አዳዲሶቹ የሸገር ጭማቂ ቤቶች

0
1113

በአዲስ አበባ ከተማ ዘመናዊ ሕንጻዎች ያሉባቸውን እና በአንጻሩ ገና በኹለት እግራቸው ለመቆም የሚንገዳገዱ ሰፈሮችን ተመሳሳይ የሚያደርጋቸው አንድ ነገር አለ። ይህም በየደጁ የተከፈቱ የሚመስሉ በርካታ ጣፋጭ ኬኮችን የሚያቀርቡ ካፌዎች፣ ጥላ ሥር ሆነው ‘ኑ ቡና ጠጡ’ የሚሉ ባለ ቡናዎች፣ ምግብና መጠጥ ቤቶች መታየታቸው ነው። ከዚሁ ጋር ሳይርቅ ቀድሞ በብዙ ርቀት ይገኙ የነበሩ የጭማቂ (‘ጁስ’) ቤቶች አሁን በረድፍ ሆነዋል። ይህም ተጠቃሚ ለመኖሩ ማሳያ ነው። አዲስ ማለዳም ወደ ተወሰኑት ጭማቂ ቤቶች ጎራ ብላ ነበር።

ሕሊና እና ኹለት ጓደኞቿ ገርጂ መብራት ኀይል አካባቢ በሚገኘው ሐበሻ አትክልትና ጁስ ቤት ተሰብስበዋል። በሳምንት ውስጥ አንድ ወይም ኹለት ጊዜ ሰብሰብ ብለው መጫወት ሲፈልጉ ምርጫቸው አትክልት ቤት እንደሆነ ሕሊና ከአዲስ ማለዳ ጋር ባደረገችው አጭር ቆይታ ትናገራለች። በእነዚህ የጁስ ቤቶች በተጨማሪ በርገር እና መሰል ምግቦች የሚቀርቡ መሆኑም ለተሰባሰቡ ጓደኛማቾች ምርጫውን አብዝቶ ቦታውን ተመራጭ እንዳደረገላቸው ትገልጻለች።

ይሁንና ሕሊናም ሆኑ ጓደኞቿ በደንበኝነት በሚያውቋቸውና ሥራ ይበዛባቸዋል ብለው በሚያምኗቸው የፍራፍሬ ጭማቂ ወይም ጁስ ቤቶች ይጠቀማሉ እንጂ የማያውቁት አዲስ ቦታ ጭማቂ አዝዘው ለመጠጣት አይደፍሩም። በጋራ ከሕሊና ሐሳብ ጋር የሚስማሙ ጓደኞቿም ፍራፍሬዎች ቢበላሹ ጤናን ለማወክ በጣም ቅርብ መሆናቸውና ለመበላሸትም ብዙ የማይፈጁ ናቸው ብለው ስለሚያምኑ ከሚያውቋቸውና አሠራራቸው ግልጽ ሆነው ከሚታዩ ጭማቂ ቤቶች ውጪ ከመጠቀም ይቆጠባሉ።

ከመካከላቸውም ከዚህ ቀደም ከተበከለ ምግብ ጋር የተያያዘ የጤና እክል የገጠማቸው መኖራቸውን ተናግረዋል። ምንም እንኳን ያ አጋጣሚ ቢከሰትም ከፍራፍሬ ጭማቂ አልተለያዩም። በየቤታቸው ፍራፍሬ ገዝቶ መጠቀም ቢችሉ እንኳን ሰብሰብ ብሎ ጥሩ ጊዜ እያሳለፉ ጭማቂ መጠጣቱን ስለመረጡ፣ በጭማቂዎች ውስጥ ሎሚን በብዛት በመጠቀም እንዲሁም ንጹሕ ጭማቂ ያቀርባሉ ብለው ያመኗቸው አትክልት ቤቶች በመሔድ ተጠቃሚነታቸውን ቀጥለዋል።

