ኦኬሎ አኳይ ማን ናቸው?

0
1050

ኦሌሎ አኳይ ኦቻላ የቀድሞው የጋምቤላ ርዕሰ መስተዳድር ናቸው። ለዘጠኝ ወራት በክልል ፕሬዘዳንትንት፣ ለስምንት ዓመታት በስደት እንዲሁም ለአራት ዓመታት በእስር አሳልፈዋል። በኢፌዴሪ ለመጀመሪያ ጊዜ ብቸኛው የተቃዋሚው የጋምቤላ ሕዝቦች ዴሞክራሲያዊ ኮንግረስ (ጋሕዴኮ) አመራር አባል ሆነው የክልል ፕሬዘዳንት መሆን የቻሉም ሰው ናቸው። ለመሆኑ ኦሌሎ አኳይ ማን ናቸው ሲል የአዲስ ማለዳው ታምራት አስታጥቄ ከአኬሎ ጋር ሰፋ ያለ ቆይታ በማድረግ የአንደበት እንግዳ አድርጓቸዋል።

ትውልድ – ዕድገት – ትምህርት
የተወለድኩት መጋቢት 3/1954 ጋምቤላ ውስጥ በሚገኘው ታታ ሐይቅ አቅራራቢያ በምትገኝ ዲፓ በምትባል መንደር ውስጥ ነው። በአባቴ በኩል በአጠቃላይ ዘጠኝ ወንድሞችና እና እህቶች አሉኝ።

ዕድሜዬ ለትምህርት እንደደረሰ በ1963 መደበኛ ትምህርት የጀመርኩ ሲሆን እስከ 6ኛ ክፍል በአሜሪካ ሚሽነሪዎች በተከፈተ ትምህርት ቤት፣ 7ኛ ክፍልን አቦቦ ከተማ በሚገኝ ትምህርት ቤት፤ ከዚያም በኋላ በ1970 ደንቢ ዶሎ በመሔድ ቄለም አጠቃላይ ከፍተኛ ኹለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት በመግባት፤ በመካከል ለአንድ ዓመት በሕመም ምክንያት ካቋረጥኩት በስተቀር የኹለተኛ ደረጃ ትምህርቴን በጥሩ ውጤት በ1975 አጠናቅቄያለሁ።
ነርሲንግ ለመግባት የመግቢያ ፈተና ተፈተንኩና ነቀምት ተመድቤ በዛም የአሜሪካ ሚሽነሪ ትምህርት ቤት ገባሁ፤ በ1978 ትምህርቴን ጨርሼ ተመረቅኩኝ። በጋምቤላ ታሪክ ውስጥ ኹለተኛው ነርስ እኔ ነኝ።

በጅማ ዩኒቨርሲቲ የማኅበረሰብ ጤና አጠባበቅ (Public Health) በ1990 በመጀመሪያ ዲግሪ ተመርቄያለሁ።
ኹለተኛ ዲግሪዬን በተመሳሳይ በኅብረተሰብ ጤና ትምህርት ተከታትዬ የሚሰጡ ኮርሶችን በጠቅላላ ከጨረስኩ በኋላ የመመረቂያ ጽሑፍ ዝግጅት ላይ በነበርኩበት ወቅት በድንገት ከፍተኛ የመንግሥት ኀላፊነት ቦታ እንድይዝ በመደረጉ በማመልከቻ ትምህርቴን አቋርጫለሁ።

ቤተሰብ
ለመጀመሪያ ጊዜ ትዳር የመሰረትኩት በ1979 ሲሆን በፍቺ ተጠናቅቆ ሌላ ኹለተኛ ትዳር መስርቻለሁ። በአጠቃለይ በትዳር ውስጥ እና ከትዳር ውጪ ስምንት ልጆችን ያፈራሁ ሲሆን ሦስቱ ሴቶች ሲሆኑ የተቀሩት ደግሞ ወንዶች ናቸው።
የአምስት የልጅ ልጆች ባለጸጋም ሆኛለሁ። ልጆቼም በኢትዮጵያ፣ በሰሜን አሜሪካ እና ኖርዌይ ይኖራሉ።

