ንግድ በተለያዩ የኢኮኖሚ ተዋናዮች መካከል የሚደረግ በፍቃደኝነት ላይ የተመሠረተ ልውውጥ ነው። ንግድ እንደየአገሩ ነባራዊ ሁኔታ በሚወጡ ሕጎች የሚተዳደር ሲሆን፣ መንግሥታትም የአገራቸውን የንግድ ስርዓት በሚያወጧቸው ሕጎች መሠረት ይቆጣጠራሉ።
በኢትዮጵያም ንግድ የረዥም ጊዜ ታሪክ ያለው ሲሆን፣ ዓለም ዐቀፋዊ መልክ ባለው አሁናዊ የንግድ ስርዓትና ገበያ ውስጥ በርካታ ጥያቄዎች ሲነሱ መስማት የተለመደ ሆኗል። ከሰሞኑም የመኪና እና መኖሪያ ቤት ዋጋ ላይ የታየው ከፍተኛ የዋጋ ጭማሪ ብዙዎችን በማነጋገር ላይ ይገኛል።
አዲስ አበባ ውስጥ ባለ የመኪና መሸጫ ቦታ መኪና ለመግዛት ሲጠይቁ አዲስ ማለዳ አግኝታ ያነጋገረቻቸው ግለሰብ እንደሚሉት፣ ሱዙኪ ዲዛየር (Suzuki Dzire) መኪናን ባለፈው ዓመት ጓደኛቸው በአንድ ነጥብ ሦስት ሚሊዮን ብር ገዝተው እንደነበር ያስታውሳሉ። በአሁኑ ሰዓት ግን ኹለት ነጥብ ኹለት ሚሊዮን ብር እንደደረሰ ገልፀዋል።
የመኪና ዋጋን በመኪና መሸጫዎች መጠየቅ ከጀመሩ አንድ ወር እንዳለፋቸው የሚገልጹት ግለሰቡ፣ በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ በተመሳሳይ መኪና ላይ እስከ አምስት መቶ ሺሕ ብር ድረስ ጭማሪ አንዳጋጠማቸው ተናግረዋል።
የኢኮኖሚ ባለሙያው ወንድምአገኝ መስፍን (ዶ/ር)፣ የመኪና ዋጋ ከጊዜ ወደ ጊዜ መጨመሩ የሚታይ እውነት ሲሆን፣ በ2014 መጨረሻዎቹ አራትና አምስት ወራት ለታየው ጭማሪ የተለያዩ ምክንያቶችን ማንሳት ይቻላል ብለዋል። መኪናም ሆነ የመኪና መለዋወጫዎች ከውጪ የሚገቡ እንደመሆናቸው መጠን በዓለም ዐቀፍ ገበያው የሚፈጠሩ ለውጦች የአገራችን ገበያ ላይ ተፅእኖ ያሳድራሉ ያሉት ባለሞያው፣ ወቅታዊ የሆነውና የዓለምን ኢኮኖሚ የፈተሸው የሩሲያና ዩክሬን ግጭት ልክ እንደሌሎቹ ዘርፎች ሁሉ የመኪና ንግዱ ላይም በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ ተፅዕኖ አሳድሯል ብለዋል።
ከኹለቱ አገራት መኪናን ባናስገባ እንኳን በጥሬ እቃዎች ዋጋ ላይና በሌሎች የመኪና አምራች አገሮች ላይ ባሳደሩት ተፅእኖ የመኪና ዋጋ መወደድ ላይ አሻራ እንዳለው አክለዋል። ከዚሁ ጋር በተያያዘም የአገራችን ብር ከዶላር ጋር ያለው የዋጋ ንጽጽር ከጊዜ ወደ ጊዜ ዝቅ እያለ መሄዱ ከዓለም ዐቀፍ ገበያው በተለየ የአገራችንን ገበያ እንደጎዳው ገልጸዋል።
የነዳጅ ዋጋ መጨመሩን ተከትሎ የመኪና ዋጋ መቀነስ አለበት የሚሉ አስተያየቶች ቢኖሩም፣ የነዳጅ ዋጋው በመኪና ዋጋ ላይ ያለው ተፅእኖ ዝቅተኛ ነው ያሉት ወንድምአገኝ በዚህም ምክንያት የነዳጅ ዋጋ ጭማሪ መኪና እንዲቀንስ አላደረገም ብለዋል።
ዓለም ዐቀፍና አገራዊ የኢኮኖሚ ችግሮችን አልፈውና አስፈላጊውን የግብር ክፍያ ጨርሰው በመኪና መሸጫ ቦታዎች የደረሱ መኪናዎች በቀናት ልዩነት ከፍተኛ የዋጋ ጭማሪ የሚያሳዩበት ምክንያት ምንድን ነው የሚል ጥያቄም አዲስ ማለዳ አንስታለች። የኢኮኖሚ ባለሙያው ሲመልሱ፣ ይህ የመኪና ገበያውን ውድቀት የሚያሳይ ነው ብለዋል።