አንዳንድ የፍራፍሬ ጭማቂ ቤቶችም ይህንን የሕሊናን እና የጓደኞቿን ስጋት የተረዱት ይመስላል። መጋቢት 17/2005 ሥራውን አሃዱ ብሎ የጀመረው የዮሮ ሼክ ጁስ ዋና ሥራ አስኪያጅ አለበል ቢልልኝ፤ ንጽሕና እና ጥራቱን የጠበቀ የፍራፍሬ ጭማቂ ማቅረብ ወሳኝ እንደሆነ ይናገራሉ። እርሳቸው የሚመሩት ድርጅትም ንጽሕናውን የጠበቀና ጥራት ያለው ጭማቂ ማቅረብን ዓላማው አድርጎ የተነሳ መሆኑን ይገልጻሉ።

አለበል ከአዲስ ማለዳ ጋር ባደረጉት ቆይታ ሲናገሩ፤ ጭማቂ ቤቱ ሥራ ሲጀምር ከተለመደው መንገድ ወጣ ማለትን መርጧል ብለዋል። “ብዙ ሰው የፍራፍሬ ጭማቂ የመጠጣት ፍላጎት አለው። ነገር ግን ለጤንነቱ ስለሚሰጋና ንጽሕናውን ስለሚፈራ አይጠጣም ነበር” ያሉት አለበል፤ ዮሮ ሼክ ጁስ ሥራውን ሲጀምር በንጽሕና እንዲሁም ደንበኛ ሊመለከት በሚችልበት ሁኔታ ጭማቂ ማዘጋጀትን መርጠው በዛ መንገድ ሥራውን እንደቀጠሉ ይናገራሉ።

ታድያ ግን ከሚያቀርቡት ጭማቂ ጋር ሥያሜያቸው ሳያስጨንቃቸው አልቀረም፤ አለበል እንዳሉትም “ሁሉም ሰው ቢዝነስ ሲጀምር ሥያሜውን በውጪ ሥም ሲያደርግ ትኩረት ይስባል። ያንን አስበን ንጽሕናውን ጠብቀን መሥራቱ ላይ ሳንዘናጋ ኢውሮፕ ጁስ ቤት ብለን ነው የጀመርነው።”

ይህም ቤቱ ተቀባይነት እንዲያገኝ አንድ አስተዋጽዖ ነበረው። በዚህም መሠረት ሃያ ኹለት ከጌታሁን በሻህ ሕንጻ ወደ ቦሌ የሚወስደው መንገድ ላይ ጠበብ ያለች ክፍል ካላት ቤት ውስጥ በረንዳው ላይ ሳይቀር በርካቶች መኪናቸውን አቁመው ጎራ ማለት አዘወተሩ። ኢውሮፕ ጁስ ቤት መጠሪያም በደንበኞች አጠራር ዮሮ ተባለ፤ ከዛን ጊዜ ጀምሮም በአዲስ አበባ አምስት በሚጠጉ አካባቢዎች ቅርንጫፍ ከፍቶ አሁን ድረስ ዮሮ ሼክ ጁስ ደንበኞቹን እያስተናገደ ይገኛል። አለበልም “ውጤቱ እንዳሰብነው ጥሩ ነበር” ሲሉ ያስታውሳሉ።

በእርግጥ ዮሮ ሼክ ጁስ ለብዙዎች በሚታይ መልኩ በጭማቂ ላይ አዲስ አቀራረብ ይዞ የመጣና ፍላጎትም የፈጠረ ድርጅት ነው ማለት ይቻላል። በዚህ አጋጣሚ በተፈጠረው ውድድር የገቡ ነባር ጭማቂ ቤቶችም አቀራረባቸውን በተወሰነ መልኩ ቀይረዋል። አንዳንዶችም ቋሚ ደንበኞች ያሏቸው በመሆናቸው ደንበኛ ማጣት ሳያሳስባቸው ሥራውን በቀደመው አሠራር ቀጥለዋል። ለምሳሌም አራት ኪሎ ብርሃንና ሰላም ማተሚያ ድርጅት አለፍ ብሎ መደዳውን ያሉ ጭማቂና አትክልት ቤቶችን መታዘብ ይቻላል።

