በቻይና 200 የኢትዮጵያ ባቡር ፉርጎዎች በ 400 ሚሊዮን ብር ዕዳ ተይዘዋል

0
440

ለኢትዮ ጅቡቲ ምድር ባቡር አገልግሎት እንዲሰጡ ታስበው የዕቃ እና የመንገደኞች ማጓጓዣ ኹለት መቶ የባቡር ፉርጎዎች 14 ሚሊዮን ዶላር ከኢትዮጵያ በኩል ባለመከፈሉ ከቻይናው የባቡር አምራች ኩባንያ ፉርጎዎችን መረከብ እንዳልተቻለ ተገለፀ።

የኢትዮ ጅቡቲ ምድር ባቡር ዋና ሥራ አስኪያጅ ኢንጅነር ጥላሁን ሳርካ ለአዲስ ማለዳ እንደተናገሩት፣ መንግሥት የባቡር ፕሮጀክቱ በተጀመረበት ወቅት 65 በመቶ የሚሆነው የባቡሩ ክፍል በውጭ ባለሙያዎች እንዲገጣጠምና ቀሪው ደግሞ ለአገር ውስጥ ኩባንያዎች እንዲሰጥ አቅጣጫ አስቀምጦ እንደነበር አስታውቀዋል። ይህንም ተከትሎ 35 በመቶ የሚሆነው የባቡር መገጣጠም ሥራ ብረታ ብረትና ኢንጅነሪንግ ኮርፖሬሽን (ሜቴክ) ውል ፈፅሞ ወስዶ ነበር።

ይሁን እንጂ ሜቴክ የመገጣጠሙን ሥራ አሳልፎ ለአንድ የቻይና ኩባንያ በመስጠት ሥራውን ሲያከናውን እንደነበር ለማወቅ ተችሏል። ዋና ሥራ አስኪያጁ ሲገልፁም በሜቴክ ትዕዛዝ ሲገጣጠሙ የነበሩት ባቡሮች ከግማሽ በላይ ገብተው፤ ኹለት መቶ የሚሆኑ ፉርጎዎች ማለትም ወደ አራት ሙሉ ባቡሮች (አራት ትሬን ሴት) ቀሪ ክፍያ ባለመፈፀሙ የተነሳ የቻይናው ኩባንያ ከኢትዮጵያ መንግስት የክፍያ ማረጋገጫ ካልተሰጠው ፉርጎዎችን እንደማይሰጥ ማስታወቁን ገልፀዋል።

ጥላሁን አያይዘውም በተደጋጋሚ ወደ ሜቴክ ጉዳዩን ብናሳውቅም በመሥሪያ ቤቱ በተካሔደው ከፍተኛ ሪፎርም ምክንያት የባቡሩን ጉዳይ የሚመለከተው ሰው ማግኘት ከባድ ሆኖብናል ሲሉ አስታውቀዋል። በቻይናው የግንባታ ከባንያ ሲሲኢሲሲ የተገነባው ኢትዮ ጅቡቲ ምድር ባቡር አሁን ካሉት ባቡሮች በተጨማሪ ሌሎች አራት ባቡሮችን ለመጨመር ፍላጎት እንዳለው ጥላሁን ለአዲስ ማለዳ አስታውቀዋል።

ከዚህም ጋር ተያይዞ በቻይናዊው ኩባንያ የተያዙት ኹለት መቶ ፉረጎዎች በአስቸኳይ ካልተለቀቁ አራት ባቡሮችን ለመጨመር ሌላ ተጨማሪ ወጪ ለማውጣት እንደሚገደዱ እና ድርጅቱንም ኪሳራ ላይ እንደሚጥሉ ጥላሁን አስታውቀዋል። በጉዳዩ ላይ የብረታ ብረትና ኢንጅነሪንግ ኮርፖሬሽን ዋና ዳይሬክተር ብርጋዴር ጄነራል አሕመድ ሃምዛ ለአዲስ ማለዳ እንደተናገሩት 5 መቶ ያህል ፉርጎዎችን ለመገጣጠም ታስቦ ከቻይናው ኖሪንኮ ጋር ውል የተገባ ቢሆንም ከ500 ፉርጎዎች ውስጥም 300 የሚሆኑት ወደ አገር ውስጥ ገብተው ቀሪዎቹ ግን አሁንም ቀሪ 14 ሚሊዮን ዶላር ቀሪ ክፍያ ስለሚኖርባቸው ማስገባት እንዳልተቻለ አስታውቀዋል።
ዋና ዳይሬክተሩ አያይዘውም ገንዘቡ በተለያዩ ጊዜያት ለባቡሩ ግንባታ በሚል ወጪ እንደተደረገና በአግባቡ ባለመዋሉ አሁን ባቡሮችን ለመረከብ ገንዘብ ካዝና ውስጥ አለመኖሩን ለአዲስ ማለዳ አስታውቀዋል።

ቀሪዎቹን የባቡር ፉርጎዎች ክፍያ ፈፅሞ ወደ አገር ውስጥ ለማስገባት በሜቴክ አካውንት ውስጥ ገንዘቡ አለመኖሩን ተከትሎ ለገንዘብ ሚኒስቴር ያልተከፈለውን ከ 14 ሚሊዮን ዶላር እና ውሉን በማያያዝ ሜቴክ መክፈል እንደማይችል በ 2011 ሰኔ አሳውቀናል ሲሉ የብረታ ብረት ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን ዋና ዳይሬክተር አህመድ ሀምዛ ተናግረዋል።

በውሉ መሰረት ምድር ባቡር ኮርፖሬሽን ባቡሮቹን ሊያገኝ ስለሚገባ ለመንግሥት ካፒታሉ ወደ እኛ ይታሰብ እና ለኖሪንኮ ክፍያው ተፈፅሞ ፉርጎዎቹ ወደ አገር ውስጥ የሚገቡበትን መንገድ በምክረ ሃሳብ ደረጃ ለገንዘብ ሚኒስቴር ማቅረቡንም ለአዲስ ማለዳ አክለው ገልፀዋል። ከእነዚህ አማራጮች ውጪ ሜቴክ አሁን ባለበት ሁኔታ ገንዘቡን ሊከፍል እንደማይችልም ተናግረዋል።
ኤርሚያስ ሙሉጌታ በዚህ ዜና ላይ አስተዋጽኦ አድርገዋል።

ቅጽ 1 ቁጥር 50 ጥቅምት 8 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here