ሥራ – የኢሠፓ ጸሐፊነት
በ1978 እኔን ጨምሮ ሰባት ባለሙያዎች ኢሊባቡር በሚባለው ክፍለ ሃገር ተመደብን፣ እኔም በኢሊባቡር ስር በሚገኘው ጋምቤላ ተመደብኩኝ። በወቅቱ ሥራ የጀመርኩት በጤና ጣቢያ ኀላፊነት ሲሆን በሰፈራ ፕሮግራም ላይም ተሳትፌያለሁ። በመቀጠል በጋምቤላ የጤና ማስተባበሪያ ቢሮ የእናቶች ጤና አስተባባሪ በመሆን አገልግያለሁ።

ሸንጎ የሚባል አዲስ የአስተዳደር መዋቅር መዘርጋቱን ተከትሎ በሙያዬ በአዲሱ መዋቅር ጤና መምሪያ ሥር የቤተሰብ ጤና ክብካቤ ቡድን መሪ በመሆን ተመደብኩ። በዛውም ዕድገት መጣ፤ ጥቅሙንም አጣጣምኩት።

ከሙያዬ በተጨማሪ የፖለቲካ ተሳትፎ ስለነበረኝ የኢትዮጵያ ሠራተኞች ፓርቲ (ኢሠፓ) አባል ነበርኩኝ። ለፖለቲካው የተመለመልኩት ነቀምት ተማሪ በነበርኩበት ወቅት ነበር። በፖለቲካ ተሳትፎዬ የኢሠፓ የታችኛው መዋቅር በጤና መምሪያ ሥር መሠረታዊ ድርጅት አንደኛ ጸሐፊ ሆኜ እስከ መንግሥት ለውጥ 1983 ድረስ አገልግያለሁ።

ሥራ – ኢሕአዴግ – የተቃውሞ ፖለቲካ
የመንግሥት ለውጥን ተከትሎ በነበረኝ አነስተኛ የፖለቲካ ተሳትፎ ምክንያት ለኹለት ሣምንታት ታስሬ ተለቀቅኩኝ።
በሽግግር መንግሥት ወቅት ለአንድ ዓመት ተኩል ለሚሆን ጊዜ የጤና ቢሮ ኀለፊ ሆኜ አገልግያለሁ። በሐምሌ 14/1986 በሦስት ዋና ምክንያቶች ሥራዬን በገዛ ራሴ ፈቃድ ለቅቄያለሁ።

ሥራዬን ለመልቀቅ የመጀመሪያው ምክንያቴ ጤና ጥበቃ ለሦስት ጤና ጣቢያዎች የመደበው 90 ሺሕ ብር ሥራ ላይ እንደዋለ ተደርጎ በመቅረቡ ነው። ይህም ወንጀል መሆኑን በማጋለጤ ቂም እንዲያዝብኝ ሆኗል። ኹለተኛው ሰበብ ደግሞ ለኦፕራሲዮን የሚያገለግል ኦክሲጅን ታንከር ከአዲስ አበባ ተሞልቶ ነበር የሚመጣው፤ ይሁንና የጦር መሣሪያ እያዘዋወርኩ ተደርጎ ተቆጥሮብኛል። የመጨረሻው ጤና ጣቢያዎቹ ለመብራትነት ኬሮሲን ይጠቀሙበት የነበሩበትን ሁኔታ ከተባበሩት መንግሥታት የሕፃናት ድርጅት (‘ዩኒሴፍ’) ጋር በመነጋገር 25 የፀሐይ ብርሃን ሳሕኖችን (Solar System Panels) እንዲጠቀሙ በማድረጌ እንደ ሰላይ ተደርጌ ተቆጥሪያለሁ።
ይሁንና እስከ ኅዳር 1986 ድረስ የሚተካኝ ባለመኖሩ እንዲሁም በሙያዬ ልመደብ ባለመቻሉ በሥራው ላይ ቆይቻለሁ።
የመጀመሪያ ዲግሪየን ይዤ ወደ ጋምቤላ እንደተመለስኩ የማኅበረሰብ ጤና እቅድና ፕሮግራም ውስጥ አገልግያለሁ። ከጥቂት  ወራት በኋላ ወደ ቀደመ ቦታዬ ተመድቤ የቤተሰብ ጤና ቡድን መሪ በመሆን ተልዕኮዬን ፈጽሜያለሁ።

ከተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲ አባልነት እስከ ሥራ አስፈጻሚነት
የጋምቤላ ሕዝቦች ዴሞክራሲያዊ ኮንግረስ (ጋሕዴኮ) የሚባል ተቃዋሚ ፓርቲ ተቀላቅዬ በ1992 በተካሔደው ምርጫ ላይ በመሳተፍ ከኢሕአዴግ አጋር ከሆነው የጋምቤላ ሕዝቦች ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ጋሕዴግ) ጋር ተወዳደርን። መጨረሻ እኛ አሸነፍን፤ ከ53 ወንበር 38ቱን አገኘን። ኢሕአዴግ ይህንን ባለመፈለጉ ውጤቱን ገልብጦ ለእኛ 13 ወንበር ብቻ ሰጥቶን የተቀረውን 40 ወሰደብን። ለእኛ የተለቀቁት ወንበሮች በጣም አስቸጋሪና ለእነሱም አደገኛ የሆኑትን ምርጫ ጣቢያዎች ያካትታል። ምንም እንኳን የእኔን ወንበር ባይነኩትም በድርጊቱ በጣም ተበሳጭቻለሁ።

በ1993 የክልሉን ምክር ቤት የመጀመሪያው ስብሰባ ላይ ከተሳተፍኩ እንደምታሰር ዛቻ ይደርሰኝ ነበር። ይሁንና በወቅቱ እኔ አዲስ አበባ የኹለተኛ ዲግዬን ለመከታተል የሚያስችለኝን ዕድል ተወዳድሬ በማግኘቴ የምክር ቤት አባል ብሆንም ተሳታፊ ግን አልነበርኩም።

በ1995 ትምህርቴን ተከታትዬ የመመረቂያ ጥናት ለማካሔድ ብቻ በቀረኝ ወቅት ከምርጫው ጋር በተያያዘ ጋምቤላ ማካሔድ ያልተቻለው ስብሰባ አዲስ አበባ ውሃ ሀብት ልምት ሚኒስቴር እንዲካሔድ በመወሰኑ ተሳታፊ ለመሆን ቻልኩኝ። በዚህ ወቅት ዓላማውም ፍላጎቱም ባልነበረኝ ሁኔታ የሥራ አስፈፃሚ አባል ተደርጌ ተመረጥኩ። በዚህም ምክንያት ለጥናቴ መረጃ ለማሰባሰብ ዝግጅት ላይ የነበርኩት ሰውዬ በሹመት ወደ ክልሉ ተመለስኩኝ።

ኢታንግ – የአኝዋክና የኑዌር የግጭት ማዕከል እንዴት ሆነች?
ጋሕዴግ የ1992 ምርጫ ካሸነፈ ከአኝዋክ እውቅና ውጪ የኢታንግ ወረዳን ለኑዌር አስረክባለው ብሎ ቃል በገባው መሰረት ውጤቱ ተገልብጦ ወረዳው ላይ ግንባሩ እንዲያሸንፍ ይደረጋል። ኑዌሮች ቃል በተገባው መሰረት ኢታንግ ይሰጠን አለበለዚያ እርምጃ እንወስዳለን በማለት ሰኔ 30/1993 ባለመግባባት ለብዙ አኝዋኮች ሞት ሰበብ ሆነ። ኢታንግም የአኝዋክ እና የኑዌር የግጭት ማዕከል ሆነች። ጋምቤላ መካሔድ ያልቻለው ስብሰባም አዲስ አበባ እንዲካሔድ የተወሰነው በዚህ ምክንያት ነው።

ከአቅም ግንባታ ማስተባበሪያ ቢሮ ኀላፊነት እስከ ፕሬዘዳንትነት
ጋምቤላ በተመለስን ማግሥት የክልሉ የአቅም ግንባታ ማስተባበሪያ ቢሮ ኀላፊ ሆኜ ተመደብኩ። በቢሮ ኀላፊነት ከታኅሣሥ እስከ መጋቢት 1995 ድረስ ለሦስት ወራት እንደሠራሁ ከአኝዋክ፣ ኑዌርና መዠንገር ብሔረሰቦች ግጭት ጋር በተያያዘ በወቅቱ የነበረው ፕሬዘዳንት ኡኬሎ ኚጌሎ ከሥልጣኑ እንዲወርድ በመታሰቡ ማን ይመረጥ የሚለው የጋሕዴግ የኢሕአዴግ ምክር ቤት አባላት የሆኑት አምስት ግለሰቦች በድብቅ ተወያይተው ምርጫ 1997 እስኪካሔድ ድረስ ክልሉን እንድመራ በምክር ቤቱ ሹመቴ መጋቢት 7/1995 እንዲጸድቅ ተደረገ።

