የአፋር – ሶማሌ የድንበር ውዝግብ እና ውጤት አልባዎቹ መፍትሔዎች

0
561

በአፋር እና በሶማሌ አጎራባች ሕዝቦች መካከል የተነሳው ግጭት መንስዔ እና ሒደት በድንበር ውዝግብነት ብቻ የማይገለጽ፤ ሰፋ ያለ ማኅበራዊ እና ፖለቲካዊ ትንታኔ የሚያስፈልገው መሆኑን የሚገልጹት ሚኒሊክ አሰፋ፥ ይህንኑ የድንበር ውዝግብ በኢትዮጵያ መንግሥት ቅርጽ እና ስርዓት ውስጥ የተስተናገደበትን መንገድ እና ቀጣይ ሒደት በሥራ ላይ ካሉ ሕጎች አንጻር ተንትነዋል።

በድንበርተኞቹ የአፋር ሕዝቦች እና ኢሳ በሚል መጠሪያ በሚታወቁት የሶማሌ ጎሳዎች መካከል የሚነሱ ግጭቶች መቼ እንደጀመሩ የሚያሳዩ ተጨባጭ ማስረጃዎች ባይኖሩም ከጥቂት ከብት ጠባቂ ወጣቶች ግብግብነት ያለፈ፣ የተካረረ እና በጦር መሣሪያ የታገዘ ግጭት ለመጀመሪያ ጊዜ በታሪክ የተመዘገበው ከኹለተኛው የጣልያን ወረራ በኋላ መሆኑን ጥናቶች ይጠቁማሉ። የኹለቱም ወገኖች ሕዝቦች አርብቶ አደር እንደመሆናቸው መጠን የግጭቶቹ ዋነኛ መንስዔ የግጦሽ መሬት እና በአዋሽ እና ኤረር ወንዞችን መሰረት አድርጎ የመጠጥ ውሃን ለመቆጣጠር የሚደረግ ሽኩቻ መሆኑ የሚገርም አይሆንም። በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዘመነ መንግሥት በኹለቱ ሕዝቦች መካከል የሚከሰቱ ግጭቶችን ለማስቀረት የኢሳ ጎሳ አባላት ወደ ኤረር ወንዝ ምዕራባዊ አቅጣጫ እንዳያልፉ ተከልክለው ነበር። ሆኖም በደረቃማ ወቅቶች የኢሳ ጎሳ አባላት ለከባድ የውሃ እና የሣር እጦት እንዳረጋለን በሚል የጦር መሣሪያ ሳይታጠቁ ወደ ተከለከሉባቸው ስፍራዎች በመግባት የውሃ እና የግጦሽ ሣር ችግራቸውን እንዲያስተሳግሱ ይደረግ እንደነበር የቀድሞ የፌዴራል ጉዳዮች ሚኒስቴር በ1997 ያስጠናው የጥናት መዝገብ ያስረዳል። በደርግ የሥልጣን ዘመንም የኹለቱ ተጎራባች ሕዝቦች ግጭትን ለመቆጣጠር ተመሳሳይ እርምጃዎች እየተወሰዱ ቢቆዩም የአዲስ አበባ – አሰብ መንገድን ተከትሎ አዳዲስ ከተሞች መቆርቆራቸው ግጭቶቹ መልካቸውን እየቀየሩ እንዲኼዱ አድርጓቸዋል። በዚህ ምክንያት በአሁኑ ሰዓት በኹለቱ አጎራባች ማኅበረሰቦች መካከል የሚነሳው የድንበር ውዝግብ በዋናነት አደይቱ፣ ገዳማይቱ እና ዑንድፎ በተባሉ ትናንሽ ከተሞች ይገባኛል ጥያቄ ላይ የሚያተኩር ነው።

