመፈጠሩ እና እንደ ሃገር የሚያስተሳስሩንን ገመድ በማላላት ለንፁሃን መሞት እና መንገላታት ምክንያት ሆኗል።

ታዲያ ይህ ሁሉ ተደማምሮ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ሽልማት የሃገሪቱን እና ቀጠናውን የሰላም ሁኔታ ዋስትና የማይሰጥ ለመሆኑ አመላካች ነው። ዐቢይ አሕመድም ከዚህ ቀደም የኖቤል ሽልማት አሸንፈው ከነበሩት የማይናማሯ መሪ ኡንግ ሳን ሱ ኪ ሊማሩ ይገባል። መሪዋ ሽልማቱን ባሸነፉበት ወቅት በሃገራቸው የነበረውን አምባገነናዊ ስርዓት በመቃወም ለከፈሉት ዋጋ እውቅና ቢቸራቸውም በሮሂንጋ ላይ በተፈፀመው ዘር ማፅዳት ዘመቻ ላይ ትእዛዝ በመስጠት እንዲሁም እንዳላዩ በማለፋቸው ዓለም ሽልማታቸውን እንዲቀሙ ዘመቻ እንደከፈተባቸው ይታወሳል።

በኢትዮጵያ የሚካሄደውን ምርጫ ተከትሎ የሃገሪቱ ፖለቲካ እና የግጭት ነጋዴዎች ሊጠቀሙበት ይችላል የሚል ስጋት ይታያል። ስለዚህም የኖቤል የሰለም ሎሬት የሆኑት ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሕግ የበላይነትን ማረጋጋጥ ይገባቸዋል። የዜጎችን ደኅንነት ሁኔታ ማረጋገጥ እና በክልሎች መካከል ያለውን ውጥረት በሕዝቦች መካከል በሚደረግ ውይይት መፍታት ያስፈልጋል።

በተመሳሳይም በገዢው ፓርቲ ውስጥ የሚታየውን ውጥረት በማርገብ እና ሃገርን ከፓርቲ በመነጠል በፉክክር ኢትዮጵያን እና ኢትዮጵያዊያንን ከገቡበት ጭንቀት ማውጣት አለበት። ከኤርትራ ጋር ያለውን የሰላም ስምምነት ጉዞም ከጥቂት ሰዎች ድርድር ወደ ተቋማዊ መሰረት በማሸጋገር የተቀበሉትን ሽልማት የሚመጥን ሥራ እንዲሰሩ አዲስ ማለዳ ታሳስባለች።

ቅጽ 1 ቁጥር 50 ጥቅምት 8 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here