ወደ ወለጋ ያቀኑ ተማሪዎች መንገድ በመዘጋቱ ወደ ትምህርት ገበታቸው መመለስ አልቻሉም ተባለ

0
944

• ትራንስፖርት ላይ የነበሩ 16 ሰላማዊ ሰዎች ታግተው መገደላቸውም ተሰምቷል

ከተለያዩ የክልል ከተሞች ለአዲስ ዓመት በዓል ቤተሰብ ለመጠየቅ ወደ ወለጋ ያቀኑ በመቶዎች የሚቆጠሩ ተማሪዎች መንገድ በመዘጋቱ ወደ ትምህርት ገበታቸው መመለስ አለመቻላቸውን ታማኝ ምንጮች ለአዲስ ማለዳ ገለጹ።

ተማሪዎቹ ከአሶሳ፤ አዲስ አበባ፤ ከወሎ፤ ከደብረ ማርቆስ፤ ከፍኖተ ሰላም፤ ከአዳማና ሌሎች አካባቢዎች በሚገኙ ኹለተኛ ደረጃና ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ሲማሩ ቆይተው ለእረፍትና ለአዲስ ዓመት በዓል ወለጋ ወደሚገኙ ቤተሰቦቻቸው ያቀኑ ናቸው።

ሥሜ ባይጠቀስ ያሉ በነቀምቴ የሚገኙ አንድ ሚሊሻ፣ መንገድ በመዘጋቱ ምክንያት ወደ ትምህርት ገበታቸው መመለስ ያልቻሉት ተማሪዎች ብዛት በመቶዎች የሚቆጠር ነው ብለዋል። በተያያዘም፤ ቁጥራቸውን ቢያንስ እስከ 500 እንደሚሆን ገምተዋል።

አክለውም፣ ‹‹ትምህርት በተያዘው ዓመት መስከረም 9/2015 በይፋ መጀመሩ ይታወቃል፣ ይሁን እንጂ ተማሪዎቹ ወደሚማሩበት ትምህርት ቤት መመለስ አልቻሉም›› ብለዋል።

መንገዱ የተዘጋው በነቀምት ዞን ውስጥ በምትገኝ ‹‹ጽጌ›› ተብላ በምትጠራ ቦታ መሆኑ ተመላክቷል። ተዘጋ የተባለው መንገድ ከወለጋ ወደ አዲስ አበባ፤ አሶሳ፤ ደብረ ማርቆስ፤ ፍኖተ ሰላም፤ ወሎ፤ አዳማ እና ሌሎች የክልል ከተሞች የሚወስድ ነው።

ሌላኛው የነቀምቴ ነዋሪ በበኩላቸው፣ ቁጥራቸው እስከ 500 የሚገመት ተማሪዎች መንገድ ተዘግቶባቸው ወደነበሩበት ትምህርት ቤት መሄድ አልቻሉም ሲሉ ተናግረዋል። ተማሪዎቹ ከሰላማዊ ቦታ የጸጥታ ችግር ወዳለበት ቦታ ለምን እንደሄዱ ሲጠየቁም፤ ‹‹ከአዲስ ዓመት በዓል በፊት መንገዱ ሰላማዊና ክፍት ነበር። በየቦታውም ጥበቃ የሚያደርጉ ሚሊሻዎች ነበሩ።›› ነው ያሉት።

ሚሊሻ መሆናቸውን ገልጸው ለአዲስ ማለዳ መረጃ ያቀበሉ ምንጭ በበኩላቸው፣ ‹‹ከአዲስ ዓመት በዓል በፊት እኔም በተለያዩ ኬላዎች እየተዘዋወርኩ ጥበቃ ሳደርግ ነበር። ያኔ መንገዱ ሰላማዊ ነበር። ብዙ ተማሪዎችም ትምህርት ከተዘጋ ጊዜ ጀምሮ እስከ አዲስ ዓመት በዓል ድረስ ከተለያዩ ቦታዎች ቤተሰቦቻቸውን ለመጠየቅ ሲመጡ ተመልክቻለሁ።›› ብለዋል።

እንደ ገለጻው ከሆነ፤ መንገዱ የተዘጋው በኦነግ ሸኔ ታጣቂዎች ሲሆን፤ ለመውጣት ያሰቡ ቁጥራቸው በውል የማይታወቅ በርካታ ተማሪዎች በታጣቂ ቡድኑ ስለመታገታቸው ተነግሯል። ሌላኛው የአካባቢው ነዋሪ ‹‹በታጣቂ ቡድኑ የታገቱ ሰዎች በሕይወት ተመልስው አያውቁም።›› ሲሉ አስታውሰው፤ ሰሞኑን የታገቱት ተማሪዎችም በሕይወት መኖራቸው አጣራጣሪ ነው ብለዋል።

ለበዓል ወደ ነቀምት ያቀኑት ተማሪዎች ብቻ ሳይሆኑ በሥራ ምክንያት ከወለጋ ወደተለያዩ የክልል ከተሞች የሚኖሩ ሰዎችም ናቸው። በበዓል ምክንያት ወደ ነቀምቴ ያቀና አንድ የባንክ ቤት ሠራተኛ (ሥሙን አላስታወሱም) ወደ ሥራ ቦታው ለመመለስ ሲሞክር ‹‹በኦነግ ሸኔ ታጣቂዎች ተገድሏል›› ብለዋል።

በተያያዘም፤ ባሳለፍነው ጳጉሜ 4/2014 በነቀምቴ ዙሪያ ሀሮ በተባለ ቦታ ትራንስፖርት ላይ ከነበሩ 30 ሰዎች መካከል 16ቱ በኦነግ ሸኔ ታጣቂዎች ስለመገደላቸው ተጠቅሷል።

የዘጠኙን ሰዎች ሬሳ ሲነሳ እንደተመለከቱም፣ ሚሊሻ ነኝ ያሉት የአዲስ ማለዳ ምንጭ ገልጸዋል። በሌላ በኩል የተገለጸው፤ ከሳምንታት በፊት በኡኬ ከተማ 55 ሰዎች የኦነግ ሸኔ ታጣቂ ቡድን መገደላቸው ነው።

ቀሪ የአካባቢው ነዋሪዎችም በጥቃቱ ምክንያት ተበታትነው ያሉበት አይታወቅም ተብሏል። ሚሊሻው በተለይም በሰላማዊ ቦታ የነበሩ ተማሪዎች ትምህርታቸው ከመቋረጡም ባሻገር በሕይወታቸው ላይ ጉዳት እንዳይደርስ መንግሥት የመከላከያ ኃይል ሊልክ ይገባል ብለዋል።


ቅጽ 4 ቁጥር 203 መስከረም 14 2015

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here