ሦስቱ ከተሞች አመሰራረት ላይ ኹለት ተቃራኒ ሐሳቦች ሲቀርቡ ይስተዋላል። ከአፋር ክልላዊ መንግሥት ወኪሎች እና የአገር ሽግሌዎች በኩል የሚቀርቡ ማስረጃዎች ሦስቱም ከተሞች የተመሰረቱበት ስፍራ ታሪካዊ የአፋር ሕዝቦች መኖሪያ የነበረ መሆኑን ያስረዳሉ። ሆኖም ከደርግ ውድቀት በኋላ ገዳማይቱ እና ዑንድፎ የተባሉት ከተሞችን የሶማሌ ኮንትሮባንድ ነጋዴዎች የአፋር ነዋሪችን ከስፍራው በማባረር እንደመሰረቷቸው ይናገራሉ። ከኢሳ (ሶማሌ) የጎሳ መሪዎች እና ከክልሉ ተወካዮች የሚቀርቡ ማስረጃዎች ደግሞ ከተሞቹ ለበርካታ ዐሥርት ዓመታት የቆዩ እና የከተሞቹ መሥራቾችም እነርሱ መሆናቸውን ይጠቁማሉ። ሆኖም ከኹለቱ ብሔረሰቦች ውጪ የሆኑ የከተሞቹ ነዋሪዎች እና ሌሎች እማኞች ከተሞቹ የተመሰረቱት በቅርብ ጊዜ መሆኑን እና ከከተሞቹ ምስረታ በፊት በአከባቢው የአፋር አርብቶ አደሮች ይኖሩ እንደነበር ያረጋግጣሉ። አደይቱ ከተማ ደግሞ በ1962 የአዋሽ-አሰብ (ጅቡቲ) መንገድ ሲገነባ የመንገድ ተቋራጭ ድርጅቱ ያረፈበትን ካምፕ ተከትላ መመስረቷን ኹለቱም ወገኖች የማይክዱት ሐቅ ሆኖ ተመዝግቧል። ነገር ግን በምስረታ ወቅት በቦታው የነበሩት የየትኛው ወገን ሕዝቦች ናቸው የሚለው የሚለው አከራካሪ ቢሆንም ከተማዋ ስትቆረቆር በቦታው ይኖር የነበረውን የአፋር ቤተሰብ ኢሳዎች በኀይል አስወጥተው ቦታውን እንደተቆጣጠሩት ገለልተኛ አስረጂዎች ይጠቁማሉ።

አሁን ባለው የአሰፋፈር ሁኔታ ሦስቱ ከተሞች ላይ በዋናነት የሶማሌ ማኅበረሰብ አባላት ይኖራሉ። ነገር ግን የአፋር ማኅበረሰብ ወኪሎች “ይህ ሁኔታ በተለያየ ወቅት በተደረጉ ደም አፋሳሽ ግጭቶች ሶማሌ ዎች የአፋር ነዋሪዎችን በማባረር ቦታዎቹን መቆጣጠራቸውን የሚያሳይ እንጂ፤ የቦታዎቹን ታሪካዊ ባለቤትነት የሚያስረዳ አይደለም” በማለት ይከራከራሉ። የሶማሌ ጎሳ አባላት ከነበረባቸው አስከፊ የውሃ እና የግጦሽ ሣር እጦት የተነሳ ባለፉት መንግሥታት የኤረር ወንዝን እንዳያልፉ የተጣለባቸውን ክልከላ ጥሰው ከወንዙ በስተምዕራብ በኩል በኀይል ለመስፈር መገደዳቸውን ከሚያሳዩ ማስረጃዎች ውጪ ከከተሞቹ ምስረታ በፊት አካባቢው የአፋሮች ይዞታ መሆኑን የሚያስረዱ ማስረጃዎች በርካታ ናቸው። ሆኖም በከተሞቹ ሰፍረው የሚገኙ የሶማሌ ማኅበረሰቦች በከተሞቹ ባለው የንግድ እንቅስቃሴ እና በአካባቢው የተፈጥሮ ሀብት ላይ ጥገኛ ሆነው ኑሯቸውን ከመሰረቱ በአማካይ ከሦስት ዐሥርት ዓመታት በላይ ተቆጥረዋል። የከተሞቹ ነዋሪዎች ከአርብቶ አደርነት ወደ ከተሜነት የተለወጡ በመሆናቸው ስፍራውን ለቀው እንዲኼዱ ማድረግ ከባድ ማኅበራዊ ቀውስ መፍጠሩም አይቀሬ ነው።