በተሾምኩበት ጊዜ ንግግር እንዳደርግ ተጋብዤ ያልተዘጋጀሁበትን ነገር ግን በሰዓቱ ማለት የሚገባኝ የመዋቅር ለውጥ እንደማደርግ በአጽንዖት ጠቅሼ ተቀመጥኩኝ። የፕሬዘዳንትነት የሥልጣን ዘመኔ እስከ ታኅሣሥ 30/1996 ለዘጠኝ ወራት ይዝለቅ እንጂ ብዙ ተግዳሮቶችና ከባድ ጊዜዎችን አሳልፌበታለሁ። ሹመቱ እሳት ውስጥ እንደመግባት የሚቆጠር ነው።

ኢታንግ ወረዳ ላይ ከአኝዋኩ እና ከኑዌር ከእያንዳንዳቸው 100 ሰዎች እንዲመረጡ በማድረግ የእርቀ ሰላም ጉርቶንግ በሚባል ባሕላዊ ስርዓቱን በጠበቀ መልኩ እንዲካሔድ በማድረግ ሥራዬን ጀመርኩኝ፤ ችግሩ ከሕዝቡ ሳይሆን ከፖለቲካ ልኂቁ መሆኑን ተገነዘብኩ። በኋላም የመዠንገር ብሔረሰብ ተወካዮች ተጨምረው በጋምቤላ ምክር ቤት አዳራሽ የጉርቶንግ ስርዓት በድጋሜ ተከናውኗል።

በማስከተልም የመዋቅሩን ሥራ በአዲስ መልክ ሠራሁት፤ ሰዎች በሙያቸው እንዲመደቡ በማድረግ። ነገር ግን 80 በመቶውን ብቻ ነበር ላከናውን የቻልኩት።
ይሁንና በጋምቤላ ከተማ ታኅሣሥ 3/1996 መከላከያ አኝዋኮችን መግደል ጀመረ። የግድያው ምክንያት የአገር ውስጥ ከስደት እና ስደት ተመላሽ ድርጅት (‘አራ’) ስምንት ሠራተኞች ባልታወቁ ሰዎች ከጋምቤላ ከተማ 35 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ተገድለው በመገኘታቸው ነው። መከላከያ ግን ገዳዮቹ አኝዋኮች ናቸው በማለት ባልተረጋገጠ መረጃ ሕገወጥ ግድያ ፈጽመዋል።

ድርጊቱ ከክልሉ አቅም በላይ መሆኑን ሳውቅ ጉዳዩን ወደ ሚመለከተው የፌደራል ጉዳዮች ሚኒስቴር በመደወል በክልሉ ውስጥ የሚገኘው መከላከያ ሠራዊት ሙሉ ለሙሉ እንዲወጣ ያልኩት ሐሳብ ጅማ ያለው መከላከያ እንዲሔድልህ አድርግ የሚል ከሥልጣኔ ጋር ፈጽሞ የማይሔድ ምላሽ አገኘሁ። እንዴት አንድ የክልል ፕሬዘዳንት የመከላከያ ሠራዊትን ሊያዝ ይችላል በሚል ልሞግት ብሞክርም ሰሚ ጆሮ በማጣት ልፋቴ ባክኖ ቀረ።
ከታኅሣሥ 3-5 ባሉት ጊዜያቶች ብቻ 424 አኝዋኮች ተገድለዋል፤ ሁሉም ወንዶች ናቸው።

ይባስ ብሎም የፌደራል ጉዳዮች ሚኒስትር የጋምቤላ ግጭት በአኝዋክና ኑዌር መካከል የተደረገ አስመስሎ መግለጫ ሰጠ። ሚኒስቴሩ መግለጫ በሰጠበት ዕለት ለጀርመን ድምጽ ሬዲዮ ማስተባበያ ቃለ ምልልስ ሰጠሁ፤ የደንብ ልብስ የለበሱ ሰዎች ግድያዎቹን እንደፈጸሙ አጋለጥኩኝ። የእኔ ምላሽ በነጋታው በተላለፈው የሬዲዮ ጣቢያው ስርጭት ቀርቧል።

ብዙ ነገሮች መፈጠር ጀመሩ። የፌደራል ጉዳዮች ምክትል ሚኒስትር ዶክትር ገብረኣብ በርናባስ ያለ እኔ እውቅና ክልሉ ድረስ በመምጣት ከሕግ ውጪ የሆኑ ሥራዎችን ሲሠሩ ከረሙ።

