የትምህርት ቁሳቁስ ዋጋ ንረት

0
1529

ቅድመ ነገር

አዲስ ዓመትን ተንተርሰው ከሚመጡ በርካታ ጉዳዮች መካከል የትምህርት ጅማሮ አንዱ ነው። ታዲያ በኢትዮጵያ ከመስከረም ወር ጀምሮ ተማሪዎች ወደ ትምህርት ገበታቸው የሚመለሱበት ወቅት ነው። በመሆኑም ትምህርት ሚኒስቴር ተማሪዎች ወደ ትምህርት ገበታቸው እንዲመለሱ ጥሪ ሲያቀርብ ሰነባብቷል።

አሮጌው ዓመት 2014 ተገባዶ አዲሱ ዓመት 2015 ሰተት ብሎ ከገባ 14 ቀናትን ያስቆጠረ ሲሆን፤ ባሳለፍነው መስከረም 9/2015 ትምህርት ስለመጀመሩ ትምህርት ሚኒስቴር በይፋ አሳውቋል። ሆኖም ኹሉም ተማሪዎች ባይሆኑም፣ በጥሪው መሠረት በክፍል ውስጥ የተገኙ ተማሪዎች ትምህርት ስለመጀመራቸው እየተነገረ ነው።

ወላጆችን ጨምሮ ተማሪዎች የትምህርት መጀመሩ እሰየው ያሰኛቸው መሆኑን በደስታ እየገለጹ ይገኛሉ። ወዲህ ግን ወላጆች በጥልቁ ያማረራቸው ጉዳይ ስለመኖሩም አልደበቁም። ነገሩ ወዲህ ነው። ያማረራቸውም የትምህርት ቁሳቁስ የዋጋ ንረት መሆኑን ይናገራሉ።

ታዲያ ከአስቤዛ ግዥ ጋር ተደርቦ አዲስ ዓመት በጠባ ቁጥር የዋጋ ጭማሪ እያሳየ የሚመጣው የትምህርት ቁሳቁስ እንዳማረራቸው በተለይም ወላጆች ከዓመት ወደ ዓመት ያለውን የዋጋ ልዩነት በሰፊው ያብራራሉ። የኢኮኖሚ ባለሙያዎች በበኩላቸው፣ በአንድ አገር ውስጥ ጦርነት ሲከሰት የዋጋ ንረት መፈጠሩ እንደማይቀር ቀድመው ሲገልጹ ነበር።

ለአብነትም በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የኢኮኖሚክስ ትምህርት ኃላፊ ዓለማየሁ ገዳ (ፕ/ር)፣ በ2013 ጦርነቱ ሲጀማር ሊያስከትላቸው የሚችሉ ተግዳሮቶችን እንዲህ ሲሉ ገልጸው ነበር፤ ‹‹ጦርነቱ የሚያስከተለውን መዘዝ ግምት ውስጥ ስናስገባ፤ የዋጋ ንረቱ ቢያንስ ለቀጣይ አንድ ዓመት ወይም ኹለት  ዓመታት  ምናልባትም  ከፍ  ባለ  ደረጃ  የሚቀጥል ይሆናል።››

ታዲያ የሆነውም ዓለማየሁ እንዳሉት ነው። በተለይም ጦርነቱ ከተጀመረ ወዲህ በምግብ ነክ ነገሮችም ሆነ ሌሎች ቁሳቁሶች ላይ የዋጋ ንረት ተስተውሏል። የተለያዩ ቁሳቁሶችም ላይ የተከሰተው የዋጋ ጭማሪ የማኅበረሰቡ የራስ ምታት ከሆነ ውሎ አድሯል።

ጦርነቱ ለዋጋ መናር ዋነኛ መንስኤ መሆኑን የምጣኔ ሀብት አማካሪ ዮሐንስ አረጋዊ ይናገራሉ። ከጦርነቱ ባሻገር ያልተገባ የነጋዴዎች ጠቅላይነት ለዋጋ ንረቱ መንስኤ ነው ባይ ናቸው። የነጋዴዎች ጠቅላይነትን የምጣኔ ሀብት አማካሪው ሞኖፖሊ (Monopoly) ብለውታል።