የደርግ መንግሥት ወድቆ የሽግግር መንግሥቱ እና የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ሲቋቋም የኹለቱ ተጎራባቾች ግጭት ተቋማዊ ቅርጽ በመያዝ የክልሎች የድንበር ውዝግብ ሆኖ ቀርቧል። በዚህም ሦስቱ ከተሞች ላይ የተነሳውን የይገባኛል ውዝግብ ለመፍታት የፌዴራሉ መንግሥት የተለያዩ ሙከራዎችን አድርጓል። በሕገ መንግሥቱ መሠረት በክልሎች መካከል የሚነሱ አለመግባባቶችን የመፍታት ሥልጣን የፌዴሬሽ ምክር ቤት ነው። የወሰን አከላለልን የሚመለከተው የሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 47፤ በክልሎች መካከል የወሰን አለመግባባቶች በሚኖሩ ጊዜ ጉዳዩ በክልሎቹ ስምምነት እንደሚፈታ በማስቀመጥ፤ ክልሎቹ መግባባት ላይ መድረስ ካልቻሉ ግን የፌዴሬሽን ምክር ቤት “የሕዝብን አሰፋፈር እና ፍላጎት መሰረት በማድረግ ይወስናል” የሚል ድንጋጌ አስቀምጧል።

የፌዴሬሽን ምክር ቤትን ለማጠናከር እና ሥልጣን እና ተግባሩን ለመዘርዘር በወጣው አዋጅ ቁጥር 251/1993 አንቀጽ 28 ላይ እንደተቀመጠው ምክር ቤቱ የሕዝብ ፍላጎትን ከግምት የሚያስገባው የሕዝብ አሰፋፈርን በማጥናት አከራካሪው አከባቢ ወዴት መካለል እንዳለበት መወሰን ያልተቻለ እንደሆነ ብቻ ነው። የሕዝቡ ፍላጎት የሚታወቀው ደግሞ በሕዝበ ውሳኔ መሰረት መሆኑን ይህ አዋጅ ያስቀመጠ ሲሆን አከራካሪው አካባቢ አብላጫው ሕዝብ ድምፅ ወደ ሰጠበት ክልል ወሰን ይካለላል። ይህ አሰራር መሰረታዊ የዴሞክራሲ መርሆችን ያገናዘበ ቢሆንም ሕዝብ ያልሰፈረባቸው አከባቢዎች ላይ የሚነሱ የድንበር ውዝግቦችን መፍታት የሚችል ባለመሆኑ፤ በአከራካሪ ይዞታዎች ዙሪያ ያሉ የታሪክ ማስረጃዎች ከግምት እንዲገቡ ባለማስቻሉ፤ እንዲሁም ምክር ቤቱ ሕዝበ ውሳኔን ከማስተባበር በቀር ተጨባጭ የሆነ የዳኝነት (‘ጁዲሺያል’) ሥልጣን እንዳይኖረው በማድረጉ በብዙዎች ዘንድ ሲተች ቆይቷል።

ሆኖም በአፋር እና በሶማሌ ክልሎች መካከል የተነሳው የይገባኛል ውዝግብን ለመፍታት የፌዴራሉ መንግሥት የወሰደው እርምጃ፤ ሕገ መንግሥቱ ካስቀመጠው መደበኛ መንገድ ውጪ በአስፈጻሚው አካል በኩል መፍትሔ ከተበጀላቸው እንደ ድሬዳዋ ካሉ በርካታ የድንበር ውዝግቦች ውስጥ የሚመደብ ነው። በክልሎች መካከል የሚነሱ ግጭቶች ላይ መፍትሔ የማፈላለግ ኀላፊነትን ጨምሮ የተመሰረተው የቀድሞ የፌዴራል ጉዳዮች ሚኒስቴር (አሁን በሰላም ሚኒስቴር ሥር የተካተተ) ከምስረታው አንስቶ ከሠራባቸው ግጭቶች መካከል ዋነኛው ይህ የአፋር እና የሶማሌ ክልል ሕዝቦች እና መንግሥታት መካከል የነበረው የድንበር አለመግባባት ነው።

