እንደዘመኑ እኛም እንለወጥ!

0
654

በዓለማችን ካሉ አገራትና ሕዝቦች መካከል የራሳቸው የዘመን አቆጣጠር ኖሯቸው ወቅታቸውን እያደሱ የሚቆጥሩ የተወሰኑ አገራት አሉ። እኛም ኢትዮጵያዊያን በርካታ ምዕተ ዓመታትን ያሳለፈ የዘመን መቁጠሪያ ያለን ነን። በየባህሉ የተለያየ የመቁጠሪያ ዘዴና ወቅት ቢኖርም እንደ አገር የምንጠቀምበትና ተፈጥሮ የምትለወጥበትን ዓመት መስከረም አንድ ላይ እንጀምራለን።

እንደአገር አዲስ ዓመትን ማክበር የጀመርነው መቼ እንደሆነ እርግጠኛ ሆኖ ሁሉም የሚስማማበት ቀን ባይኖርም፣ ኖህና ልጆቹ ከመርከብ ወርደው ባዩት ያቆጠቆጠ ልምላሜ ተደስተው የበሰበሰውን እንጨት አሰባስበው ደመራ አብርተው አዲስ ዘመን ብለው መቁጠር ከጀመሩ ወዲህ እንደሆነ ይነገራል።

አዲስ ዓመት ተብሎ የዘመን መለወጫን ማክበሩ ከተቆጠረበት ረጅም እድሜ አኳያ በሁሉም ሕዝብ መከበሩ የጊዜን ጥቅምና የመቁጠርን አስፈላጊነት እንደሚያመለክት ይታመናል። እንዲህ ዓይነት በባህላዊም ሆነ በዘመናዊ መንገድ ጥልቅ ጠቀሜታ ያለውን መሸጋገሪያ በተለመደ መልኩ ለማክበር ብቻ ሳይሆን፣ ለውስጣዊ አስተሳሰባችን መቀየሪያም መጠቀም እንዳለብን አዲስ ማለዳ ታምናለች።

የሰው ልጅ ማናቸውንም ነገር ለመለወጥ ከመነሳቱ በፊት በቅድሚያ ራሱን ለውጦ፣ ለለውጡም ራሱን አዘጋጅቶ በእቅድ እየተመራ መሆን ይኖርበታል። ራሱን መለወጥ ያልቻለ ሌላን እለውጣለሁ ማለት እንደማይቻለው፣ በቅድሚያ ከየትና ወዴት እንደምንለወጥ ማሰላሰልና ማወቅ አለብን።

ሰው ያለበትን ካላወቀ የሚሄድበትን አቅጣጫም ሆነ ወዴት እንደሚሄድ መዳረሻውን ማወቅ እንደሚሳነው እሙን ነው። እንደአገር ከማሰባችን በፊት እያንዳንዳችን የራሳችን መንግሥት ሆነን በራሳችን እጣ ፋንታ ላይ ራሳችን ብቻ መወሰን እንዳለብን ልንረዳ ይገባል። የራሳችንን ድክመትም ሆነ የብቃታችንን መንስዔና ውጤት ተረድተን በዝርዝር ማንነታችንን ማወቅ ይጠበቅብናል።

ስለራሳችን ለማሰላሰልና ደጉ ባህሪያችንን ወይም ጥሩ ጠባያችንን ከመጥፎው ለመለየት ቁጭ ብለን የምናሰላስልበት የጥሞና ጊዜም ያስፈልገናል። በሰው ተመርተን አልያም በዘፈቀደ የምንወስነው በሌላ በተመሳሳይ ዕይታ ሊቀየርና ሊቀለበስ ስለሚችል፣ የማይወላውል የማይመለስ ለውጥ ለማምጣት አስቀድመን በሐሳብ ደረጃ መለየት አለብን።

ከራሳችን የምንጠላውን አልያም እንዳይቀጥልብን የምንፈልገውን ጠባይ ከለየን በኋላ መንስኤው ልምድንም ሆነ ባህልን መሠረት ያደረገ ስለመሆኑ አሰላስለን የምንለወጥበትን ሆነ የምናስቀርበትን ዘዴ መማተር ይገባናል። እንደአዲስ ማለዳ እምነት ሰው ራሱ ቆርጦ ካልጀመረ ሌላ ቢወተውተውም ሆነ ለሰው ብሎ ቢጀምር እንደማያዛልቀው ነው።

ለውጥ ማለት መጀመሪያ የምናስቀረውን ወይም አንሶ የምንጨምረውን ለይተን ማወቅ ሲሆን፣ ይህን አጥርተን ከለየን በኋላ ቀጣዩ መሆን የምንፈልገውን በግልፅ አስቀምጠን መቀየርም ሆነ መጨመር እንደምንችል በራሳችን ሙሉ በሙሉ መተማመን ነው። በራስ መተማመንን ማጎልበት የሚሳነን ከሆነ እንደአማኝነታችን በፈጣሪ ተማምነን የጀመርነው በጎ ሥራና ዓላማ እንደሚፈጸምልን በማመን በትዕግስት መጠበቅ ይጠበቅብናል።

ኢትዮጵያዊያን ተስፋ መቁረጥ ሳይኖርብን ምንም እንቅፋት ቢገጥመን መቋቋም እንደምንችል አስበን፣ መለወጥ ወደምንፈልገው አስተሳሰብም ሆነ አመለካከት አልያም ቁመና ማምራት ይቻለናል ብለን መጀመር ይኖርብናል።

