ሽምግልና ይከበር!

0
1238

የሰው ልጆች አብረው ሲኖሩ ግጭት መፈጠሩ አይቀሬ ስለሆነ አለመግባባታቸውን የሚፈቱበት ሰላማዊ ሥርዓት መኖሩ አስፈላጊ ነው። ጉልበትን ተጠቅሞ ግጭትን ለመፍታትም ሆነ እልባት ለመስጠት ኃይል አማራጭ ሊሆን ቢችልም፣ መፍትሔነቱም ጊዜያዊ መሆኑ አይቀርም።

ግጭትን ለማብረድም ሆነ ዘላቂ እርቅን ለማምጣትና ወደነበሩበት ቅርርብ ለመመለስ ሽምግልናን የመሰለ ውጤታማ መንገድ እንደሌለ እሙን ነው። በአገር ሽማግሌዎችም ሆነ በሃይማኖት አባቶች የሚደረግ የማሸማገል ድርጊት ከግጭት አስቀድሞም ሆነ ከግጭት በኋላ ውጤታማ ስለመሆኑ በርካታ ምሳሌዎችን ማቅረብ ይቻላል።

በዓለማችን የተካሄዱ አብዛኞቹ ጦርነቶችም ሆኑ አለመግባባቶች ከብዙ ደም ማፋሰስም በኋላ ቢሆን በእርቅ ስምምነት እንደተቋጩ ይታወቃል። አሸናፊ ወገን ቢኖር እንኳን ሰላማቸው ዘላቂ እንዲሆን በአሸማጋዮች አማካኝነት ድርድር አድርገው ይስማማሉ። አንደኛው ወገን ጉልበትን ተጠቅሞ ሌላውን የሚጫን ፍትሐዊ ስምምነት የማያደርግ ከሆነ፣ እንደኹለተኛው የዓለም ጦርነት መነሻ ሌላ ጦርነትን መጥመቁ አይቀሬ ነው።

ሰው ያመነበትን ነገር ጉልበተኛ ስላስገደደውም ሆነ አማራጭ ስላጣ ጊዜ እስኪደግፈው ያምን ይሆናል እንጂ፣ በዘላቂነት ሰጥ ለጥ ብሎ ለማይፈቅደው እንደማይገዛ አዲስ ማለዳ ትረዳለች።

ሰላም ለማምጣት ተፋላሚ ወገኖች ትልቁን ድርሻ ቢወስዱም፣ አሸማጋዮችም የሚጫወቱት ሚና ከፍተኛ ነው። የተጣላ ተፋላሚ ወገን ይቅርና ኹለት ግለሰቦች ቢጋጩ እርስ በርስ ለመታረቅ ወይም ለግጭታቸው መፍትሔ ለመፈለግ የሽምግልና ሚናው የጎላ ነው።

የሰው ልጅ በአብዛኛው ግብዝ ነው እንደመባሉ፣ ራሱ ጠይቆ ለመታረቅም ሆነ ለመስማማት ባሕሪው ላይፈቅድለት ይችላል። ስለዚህም ተብሎ በማኅበረሰቡ ውስጥ ያሉ ተሰሚነት ያላቸው የእድሜ ባለጸጋዎች በራሳቸው ተነሳሽነትም ሆነ በማኅበረሰቡ ጥያቄ፣ አልያም በተጋጩት አካላት አሳሳቢነት ሊያሸማግሉ ይችላሉ።

ታዲያ እኚህ ትልቅ ማኅበራዊ ኃላፊነትን የሚወጡ ሽማግሌዎችም ሆኑ አደራዳሪዎች ለዘመናት የቆየው ሥርዓት እንዳይፈርስና እርስ በርስ መተማመኑ እንዳይጠፋ ሊከበሩ ይገባል። ቃላቸው እንዳይታጠፍም እነሱ ብቻ ሳይሆኑ ሊያስታርቋቸው የሚለፉላቸው ወገኖችም ሆኑ አጠቃላይ ማኅበረሰቡ ተግባራዊ ለማድረግ መሥራት እንደሚጠበቅበት አዲስ ማለዳ ማስገንዘብ ትወዳለች።