መኪና አንዴ የታክስ ሂደትን አልፎ አገር ውስጥ ከገባ በኋላ ይህን ያህል የዋጋ ጭማሪ የሚያመጣበት ምክንያት የለም ያሉት ባለሙያው፣ ይህ የግብይት ስርዓቱን ድክመት ማሳያ እንደሆነ ገልጸዋል። የአገሪቱ የታክስ ስርዓትም ለተያያዥ የዋጋ ጭማሬዎች አስተዋጽኦ ያለው ሲሆን፣ ከጎረቤት አገራት አንጻርም ለመኪና የሚከፈለው ግብር ከፍተኛ ነው ብለዋል።
መኪና የማሻሻጥ ሥራ የሚሠሩት ዳዊት ለገሰ እንደሚሉት ደግሞ፣ የአገሪቱ የዋጋ ግሽበት ከፍተኛ በመሆኑ ገንዘብ ያላቸው ሰዎች ገንዘባቸውን ባንክ ውስጥ ከማስቀመጥ ይልቅ ንብረት ላይ ለማሳረፍ መፈለጋቸው ከፍተኛ የመኪና ፍላጎት እንዲኖር አድርጓል። ይህም የመኪና አቅርቦትና ፍላጎት እንዳይጣጣም አድርጎ፣ ገበያው ላይ ያሉት መኪኖች ዋጋቸው ከፍ እንዲል አስገድዷል ብለዋል።
በዚህ ሐሳብ የሚስማሙት ወንድምአገኝም ከሠላሳ በመቶ በላይ የደረሰው አገራዊ የዋጋ ግሽበት የብርን አቅም ክፉኛ እየቀነሰው በመሆኑ ገንዘብ ያላቸው ሰዎች ገንዘባቸውን በመጠቀም ከችግር ለማምለጥ ይጣጣራሉ ብለዋል።
በአገሪቱ የውጭ ምንዛሬ ግብይት ላይ የመኪና ነጋዴዎች ከፍተኛ ተፅእኖ እያሳደሩ እንደሚገኙ ሲነገር፣ በጥቁር ገበያ አንድ የአሜሪካ ዶላርን እስከ አንድ መቶ ብር በሚደርስ ዋጋ ይገዛሉ የሚሉ ሪፖርቶች ወጥተዋለ። ይህም በተዘዋዋሪ የአገሪቱ ኢኮኖሚ ላይ ከፍተኛ አሉታዊ ተጽእኖ እንዳለው አስተያየት ሰጪዎች ይናገራሉ።
በመኖሪያ ቤት ሽያጭ ድለላ ሥራ ላይ የተሰማሩት ሚኪያስ ከበደ (የአባታቸው ሥም የተቀየረ) እንደሚሉት፣ ለመኖሪያም ሆነ ለንግድ ቤቶች የሽያጭ ዋጋ መወደድ ትልቁን ምክንያት የሚወስዱት ደላሎች ናቸው። እንደ ሚኪያስ ገለጻ፣ ከፍተኛ የገንዘብ አቅም ያላቸው ደላሎች ቤቶችን ከሻጭ እየገዙና የተወሰኑ እሴቶችን ጨምረውባቸው እጅግ በከፍተኛ ዋጋ ለሽያጭ ያቀርቧቸዋል።
ለምሳሌ ሲያነሱም ከአራት ወር በፊት በአራት ሚሊዮን ብር የተገዛን ቤት፣ ግቢውን በመከፋፈልና አነስተኛ ስፋት ያላቸውን የብሎኬት ቤቶች በመገንባት የመሸጫ ዋጋውን ኻያ ሚሊዮን ብር አድርሰውታል ብለዋል። ከሰባት ወር በፊት ሦስት ነጥብ አምስት ሚሊዮን ብር የተሸጠ ቤትም በአሁኑ ጊዜ የመሸጫ ዋጋው ሰባት ሚሊዮን ብር እንደደረሰ የሚገልጹት ሚኪያስ፣ የተወሰኑ ደላሎች ገበያውን እንደተቆጣጠሩትና የገበያው ዋጋ በነሱ እንደሚወሰን ተናግረዋል።
ቤት መግዛት ከባድ እንደሆነ የገለጹ አስተያየታቸውን ለአዲስ ማለዳ የሰጡ ሥማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ ግለሰብም፣ በተለምዶ ሰቱዲዮ የሚባለውን የጋራ መኖሪያ ቤት ከጥቂት ወራት በፊት ወንድማቸው በስምንት መቶ ሺሕ ብር እንደገዛ ገልጸው በተመሳሳይ ቦታ የሚገኝ ተመሳሳይ ቤት በዚህ ሰዓት የአንድ ነጥብ አራት ሚሊዮን ብር ዋጋ እንዳለው ተናግረዋል። ለዚህ ምክንያቱ በርካታ ሊሆን እንደሚችል ያነሱት ግለሰቡ፣ በተለይ በግልም ሆነ በመንግሥት ተቋማት ተቀጥረው የሚሠሩና ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው ሰዎች ቤት መግዛትን እንዳያስቡ ሆነዋል ብለዋል።