ራሳችንን በፈለግነው አቅጣጫና መጠን በቀየርን ቁጥር እንደቡድንም ሆነ እንደ አገር መቀየርም ሆነ መለወጥ እንደማይሳነን አዲስ ማለዳ ትረዳለች። እንደአገር ካለንበት አዘቅት ለመውጣት የገባንበትን መንስኤ ጠንቅቆ ማወቅ ይገባል።

በራሳችን ጉልበት ወይም አቅም ሁሉን ፍላጎታችንን መቀየር የማይቻለን እንኳ ቢሆን፣ ሌላው እንዲቀየር የራስን ተሞክሮ በማቅረብ አልያም ግንዛቤ የሚያገኝበትን መንገድ በማቅረብ በመካከላችን ልዩነት ሳይሰፋ ለመቀራረብና በአንድ አስተሳሰብ ለመዝለቅ መሥራት ያስፈልጋል።

እንደአገር ለውጥ ያስፈልጋል ማለት ከተጀመረ በርካታ ዓመታት ተቆጥረዋል። “ወግ አጥባቂ” በአንድ ወገን፣ ሌላውም “ተራማጅ” እየተባለ ደም ያፋሰሰም ውጊያ እርስ በርሳችን ብናደርግም እስካሁን የታለመው ለውጥና መሻሻል ተግባራዊ አልተደረገም።

ከላይ እንዳልነው አንዱ ቡድን ሌላውን ለመቀየር ጉልበትን በዋናነት የተጠቀመባቸው መንገዶች ስለነበሩ የባሰ አዘቅት ውስጥ ጨመሩን እንጂ እንድንመነደግ አላደረጉንም። ለውጡ ከራስ ቢጀምር በአጭር ጊዜ ያለምንም እንከን በትንሽ መስዋዕትነት ሊሳካ በቻለ ነበር።

ለራሳችን ያለንን አመለካከት ከማስተካከል ጀምረን፤ ስለሰው ልጅ ሁሉ ያለንን ግንዛቤ በማጥራት፤ ስለጥላቻ ጉዳትና ክፋት፤ ስለመተሳሰብ እንዲሁም እርስ በርሳችን እንድንናናቅና እንድንገዳደል የሚያደርጉንን ውስጣዊ አስተሳሰባችን ላይ መሥራት ይጠበቅብናል። የጥላቻና የእበልጣለሁ አስተሳሰብ ወይም በማንኛውም መልኩ የመቦዳደንና የማነጻጸር አስተሳሰብ በውስጣችን እስካለ ድረስ ምንም ሀብት ቢመጣም ሆነ ኃያል ብንሆን እንደማያዛልቀን ልንረዳ በተገባን ነበር።

በቡድን የሚመጡ መቆረቋቆዞች መነሻቸው የግል አስተሳሰብ እንደሆነ በተረዳን ቁጥር ለለውጥ መቃረባችንን እንገነዘባለን። ከልጅነት ጀምሮ የሚነገሩንና የምንስላቸው ውስጣዊ ግንዛቤዎቻችን ካልተቀየሩ እንደግለሰብም ሆነ እንደአገር መለወጥ አዳጋች ይሆንብናል።

በሌላ በኩል፣ አንድን ነገር ለመለወጥ ግዴታ የመለወጫ ጊዜን መጠበቅ ግድ ላይል ይችላል። ምግባሩም ሆነ ተግባሩ ጥሩ አለመሆኑን እንዳወቅን አልያም የተሻለ ስለመኖሩ የተገነዘብን እለት ለውጡን ተግባራዊ ለማድረግ መጣር እንጂ ጊዜ መስጠት እንደማይገባ አዲስ ማለዳ ትረዳለች።

ይህ ቢሆንም ግን፣ ሰው ነንና የተለወጥንበትን ወይም መለወጣችንን ከግንዛቤ የምናስገባበት ጊዜ ያስፈልገናል። ይህ አስተሳሰብ በብዛት ስለሚገድበን አንድ አመለካከትን ወይም ባህሪን ለመለወጥ አዲስ ዓመትን ተመራጭ እናደርጋለን። ይህ የሚሆነው በዚህ ዓመት ወይም ከዚህ ጊዜ ጀምሬ ተለወጥኩ ብሎ ለወሬ ለመንገር እንዲመች ብቻ ሳይሆን፣ የዘመን መለወጫው ሰሞን ስለሚታወሰን የተለወጥነውን አስተሳሰብ እያስታወሰን ሳንዘነጋው እንድንታትርበት መሆኑ ይታመናል።

የልደት ጊዜያቸውን ለመለወጫነት መነሻ የሚያደርጉትን ያህል፣ የግል ለውጥ ብቻ በማይጠቅምብት እንደአገራችን ሁኔታ ግን ሁሉም የሚያከብረው ወቅት ለጋራ ለውጥ እጅግ ጠቃሚ መነሻ መሆኑ ይታመናል።

ለመግባባትም ሆነ ለመረዳዳት እንዲመቸን የ2015 መጀመሪያ የሆነውን ዘመን መለወጫ የጋራ ባህሪያችንን እና መገለጫችንን ወደ በጎው የምንቀይርበት እንዲሆን አዲስ ማለዳ ትመኛለች።


ቅጽ 4 ቁጥር 201 ጷጉሜን 5 2014

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here