ለውጪ ገበያ የሚቀርብ ደረቅ እንጀራ ዝቅተኛው መሸጫ ዋጋ 1 ነጥብ 2 ዶላር ሆነ

0
1808

ከኢትዮጵያ ለውጪ ገበያ የሚቀርብ ደረቅ እንጀራ ዝቅተኛው የመሸጫ ዋጋ ተመን 1 ነጥብ 2 ዶላር መሆኑን የምግብ፣ መጠጥና ፋርማሲዩቲካል ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት ለአዲስ ማለዳ አስታወቀ።

የምግብ መጠጥና ፋርማሲዩቲካል ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት ለአዲስ ማለዳ እንደገለጸው፣ ኢትዮጵያ ወደተለያዩ ውጪ አገራት ለምትልከው እንጀራ የመሸጫ ዋጋ የተቀመጠ ተመን ያልነበረ  ሲሆን፣ ከነሐሴ ወር 2014 ጀምሮ ግን ራሱን የቻለ የመሸጫ ዋጋ በማውጣት ወደ ተግባር ተገብቷል ተብሏል።

በዚህም መሠረት ለአሜሪካ የአንድ እንጀራ መሸጫ ዋጋ 1 ነጥብ 3 የአሜሪካ ዶላር፣ ለካናዳ የአንድ እንጀራ መሸጫ ዋጋ 1 ነጥብ 2 የአሜሪካ ዶላር፣ ለአውሮፓ እና ለሌሎች ለተለያዩ አገራት ደግሞ ከ1 ነጥብ 2 የአሜሪካ ዶላር በላይ የመሸጫ ዋጋ እንዲሆን ተወስኖ ወደ ሥራ እንደተገባ ተጠቁሟል።

ይህም 1 ነጥብ 2 የአሜሪካ ዶላር ትንሹ የመሸጫ ዋጋ 1 ነጥብ 3 የአሜሪካ ዶላር ደግሞ ትልቁ የመሸጫ ዋጋ ሆኖ እንደተቀመጠ እና ይህም መውጣቱ ለኢትዮጵያ ጉልህ ሚና እንዳለው ነው የተነገረው።

ለዚህም ከዚህ በፊት በነበሩ ዓመታት የደረቅ እንጀራ የመሸጫ ዋጋ አለመውጣቱን ተከትሎ ወደ አንዳንድ አገራት ኢትዮጵያ ውስጥ ይሸጥበት ከነበረው በታች ማለትም በቅናሽ የመገበያያ ገንዘብ የሚሸጥበት ሁኔታ እንደነበርም ተገልጿል።

የደረቅ እንጀራ የመሸጫ ዋጋ ተመኑ ከመውጣቱ በፊት ከነበረው ዓመት ጋር ሲነጻጸር፣ ተመኑ ተግባራዊ ከተደረገበት እና ወደ ሥራ ከተገባበት ከነሐሴ ወር 2014 ጀምሮ ያለው ሁኔታ ቀድሞ ይሸጥበት ከነበረው አንጻር ከፍተኛ እድገት እንዳለው እና 27 በመቶ ብልጫ ማሳየቱ ነው የተጠቀሰው።

ወደተለያዩ አገራት ደረቅ እንጀራ የሚልኩ በርካታ የንግድ ተቋማት በኢትዮጵያ ያሉ ሲሆን፣ ከተቀመጠው ከመሸጫ ዋጋ በታች መሸጥ እንደማይቻል እና ተቋሙ ጠንካራ ቁጥጥር እንደሚያደርግ ተመላክቷል።

ኢትዮጵያ ወደተለያዩ አገራት ለሽያጭ ለምትልካቸው የእንጀራ የመሸጫ ዋጋ ተመን ማውጣቷ የጥራት ደረጃ እንዳለው ከማመላከት ባሻገር፣ ለኢትዮጵያ የተሻለ ዶላር ገቢ እንደሚያስገኝ ተነግሯል።

ኢትዮጵያ ወደ አሜሪካ፣ አውሮፓ እና ሌሎች አገራት በከፍተኛ ሁኔታ ደረቅ እንጀራ እንደምትልክ እና ወደ ውጭ ለምትልከው እንጀራ የመሸጫ ዋጋው በየጊዜው ከፍ እና ዝቅ ማለቱንም ተከትሎ ተመኑን ለማውጣት እንደተገደደ እና ከወጣው ወይም ከተቀመጠው ተመን አሳንሶ መሸጥ እንደማይቻል ተነግሯል።

የምግብ መጠጥና ፋርማሲዩቲካል ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት ከኢትዮጵያ ወደ ውጪ አገር እንጀራን የሚልኩ ሰዎች በፈለጉት ዋጋ እየላኩ በመሆኑ የመሸጫ ዋጋው ከፍ ወይም ዝቅ ስለሚል የመላኪያ ቋሚ ዋጋ ለማስቀመጥም ተገዷል ተብሏል።

በኢትዮጵያ ለጊዜው በቁጥር ማስቀመጥ ባይቻልም በርካታ የእንጀራ ላኪ የንግድ ድርጅቶች እና በርካታ ቁጥር የሚሸፍን ደረቅ እንጀራ በየወቅቱ ወደተለያዩ  አገራት ይላካል ነው የተባለው።

ከነሐሴ ወር 2014 በፊት ባነበሩት ጊዜያት እንጀራ ላኪዎች በፈለጉት ዋጋ ይልኩ እንደነበር እና በዝቅተኛ ዋጋ ሲላክም ኢትዮጵያ የምታስገባው የዶላር ገቢ ያነሰ እንደነበር ተመላክቷል።

ቀድሞ በነበረው መረጃ መሠረትም አንድ እንጀራ ወደ ውጪ የሚላክበት ዋጋ ከ0.5 እስከ አንድ ዶላር ብቻ ነበር። የተቀመጠውን የእንጀራ የመሸጫ ዋጋ ተንተርሶ ኢትዮጵያ በዓመት ከ10 ሚሊዮን ዶላር በላይ ገቢ ወደ ውጪ ከሚላክ እንጀራ የምታገኝበትም ሂደት እንዳለ ተነግሯል።


ቅጽ 4 ቁጥር 202 መስከረም 7 2015

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here