በቤቶች ዋጋ ጭማሪ ላይ እንደመኪና ዋጋ ዓለም ዐቀፋዊ ሁኔታዎች የበዛ ተፅእኖ አያሳርፉም የሚሉት የኢኮኖሚ ባለሙያው ወንድምአገኝ፣ የዋጋ ጭማሪው በቀጥታ ከመሬት የገበያ ስርዓት ጋር ይያያዛል ብለዋል። ሻጭና ገዢን ከማገናኝትና ከማደራደር ያለፈ ድርሻ አላቸው ስለሚባሉት ደላሎች ሲናገሩ፣ የገበያ ውድቀት ሲኖር ዋጋን የሚወስነው ገበያው ወይም ገዥና ሻጭ ሳይሆኑ በኹለቱ መካከል ያሉ ደላሎች ይሆናሉ ብለዋል።
የደላሎች መኖር የገበያውን የመረጃ ፍሰት በማሳለጥ ረገድ ጠቀሜታ ቢኖረውም፣ በዋጋዎች ላይ ያላቸው ጣልቃ ገብነት ግን አግባብ እንዳልሆነ ገልጸዋል። ይህንንም ስርዓት የሚያስይዝ ሕግ መኖሩን እንደማያውቁ የገለጹት ባለሙያው፣ ከገዥና ሻጭ ከሚያገኙት የአገልግሎት ክፍያ (commission) ተጨማሪ የሆነ ገንዘብ ለማግኘት እንዲህ ዓይነቱን ጣልቃ ገብነት እንደሚያካሂዱ ገልጸው በመንግሥት ቁጥጥር ሊደርግበት እንደሚገባ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።
በአጠቃላይ በአገሪቱ ፍትሀዊ ገበያ የለም እስከሚባል ድረስ የገበያ ስርዓቱ የተበላሸ ነው የሚሉት ወንድምአገኝ፣ በስርዓት የማይመራ ገበያ ከጥቅሙ ጉዳቱ እንደሚያመዝን አክለዋል። ባለሙያው የአገሪቷ ትልቁ ኢኮኖሚያዊ ፈተና የዋጋ ግሽበት ነው ብለው፣ ለዚህም አገራዊና ዓለም አቀፋዊ ችግሮች ተፅእኖ ማሳደራቸው እንዳለ ሆኖ የተፈጠሩትን ችግሮች እንደመልካም አጋጣሚ በመጠቀም የግል ሀብት ለማፍራት የሚደረጉ ጥረቶች ሁኔታዎችን አባብሰዋል ብለዋል።
ይህንንም ማስተካከል ብዙ ጊዜ ሊወስድ የሚችል ቢሆንም በመንግሥትም ሆነ በግለሰብ ደረጃ ሊወሰዱ ይገባሉ የሚሏቸውን እርምጃዎችም ጠቅሰዋል። አሁን ባለው የኢኮኖሚ ሁኔታ ይበልጥ ተጎጂ የሆነው ድሀው የማኅበረሰብ ክፍል እንደመሆኑ እሱን መደጎም እንደሚያስፈልግም ገልጸዋል።
በተጨማሪም መንግሥት የገንዘብ ፖሊሲውን ጠንካራ ማድረግና ጥቁር ገበያውን መቆጣጠር እንዳለበት አሳስበዋል። ድሀውንም እንዲገብር የሚያደርገው የግብር ፖሊሲንም ማስተካከል እንደሚገባ አሳስበው፣ የዋጋ ግሽበቱና ግብሩ ተዳምረው ከሚያሳድሩበት ጫና መገላገል እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል። ለዚህም ግብር የማይቆረጥበትን የገቢ መጠን ከፍ በማድረግ ከድሀው የሚወሰደውን ግብር በማስቀረት ወይም በማሳነስ መደጎም ያስፈልጋል ብለዋል።
የደላሎችን ሚና የሚወስን የሕግ አግባብ ሊኖር ይገባል ያሉት ወንድምአገኝ፣ እያንዳንዱ ግለሰብም የሚፈጽመው ግዢና ሽያጭ ላይ ጥንቃቄ ሊያደርግና አላስፈላጊ ወጪዎችን ሊያሰቀር እንደሚገባ ተናግረዋል።
የመኪናና ቤት መሸጫ የዋጋ ንረቶች እንደ ማሳያ ቢነሱም፣ አጠቃላይ የገበያ ስርዓቱ ችግሮች የሚጎበኙት ነውና ሁሉም የየድርሻውን ተወጥቶ ገበያው ቢሻሻል ጠቃሚነቱ ለሁሉም የኅብረተሰብ ክፍል ነው።
ቅጽ 4 ቁጥር 204 መስከረም 21 2015