የፌዴራል ጉዳዮች ሚኒስቴር በክልሎች መካከል የሚነሱ አለመግባባቶችን የመፍታት ሥልጣኑ ከሕገ መንግሥቱ የሚመንጭ ባይሆንም በአገሪቱ የሕግ ሥርዓት ውስጥ የክልሎች የበይነ መንግሥታት ግንኙነትን የሚያሳልጥ ተቋም ካለመኖሩ አንጻር ክልሎች ያልባቸውን አለመግባባት በስምምነት እንዲፈቱ የማስተባበር ሥራ መሥራቱ ኢ-ሕገ መንግሥታዊ የሚባል አይሆንም። የፌዴራል ጉዳዮች ሚኒስቴር በታሪክ ውስጥ በኹለቱ ሕዝቦች መካከል የነበረውን ግንኙነት እና የአሰፋፈር ሁኔታ በማጥናት እንዲሁም የሦስቱ ከተሞች እና አካባቢያቸው የሚኖሩ የኹለቱም ሕዝቦች ተወካዮችን እና ሽማግሌዎችን በማሳተፍ የግጭቱን መንስዔ ለመረዳት ጥረት አድርጓል።

በሒደቱም የአፋር ማኅበረሰብ እና መንግሥት ተወካዮች ታሪክ ከሚሰጣቸው የተሸለ የባለቤትነት መብት አንጻር ጉዳዩ ላይ ያሉ ማስረጃዎች በጥናት ተረጋግጠው ከተሞቹ ወደ አፋር አስተዳደር እንዲካለሉ ሲሉ የመፍትሔ ሐሳብ ሲያቀርቡ ቆይተዋል። በተቃራኒው የሶማሌ ክልል ተወካዮች እና የከተሞቹ ነዋሪዎች የሆኑ የሶማሌ ማኅበረሰብ አባላት ሕገ መንግሥቱ መሰረት ጉዳዩ በሕዝበ ውሳኔ እንዲፈታ ግፊት ለማሳደር ሞክረዋል። ይህም ከተሞቹ ውስጥ ሙሉ በሙሉ ሊባል በሚችል ደረጃ ሰፍረው የሚገኙት የሶማሌ ሕዝቦች ከመሆናቸው አንጻር የሕዝበ ውሳኔው ውጤት ሶማሌዎችን ተጠቃሚ እንደሚያደርግ እርግጥ ስለሆነ ነው። የፌዴራል ጉዳዮች ሚኒስቴር ጉዳዩን አስመልክቶ የራሱን አቋም በመያዝ የመፍትሔ ሐሳቦችን አቅርቧል። እንደ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ማጠቃለያ ከሆነ ሦስቱ ከተሞች የተመሰረቱበት አካባቢ በታሪክ የአፋር ሕዝቦች የነበረ ሲሆን የሶማሌ ማኅበረሰብ አባላት በተለያዩ ጊዜያት በተቀሰቀሱ ግጭቶች ወቅት ነዋሪዎችን በማባረር ቦታዎቹን መቆጣጠራቸውን እና የኤረር ወንዝን ተሸግረው በከተሞቹ የሠፈሩትም ባለባቸው የውሃ እና የግጦሽ ሣር ችግር ምክንያት ሳይሆን የኮንትሮባንድ ንግድን ለመከወን መሆኑን ሚኒስቴሩ ደምድሟል።

በዚህም ሦስቱ ከተሞች በአፋር ክልል አስተዳደር ሥር እንዲካለሉ፤ የሶማሌ ማኅበረሰብ አባላት ግን በከተሞቹ የመኖር እና መሰረተ ልማትን/የመንግሥት አገልግሎቶችን የመጠቀም መብታቸው እንዲጠበቅ የውሳኔ ሐሳብ ቀርቧል። ይህም የውሳኔ ሐሳብ የኹለቱ ክልል አስተዳደሮች ተቀባይነት አግኝቶ በ2007 ሊጸድቅ ችሏል። ሆኖም ይህ ስምምነት የሶማሌ ማኅበረሰብ አባላትን ያስከፋ መሆኑ እና በውሳኔ ሐሳቡ የተስማሙ የወቅቱ የሶማሌ ክልል አመራሮችም ከፌዴራል መንግሥቱ ተጽዕኖ ነፃ አለመሆናቸው የብዙዎች እምነት ነው።

