ኢትዮጵያን ከጫፍ እስከ ጫፍ አቋርጦ ወደ ደቡብ ሱዳን የሚያልፍ የፋይበር ኦፕቲክ መስመር ዝርጋታ ለማድረግ ከስምምነት መደረሱ ተነግሯል።
የመግባቢያ ስምምነቱ የተደረገው በጅቡቲ መንግሥትና በደቡብ ሱዳን መንግሥት መካከል መሆኑን ዓለም ዐቀፍ የሚዲያ ተቋማት ዘግበውታል። የቻይናው ሲጂቲኤን እንዳስነበበው፣ የኹለቱ አገራት ባለሥልጣናት ካካሄዱት ድርድር በኋላ የፋይበር ኦፕቲክ መስመር ለመዘርጋት የሚያስችላቸውን የመግባቢያ ስምምነት በሳምንቱ መጀመሪያ ለመፈራረም እንደቻሉ ነው።
ከጅቡቲ ተነስቶ ኢትዮጵያን አቋርጦ ደቡብ ሱዳን ዋና ከተማ ጁባ ይደርሳል የተባለው የመሬት ውስጥ ዝርጋታ ምን ያህል ኪሎሜትሮችን እንደሚሸፍን በመረጃው አልተካተተም።
እንደ ኢትዮጵያ ወደብ የሌላት ደቡብ ሱዳን፤ የፋይበር ኦፕቲክ ዝርጋታው እጅግ ይጠቅማታል ማለታቸውን የአገሪቱ የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ፣ የኮምዩኒኬሽንና የፖስታ አገልግሎት ሚኒስቴር መሥሪያ ቤት አሳውቋል። በጅቡቲ ከፍተኛ ባለሥልጣናትና ከደቡብ ሱዳን የኢንፎርሜሽን ሚኒስትር መካከል የተፈረመው የመግባቢያ ሰነድ ለቀጣይ ሥራዎች በር የሚከፍት ነው ተብሎለታል።
የባለሙያዎች ስብስብን የያዘ ኮሚቴ ከኹለቱም አገር ዜጎች ተዋቅሮ፣ ባለሙያዎቹ ሥራ እንዲጀምሩ ያደርጋል የተባለለት የመግባቢያ ሰነድ፣ በቀጣይ ስለሚኖሩ ቴክኒካዊ ጉዳዩች ለመሥራትና አጠቃላይ ስምምነት ለማድረግ የሚያግዝ ነው ተብሏል።
የደቡብ ሱዳን የኢንፎርሜሽን ሚኒስቴር መሥሪያ ቤትን ዋቢ አድርጎ መረጃውን ይፋ ያደረገው የዜና አውታሩ፣ ከደቡብ ሱዳን የኢንፎርሜሽን ሚኒስቴር ከሆኑት ሚካኤል ማኩይ ጋር ስምምነቱን የፈረሙት የጅቡቲ ባለሥልጣናት እንደሆኑ ቢናገርም፣ ረጅም ርቀት አቋርጧት ስለሚያልፈው ኢትዮጵያ ግን ምንም የተባለ ነገር የለም።
ከኢትዮጵያ ባለሥልጣናት ጋር ስምምነት ስለመደረጉም ይሁን በየት በየት እንደሚያልፍ ስለመታወቁ በዘገባው ላይ ባይካተትም፣ ደቡብ ሱዳን ይህን የፋይበር ኦፕቲክ ዝርጋታ የምታደርገው ብቸኛው እንዳልሆነ ተጠቅሷል። በኬንያ በኩልም ሌላ የመስመር ዝርጋታ እንደሚደረግ የተጠቆመ ሲሆን፣ የአገሪቱን ቀርፋፋ የኢንተርኔት አገልግሎት ለማቀላጠፍና ወጪንም ለመቀነስ ያግዛል መባሉ ተሰምቷል።
ስምምነቱ ከሰባት ዓመት በፊት የተፈረመውንና ከኬንያ በኩል የሚዘረጋው የፋይበር ኦፕቲክ መስመር በዓለም ባንክ እርዳታ እንደሚከናወን ያመላከቱት ባለሥልጣናቱ፣ ኢትዮጵያን አልፎ የሚዘረጋውን መስመርን ማን እንደሚደግፈውም ሆነ በማን እንደሚከናወን ከማመልከት ተቆጥበዋል ተብሏል። ፕሮጀክቱ የሚተገበርበት ዝርዝር ቴክኒካዊ ጉዳይ ላይ የሚያጠናውና አሁን የሚመሠረተው የባለሙያዎች ቡድን ስምምነት ሲደረስ መረጃው እንደሚወጣ ተጠቁሟል።
የኔትወርኩ ዝርጋታ ለደቡብ ሱዳን እጅግ አስፈላጊና ከዓለም አገራት ጋር የሚያቆራኛት መሆኑን የተናገሩት ባለሥልጣናቱ፣ አገራቸው እስካሁን የምታወጣውን ከፍተኛ ወጪ ያስቀርላታል ሲሉ መናገራቸውንም ዘ ኢስት አፍሪካን አስነብቧል።
ለዝርጋታው የተያዘው በጀትም ሆነ ኢትዮጵያ በስምምነቱ ላይ ያላት ድርሻም ሆነ ተጠቃሚነት ዙሪያ ምንም ያልተባለ ሲሆን፣ አዲስ ማለዳ ዝርዝር መረጃ ለማግኘት ያደረገችው ሙከራ ሳይሳካ ቀርቷል።
የደቡብ ሱዳን ከፍተኛ ባለሥልጣናትን ያካተተ የልዑካን ቡድን በዚሁ ሳምንት በአዲስ አበባ የገባ ሲሆን፣ በገንዘብ ሚኒስቴር ሚኒስትር አሕመድ ሽዴ የተመራው የሚኒስትሮች ቡድን እና በደቡብ ሱዳን ምክትል ፕሬዝዳንት ታባን ዴንገ ጋጅ ከተመራው የሚኒስትሮች ቡድን ጋር በኹለቱ አገሮች የመሠረተ ልማት አውታሮች ግንባታና አጠቃቀም የጋራ ምክክር ማድረጋቸውን ገንዘብ ሚኒስቴር አስታውቋል።
የኹለቱ አገራት ከፍተኛ ባለሥልጣናት ኢትዮጵያና ደቡብ ሱዳን በመንገድ መሠረተ ልማት፣ በኢነርጂ፣ በቴሌኮምዩኒኬሽን፣ በውሀ ላይ ትራንስፖርትና በሌሎች የኢኮኖሚ ዘርፎች ተሳስረው የጋራ ተጠቃሚነታቸውን ወደ ከፍተኛ ደረጃ በሚያሳድጉበት እቅድ ላይ ሰፊ ውይይት አድርገው መግባባት ላይ ደርሰዋል ተብሏል። ይሁን እንጂ ስለ መስመር ዝርጋታው በይፋ የተነገረ ነገር የለም።
ቅጽ 4 ቁጥር 203 መስከረም 14 2015