ኢትዮጵያ በታሪኳ ግጭት ተለይቷት እንደማታውቀው ሁሉ፣ አደራዳሪና አስማሚ ሽማግሌዎችንም አጥታ አታውቅም። ከታሪክ እንደምንረዳው፣ እነዚህ በየዘመናቱ መኳንንቱንም ሆነ ተራውን ማኅበረሰብ የሚያሸማግሉ የአገር ሽማግሌዎችም ሆኑ የሃይማኖት አባቶች ተሰሚነታቸው የጎላ ነበር።

ከቅርብ ዓመታት ጀምሮ ግን ይህ የክብራቸው ሁኔታ የተቀየረ ይመስላል። አፄ ቴዎድሮስ ከባላንጣዎቻቸው ጋር ያደረጉት በርካታ ሽምግልናና ድርድር ውጤታማ ሆኖ በአብዛኛው የዘለቀ ቢሆንም፣ ከወንበዴና ባሪያ ሻጮች ጋር ያደረጉትና ለእርቅ ጠርተው የወሰዱባቸው እርምጃ ከዛ ጊዜ በኋላ በቀሪ ዘመናቸው አብዛኛው እንዳያምናቸው ማድረጉ በታሪክ ተመዝግቦ ይገኛል።

ከንጉሠ ነገሥቱ በኋላ የነገሡት አፄ ዮሐንስም ሆኑ አፄ ምኒልክ፣ እንዲሁም ንጉሥ ተክለሃይማኖት እርስ በርሳቸው በነበራቸው ሽኩቻ ሕዝብ እንዳያልቅ ሲባል ቅራኔያቸውን በእርቅና በድርድር እንዲፈቱ ሽማግሌዎችና የሃይማኖት አባቶች የነበራቸው ሚና ከፍተኛ ነበር። አንዳቸው ሌላኛቸውን ማክበር ብቻ ሳይሆን የአሸማጋዮቹ ቃል እንዳይታጠፍ ጉልበት እያላቸው ያደረጉት ታማኝነት እስከአሁን ሲያስመሰግናቸው ቆይቷል።

ይህ የሽማግሌ ሚና የሚከበርበትና ቃልን ማፍረስ እንደጦር የሚፈራበት ዘመን ቀስ በቀስ እንዲመናመንና ሰው ጥላውንም እንዳያምን የተደረገበት ዘመን ላይ የደረስን ይመስላል። ይህ የሆነበት የራሱ ምክንያትና ሂደት ቢኖረውም በታሪክ የተቀመጡ አንኳር ጉዳዮችም ነበሩ።

አፄ ምኒልክ አልጋውን እንዲወርሱ በተናዘዙላቸው ልጅ እያሱ እና መኳንንቱ በሚደግፏቸው አፄ ኃይለ ሥላሴ መካከል የነበረው ቅራኔ ወደ ጦር መማዘዝ ሲያመራ ሽማግሌዎች መሃል ገብተው ነበር። የቶራ መስክን ድል የጨበጡት ንጉሥ ሚካኤል ወደ መናገሻዋ ከተማ ገስግሰው ሥልጣኑን ሙሉ በሙሉ እንዳይቆጣጠሩ የሰጉ ባላንጣዎቻቸው ሽማግሌ ልከው ግስጋሴያቸውን አስቁመው ነበር።

አለመግባባታቸውን በእርቅ እንዲፈቱና ተጨማሪ ደም መፋሰስ እንዳይከሰት ብለው አሳምነው ለሳምንታት አዘናግተው ካስቀመጧቸው በኋላም፣ አጋዥ ኃይል ሲደርስላቸው በሰገሌ ጦርነት ገጥመው የእርቁን ቃል አጥፈው ጉድ በመሥራታቸው ታሪካቸው ላይ የሽምግልና ተግባር ለሴራ ማስፈጸሚያ መሆኑ ተመዝግቧል።

