የድምጻዊው ድንገተኛ እረፍት

0
1017

የመስቀል በዓል በዋለበት በዚህ ሳምንት ከተሰሙ እጅግ አሳዛኝ ክስተቶች መካከል አንደኛው ነው፤ የድምጻዊ ማዲንጎ አፈወርቅ ዜና እረፍት። ብዙዎችም ከበዛ ድንጋጤ ጋር ባለማመን ውስጥ ሆነው ነው ዜናውን ሲቀባበሉት የነበረው። በእርግጥም ድንገተኛ እና እጅግ አስደንጋጭ ዜና ነበር።

ይህን ተከትሎም በማኅበራዊ ገጾች ላይ ሐዘናቸውን እየገለጹ ሐሳባቸውን ሲያጋሩ የነበሩ ሰዎች ጥቂት አይደሉም። በአንጻሩ ደግሞ ይህንኑ አስታክከው ‹ዓለም ከንቱ!› እያሉ የሰው ልጅ እንዲነቃ ሲያሳስቡና ክስተቱን መነሻ አድርገው ‹ሲሰብኩ› የታዩ ነበሩ።

አንዳንዶች መለስ ብለው የድምጻዊ ታምራት ደስታን ኅልፈት በማውሳትና ተመሳሳይነት አለው በማለት ሲጠቅሱ ተስተውሏል። ‹የሕክምና ስህተት› ይሆናል ሲሉ በስጋት ሐሳባቸውን ያነሱም አልጠፉም። በተለይም ‹ድምጻዊ ማዲንጎ ለሕክምና ያቀናበት መካከለኛ ክሊኒክ ታሽጓል።›› መባሉን ተከትሎና በተያያዘ የተነሱ ጉዳዮች፤ ተጨማሪ እውነት ይሁኑ ሐሰት ካልተረጋገጡ ‹መረጃዎች› ጋር ተዳምረው፣ በርካቶች ነገሩ ከሕክምና ስህተት ጋር የተገናኘ ሊሆን ይችላል እንዲሉ ሳያደርግ አልቀረም።

በሌላ በኩል ደግሞ አንድ የማኅበራዊ ድረገጽ ላይ ጦማሪ የመስከረም ወር መግቢያ ላይ ለአንባብያን ያቀረበው አንድ አጠር ያለ ጦማር ነገሩን ይበልጥ አስደንጋጭ አድርጎታል። ጦማሪው አሁን ላይ ባለሀብቶች ከፍተኛ መጠን ያለው ብር በመመደብ ‹በዚህ ወር ታዋቂ ሰው ይሞታል አይሞትም?› እያሉ ማስያዝ ወይም መቆመር መጀመራቸውን የሚናገር ጽሑፍ ነው ያስነበበው።

ምንም እንኳ የዚሀ ጽሑፍ አቀራረብና አጻጻፍ ቀልድና ጨዋታ ቢመስልም፣ ብዙዎች በቁምነገር የተቀበሉት ይመስላል። በድምጻዊው ኅልፈት የተሰማቸውን ከመግለጽ ጎን ለጎን ‹ይህ ነገር እውነት ነው ወይ?› ብለው የሚጠይቁና፣ ከዛ ሲያልፍ ደግሞ እውነት ይሁን አይሁን ባይታወቅም በጉዳዩ ላይ ትችት እያቀረቡ ያሉ ነበሩ።

ከዛ ባለፈ ደግሞ በድምጻዊው ኅልፈት ዙሪያ ሲያነሱ፣ የሰማይ እጣ ፋንታን ጭምር እየመዘዙ የሚነታረኩም አልጠፉም። አንዳንድ ‹ሀይማኖታዊ› ነን ያሉ ማኅበራዊ ገጾች ሳይቀሩ፣ ‹ለዚህ ነው (ሞት እንዲህ ስለሚወስድ ነው) በእኛ ሀይማኖት ጥላ ስር ሁኑ የምንለው!› በሚል ያስነበቡት መልዕክት እጅግ ሲያስኮንናቸው፤ ከብዙዎችም ትችት ሲያሰነዝርባቸው ታይቷል።

በሌላ በኩል ተደብቀው የቆዩ የድምጻዊው የበጎ አድራጎት ሥራዎች በተለያየ አውድ ሲነገሩ ተደምጧል። ‹ሥሜ አይጠቀስ፣ ማንነቴ አይነገር› እያለ ያገዛቸው ሰዎች በርካታ መሆናቸውንም ይህንኑ በማስተባበር ሲሠሩ የቆዩ የሚድያ ባለሞያዎች ሲመሰክሩ ተሰምቷል። ከዛም ባሻገር ለአገሩ በሙያው በሰጠው አገልግሎት ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ጀምሮ በተለያዩ የመንግሥት ኃላፊነት ላይ ባሉ ሰዎች ሥራውና ሥሙ ተነስቷል።

የድምጻዊ ማዲንጎ አፈወርቅን ኅልፈት ተከትሎ፣ በለጋነት እድሜና ብዙ ለመሥራት በሚችሉበት ወቅት ከዚህ ዓለም በሞት የተለዩ አንጋፋ ከያኒያን ታውሰዋል። ለሁሉም የነፍስ እረፍትን እንመኛለን። ለድምጻዊ ማዲንጎ አፈወርቅ ቤተሰቦች፣ ወዳጆች፣ የሥራ አጋሮችና አድናቂዎቹ፣ ሐዘን ለተሰማቸውም ሁሉ መጽናናትን ይስጥልን!


ቅጽ 4 ቁጥር 204 መስከረም 21 2015

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here