ለባለልዩ ተሰጥኦው አዳን ሁሴን ድጋፍ እንደሚደረግ ተገለጸ

0
1082

ሰኞ መስከረም 23 ቀን 2015 (አዲስ ማለዳ) የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ከእንስሳት አዛባ፣ ጨውና ሌሎች አነስተኛ ቁሳቁሶችን በመጠቀም ኤሌክትሪክ ማመንጨት ለቻለው ለባለ ልዩ ተሰጥኦው አዳን ሁሴን አስፈላጊውን ድጋፍ እደሚያደርግ አስታወቀ፡፡

በውሃና እና ኢነርጂ ሚኒስቴር ሚኒስትር ዶ/ር ኢ/ር ሀብታሙ ኢተፋ የተመራ ልኡክ በቦረና ዞን ዋጫሊ ወረዳ ዌብ ከተማ በመገኘት የታዳጊ አዳን ሁሴን ባዮጋዝ በመጠቀም ኤሌክትሪክ የማመንጨት ፈጠራን ጎብኝተዋል።

ሚኒስትሩ እንደገለጹት፤ የአዳን ሁሴን ፈጠራ ሀይልን በቀላሉ በቤተሰብ ደረጃ በማመንጨት ጥቅም ላይ ማዋል እንደሚቻል ያሳየ መሆኑን ገልጸው፤ በሶስት ጉዳዮች ላይ ትኩረት በማድረግ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ እገዛ እንደሚያደረግ አስታውቀዋል።

የሚመነጨውን ኤሌክትሪክ መጠን መቆጣጠር እንዲቻል እገዛ እንደሚደረግ፤ ፈጠራውን የማዘመን ሥራዎች በማከናወን ማገዝና፤ ታዳጊው የባለቤትነት መብቱ እንዲረጋገጥ ድጋፍ እንደሚደረግም አስታውቀዋል፡፡

የውሃና ኢነርጂ ሚኒሰቴር፤ የኢነርጂ ልማት ዘርፍ ሚነስተር ዴኤታ ዶ/ር ኢ/ር ሡልጣን ወሊ በበኩላቸው፤ የታዳጊው ፈጠራ ባዮጋዝ የመጠቀምን ፋይዳ ወደ ህብረተሰቡ ለማስረጽ መልካም አጋጣሚ ተገደርጎ መወሰድ እንደሚችል ጠቅሰወው ታዳጊውን ለማገዝ ድጋፍ እንደሚደረግ ገልጸዋል፡፡

የብሔራዊ ባዮጋዝ ፕሮግራም አስተባባሪ ተመስገን ተፈራ በበኩላቸው፤ የታዳጊ አዳን ሁሴን ፈጠራ የባዮጋዝ ቴክኖሎጂን አንድ ደረጃ ያሳደገ መሆኑን ገልጸው፤ የአቅም ማጎልበት ስልጠናዎችን በመስጠት፤ ፈጠራውን በማስፋፋትና እስታንዳርድ በማውጣት ፈጠራውን እንደሚያግዙ መናገራቸውን ከውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ አመላክቷል፡፡

በቦረና ዞን ዋጪሌ ወረዳ ዌብ ከተማ የሚኖረው የ16 ዓመቱ የ9ኛ ክፍል ተማሪ አዳን ሁሴን ዲዳ የተለያዩ የፈጠራ ሥራዎችን የማከናወን ልምድ ያለውና፤ የኤሌክትሪክ ሃይል ከመፍጠሩም አስቀድሞ የተለያዩ ነገሮችን በመፍጠር የሚታወቅ ባለ ልዩ ተሰጥኦ ታዳጊ መሆኑን በአካባቢው የሚያውቁት ኹሉ ይናገራሉ።

ከፈጠራ ሥራዎቹ መካከል የተለያዩ ቁሶችን በመጠቀም የኤሌክትሪክ ሃይል በመፍጠሩ ከሚማርበት ቱላ ዌብ ኹለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት በተጨማሪ በዌብ ከተማ 37 መኖሪያ ቤቶች መብራት እንዲያገኙ አድርጓል።

አዳን ኤሌክትሪክ ማመንጨት የቻለው ከእንስሳት አዛባ፣ ጨውና ሌሎች አነስተኛ ቁሳቁሶችን በመጠቀም መሆኑን ይናገራል።የፈጠራ ሥራውን እውን ለማድረግ ከዘጠኝ ጊዜ በላይ ተደጋጋሚ ሙከራ ማድረጉን አስታውሶ በ10ኛ ሙከራው የተሳካለት ሲሆን፤ የሚማርበትን ትምህርት ቤት ጨምሮ የአካባቢውን ነዋሪዎች የመብራት ተጠቃሚ ማድረግ ችሏል።

የፈጠራ ሥራው አሁን ባለው ሁኔታ ያለምንም መቆራረጥ ለአምስት ወራት አገልግሎት እንደሚሰጥ የሚናገረው ተማሪ አዳን፤ ከፈጠራ ውጤቱም በወር እስከ 7 ሺሕ ብር ገቢ እያገኘ መሆኑን ገልጿል።

የፈጠራ ውጤቱን ይበልጥ ለማሻሻል እና ከፍ ለማድረግ ሳይንሳዊ ስልጠና ያስፈልገኛል የሚለው ታዳጊው ከአምስት ወራት በኋላ የኤሌክትሪክ ሃይል ግብአቶቹ ላይ እድሳትና ማሻሻያ በማድረግ አገልገሎቱ የሚቀጥል መሆኑን ተናግሯል።

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here