ታኅሣሥ 29/1996 ግምገማ ተብሎ ስብሰባ በኢሕአዴግ ተጠራ። የጋሕዴግ አመራሮች፣ የኢሕአዴግ ተወካዮች እና የደኅንነት አባላት ከአዲስ አበባ መጥተዋል።
የግምገማው አጀንዳ በጋምቤላ የተከሰተው ግጭት የአመራር ችግር ነው የሚል ነው፤ ብዙ ተባለ። እኔም የአመራር ችግር ከሆነ ራሱ ኢሕአዴግ ነው መጠየቅ የሚገባው ስል ተሟገትኩ። በመጨረሻም አኝዋኮችን የገደለው ኢሕአዴግ ራሱ ነው፤ ኑዌሮች አይደሉም። የ1993 በአኝዋክ እና ኑዌር መካከል የነበረው ግጭት በእርቀ ሰላም – ጉርቶንግ ተፈትቷል በማለት የአሁኑ ችግር እና የ1993ቱ በምንም መልኩ እንደማይገናኝ አስታወቅኩኝ።

ከኑዌር የሆነውን ሰብሳቢ አጥቅተው ወደኔ ሊመጡ መሆኑ ገብቶኝ ያለ ሦስተኛ ወገን ስብሰባውን እንደማልቀጥል ሳስታውቃቸው ስብሰባው እንዲበተን ተደረገ።
ከዛ ወደ ቤቴ ሔድኩኝ። እኔ በሌለሁበት ግን ስብሰባውን ቀጠሉ፤ እኔ ወጥቻለሁ። መጀመሪያ ኦኬሎ ካልወጣ ወይም 59 ወንድ እና አንድ ሴት ብቻ እንደሞቱ ካልፈረመ የጋምቤላ ችግር አይፈታም አሉ። አማራጩ መፈረም ወይም መገደል ነው።

ምሽት 5 ሰዓት ላይ አንድ ስልክ ተደወለልኝ፤ “ምን ታደርጋለህ? የአንተ ጊዜ አብቅቷል” አለኝ። ጠዋት ቢሮ ገብቼ ዶክመንት ብቻ ይዤ እቃዬን አስገብቼ ከቤቴ አጎበር ወሰድኩ።

ስደት
ታኅሣሥ 30 ከጠዋቱ ኹለት ሰዓት ከሩብ የአምስት ወር ነፍሰ ጡር ለነበረችው ባለቤቴ ሳልነግር የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ታርጋ ያለው የኤች አይ ቪ ኤድስ ጽሕፈት ቤት መኪና ያዝኩና አቦቦ ደረስኩ።

መኪናው የመንግሥት በመሆኑ ሹፌሩ እንዲመልስ ነገርኩት። አብሮኝ መሰደድ እንደሚፈልግ ሲነግረኝ መኪናውን አድርሶ መመለስ እንደሚችል ነገረኩት።
ከስምንት ቀናት አድካሚ የእግር ጉዞ በኋላ ደቡብ ሱዳን ደረስን።

በደቡብ ሱዳን ብዙም ሳልቆይ የጋምቤላ ፕሬዘዳንት መሆኔን ሲያውቁ ሒደቱን አፍጥነውልኝ በአጭር ጊዜ ውስጥ ኖርዌይ አገር እንድሔድ አደረጉኝ። በዛው በኖርዌይ የፖለቲካ ጥገኛ ሆኜ ሕይወቴን እንደ አዲስ ጀመርኩ።

የኖርዌይ ቆይታ
በኖርዌይ የፖለቲካ ጥገኛ በመሆኔ ዜግንት እስኪሰጠኝ ድረስ ለሰባት ዓመታት ከአገር መውጣት አልቻልኩም፤ ሥራም መሥራት አልተፈቀደልኝም። በቆይታዬ ቋንቋ መማር እና ባለቤቴንና ልጆቼን ወደ እኔ እንዲመጡ ለማድረግ ሒደቱን ስከታተል ነበር። በኋላም ባለቤቴና አራት ልጆቼ ተቀላቀሉኝ።

በስደት ቆይታዬ አኝዋኮች የተጨፈጨፉበትን ሁኔታ በሚዲያ ማጋለጡን ተያያዝኩት። በዚህ ጊዜ ኢሕአዴግ ኖርዌይ ድረስ መጥቶ መዋሸት ጀመረ። ሕዝብ ያስጨፈጨፍኩት እኔ እንደሆንኩኝ ታሪክ ገልብጠው ማውራትና ማስወራት ጀመሩ።