ይህም ሆኖ በኹለቱ አጎራባች ክልሎች መካከል የሚነሳው ግጭት በተለያዩ ጊዜያት እያገረሸ የብዙዎችን ሕይወት ቀጥፏል። ከአንድ ዓመት ገደማ በፊትም የሶማሌ ክልል አስተዳደር በፌዴራሉ መንግሥት አግባቢነት የፈረመውን ስምምነት በማፍረስ ሦስቱ ከተሞች ላይ ያለውን የይገባኛል ጥያቄ በድጋሚ ማንሳቱን ተከትሎ ተከታታይ ግጭቶች እና ውዝግቦች ተስተውለዋል። በቅርቡ የተስተዋሉ ግጭቶችን ተከትሎ የአፋር ክልል ርዕሰ መስተዳድር አወል አርባ እና የሶማሌ ክልል አቻቸው ሙስጠፌ መሐመድ ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ጋር ውይይት ማድረጋቸውን ይታወሳል። ከዚህ ውይይት በኋላ ርዕሰ መስተዳድሮቹ በጉዳዩ ላይ መግለጫ የሰጡ ሲሆን የሶማሌ ክልል ርዕሰ መስተዳድሩ ሙስጠፌ መሐመድ “የሕዝብ ጥያቄና የመሬት ይገባኛል ጥያቄዎችን በሕግ አግባብ እና በሕገ መንግሥቱ መሰረት እንዲፈቱ አቅጣጫ መቀመጡን ተናግረዋል። ይህ አቋም ከዚህ በፊት አለመግባባቱን ለመፍታት የተደረጉ ጥረቶችን እና ስምምነቶችን እውቅና እንደመንፈግ ሊቆጠር የሚችል ነው። ይህም በአለመግባባቱ ዙሪያ አዲስ ድርድር ሊድረግ እንደሚችል አልያም ጉዳዩ ወደ ፌዴሬሽን ምክር ቤት ሊያመራ እንደሚችል የሚጠቁም ነው።

ጉዳዩ ወደ ፌዴሬሽን ምክር ቤት አምርቶ በሕዝበ ውሳኔ የሚፈታ ከሆነ በአከራካሪዎቹ ከተሞች ላይ አብላጫ ቁጥር ያላቸው ነዋሪዎች የኢሳ ጎሳ አባላት ከመሆናቸው አንጻር ውጤቱ ከተሞቹን ወደ ሶማሌ ክልል እንዲካልሉ የሚያደርግ መሆኑ እሙን ነው። ይህም የአፋር ሕዝቦች በአከባቢው ላይ ያላቸውን ታሪካዊ ጥያቄ የሚመልስ ባለመሆኑ ከፍተኛ ቅሬታ ሊያስነሳ ይችላል። ጉዳዩ አዲስ ድርድር ወደ ማድረግ የሚያመራ ከሆነም የነባሩ ስምምነት ዕጣ ፈንታ ምን እንደሚሆን የሚደነግግ የሕግ ማዕቀፍ በሕግ ስርዓታችን ውስጥ የለም።

ከላይ እንደተገለፀው በክልሎች መካከል የሚነሳ የድንበር ውዝግብ በቀዳሚነት እንዲፈታ የሚጠበቀው በክልሎቹ ስምምነት መሆኑ ይታወቃል። ነገር ግን ተከራካሪ ክልሎች ያጸደቁትን ስምምነት እንዴት ማሻሻል እንድሚችሉ ወይም አንደኛው ወገን የድንበር ስምምነቱን በሚጥስበት ጊዜ ምን ዓይነት ውጤቶች እንደሚከትሉ የአገሪቱ ሕገ መንግሥት በግልፅ አያስቀምጥም።