አበራ ኃይሉ (ሥማቸው የተቀየረ) ብዙ ጊዜ ቁርሳቸውን የሚመገቡት አራት ኪሎ ከነማ መድኀኒት ቤት አጠገብ ከሚገኙ አትክልትና ጭማቂ ቤቶች በአንዱ ነው። ጣፋጭ ዳቦን ከአቮካዶ ጭማቂ ጋር መጠቀም ያዘወትራሉ። በጤናቸው ላይ ችግር ገጥሟቸው እንደማያውቅና የቤቱ ደንበኛና የብዙ ጊዜ ተጠቃሚ በመሆናቸውም በእምነት እንደሚጠቀሙ ይገልጻሉ።

“ፍራፍሬ መመገብ ለጤናም ጥሩ እንደሆነ በተለያየ ጊዜ ሲነገር ሰምቻለሁ” የሚሉት አበራ፤ ፍራፍሬ ለጤና የሚሰጠውን ጥቅም አስበው ባይሆንም የፍራፍሬ ጭማቂ ስለሚወዱ አዘውትረው እንደሚጠቀሙ ያነሳሉ። በተረፈ ግን የፍራፍሬና አትክልት መሸጫ ቤቶች ለደንበኞቻቸው ጤንነት መጨነቅና ለሚያቀርቡት ምግብ መጠንቀቅ አለባቸው ሲሉ ገልጸዋል። “የእነዚህ ቤቶች ሥራ የእኛ ጤናማ መሆን ነው። ጥሩ ነገር የማያቀርቡ ከሆነ የእነርሱም ሥራ ስለሚበላሽ፤ ሀብታቸውም ደንበኞቻቸው ስለሆንን ጥሩ ነገር ማቅረብ ላይ ሊጠነቀቁልን ይገባል” ሲሉም አስተያየታቸውን ይሰጣሉ።

የሥነ ምግብ ባለሙያ የሆኑት ዶክተር አብዱላዚዝ አሊ ፍራፍሬዎችን አብዝቶ መጠቀም በጎ ተጽዕኖ አለው ሲሉ ይናገራሉ። ቅባት የበዛባቸው፣ ሥጋ እንዲሁም መሰል ምግቦች ለጤና ሲባል ገደብ እንደሚደረግባቸው፤ ነገር ግን ፍራፍሬና አትክልት ግን ለጤና ጉዳት የሌላቸው በመሆኑ ያለገደብ መመገብ የሚችሏቸው ምግቦች እንዲሁም ጤናማ ናቸው ሲሉ አብዱላዚዝ ይናገራሉ። እነዚሁ ከተፈጥሮ የሚገኙ ምግቦች ለሰውነት አስፈላጊውን ንጥረ ነገር፣ ቫይታሚንና ሚንራሎች በተለይም አሰር (‘ፋይበር’) ያላቸው በመሆኑ፣ የሚደገፉ የምግብ ዓይነቶች መሆናቸውን አያይዘው ይጠቅሳሉ።

“ይህን ስንል ግን ትኩሶቹን ነው እንጂ የታሸጉትን አይደለም” ሲሉ ያከሉት አብዱላዚዝ የሚጨመቀው ይለያያል፤ “በቤት የሚጨመቀውን የምንጠቀመው በማጥለል ስለሆነ ምናልባት አሰሩ ጠልሎ ይቀራል፤ ከዛም ውሃውን ብቻ ነው የምንወስደው። ፋይበር አንዱ የፍራፍሬ ጥቅም ስለሆነ ያንን እናጣ ይሆናል፤ ጥቅሙንም እንቀንሳለን።” ዶክተር አብዱላዚዝ እንዳሉት።

በፋብሪካ ታሽገው የሚቀርቡ የፍራፍሬ ጭማቂ መጠጦች ግን ብዙውን ጊዜ በመቆየት ምክንያት የምግብነት ይዘታቸውን ያጣሉ። ከዛም ባለፈ ለማቆያ ተብሎ ጥቅም ላይ የሚውሉ ተፈጥሯዊ ያልሆኑ ኬሚካሎች በጤና ላይ ጉዳት እንዲያደርሱ ሊያደርግ እንደሚችል በተለያየ ጊዜም ሲነገር እንሰማለን። ይህም ተጠቃሚ ጥንቃቄ ሊያደርግበት የሚገባ ጉዳይ ነው። በፍራፍሬ ጭማቂ ብቻም ሳይሆን የተለያዩ ወደ ሰውነት በሚገቡ ምግቦችን በተመለከተ ሲነሳ የታሸጉትን መጠቀም ላይ መቆጠብ እንዲኖር የጤና ባለሙያዎች ከመናገር ቦዝነው አያውቁም።