በሚገርም ሁኔታ እስከ 2006 ከጭፍጨፋው ጋር በተያያዘ ምርመራ ሳይደረግ ቆየ፤ እኔ ግን መናገሬን አላቋረጥኩም። የኋላ ኋላ ኢሕአዴግ የምርመራ ኮሚሽን አቋቁሞ ራሱ ሊያደርግ ወሰነ። በምርመራ ኮሚሽኑ ውጤት መሰረት 61 ሰዎች ብቻ ገድያለሁ የሚለውን አመነ፤ ከተገቢው በላይ ኀይል መጠቀሙን ጭምር ተናዘዘ።

የጋምቤላው ጭፍጨፋ ዓለም ዐቀፍ ትኩረት በመሳቡ ‘ሂውማን ራይትስ ዎች’ ምርመራውን ተቀላቀለ። ምርመራው ተጠናቆ ይፋ ሊደረግ ባለበት ሁኔታ በኢትዮጵያ መንግሥት በተለይ በቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ቀጥተኛ ትዕዛዝ ሪፖርቱ እንዲታፈን ተደረገ። ይሁንና መራማሪው ናይሮቢ ሲደርስ መረጃውን ለቀቀው። ጭፍጨፋውንም ያካሔደው የመከላከያ ሠራዊት እንደሆነ በምርመራው እንደደረሰበት ይፋ አደረገ።

በሪፖርቱ መሰረት 762 አኝዋክ የመግደል እቅድ ተይዞ እንደነበር፤ በመጀመሪያው ዙር 512 እና በኹለተኛው ደግሞ 250 ሰዎችን ለመግደል። ምክንያቱ ደግሞ ቂም በቀል ብቻ ሳይሆን የጋምቤላ ነዳጅ ከመውጣቱ በፊት ግድያው ለመፈጸምና ፍርሃት ለማስፈን ታቅዶ እንደነበረ ሪፐርቱ ጠቅሷል።

እቅዱ ቀደም ተብሎ የተዘጋጀው በመለስ ዜናዊ፣ ኡመት ኡቦንግ ኡሎም፣ አዲሱ ለገሰ፣ በረከት ስምዖን፣ ሳሞራ የኑስ፣ ዩናስ ገብረመስቀል፣ ታደሰ ኃይለሥላሴ፣ ዶክተር ገብረኣብ በርናባስ፣ የወቅቱ መከላከያ ሚኒስትር አባ ዱላ ገመዳ፤ የወቅቱ የፌደራል ጉዳዮች ሚኒስትር አባይ ፀሐዬ፣ አልማው አላምረው፣ ጸጋዬ በየነ እና ስብሐት ነጋ ናቸው።

በሌላ በኩል ደግሞ በ‘ጄኖሳይድ ሪፖርት’ (ማርች 3/2010 እ.ኤ.አ.) በወጣ ሪፖርት ከታኅሣሥ 3 እስከ ግንቦት 1996 ድረስ በአጠቃላይ ከ 2 ሺሕ 500 በላይ ወንድ አኝዋኮች እና 164 የተደፈሩ ሴቶች፣ ከ20 ሺሕ በላይ አኝዋኮች ተሰደዋል እንዲሁም ከ2 ሺሕ በላይ ቤቶች በጋምቤላ ከተማና በፍኙዶ ከተማ ተቃጥለዋል፣ የንብረት ውድመት የእርሻ ማሳ ቃጠሎ መድረሱንም ሪፖርቱ አካትቷል።

አንድ መታወቅ ያለበት ነገር ቢኖር መለስ ዜናዊ በቀጥታ ግድያው እንዲፈጸም ማዘዙ እና የሚገደሉትን የአኝዋክ ዝርዝር ያዘጋጀው ደግሞ ኡሞድ ኡበንግ ኦሎም ነው። ኹለቱም ግን አሁን በሕይወት የሉም።