በኢትዮጵያ 70 በመቶ የሚሆኑት ሕዝቦች በድህነት ቀንበር ስር ያሉ መሆናቸው ይነገራል። ሆኖም የነጋዴዎች የጠቅላይነት ጉልበት በንግድ ልውውጥ ጊዜ ጭቆና የሚያደርሰው በአብዛኛው የማኅበረሰብ ክፍል ላይ መሆኑ ነው የተነገረው። በነጋዴዎች ፍላጎት የሚመራው ነጻ ገበያ በተለይም የድሆችን አቅም ያላማከለና ጭቆና የሚያደርስ ነው ያሉትም የምጣኔ ሀብት አማካሪው ዮሐንስ ናቸው።

የዋጋ ንረት

ማንኛውም ዓይነት አስቤዛና ቁሳቁስ የዋጋ ጭማሪ በማሳየቱ ከከተማ እስከ ክፍለ አገር ያሉ ሰዎችን ያማረረ ጉዳይ መሆኑ እሙን ነው። ነገር ግን፣ ይህ ዘገባ በይበልጥ የሚያተኩረው የትምህርት ቁሳቁሶችን በተመለከተ በመሆኑ ደብተር፤ እስክርቢቶ፤ እርሳስ፤ የደንብ ልብስ (ዩኒፎርም) እንዲሁም ቦርሳ ላይ በ2015 የተስተዋለውን የዋጋ ለውጥ አዲስ ማለዳ ለመቃኘት ሞክራለች።

በዚህ የገበያ ቅኝት መሠረት በ2015 የትምህርት ዘመን ደብተር፤ እስክርቢቶ፤ እርሳስ፤ ቦርሳ እንዲሁም ዩኒፎርም ከፍተኛ የዋጋ ጭማሪ አሳይተዋል።

በተለያዩ ሱቆችና የጽሕፈት መሣሪያ መደብሮች ‹ሲነር ላይን› እና ‹ራዲካል› ደብተር ደርዘኑ (12 ፍሬ ደብተር) 840 ብር እየተሸጠ መሆኑን አዲስ ማለዳ በአዲስ አበባ ከተማ በመዘዋወር ተመልክታለች።

የደብተር ዋጋ ከዚህም ሊልቅ እንደሚችል ነጋዴዎችም አልደበቁም። ወላጆች በበኩላቸው ሲነር ላይን፤ ራዲካል፤ ስኩየር እንዲሁም ዳብል ላይን ደብተሮችን አቀላቅሎ የሚገዛ ሰው እስከ አንድ ሺሕ ብር እንደሚያወጣ ገልጸዋል።

በሌላ በኩል እስክርቢቶ፤ እርሳስና መቅረጫ፤ የተለያየ ቀለም ያላቸው የስዕል ደብተርን ጨምሮ በአጠቃላይ እስከ 700 ብር ወጪ እንደሚጠይቅም በተለይም ልጆቻቸውን ገና በኬጂ ትምህርት ቤት ያስገቡ ወላጆች ምስክርነት ሰጥተዋል።

ከአንድ ዓመት በፊት ከ400 እስከ 600 ብር ሲሸጥ የነበረው የተማሪዎች ደብተር መያዣ ቦርሳ ወደ አንድ ሺሕ 200 ብር ከፍ ያለ ሲሆን፤ ወላጆችም ልጆቻችንን ከትምህርት ገበታ አናቋርጥም በሚል እልህና ወኔ ለመግዛት ተገደዋል። አንዳንዶች ገቢያቸው አነስተኛ በመሆኑ የትምህርት ቁሳቁስ ባለሟሟላታቸው ትምህርት መጀመር እንዳልቻሉም ተመላክቷል።

እስከ 1 ሺሕ 700 ብር የሚሸጠው ተንጠልጣይ ቦርሳ ሲሆን፤ ተጎታቹ ደግሞ ዋጋው ላቅ ያለ መሆኑን አዲስ ማለዳ አረጋግጣለች። የተጎታቹ ቦርሳ ዋጋም ከ2 ሺሕ 500 እስከ 3 ሺሕ 400 ነው።

