በመንግሥት ትምህርት ቤቶች የመመዝገቢያ ክፍያ የከፈሉ ተማሪዎች ገንዘባቸው እንዲመለስላቸው ጠየቁ

0
1337

በአማራ ክልል የመንግሥት ትምህርት ቤቶች የምዝገባ ክፍያ ከመታገዱ በፊት ክፍያ የከፈሉ ተማሪዎች የከፈሉት ገንዘብ ተመላሽ እንዲሆንላቸው ጠየቁ።

የአስራ አንደኛ ክፍል ተማሪ የሆነው ኃይለገብርኤል አዳሙ፣ አስራ አንደኛ ክፍልን ለመማር በተመዘገበበት ትምህርት ቤት ለምዝገባ 500 ብር በትምህርት ቤቱ የባንክ ደብተር ቁጥር እንዳስገባ ተናግሯል። ይሁንና ክፍያውን ከከፈለ በኋላ ጓደኞቹ ሳይከፍሉ እንደተመዘገቡ ገልጾ የከፈለው ገንዘብ እንዲመለስለት ማንን መጠየቅ እንዳለበት ግራ እንደገባው አሳውቋል።

አስረኛ ክፍልን በተማረበት ትምህርት ቤትም ለትራንስክሪፕት በሚል አራት መቶ ብር እንደከፈለ የገለጸው ኃይለገብርኤል፣ ቅድሚያ ለትምህርት በመስጠት ይህንን የመመዝገቢያ ክፍያ እንደከፈለ ተናግሮ፣ ገንዝቡ የትምህርት ቁሳቁስ ለማሟላት ይረዳው እንደነበር አሳውቋል።

የመንግሥት ትምህርት ቤቶች እንኳን የምዝገባ ክፍያ ሊጠይቁ ይቅርና የደንብ ልብስና የትምህርት ቁሳቁሶችን አሟልተው ለተማሪዎች እንደሚሰጧቸው የአዲስ አበባ ከተማን ተሞክሮ አንስቶ፤ ይህን ማድረግ ባይቻል እንኳን ወጥ በሆነ መንገድ የምዝገባ ክፍያው ቀርቶ ቀድመው የከፈሉት ገንዝብ እንዲመለስ ጠይቋል።

መስከረም ተደራራቢ ወጪዎች ያሉበት ወር እንደመሆኑና ወቅታዊው የደንብ ልብስና የትምህርት መሣሪያዎች ዋጋ መናር ልጃቸውን ለማስተማር ከባድ እንዳደረገባቸው የሚገልጹት ሥማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ አንዲት እናት፣ ተቀጥረው እንጀራ በመጋገር ከሚያገኟት ገቢ ላይ ቀንሰው ልጃቸው ትምህርት እንድትማር ሲሉ የምዝገባ ክፍያ ከፍለው እንዳስመዘገቧት ተናግረዋል።

ይሁንና ልጃቸውን ካስመዘገቡ በኋላ የምዝገባ ክፍያው እንደቀረ ሰምተው ልጃቸው ወደምትማርበት ትምህርት ቤት ሄደው የከፈሉት ገንዘብ እንዲመለስላቸው ቢጠይቁም ምላሽ እንዳላገኙ ተናግረዋል። አንዴ አምኜ ክፍያውን ብከፍልም ገንዘቡ ተመላሽ ቢሆንልኝ ግን ለልጄ የትምህርት ቁሳቁስ እንዳሟላላት ይረዳኛል ብለዋል።

ልጆቻቸውን ለማስመዝገብ የምዝገባ ክፍያዎችን እንደከፈሉ የተናገሩት ሌላው ሥማቸው እንዲጠቀስ ያልፈቀዱ አባትም፣ አንደኛ ክፍል ለተመዘገቡት ኹለት ልጆቻቸው በትምህርት ቤቱ ቦታ እንዳይሞላባቸው በሚል ቀድመው እንዳስመዘገቧቸው ገልጸዋል። ይሁንና የምዝገባ ክፍያዎች ይቁሙ ተብሎ በሚዲያ ሲሰሙ የከፈሉት ገንዘብ ተመላሽ እንዲሆን የጠበቁ ቢሆንም፣ እስካሁን ምንም ዓይነት መረጃ እንዳልደረሳቸው ተናግረዋል።

ልጆቻቸውን ባስመዘገቡበት ሰዓትም በርካታ ሰዎች የምዝገባ ክፍያ ሲጠየቁ አንከፍልም በማለት ይመለሱ እንደነበር ገልጸው፣ የክልሉ ትምህርት ቢሮ የወሰነው ውሳኔ ትክክል ነው ብለዋል። ይሁንና ከሁሉም ነገር የልጆቻቸውን ትምህርት አስቀድመው በክፍያ ያስመዘገቡ ወላጆች ገንዘባቸው እንዲመለስላቸው ጠይቀዋል።

አዲስ ማለዳ ባደረገችው ማጣራትም ወደ አዲስ ትምህርት ቤት የሚመዘገቡ ሁሉም ተማሪዎች የምዝገባ ክፍያ እንዲቆም እስከታዘዘበት ጳጉሜ 2/2014 ድረስ ክፍያውን ይጠየቁ የነበረ ሲሆን፣ 2014 ሲማሩበት በነበረው ትምህርት ቤት የቀጠሉት ግን አልተጠየቁም።

ይህንን ጥያቄ ለመጠየቅና በክልሉ ትምህርት ቢሮ በኩል ያለውን ምላሽ ለማካተት አዲስ ማለዳ ተደጋጋሚ የስልክ ሙከራ ብታደርግም ስልኮች ባለመነሳታቸው ምክንያት ምላሻቸውን ማካተት አልቻለችም።

የክልሉ ትምህርት ቢሮ ጳጉሜ 2/2014 ለሁሉም ዞኖችና ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮዎች በጻፈው ደብዳቤ፣ ምንም ዓይነት የምዝገባ ክፍያ እንዳይጠየቅ ያሳሰበ መሆኑ ይታወሳል። ቀድመው ስለከፈሉ ተማሪዎች ግን በደበዳቤው ላይ የገለጸው ነገር የለም።


ቅጽ 4 ቁጥር 203 መስከረም 14 2015

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here