እንዴት ታሰሩ?
ሰባት ዓመቱን ስጨርስ ወደ ስደተኛ መጠለያ ካምፕ ሔጄ ሒደቱን ልጨርስ አልኩኝና ከኬንያ ጨርሼ ሱዳን ሔድኩኝ። ሱዳን ስደርስ አንድ ደቡብ ሱዳናዊ ኦኬሎ አንተ ነህ አለኝ፤ አዎን አልኩትና በዛ የማውቀውን ሰው ላገኝ በስፍራው እንደተገኘሁ ነገርኩት። ማደሪያ አሳየኝ፣ እርሱ መልዕክት አስተላለፈ። ደቡብ ሱዳናውያን መልዕክት ደርሷቸው መጋቢት 18/2006 ላይ ያዙና አሰሩኝ።

ሱዳኖቹ ከቀናት ድርድር በኋላ 23 ሚሊዮን ዶላር በማስከፈል ለሦስት የታጠቁ የኢትዮጵያ የደኅንነት ሰዎች አስረከቡኝ። የደኅንነት ሰዎቹም በአንቶኖቨ አውሮፕላን ጋምቤላ አየር ማረፊያ በመውሰድ አሳደሩኝ። በነጋታው መጋቢት 19/2006 ደብረ ዘይት አየር ኀይል አቆዩኝ። ሊገድሉኝ አስበው ሳይሳካ በመቅረቱ ወደ ማዕከላዊ አዘዋውረው በጨለማ ክፍል አሰሩኝ። እዛም ለ21 ቀናት ቆየሁ፤ ምግብ ይሰጣሉ፤ ነፋስና ፀሐይ የለም።

የእስር ቤት ቆይታ
በማዕከላዊ ጥፊ፣ ድብደባና ማስፈራራት ይካሔድብኝ ነበር። በመጀመሪያ በአገር ክህደት ሊከሱኝ አስበው ነበር በኋላ ላይ ግን ሽብርተኛ ብለውኝ ቂሊንጦ እስር ቤት ወረወሩኝ። መቀመጫዬ ላይ በርግጫ የተመታሁት ለበሸታ (Perianal Festula) ዳርጎኛል። ኖርዌይ ከተመለስኩ በኋላ ዶክትር ለማግኘት አንድ ዓመት ፈጅቶብኝ ኹለት ጊዜ ኦፕራሲዮን አድርጌያለሁ።

ቂሊንጦ ክስ የተመሠረተብኝ በሽብርተኝነት ነው። ራሳቸው የሠሩት ሥራ እና የፈጸሙትን ግድያ ነው ወደ እኔ ያስተላለፉት።
ብዙ ክስ ነበረብኝ። የሽብር ክሱ ከግንቦት 7 ሊቀ መንበር ከዶ/ር ብርሃኑ ነጋ፣ ከኦነጉ ሊቀመንበር ከዳዉድ ኢብሳ፣ የጋምቤላ ሕዝቦች ነፃነት ንቅናቄ (ጋሕነን) ሊቀ መንበር በሬ አግድ እና የጋምቤላ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ጋዴን) ሊቀመንበር አፒ ኡጁሉ ጋር አሲረሃል በሚል ነው። በተጨማሪም ከደቡብ ሱዳን አማጺ ቡድን መሪ ዴቪድ ያውያው ጋርም ግንኙነት በመፍጠር መንግሥት ለመገልበጥ በማቀድ ተከስሻለሁ።

በክስ ሒደቱ ጠበቃ አልፈልግም አልኩኝ፤ መንግሥት የሾመው ጠበቃ መከሰስ የለባቸውም አለ። ደቡብ ሱዳን ነው የተያዙትና ወደዚያው መልሷቸው አለ። ይህን በማለቱም ጠበቃው ከሥራው ተባረረ።

ከዛ በኋላ አምሃ መኮንን ጠበቃ ሆነልኝ፤ ኖርዌይ ኤምባሲ እየሔደ ሥራው ተጀመረ።
ከኹለት ዓመት ክርክር በኋላ በ2008 የሽብር ክሱ ውድቅ ተደረገ። ከዛ ደግሞ ጋምቤላን ከኢትዮጵያ ለመገንጠል አሲረሃል በሚል በወንጀለኛ አዋጅ ቁጥር 241 መሰረት ዘጠኝ ዓመት ተፈረደብኝ፤ ወደ ቃሊቲ ገባሁ።
የእስር ቆይታዬ በድምሩ ሦስት ዓመት ከ11 ወር ነው።

ከእስር ስለመፈታት
[ጠቅላይ ሚኒስትር] ኃይለማርያም ደሳለኝ ከሥልጣናቸው በፈቃዳቸው ከመልቀቃቸው አንድ ቀን በፊት ተፈታሁ። ፓስፖርቴ እስር ቤት ስለጠፋ ጊዜያዊ ፓስፖርት የኖርዌ ኤምባሲ ሰጥቶኝ ወዲያውኑ ወደ ኖርዌይ መልሶኛል።

