መነሻ ገጽዜናአቦል ዜናየዩኒቨርሲቲ ምሩቆች የወጪ መጋራት ክፍያቸውን በአግባቡ እየከፈሉ እንዳልሆነ ተገለጸ

የዩኒቨርሲቲ ምሩቆች የወጪ መጋራት ክፍያቸውን በአግባቡ እየከፈሉ እንዳልሆነ ተገለጸ

በመንግሥት ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ትምህርታቸውን የተከታተሉ ምሩቃን የወጪ መጋራት ክፍያቸውን በአግባቡ እየከፈሉ አለመሆኑን ትምህርት ሚኒስቴር ገለጸ።

የትምህርት ሚኒስቴር የሕዝብ ግንኙነትና ኮምዩኒኬሽን ኃላፊ አመለወርቅ ህዝቅኤል እንዳሉት፣ በተለይ በግል ድርጅቶች ተቀጥረው የሚሠሩ ሠራተኞች እና የግል ሥራ የሚሠሩ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ምሩቆች በበቂ ሁኔታ ያለባቸውን የወጪ መጋራት ክፍያ እየከፈሉ አይደለም።

አዲስ ማለዳ ያነጋገረችው በኤሌክትሪክ ምህንድስና በ2006 የተመረቀና የግሉን ሥራ በመሥራት ላይ የሚገኝ ሥሙ እንዲጠቀስ ያልፈለገ ወጣት፣ የወጪ መጋራቱን እስካሁን መክፈል አለመጀመሩን ይገልጻል። የቅጥር ሥራ እስካልሠራ ድረስ ክፍያውን የመክፈል ግዴታ እንደሌለበት እንደሚያምንም ተናግሯል።

ይሁንና በከፍተኛ ትምህርት የወጪ መጋራት ደንብ ቁጥር 154/2000 እንዲሁም የከፍተኛ ትምህርት ወጪ መጋራት ክፍያ አሰባሰብና አፈጻጸም መመሪያ ማሻሻያ ቁጥር 02/2009 መሠረት ማንኛውም የወጪ መጋራት ተጠቃሚ ከተመረቀ ከአንድ ዓመት በኋላ ጀምሮ፣ ተቀጣሪ ከሆነ ከወር ገቢው ቢያንስ ዐስር በመቶውን በመሥሪያ ቤቱ በኩል እንዲከፍል፣ በግሉ የሚሠራ ተጠቃሚ ከሆነ ደግሞ የሚችለውን ያህል መጠን መክፈል እንዳለበት ይደነግጋል።

ይህንን አንስታ አዲስ ማለዳ ለጠየቀቻቸው ጥያቄ አመለወርቅ ሲመልሱ፣ የወጪ መጋራት ውል ተጠቃሚዎች በተለያየ መንገድ እዳቸውን እንደሚከፍሉ ገልጸው፣ የግል ሥራ የሚሠሩ ተጠቃሚዎች ላይ ግን ያለመክፈል ችግር እንዳለ ተናግረዋል። እንደ አመለወርቅ ገለጻ ምንም እንኳን ተጠቃሚዎች ከከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ሲመረቁ ያለባቸውን እዳ የሚያረጋግጥ ደብዳቤ የሚቀበሉ ቢሆንም፣ አከፋፈሉ ላይ የግንዛቤ ችግር እንዳለ ተናግረዋል።

ምሩቆች የድኅረ ምረቃ ትምህርት ለመቀጠል እና ከአገር ለመውጣት ሲፈልጉ በቀጥታ ያለባቸውን ክፍያ እንደሚከፍሉ ገልጸው፣ ያለውን የግንዛቤ ችግር ለመፍታትም ሚኒስቴር መሥሪያ ቤታቸው እንደሚሠራ አስታውቀዋል።

በግል ድርጅት ውስጥ ተቀጥሮ እንደሚሠራና መሥራት ከጀመረም አምስት ዓመታት እንዳሳለፈ የገለጸው ሥሙ እንዲጠቀስ ያልፈለገ ሌላ ለአዲስ ማለዳ አስተያየቱን የሰጠ ግለሰብ ደግሞ፣ የወጪ መጋራት ግዴታውን እንዲከፍል በሚሠራበት ድርጅት እንዳልተጠየቀና እሱም ለመክፈል አስቦ እንደማያውቅ ተናግሯል።

በዚህ ዙሪያም አስተያየታቸውን የሰጡን አመለወርቅ፣ የግል ድርጅቶች የተቀጣሪዎቻቸውን ወጪ መጋራት ክፍያ የማስከፈል ግዴታ ያለባቸው ሲሆን፣ ይህንንም ተረድተው በአግባቡ የሚያስከፈሉ ድርጅቶች ያሉ ቢሆንም የማያስከፍሉ ድርጅቶችም አሉ። ይህንንም ለመቅረፍ ግዴታቸውን የማይወጡ ድርጅቶችን የማሳወቅ ሥራ ይሠራል ብለዋል።

ከመንግሥትም ሆነ ከግል መሥሪያ ቤት ሠራተኞች ገቢ ተቀናሽ የሚደረገው የወጪ መጋራት ክፍያ በገቢዎች ሚኒስቴር በኩል ተከፍሎ ሪፖርት ለትምህርት ሚኒስቴር እንደሚደርሰው የገለጹት አመለወርቅ፣ በመምህርነትና በጤና ሥራዎች ላይ የሚሠሩ ምሩቆች የወጪ መጋራታቸውን በአገልግሎት ይከፍላሉ ብለዋል። እስካሁን የወጪ መጋራት ግዴታቸውን ያልከፈሉ ምሩቃንን እንዲከፍሉ ለማድረግም የከፍተኛ ትምህርት ወጪ መጋራት ክፍያ አሰባሰብና አፈጻጸም መመሪያን ለማሻሻል እየተሠራ ነው ብለዋል።

የግል ድርጀቶች ሠራተኞቻቸው ግዴታቸውን እንዲወጡ እንዲያደርጉ የጠየቁት አመለወርቅ፣ የግል ሥራ የሚሠሩ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ምሩቆችም በአዋጅና መመሪያው መሠረት ያለባቸውን ክፍያ በመፈጸም ግዴታቸውን እንዲወጡ ጠይቀዋል። ትምህርት ሚኒስቴርም መመሪያ ከማሻሻል ባለፈ አሠራርና ክትትሉን በማሻሻል የክፍያ አሰባሰቡን የተሻለ ለማድረግ እንደሚሠራ አረጋግጠዋል።

በከፍተኛ ትምህርት የወጪ መጋራት ደንብ ቁጥር 154/2000 እንዲሁም የከፍተኛ ትምህርት ወጪ መጋራት ክፍያ አሰባሰብና አፈጻጸም መመሪያ ማሻሻያ ቁጥር 02/2009 መሠረት፣ ማንኛውም የወጪ መጋራት ውል ተጠቃሚ ከአስራ አምስት ዓመታት ባልበለጠ ጊዜ ውስጥ እዳውን ሙሉ በሙሉ መክፈል ይኖርበታል።


ቅጽ 4 ቁጥር 202 መስከረም 7 2015

- ይከተሉን -Social Media
ተዛማጅ ጽሑፎች

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisment -
Ads

የቅርብ ጊዜ ጽሑፎች