የዳበረ ፌዴራላዊ ሥርዓት ያላት የስዊዘርላንድ ሕገ መንግሥት በክልሎች መካከል የሚደረግ ስምምነት ላይ የሚነሱ ክርክሮች በፌዴራል መንግሥቱ ጠቅላይ ፍርድ ቤት እንዲዳኙ ሥልጣን የሚሰጥ ሲሆን ስምምነቶቹም እንደ ሕግ ተቆጥረው የፌደራሉ መንግሥት በአስገዳጅነት እንዲያስፈፅማቸው ያደርጋል። በተመሳሳይ በአገራችንም የፌዴራሉ መንግሥት በክልሎች መካከል የተገቡ ስምምነቶችን መዳኘት እና የማስፈፀም ኀላፊነት ቢወስድ ከፌዴራሊዝም መርሖዎች አንጻር ተቃውሞ የሚገጥመው አይሆንም።

የቀደሙት ስምምነቶች የተደረጉበት ሒደት ከተጽዕኖ የፀዳ ባለመሆኑ በክልሎቹ መካከል አዲስ ድርድር እና ስምምነት የሚደረግበት ሁኔታ ቢመቻች ስምምነቶቹ የሚኖራቸውን ቅቡልነት ከፍ እንደሚያደርገው ይታወቃል። ነገር ግን ድርድሮቹ የሚደረጉበት ዓውድ እና መርሕ የሕዝቦችን ዘላቂ እና ሰላማዊ ግንኙነት እንዲሁም ታሪካዊ እውነታዎችን የሚያጣጥም መሆን ይኖርበታል። በተጨማሪም በተመሳሳይ የአጎራባች ሕዝቦች መካከል ያሉ አለመግባባቶችን ለመፍታት በሌሎች አገራት ተሞክረው ውጤታማ የሆኑ እንደ የጋራ አስተዳደር ያሉ መንግሥታዊ አወቃቀሮችን ለመሞከር ክፍት የሆነ ፖለቲካዊ ዝግጁነት ያስፈልጋል። ከተሞቹ ወድ አፋር ክልል እንዲካለሉ የሚያደርግ ውሳኔም ሆነ ስምምነት በከተሞቹ የሚኖሩ የኢሳ ጎሳ አባላት የሚኖራቸውን የነዋሪነት፣ የንብረት፣ ራስን በራስ የማስተዳደር እና ሌሎች መብቶች የሚያስጥብቅ ሊሆን ይገባዋል።

መሰል አለመግባባቶችን እና ግጭቶችን በዘላቂነት መፍታት የሚያስችሉ መፍትሔዎች ከሕግ ሥርዓቱ እንዲመነጩ የሚጠበቅ ቢሆንም አሁን ባለው የሕግ ሥርዓት ውስጥ ያለው ክፍተት ለችግሮቹ መፍትሔ ከማበጀት ይልቅ ጉዳዩን የማወሳሰብ አቅሙ ከፍተኛ ነው። በመሆኑም የፌዴራሉ መንግሥት ለዚህ እና ሌሎች አንገብጋቢ የድንብር ውዝግቦች እና የማኅበረሰብ ግጭቶች የተሻለ የሚባል ጊዜያዊ መፍትሔ መፈልግ ይኖርበታል። ከዚህ ባለፈም በኹለቱ አጎራባች ማኅበረሰቦች ውስጥ ሰርፆ የቆየውን ገዳይን እንደ ጀግና የሚያይ የጦረኝነት ባሕል ለማለዘብ እና የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙንቱን ሰላማዊ ለማድረግ ከፍተኛ የጥረት ማድረግ ይጠይቃል።
በኹለቱም ወገን ግጭቶችን እያቀጣጥሉ ያሉ የበታች አመራሮች እና የኮንትሮባንድ ንግድ አንቀሳቃሾችን ጨምሮ ሌሎች የፖለቲካ ኀይሎች ተጠያቂ የሚሆኑበት አልያም ሕጋዊ በሆነ መንገድ በምህረት የሰላም ጥረቶችን እንዲቀላቀሉ የሚደረግበት ሁኔታ ሊመቻች ይገባል።
ሚኒሊክ አሰፋ የሕግ ባለሙያ ሲሆኑ በኢሜይል አድራሻው minilikassefa@gmail.com ይገኛሉ።

ቅጽ 1 ቁጥር 51 ጥቅምት 15 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here