በኋላ ላይ “አያሌው ሞኙ ሰው አማኙ” ያስባለው ታሪክ፣ እንዲሁም የበላይ ዘለቀ አጠራርና አሟሟት መንግሥትን ከማመን ይልቅ ሽምግልና የመጡትን ወደአለማመን ተቀይሮ እንደነበር ከታሪካቸው መመልከት ይቻላል። ደርጉ ሲቋቋምም ለስምምነት ተብሎ ቢሆንም፣ ቃል ታጥፎ እርምጃ ይወሰድባቸዋል በሚል የማይወደዱ አባላት እጩ ተወካይ ተደርገው ስለመላካቸው ተመዝግቦ ይገኛል።

ይህ ዓይነት አለመተማመን እየጎላ ሄዶ ጫካ በነበሩ ነፍጥ ባነገቡ ቡድኖች መካከልም እርስ በርስ መጠላለፍ ብቻ ሳይሆን ሽምግልናን እንደጦር መሣሪያ አድርጎ መጠቀም ተለመደ ማለት ይቻላል። በተለይ ባለፉት ጥቂት ዐስርት ዓመታት የሕወሓት መሪዎች እንደስልት የተጠቀሙበት ይህ የማታለያ ዘዴ አሁን ድረስ እርስ በርስ መተማመን እንዳይኖር ከማድረጉ ባሻገር አሁንም ባለሥልጣናት ለማጥመጃ እየተጠቀሙበት ይገኛል።

የሰሜኑን ጦርነት በድርድር ለመፍታት የሚጥሩ አካላት የአገር ውስጥም ይሁኑ የውጪዎቹ በተደጋጋሚ ሲናገሩ፤ ለማስማማት የሚያስችል መተማመን በኹሉም ወገን እንደሌለ ሲያመላክቱ ቆይተዋል። ይህ ታሪክ ያመጣው ያለመተማመን ኹኔታ ለሚደረገው የሰላም እንቅስቃሴ እንቅፋት እንደሆነ አዲስ ማለዳ ታምናለች።

ሰላም እያደር እየራቀ የመጣ በመሰለበት በዚህ የጦርነት ወቅት፣ አማራ ክልል ባህርዳር ሆነ ተብሎ የተሰማው የባሰ አለመተማመን ውስጥ እንደተገባ የሚያሳይ ነው። መንግሥት በሽምግልና አማካኝነት ወደከተማ እንዲመጣና እንዲወያይም ሆነ እንዲደራደር ቃሉን ሰጥቶ ያስመጣውንና በርካታ ተከታይ ያለውን የጦር መሪ እንደወንጀለኛ ‹አድኜ ያዝኩ› የሚል መግለጫ ማውጣቱ በቋፍ የነበረን የሰላም ጥረት ገደል የሚከት ነው።

“ቃል ከሚጠፋ የወለዱት ይጥፋ” ብሎ የሚያምንን ማኅበረሰብ እያስተዳደርኩ ነው የሚል አካል፣ ሽምግልናን እንደ ስልታዊ ታክቲክ ተጠቀምኩበት ብሎ ሳያፍር መናገሩ መጪው ጊዜ ምን ያህል ሊከፋ እንደሚችል አመላካች ነው። ተቀናቃኝም ሆኑ ተፋላሚ ወገኖች እርስ በርስ ባይከባበሩ እንኳን፣ ለኢትዮጵያዊያን ትልቅ ቦታ ያላቸውን ሽማግሌዎችንና ተግባራቸውን እንዲያከብሩ አዲስ ማለዳ በአጽንዖት ታሳስባለች።


ቅጽ 4 ቁጥር 203 መስከረም 14 2015

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here