ሌላኛው ወላጆችን ያማረረው የዩኒፎርም ወይም የትምህርት ቤት የደንብ ልብስ ዋጋ መሆኑ ተነግሯል። የሕጻናት የትምህርት ቤት የደንብ ልብስ በ2015 ገበያ ላይ እየተሸጠ ያለው እስከ 1 ሺሕ 700 ብር ነው። ከደንብ ልብሱ ጋር የሚለበስ የሕጻናት ጫማ ዋጋው አንድ ሺሕ ብር ነው።

ለቅድመ መደበኛ ወይም ‹ኬጂ› ተማሪዎች የምሳ ዕቃ ማዘጋጀት ግዴታ መሆኑን ወላጆች በአንክሮ የገለጹ ሲሆን፤ የምሳ እቃም ዋጋው አንድ ሺሕ ብር መሆኑ ታውቋል። ታዲያ በተለይም የተማሪ ወላጆች የትምህርት ቤት ክፍያን ጨምሮ የተማሪዎች የትምህርት ቁሳቁስ እና የሌሎች አስቤዛዎች ዋጋ መናር ለኑሮ ፈተና እንደሆነባቸው ይናገራሉ።

የተማሪ ወላጆች እሮሮ

ወላጆች በ2015 የትምህርት ቁሳቁስ ላይ የሚደረገው የዋጋ ጭማሬ ልጆቻቸው ከትምህርት ገበታ እንዲደናቀፉ እስከማድረግ መድረሱን የሚገልጹም አሉ። የሺወርቅ ሞላዬ በሊስትሮ ሥራ ተሰማርተው እንደሚተዳደሩ የገለጹ ሲሆን፤ የትምህርት ቁሳቁስ ዋጋ ንረቱን ተከትሎ በ2015 የትምህርት ዘመን ልጃቸው ትምህርት ቤት መግባት እንዳልቻለ በማዘን ተናግረዋል።

አክለውም ‹‹ልጄ ከጓደኞቹ በታች ሆኗል። እያለቀሰ ነው። ምን ላድርግ ጫማ ጠርጌ ለቤት ኪራይ፤ ለቀለብ፤ ለልብስ፤ ከዚያም አልፎ ለደብተር እስክርቢቶ….አልቻልኩም።›› ነው ያሉት።

በሾላ ገበያ ለልጃቸው የትምህርት ቁሳቁስ ሲገዙ አዲስ ማለዳ አግኝታ ያነጋገረቻቸው ትዝታ ከፍያለው የተባሉ እናት፤ የትምህርት ቤት ክፍያና ቁሳቁስ መግዣ ዋጋ ካንገሸገሻቸው ወላጆች መካከል ሌላኛዋ ናቸው። የዋጋ ንረቱን አስመልክተውም፤

‹‹በዘንድሮው ዓመትስ ጭራሽ የትምህርት ቁሳቁስ የዋጋ ጭማሬው ለየት ያለ ነው። አምና እስከ 30 ብር ስገዛው የነበረውን ደብተር ዘንድሮ 70 ብር ነው የገዛሁት።›› ሲሉ በመገረም ይገልጻሉ።

አክለውም፣ ‹‹በኢትዮጵያ የረከሰው ዝምድናና የሰው ልጅ ሕልፈተ ሕይወት ነው። ኩፍ/ከፍ የማይለው ነገር ደግሞ ማሻሻያ ተደረገ ሲባል ለይስሙላ ቅንጭብ ተደርጎ ጭማሪ የተደረገለት የሚባለው የደመወዝ ጉዳይ ነው። ከኹሉም በላይ ላቅ ያለው ግን የነጋዴዎች ስግብግብነት ነው።›› ብለዋል።

የተማሪ ወላጆች ለአምስት ዓመት ገደማ ወደኋላ መለስ ብለው በማስታወስ የትምህርት ቁሳቁስ ዋጋ እስከ አምስት እጥፍ ገደማ ጭማሪ እንዳሳየ በንጽጽር ይገልጻሉ።

