የሕዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት የሚሰጡ ልዩ ባስ ተሽከርካሪዎች የሚያስከፍሉት ዋጋ ከፍተኛ ጭማሪ ማሳየቱን ተጓዦች ለአዲስ ማለዳ ገለጹ።
አዲስ ማለዳ ያነጋገረቻቸው የትራንስፖርት ተጠቃሚዎች ልዩ ባሶች የሚያስከፍሉት ዋጋ ተመጣጣኝ አይደለም ብለዋል።
በሥራ ምክንያት ከአርባ ምንጭ አዲስ አበባ የሚመላለሱት አስተያየት የሰጡ ተጠቃሚ፣ 436 ኪሎ ሜትሩን መንገድ ለመጓዝ በዚህ ሰዓት በልዩ ባስ 985 ብር፣ እንዲሁም በአገር አቋራጭ አውቶብስ ደግሞ 280 ብር እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል። በዚህም ምክንያት አገር አቋራጭ አውቶብሶችን ለመጠቀም እንደሚመርጡ የተናገሩት ተጠቃሚው፣ በኹለቱ የትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪ አውቶብሶች መካከል የዋጋ ልዩነት እንደሚኖር ግልጽ ቢሆንም፣ የዚህን ያህል መሆኑ ግን እንዳስገረማቸው ገልጸዋል።
በጉዳዩ ዙሪያ አዲስ ማለዳ ያነጋገረቻቸው ሥማቸው እንዲጠቀስ ያልፈቀዱ የልዩ ባስ ድርጅት የሥራ ኃላፊ እንዳረጋገጡት፣ ልዩ ባሶች የአገልግሎት ታሪፋቸውን የሚያወጡት ራሳቸው ሲሆኑ፣ የታለመለት የነዳጅ ድጎማ ስርዓትም ተጠቃሚ እንዳልሆኑ ጠቅሰዋል። የነዳጅ ድጎማ ስርዓቱ ተጠቃሚ ላለመሆናቸው እንደምክንያትነት ያነሱትም፣ የአገልግሎት ታሪፋቸውን ድርጅቶቹ በራሳቸው የሚወስኑ በመሆኑና ትራንስፖርትና ሎጂስቲክ ሚኒስቴር በሚያወጣው ታሪፍ ለማይሰሩ ተሽከርካሪዎች የድጎማ ስርዓት ተጠቃሚ መሆን ስለማይቻል ነው ብለዋል።
ልዩ ባሶቹ የነዳጅ ድጎማ ተጠቃሚ አለመሆናቸው የሚያስከፍሉትን ታሪፍ ተመሳሳይ አገልግሎት ከሚሰጡ የአገር አቋራጭ አውቶብሶች አንጻር ከፍተኛ እንዲሆን ያደረገው ሲሆን፣ ይህም በርካታ የትራንስፖርቱ ተጠቃሚዎችን እንዳማረረ አዲስ ማለዳ ያነጋገረቻቸው ተጓዦች ገልጸዋል።
በጉዳዩ ዙሪያ ምላሽ የሰጡት በትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴር የሕዝብ ትራንስፖርት አሽከርካሪና ተሽከርካሪ ጉዳዮች መሪ ሥራ አስፈጻሚ ከድልማግስት ኢብራሂም እንደሚሉት፣ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤታቸው የልዩ ባሶችን የአገልግሎት ታሪፍ ይከታተላል እንጂ አይቆጣጠርም ብለዋል።
ልዩ ባሶቹ ለትርፍ የተቋቋሙ እስከሆኑ ድረስ በሚያወጡት ታሪፍ ላይ ቁጥጥር መደረግ የለበትም ወይ ተብለው ለተጠየቁት ጥያቄ ሲመልሱ፣ ልዩ ባሶች እንዲቋቋሙ ሲፈቀድ ባሶቹ መንግሥት ባዘጋጃቸው የትራንስፖርት ተርሚናሎች ሳይገቡ መካከለኛ ገቢ ያላቸውን የኅብረተሰብ ክፍሎች ተደራሽ የሚያደርጉ የትራንስፖርት አማራጭ እንዲሆኑ በማሰብ የተነሳ እንደሆነ ገልጸዋል። ባሶቹ አገልግሎት መስጠት ከጀመሩበት ጊዜ አንስቶም የታሪፍ ክትትል እንጂ ቁጥጥር እንደማይደረግባቸው የተገለጸ ሲሆን፣ ለዚህም ምክንያቱ ድርጅቶቹ ሲቋቋሙ የታሪፍ ቁጥጥር የሚል ስምምነት አለመኖሩ ነው ተብሏል።
ከዚሁ ጋር በተያያዘም ድርጅቶቹ ሲቋቋሙ የመንግሥት ትራንስፖርት ተርሚናሎችን እንደማይጠቀሙ ቢገለጽም፣ በላምበረትና አየር ጤና የትራንስፖርት ተርሚናሎች ገብተው አገልግሎት መስጠታቸውን አስመልክቶ ለተጠየቁት ጥያቄ ከድልማግስት ሲመልሱ፣ ከድርጅቶቹ ጋር በመነጋገር ለክትትል ይመች ዘንድ የመንግሥት ተርሚናሎችን እንዲጠቀሙ ተደርጓል ብለዋል።
ለተርሚናሎቹም የአገልግሎት ክፍያ እንደሚከፍሉ የገለጹት ሥራ አስፈጻሚው፣ ድርጅቶቹ ወደፊት የራሳቸው የሆነ ተርሚናል ለመገንባት የመሬት ጥያቄዎች እንዳሏቸው ጠቅሰው፤ ጥያቄዎቹ ሲፈቱ ተርሚናሎቹ እንደሚገነቡ አስታውቀዋል።
የታሪፍና ተያያዥ የኅብረተሰቡ ጥያቄዎችን ከሚኒስቴር መሥሪያ ቤታቸውና የልዩ ባስ አገልግሎት ከሚሰጡ ድርጅቶች የተውጣጣ፣ በአጠቃላይ በዘርፉ ያሉትን ችግሮች ለመፍታት የተቋቋመ ኮሚቴ እንደሚያየው ከድልማግስት ገልጸዋል። በተያያዘም ድርጅቶቹ ከታለመላቸው ግብ አንጻር እያካሄዱት ያለው ሥራ ተገምግሞ ማስተካከያዎች እንደሚደረጉ ተናግረዋል።
የታለመለት የነዳጅ ድጎማ ስርዓት በመንግሥት ታሪፍ የሚወጣላቸውን የሕዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪዎችን ብቻ ተጠቃሚ በሚያደርግ መልኩ ከሰኔ 29/2014 ጀምሮ ሥራ ላይ እንደሚገኝ ይታወቃል።
ቅጽ 4 ቁጥር 203 መስከረም 14 2015