ከዚህም ባሻገር እጅግ በጣም የበሰሉ ፍራፍሬዎች ለጭማቂ ተመራጭ አድርገው የሚያስቡ መኖራቸውን ደግሞ አለበል ያነሳሉ። ፍራፍሬ አቅራቢ ነጋዴዎችም በጣም የበሰሉትን ለብቻ ለይተው ለጭማቂ አቅራቢ ሰዎች እንደሚያቆዩት ይናገራሉ። ይህ ግን ተገቢ እንዳልሆነና ፍራፍሬዎችን በጥሬውም ሳይሆን በጣምም ሳይበስሉ ነው መጠቀም የሚያስፈልገው ባይ ናቸው። በበኩላቸው በድርጅቱ በስለው የቆዩ ፍራፍሬዎችን እንደማይጠቀሙ ይጠቅሳሉ።

“ኀላፊዎች ሁሌ ሥራ ቦታ ላይ ላንገኝ እንችላለን። ስለዚህ ለሠራተኞቻችን ማንኛውንም ጭማቂ ስትሠሩ እናንተ ደስ ያላላችሁ ፍራፍሬ ካለ ጣሉት ነው የምንላቸው። ከጤንነት አኳያ ፍሬሽ ማቅረብ ስላለብን” ይላሉ አለበል። ያም ብቻ ሳይሆን ተፈጥሯዊ ያልሆኑ (‘አርቴፊሻል’) የሆኑ ነገሮችን እንደማይጠቀሙም ነው ያወሱት። እንደ ደንበኛ ትዕዛዝና ፍላጎት ግን በተለየ በወተት እንዲሁም በቫኒላ የሚሠሩ ጭማቂዎች መኖራቸውን ጠቅሰዋል።

“ሰዉ የፈለገውን ማዘዝ ይችላል፤ ለብቻቸው ተጨምቀው የሚቀርቡ እንዳሉ ሁሉ እንደሰዉ ፍላጎት ይቀላቀላል” ያሉት አለበል፤ “ስፔሻል” የሚባለው ጁስ ወይም ጭማቂ በደንበኞቻችን ተመራጭ ነው ይላሉ። “ስትሮበሪ”ም ከሁሉ የበለጠ ተወዳጅ እየሆነና እየተለመደ እንደመጣ አለበል ይጠቅሳሉ። በበኩላቸው ታድያ አሳሳቢ ጉዳይ ነው ያሉት አትክልት ሻጮች በጣም በስለው ሊጣሉ የደረሱትን ለጭማቂ ብለው ማቆየታቸውን ነው።

እንደ ዶክተር አብዱላዚዝ ሙያዊ አስተያየት አንዳንድ ፍራፍሬዎች በጣም በበሰሉ ቁጥር ጣፋጭነታቸውን በመጨመር ወደ ቀጥተኛ ስኳርነት ይቀየራሉ። እዚህ ላይ ለአብንት ማንጎን ጠቅሰዋል። ይህም ፍራፍሬዎች በተፈጥሮ ያላቸው የስኳር መጠን ጤናማና አስፈላጊ ሆኖ ሳለ እየበሰሉ ሲሔዱ ግን ስኳሩ ይዘቱን ይቀይራል ነው። ከዛ ባሻገር ደግሞ መጠንቀቅ የሚያስፈልጋው መብሰሉ በጨመረ ቁጥር ባክቴሪያ ይባዛል፣ ፍራፍሬዎችም በቀላሉ ወደ መበላሸት ያመራሉ። ስለዚህም በዚህ ላይ ግንዛቤ ቢኖር ጥሩ ነው ብለዋል። ከሁሉም ግን ሰዎች የፋብሪካ ምርት የሆኑ የታሸጉ ጭማቂዎችን ሳይሆን ትኩስ የሆኑ የፍራፍሬ ጭማቂዎችን እንዲጠቀሙ መክረዋል።

ቅጽ 1 ቁጥር 51 ጥቅምት 15 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here