ያልተደራጁና ሕጋዊ እውቅና የሌላቸው ቡድንና ግለሰቦች ለሥራቸው እንቅፋት እንደሆኑባቸው በአዲስ አበባ ከተማ የሚገኙ ጫኝና አውራጅ ድርጅቶች ለአዲስ ማለዳ አስታወቁ።
ከስድስት ዓመታት በላይ በመስኩ የሠራው የፓክ አዲስ (Pack Addis) ባለቤት ሀቢብ አበራ ለአዲስ ማለዳ እንዳስታወቁት፣ ፍቃድ የሌላቸውና በየሰፈሩ ራሳቸውን አደራጅተው የጫኝና አውራጅነት ሥራን እንሠራለን የሚሉ ቡድኖች ለሥራቸው እንቅፋት ሆነውባቸዋል። የመኪና መስታወት መስበርን ያካተተ አካላዊ ጥቃቶችንም በእነዚሁ ቡድኖች አስተናግደዋል።
በደንበኞቻቸው ጥያቄ መሠረት አገልገሎታቸውን ለማቅረብ በሚንቀሳቀሱባቸው ቦታዎች ችግሮች ሲያጋጥሟቸው የፖሊስን እርዳታ እንደሚጠይቁና በየአካባቢው ካሉ ፖሊሶች ጋር በትብብር እንደሚሠሩ የሚናገሩት ሀቢብ፣ ደንበኞቻቸውም እነዚህን ወጣቶች በመፍራት ሥራውን ለወጣቶቹ የሚሰጡበት ጊዜም እንዳለ ተናግረዋል።
ለአስራ አምስት ዓመታት አገልግሎት የሰጠው የኢዚ ሙቨርስ (Easy Movers) ዋና ሥራ አስኪያጅ ፍሬው አማረ፣ ‹‹ሙያውን እንደ ሙያ ከማስከበር አንጻርም የእነዚሁ ቡድኖች እንቅስቃሴ ከፍተኛ ተጽዕኖ አለው። የጫኝና አውራጅ እንዲሁም የእቃ ማጓጓዝ ሥራ ከፍተኛ ሥነምግባርና እምነት የሚጠይቅ ሥራ እንደመሆኑ ሥራውን ብቁ ሆኖ መሥራት ያስፈልጋል›› ብለዋል። በዘርፉ በቂ የሥራ እድል እንዳለ የሚያስረዱት ፍሬው፣ ሕጋዊና አግባብነት ባለው መልኩ በትብብር ቢሠራ ሁሉንም አካላት ማሳተፍ እንደሚቻል ተናግረዋል።
ከደንበኞች ጋር ሲዋዋሉ በቅድሚያ ለአካባቢው እንግዳ እንደሆኑና በእነዚሁ ቡድኖች ምክንያት ለሚፈጠሩ መስተጓጎሎች ኃላፊነት እንደማይወስዱ ለደንበኞቻቸው ማስረዳት ግድ እንደሆነባቸው ተናግረዋል። ሥራ ለመሥራት በሚንቀሳቀሱባቸው ቦታዎችም ‹ከእኛ ውጭ ይሄን ሥራ የሚሠራው የለም። ለሻይ ካልሰጣቸሁን መሥራት አትችሉም›› የሚሉና መሰል ሌሎች ምክንያቶችን በመዘርዘር አላሠራ እንደሚሏቸው አስረድተዋል። አብሮ ለመሥራት በሞከሩባቸው ጊዜያትም ስርቆቶች እንደሚያጋጥሟቸውና የተጋነኑ ክፍያዎችንም እንደሚጠየቁ ገልጸዋል።
ሁሉም ቦታ የሚያጋጥሟቸው ቡድኖች እንዲህ ናቸው ብሎ ለማጠቃለል ቢያስቸግርም፤ አብዛኞቹ ግን ተመሳሳይ ባህሪ እንዳላቸው የሚያወሱት ፍሬው፣ ወጣቶቹ በአግባቡ ቢሠሩ ለእነሱም መልካም እንደሚሆን ተናግረዋል። በጭቅጭቅና አለመግባባት በሚያልፉ ሰዓቶች ምክንያት በደንበኞች ላይ አላስፈላጊ የዋጋ ጭማሪዎችን፣ በድርጅታቸውም ላይ አላስፈላጊ ኪሳራዎችን እንደሚያመጣ ተናግረዋል።
አያይዘውም ወጣቶቹ በሕጋዊ መንገድ ተደራጅተውና አስፈላጊውን ሥልጠና ወስድው ወደ ሥራው ቢሰማሩ እንደነሱ ያሉ ድርጅቶችም ተጠቃሚ እንደሚሆኑ አስረድተዋል። የቀጠሯቸውን ሠራተኞች ወደ ሥራ ቦታ ለመውሰድ የትራንሰፖርት ወጪ እንደሚያወጡ፣ ይሁንና በየሰፈሩ ያሉ ወጣቶች በአግባቡ ተደራጅተው ቢሠሩ ግን ሠራተኞችን ከቦታ ቦታ ማንቀሳቀስ ሳይጠበቅባችው ከወጣቶቹ ጋር አብረው መሥራት እንደሚችሉም ገልፀዋል።
ምንም ዓይነት ሕጋዊ ማስረጃ ከማያቀርቡት ቡድኖች በተጨማሪ፣ ‹የተደራጀንበት ነው!› በማለት የታሸገ ደብዳቤ የሚይዙም እንዳሉና ደብዳቤውን ማን እንደሰጣቸው ማወቅ እንዳልቻሉ የተናገሩት ፍሬው፣ ማንነታቸው ታውቆ በትክክለኛ መንገድ ቢደራጁ ችግሩ ሊፈታ እንደሚችል ያላቸውን ተስፋ ገልጸዋል።
በአዲስ አበባ የጋራ መኖሪያ ቤቶች፣ ሪል እስቴቶችና የማኅበር ቤቶች በብዛት በሚገኙባቸው እንደ ቡልቡላ፣ ጣፎ፣ ቱሉዲምቱ እንዲሁም ኃይሌ ጋርመንትን በመሳሰሉ ሰፈሮች ከጫኝና አውራጅ ቡድኖች ጋር በተያያዘ ተደጋጋሚ ምሬቶችን መስማት የተለመደ ነው።
አዲስ ማለዳ ፖሊስን፣ እንዲሁም ፈቃድ ሰጪንና ዋጋ የመቆጣጠር ሥልጣን የተሰጣቸውን አካላት በጉዳዩ ዙሪያ ለማነጋገር ያደረገችው ሙከራ ለጊዜው ስላልተሳካ በቀጣይ የመንግሥት አካላትን ምላሽና ተጭማሪ ምልከታዎችን አካትታ የምትመለስ ይሆናል።<
ቅጽ 4 ቁጥር 201 ጷጉሜን 5 2014/p>