የዋጋ ንጽጽር

የቁሳቁሶችን ዋጋ ካለፉት ዓመታት ጋር በማነጻጸር የዚህ ዓመት ልዩነቱ የሰፋ መሆኑን በመጀመሪያ የገለጹት ከአዲስ ማለዳ ጋር ቆይታ ያደረጉት እንግዳወርቅ አብረሃ ናቸው። እንግዳወርቅ በ‹ኬጂ› እና 10ኛ ክፍል የሚማሩ ኹለት ልጆች እንዳሏቸው በመጀመሪያ አብራርተው ስለዋጋ ንረቱ የሚከተለውን ንጽጽር አስቀመጡ።

እንግዳወርቅ በ2009 አንድ ደርዘን ባለ ሀምሳ ሉክ ራዲካል እና ሲነር ላይን ደብተር በ168 ብር ገዝተው እንደነበር ያስታወሱ ሲሆን፤ 2009ኝን መነሻ በማድረግ የዋጋውን ንረት በቁጥራዊ ማስረጃ አስደግፈው ያብራራሉ። ከዛን ጊዜ ጀምሮ ያለውን የገበያ ኹኔታ ሲገልጹም፤ በየወቅቱ የዋጋ ጭማሪ እንዳሳየ አንስተው፤ በተለይም በተያዘው ዓመት ለልጆቻቸው ደብተር ሲገዙ ወደ አምስት እጥፍ ገደማ ከፍ ያለ ብር እንዳወጡ ተናግረዋል።

እንደ ማብራሪያቸው ከሆነ፤ በ2009 አንድ ሲነር ላይን ባለ 50 ሉክ ደብተር 14 ብር፤ ለደርዘን 168 ብር ወጭ አድርገው የነበረ ሲሆን፤ በተያዘው ዓመት ግን አንድ ሲነር ላይን ባለ 50 ሉክ ደብተር 70 ብር በመግዛት ለደርዘኑ 840 ብር ለማውጣት ተገደዋል። ወላጁ የዩኒፎርምና እስክርቢቶ ሲጨመርብት ዋጋው ለራስ ምታት ሕመም ያጋልጣል ብለው፤ መንግሥት መፍትሄ ካልሰጠ ልጆችን ማስተማር ከባድ ነው ብለዋል።

ሌላኛዋ ውብዓለም ሲሳይ ለ11ኛ ክፍል ልጃቸው ደርዘኑን ባለ 100 ሉክ ሲነር ላይን ደብተር በ1 ሺሕ 224 ብር እንደገዙ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል። ውብዓለም ልጃቸው ስድስተኛ ክፍል ሳለ አንድ ባለ 100 ሉክ ሲነር ላይን ደብተር 20 ብር፤ ደርዘኑን 240 ብር እንደገዙ ያስታውሳሉ። ዘንድሮ ግን አንድ ሲነር ላይን ባለ 100 ሉክ ደብተር 102 ብር፤ ደርዘኑን ደግሞ 1 ሺሕ 224 መግዛታቸውን ገልጸው ‹‹አጀብ ጉድ!›› ሲሉ ተገርመዋል።

ወላጆችን ያማረራቸው የደብተር ዋጋ መጨመር ብቻ አይደለም። ይልቁንም በዩኒፎርም፤ ቦርሳና እስክርቢቶም ያለው ጭማሪም ነው እንጂ።

አዲስ ማለዳ መርካቶ፤ አዲሱ ገበያ፤ ሾላ እንዲሁም ስድስት ኪሎና ካራ ባደረገቸው የገበያ ቅኝት የተማሪ ቦርሳዎች እና ዩኒፎርሞች እስከ 1ሺሕ 700 ብር እየተሸጡ ነው።

ከላይ በተጠቀሱት ሥፍራዎች በሚገኙ የተለያዩ ሱቆች የተማሪዎች ቦርሳም እስከ 1ሺሕ ብር እየተሸጠ መሆኑን ማረጋገጥ ተችሏል። ወላጆችም የትምህርት ቤት የደንብ ልብስ ለልጆቻቸው የሚገዙት እንደ ክፍል ደረጃቸውና እንደ ዓይነቱ ከ1 ሺሕ እስከ 1 ሺሕ 700 ብር መሆኑን መስክረዋል።

