በሦስተኛው ዙር ጦርነት ከቆቦ የተፈናቀሉ ዜጎች የሰብዓዊ ድጋፍ አልቀረበልንም አሉ

0
1157

በሦስተኛው ዙር ጦርነት ከሰሜን ወሎ ዞን ከቆቦና አካባቢዋ ተፈናቅለው በተለያዩ አካባቢዎች የተጠለሉ ዜጎች ሰብዓዊ ድጋፍ እያገኘን አይደለም አሉ።

ከሦስት ሳምንት በፊት በተቀሰቀሰ ጦርነት ተፈናቅለው ወልዲያ፣ ደሴ፣ ኮምቦልቻና ሌሎች አካባቢዎች የሚገኙ ተፈናቃዮች የሰብዓዊ ድጋፍ ባለማግኘታቸው ችግር ላይ መሆናቸውን ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል።

ተፈናቃዮች በሰሜን ወሎ ዞን ወልዲያ ከተማ፣ በሰሜን ወሎ ዞን መርሳ ከተማ፣ በደቡብ ወሎ ዞን ደሴ ከተማ እና ኮምቦልቻ ከተማ፣ በዋግ ብሔረሰብ አስተዳደር ዞን እና በተለያዩ ቦታዎች ይገኛሉ። የክልሉ መንግሥትም በቻለው አቅም የሰብዓዊ  ድጋፍ እና አልባሳትን ጨምሮ ድጋፍ እያደረገ ቢሆንም፣ በቂ እንዳልሆነ ተጠቁሟል።

የአማራ ክልል አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ኘሮግራም የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ኢያሱ መስፍን ለአዲስ ማለዳ እንደገለጹት፣ ከዚህ ቀደም በተካሄዱት ኹለት ዙር ጦርነቶች እና ከሰሞኑ ዳግመኛ በተቀሰቀሰው ጦርነት ምክንያት 8 ነጥብ 7 ሚሊዮን ሰዎች አስቸኳይ የሰብዓዊ ድጋፍ ያስፈልጋቸዋል ብለዋል።

ችግሩን ለመቅረፍ የክልሉ መንግሥት ለፌዴራል መንግሥት ጥያቄ አቅርበን አፋጣኝ ምላሽ እንዲሰጠው አሳውቀናል ያሉት ዳይሬክተሩ፣ በአገሪቷ ያለውን ተደራራቢ ችግሮችን፣ እንዲሁም የሚስተዋሉ የሰብዓዊ ድጋፍ እጥረቶችን ተከትሎ አዲስ ማለዳ መረጃውን እስካጠናከረችበት ጊዜ ድረስ ግን የተሰጠ ምላሽ የለም ብለዋል።

ለእነዚህ ዜጎች 70 በመቶ የሚሆነው የሰብዓዊ ድጋፍ በፌዴራል መንግሥት ቀሪው 30 በመቶ ደግሞ በዓለም ምግብ ኘሮግራም እና በተለያዩ መንግሥታዊ እና መንግሥታዊ ባልሆኑ ድርጅቶች ድጋፍ ይደረግ እንደነበር ያነሱት ዳይሬክተሩ ናቸው።

የኢትዮጵያ አደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር ደበበ ዘውዴ በበኩላቸው፣ አንዳንድ አካባቢዎች ኢትዮጵያ ካለችበት ወቅታዊ ተጽእኖ አንጻር እጥረት ቢኖርም፣ እጥረቱን ለመሙላት መንግሥት ከባለድርሻ አካላት ጋር እየሠራ ይገኛል ብለዋል።

የኢትዮጵያ አደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን እስከ ነሐሴ ወር 2014 ባለው ጊዜ ድረስ በአማራ ክልል በተለያዩ ጊዜ ተፈናቅለው ለሚገኙ 8 ነጥብ 7 ሚሊዮን ሰዎች ምግብ ነክ እና ምግብ ነክ ያልሆኑ ቁሳቁሶችን ድጋፍ እያደረገ መሆኑንም ተናግረዋል።

በየወሩ ከሚደረገው ድጋፍ ባሻገር፣ በየወቅቱ ተጨማሪ ተፈናቃይ እና ድጋፍ የሚሹ ዜጎች በሚኖሩበት ወቅት የክልሉ መንግሥት ሲያሳውቅ ድጋፍ እንደሚደረግ ዳይሬክተሩ ጠቁመዋል።

በዚህም መሠረት 57 ሺሕ 419 ሜትሪክ ቶን ድጋፍ ኮሚሽኑ እንዳደረገ ዳይሬክተሩ አስረድተዋል። ከኮሚሽኑ ባለፈ በዓለም የምግብ ፕሮግራም፣ በተለያዩ ተራድኦ ድርጅቶች እና በሌሎች አካላትም ጭምር ድጋፍ የሚደረግበት ሁኔታ እንዳለ ገልጸዋል።

በተጨማሪ 128 ሺሕ 283 ለሚሆኑ ሰዎች በሰሜን ወሎና በዋግኽምራ ዞን ተፈናቅለው ለነበሩ እስከ ሰኔ 3/2014 ድረስ 2 ሺሕ 504 የሚጠጋ ሜትሪክ ቶን እህል እና ምግብ ነክ ያልሆነ ቁሳቁስ መላኩን ጠቁመዋል።

በአሁኑ ጊዜ በአማራ ክልል ከ8 ነጥብ 7 ሚሊዮን በላይ ሰዎች አስቸኳይ የሰብዓዊ ድጋፍ እንደሚያስፈልጋቸው የአማራ ክልል አደጋና መከላከል ምግብ ዋስትና ኘሮግራም ያወጣው መረጃ ያሳያል።


ቅጽ 4 ቁጥር 202 መስከረም 7 2015

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here