መነሻ ገጽዜናአቦል ዜናየውል ግዴታቸውን ያልተወጡ ስምንት ድርጅቶች በግዢ ጨረታ ላይ እንዳይሳተፉ ታገዱ

የውል ግዴታቸውን ያልተወጡ ስምንት ድርጅቶች በግዢ ጨረታ ላይ እንዳይሳተፉ ታገዱ

ከመንግሥት ተቋማት ጋር የገቡትን የውል ግዴታ ያልተወጡ ስምንት ድርጅቶች በግዢ ጨረታ ላይ እንዳይሳተፉ ማገዱን የመንግሥት ግዢና ንብረት ባለሥልጣን ለአዲስ ማለዳ አስታወቀ።

የመንግሥት ግዢና ንብረት ባለሥልጣን የኮምዩኒኬሽን ዳይሬክተር ሰጠኝ ገላን ለአዲስ ማለዳ እንደገለጹት፣ በ2015 በጀት ዓመት ባለፉት ኹለት ወራት ማለትም በሐምሌና ነሐሴ 2014 ለመንግሥት መሥሪያ ቤቶች የጽሕፈት እንዲሁም ሌሎች የሚያስፈልጋቸውን ቁሳቁሶች ለማቅረብ ጨረታ ያሸነፉ ያሉ ቢሆንም፣ ውላቸውን ተግባራዊ ያላደረጉ የግል ድርጅቶችም አሉ ብለዋል።

ዳይሬክተሩ አክለውም፣ ከአራት የፌዴራል መሥሪያ ቤቶች እና በቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል የሚገኝ አንድ የክልሉ መሥሪያ ቤት ጋር የሚያስፈልግ ማንኛውንም ቁሳቁስ ለማቅረብ ውል ተዋውለው ውሉን ለመፈጸም ፍቃደኛ ያልሆኑ ስምንት ድርጅቶች በማንኛውም የመንግሥት ግዢ ጨረታ ላይ እንዳይሳተፉ ነው የተደረገው ብለዋል።

ናስር ሁሴን፣ ሥራው ታደሰ፣ ፉዓድ ሸሪፍ፣ ቦሌ ማስታወቂያ፣ ኦሊያድ መጅድና ጓደኞቻቸው፣ ሙሐመድ አሕመድ፣ ናስም አታሚዎች እና ሴፍደሊ አስመጪ ድርጅት በአጠቃላይ ስምንቱ እርምጃ የተወሰደባቸው እና በቀጣይ ማንኛውም የመንግሥት ተቋማት በሚያወጧቸው የጨረታ ሂደት ላይ እንዳይሳተፉ የታገዱ መሆናቸው ተነግሯል።

እነዚህ ከላይ የተጠቀሱት ድርጅቶች ከሀገር መከላከያ ሚኒስቴር፣ ጉምሩክ ኮሚሽን፣ ቱሪዝም ሚኒስቴር እና በስሩ ካለው ቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለሥልጣን፣ ከባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ፣ ከወለጋ ዩኒቨርሲቲ እና ከቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል ውሃና መስኖ ኢነርጅ ሀብት ልማት ቢሮ ጋር የገቡትን የጨረታ ውል ባለመወጣታቸው እርምጃው ሊወሰድባቸው እንደቻለ ዳይሬክተሩ ጠቁመዋል።

በተጨማሪ ከመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ጋር ባደረጉት ውል መሠረት ግዴታቸውን ያልተወጡ የመንግሥት የግዢና ንብረት አስተዳደር አዋጅ ቁጥር 649/2001 አንቀፅ 2 ላይ የሰፈረውን ድንጋጌን የጣሱ ናቸው ተብሏል።

በማንኛውም የመንግሥት ግዢ ጨረታ እንዳይሳተፉ ለማድረግ ባለሥልጣኑ በአዋጅ አንቀጽ 76 የሚያግዳቸውን ተጫራቾች ዝርዝር በአዋጁ 15 ንዑስ ቁጥር ስምንት እና በግዥ አፈጻጸም መመሪያ አንቀጽ 48 ንዑስ አንቀፅ 5/4 መሠረት፣ የእርምጃ ውሳኔ የተላለፈባቸውን ድርጅቶች ዝርዝር ባለሥልጣኑ እገዳው ለሚመለከታቸው አካላት ያሳውቃል ተብሏል።

በዚህም ለኹሉም የፌዴራል መሥሪያ ቤቶች፣ ክልል ለሚገኙ ለኹሉም ዩኒቨርሲቲዎች፣ ኮሌጆች፣ ማዕከላት፣ ለክልሎች እና ለከተማ አስተዳድሮች እንዲያውቋቸው ይደረጋል ነው የተባለው።

በተመሳሳይ ባለሥልጣኑ በ2014 በጀት ዓመት በተለያየ ወቅት ከመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ጋር ተያያዥነት ያላቸው ውል አንፈጽምም ያሉ፣ የተሳሳተ ማስረጃ ያቀረቡ፣ እንዲሁም ሌሎች ጥፋት ያጠፉ 58 የግል ድርጅቶች ላይ የማስጠንቀቂያ እና ከኹለት እስከ ሦስት ዓመት ድረስ መንግሥት በሚያወጣቸው ጨረታዎች ላይ እንዳይሳተፉ የሚያደርግ እርምጃ መውሰዱም ይታወቃል።

እነዚህ ተቋማት ከአዲስ አበባ ከተማ ባህል፣ ኪነጥበብና ቱሪዝም ቢሮ፣ ከአዲስ አበባ መንገዶች ባለሥልጣን፣ ከአዲስ አበባ ውኃና ፍሳሽ ባለሥልጣን፣ ከአዲስ አበባ እሳትና አደጋ አመራር ኮሚሽን፣ ከአዲስ አበባ ገቢዎች ቢሮ እና ሌሎች በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ስር ከሚገኙ የመንግሥት ተቋማት ጋር የገቡትን ውል ያልተወጡ ነበሩ።

ከዚህ መካከል የውል ግዴታን አለመወጣት ወይም ውል ለመፈጸም ፍቃደኛ ያልሆኑ 47 የንግድ ድርጅቶች፣ ቀሪዎቹ ደግሞ ሰነድ ያጭበረበሩ፣ የዋጋ ማቅረቢያ አሸናፊ የሆኑበትን ያላቀረቡ፣ በመመሳጠርና በማጭበርበር የተጭበረበረ ወይም ሐሰተኛ ሰነድ ይዘው የተገኙ መሆናቸው ተነግሯል።


ቅጽ 4 ቁጥር 202 መስከረም 7 2015

- ይከተሉን -Social Media
ተዛማጅ ጽሑፎች

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisment -
Ads

የቅርብ ጊዜ ጽሑፎች