የተለያየ ዓይነትና መጠን ያለው የትምህርት ቤት ዩኒፎርም/የደንብ ልብስ በተለያየ የክፍል ደረጃ የሚገኙ ተማሪ ልጆች ላሏቸው ወላጆች ሌላኛው የራስ ምታት ነው። በአዲስ አበባ ከተማ ባሉ ትምህርት ቤቶች የተማሪዎች የደንብ ልብስ የአፀደ ሕጻናት፤ ከአንደኛ እስከ አራተኛ ክፍል፤ ከአምስት እስከ ስምንት እና የኹለተኛ ደረጃ ተማሪዎች በሚል የተለያየ ሆኖ ስለመከፋፈሉ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በ2011 መግለጹ ይታወሳል።

ይህን ተከትሎም በተለይም ሦስትና ከዚያ በላይ ልጆቻቸውን በተለያዩ የትምህርት ደረጃ የሚያስተምሩና የደንብ ልብስ ለመግዛት የተገደዱ ሰዎች ከፍተኛ ወጪ እንደጠየቃቸው አልደበቁም።

ምን ተሻለ?

የ2015 የትምህርት ዘመን ከመጀመሩ ቀደም ብሎ ባሉት ሳምንታት ውስጥ የተለያዩ በጎ አድራጎት ድርጅቶች የትምህርት ቁሳቁስ ለማሟላት ለሚቸገሩ ተማሪዎች ደብተርና እስክርቢቶ የማሰባሰብ ሥራ ሲሠሩ ተስተውለዋል። እንዲህ ሆኖም ግን በተለይም የቤተሰቦቻቸው ገቢ አነስተኛ የሆኑ ልጆች ከትምህርት ገበታቸው ለመለየት እንደተገደዱ ወላጆቻቸው ገልጸዋል።

የምጣኔ ሀብት አማካሪው ዮሐንስ አረጋዊ በበኩላቸው፣ ለተከሰተው የትምህርት ቁሳቁስ ዋጋ ንረት መፍትሄ ያሏቸውን ነጥቦች ጠቅሰዋል። አማካሪው በመጀመሪያ ለሰው ልጅ ኑሮ ፈተና የሆነው በተለይም ከ1997 ጀምሮ እየተንሰራፋ የመጣው የምግብ ዋጋ ንረት መሆኑን አንስተው፤ አሁን አሁን ግን የቁሳቁስ የዋጋ ንረትም ስለመባባሱ ተናግረዋል።

አክለውም፤ የቁሳቁስ የዋጋ ንረቱ ጋብ እንዲል ለማድረግ በተለይም በነጻ ገበያው ላይ መንግሥት ውሳኔ መስጠት አለበት ብለዋል። አንድ ምሳሌም እንዲህ ሲሉ አንስተዋል፤ ‹‹ለትራንስፖርት የሚከፈለው ታሪፍ መጠኑ በመንግሥት ባይወሰን፤ ዛሬ አምስት ብር ከፍለን በተጓዝንብት መንገድ ምናልባትም 40 እና 50 ብር ልንጠየቅ እንችል ነበር። የትምህርት እና ሌሎች ቁስቁሶች ከዚህ የዋጋ ንረት ደረጃ የደረሱት ነጻ ገበያው ላይ መንግሥት ውሳኔ ባለማሳረፉ ነው።››

በተያያዘም፤ ጦርነት የቆመበት ጊዜ ባይኖርም ትንሽ ጋብ እንዲል ካልተደረገ የዋጋ ንረቱ ሊጨምር እንጂ ሊቀንስ ይችላል ማለት የሞኝ አስተሳሰብ ነው ብለዋል። ከዚህ በተጨማሪ በጎ አድራጊዎች የተለመደ ሥራቸውን ቢቀጥሉና ነጋዴዎችም ሰብዓዊነት ተሰምቷቸው ከልክ ያለፈ የዋጋ ጭማሪ ከማድረግ ቢታቀቡ ለኹሉም መልካም ይሆናል ሲሉ  መክረዋል።


ቅጽ 4 ቁጥር 203 መስከረም 14 2015

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here