ወቅታዊው የጋምቤላ ሁኔታን በተመለከተ
ብዙ አልከታተልም፤ ግን ለውጡ ያልደረሰት ቦታ አለ። በጋምቤላ አኝዋክና ኑዌር እንዳይተማመኑ ያደረገው ወያኔ ነው። ችግሩ አሁን ድረስ አለ። በመሆኑም በጋምቤላ ለውጡ በደንብ አልታየም።

ኹለተኛ ስደተኛ በአፍሪካ ውስጥ የአገሩ ዜጋ እንዲሆን አይደረግም። አሁን ያሉት ኑዌሮች ሁሉ ስደተኛ ሆነው በ1956 (እ.ኤአ.) ነው የመጡት። በደቡብ ሱዳን ክርስቲያን እና ሙስሊም መካከል የተፈጠረ አመጽ ተነስቶ ግጭት ሲፈጠር ኑዌሮች ነው ወደ ጋምቤላ የመጡት። በኃይለሥላሴ ጊዜ የጋምቤላ አስተዳዳሪ የነበረው ጄነራል ለማ ነበር። ጥያቄው ሲቀርብ የጋምቤላ ባላባቶች አኝዋኮች ተጠሩና እነዚህ እንግዶችን እንዴት እናድርግ ሲባል አገራቸው ሰላም እስኪሆን ድረስ ተቀበሏቸው፤ አገራቸው ሰላም ሲሆን ግን ይመለሱ ተባለ። ከዛ ቀጥሎ የሰላም ስምምነት ተፈረመና የተወሰኑ ሲመለሱ የተወሰኑ እዚሁ ቀሩ።

ከ1972 (እ.ኤ.አ.) በኋላ ሱዳን ሌላ ችግር ተፈጠረ። አሁንም ኑዌሮች ወጡና ኢትዮጵያ ገቡ። ለእነርሱ ጥሩ አጋጣሚ ነበር፤ ውሃና ሣር ስላገኙ። ስለዚህ እዚሁ ቀሩ። በ1983 (እ.ኤ.አ.) ደቡብ ሱዳን አማጺ በጆን ጋራንግ የሚመራ ቡድን መጣ።

አሁን በጋምቤላ በየስደተኞች ካምፕ ያሉት ኑዌሮች ዜግነት መስጠት አይገባም። በሌሎች የአፍሪካ አገሮችም ዜግነት መስጠት አልተለመደም፤ አይሰጥም። ዜግነት የሚሰጠው ከአፍሪካ ውጪ በሰሜን አሜሪካ፣ ካናዳ፣ አውስትራሊያና አውሮፓ ውስጥ ብቻ ነው።
ለምሳሌ በዘር ጭፍጨፋ ምክንያት ከጋምቤላ የሔዱት አኝዋኮች አሁን ባሉበት ዜግነት የሰጣቸው የለም። ወይ በጋብቻ ካልሆነ በስተቀር ዜግነት አይሰጥም።

የውጪ ፓስፖርት ያላቸው ሰዎች የፖለቲካ ተሳትፎን በተመለከተ
እኔ ፖለቲካ ውስጥ የመሳተፍ ሐሳብ አለኝ፤ የመጣሁትም ለምርጫ ለመወዳደር ነው። አሁን እዚህ መጥቻለሁ። በሰሜን አሜሪካ የሚገኘው የኢትዮጵያ ቆንጽላ ጽሕፈት ቤት የድጋፍ ደብዳቤ ጽፎልኛል። በፖለቲካ እንድሳተፍ ትብብር እንዲደረግልኝም ጠይቄአለሁ። ምርጫ ቦርድ ሔጄ ስጠይቅም ሕጉ አይፈቅድም ብለውኛል። ነገር ግን በተመዘገበው ፓርቲ ውስጥ መሳተፍ መቻል አለመቻሌን ውሳኔ በመጠባበቅ ላይ ነኝ። የማይሆን ከሆነ ግን ችግር የለውም እመለሳለሁ። የሚሆን ከሆነ በፖለቲካው ተሳትፌ የድርሻዬን ማበርከት እፈልጋለሁ።

ቅጽ 1 ቁጥር 51 ጥቅምት 15 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here