ኢትዮጵያ ከዓለማቀፉ የፋይናንስ ደኅንነት ስጋት ዝርዝር ወጣች

0
338

ክትትሉ ጠናክሮ የሚቀጥል ነው

ኢትዮጵያ በወንጀል ድርጊት የተገኘ ገንዘብን ወይም ንብረት ሕጋዊ አስመስሎ ማቅረብ (ገንዘብ ማጠብ) እንዲሁም ሽብርተኝነትንና የጅምላ ጨራሽ መሣሪያዎች ብዜትን በገንዘብ በመርዳት ለዓለማቀፉ ኢኮኖሚ ስጋት ናቸው ተብለው ከተዘረዘሩ ሃገራት ዝርዝር ወጣች።

ከዓለማቀፉ ኢኮኖሚ ጤንነት ባሻገርም ለሰላም እና ፀጥታ፣ አደጋ ለመቆጣጠር እና ለመከላከል የሚያስችል ስርዓት በመዘርጋት ከዚህ ቀደም የተሠራውን ምዘና በከፍተኛ ደረጃ ያሻሻለች መሆኗን ዓለም ዐቀፉ የፋይናንስ ግብረ- ኀይል (Financial Action Task Force FATF) በመገምገም ከሥም ዝረዝሩ እንድትወጣ ውሳኔ በማስተላለፉ አማካኝነት ከዓለም አቀፍ ትብብር ገምጋሚ ቡድን የክትትል ዝርዝር ሂደት መውጣቷን ድርጅቱ ጥቅምት 7/2012 በድረ ገፁ ላይ ይፋ አድርጓል።
ገንዘብ ማጠብን እና ሽብርተኝነትን በገንዘብ የመደገፍ ወንጀሎችን መከላከልና መቆጣጠርን አስመልክቶ የፋይናንስ ድርጊት ግብረ-ኀይል የተባለ ዓለም አቀፍ ቡድን 40 ምክረ-ሀሳቦችን አውጥቶ የሀገራትን ሁኔታ በየጊዜው ይገመግማል። ግብረ-ኀይሉ ባስቀመጣቸው 40 ምክረ-ሀሳቦች መሰረት ወንጀሎቹን በመከላከል ረገድ ኢትዮጵያ ጉልህ ክፍተት እንዳለባት በመገምገሙ ስሟ በግብረ-ኀይሉ ድረ ገፅ ሰፍሮ ቆይቷል።

ይህም ዓለም ዐቀፍ አልሚዎች መዋእለ ነዋያቸውን እንዳያፈሱ፣ ወደ ውጭ የሚላኩ የሀገራችን ምርቶችን ሀገራት በጥርጣሬ እንዲመለከቷቸው እና ደፍረው ከኢትዮጰያ ጋር እንዳይገበያዩ ከማድረጉም ባሻገር የአገር ውስጥ ባንኮች ከዓለማቀፍ ባንኮች እና የገንዘብ ተቋማት ጋር የተሳለጠ ግንኙነት እንዳይኖራቸው አድርጎ መቆየቱንና ለሃገር ገጽታም ፈተና ሆኖ መቆየቱን የሰላም ሚኒስትሯ ሙፈሪያት ካሚል ጥቅምት 11 ቀን 2012 በጽሕፈት ቤታቸው በሰጡት መግለጫ ገልፀዋል።

ኢትዮጵያ ከዚህ ክትትል ስም ዝርዝር ውስጥ እንድትወጣ ባለፉት ኹለት ዓመታት ተከታታይነት ያለው ሕጎችን እና መመሪያዎችን በማዘጋጀት የቁጥጥር ስርአቷን ለማጠንከር ስትሠራ እንደነበር የፋይናነስ መረጃ መረብ ደኅንነት ማዕከል ሕዝብ ግንኙነት ኀላፊ እንዳለ አሰፋ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል። የዓለም ዐቀፍ የፋይናንስ ግብረ- ኀይል ባለሞያዎችም ወደ አዲስ አበባ በመምጣት እና የአገሪቱን ሁኔታ በመገምገም ከገምጋሚ ቡድኑ የክትትል መዝገብ ውስጥ እንድትወጣ ማድረጉንም ጨምረው ገልፀዋል።

ገምጋሚ ቡድኑ ወደ ኢትዮጵያ ከመምጣቱ በፊትም እነዚህን ሥራዎችን ሲከታተል እንደነበር የተገለፀ ሲሆን ተከታታይ ሪፖርቶች መቅረባቸውን እና ከተቋሙ የመጡ አካላት ጉዳዩን በቅርበት ሲከታተሉት እንደነበር ተገልጿል።

ከዚህ የክትትል ዝርዝር ውስጥ መውጣቷ በቀጣይ የአውሮፓ ህብረት በሚያዘጋጀው ግራጫ ሊስት ውስጥ ላለመግባት ለሚደረገ ጥረቶች እገዛ እንደሚያበረከት የተገለፀ ሲሆን የዓለም ዐቀፉ የፋይናንስ ግብረ- ኀይል (FATF) አብዛኛዎቹ አባል ሀገራት የአውሮፓ ኅብረት ሀገራት መሆናቸውን እንዳለ ገልፀዋል።

ክትትሉ የሚቀጥል በመሆኑ የሕግ ማሻሻያዎችን አጠናክሮ በማካሔድ እና የተቋማት ግንባታ ሥራዎችን በማጠናከር ዳግም ወደ ዝርዝሩ ላለመግባት ጥረት ይደረጋል ሲሉም ኀላፊው ተናግረዋል።

ተጋላጭ የሆኑ ዘርፎችን በጥናት የመለየት ሥራ በማከናወን ላይ መሆኑን የገለጸው ፋይናንስ ደኅንነት ተቋሙ የገንዘብ እና የሂሳብ ተቋማት፤ ጠበቆች እና የሕግ አካላት ለትርፍ ያልተቋቋሙ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች፤ ሪል ስቴቶች ለሕገወጥ ገንዘብ ዝውውር እና ሽብርተኝነትን በወንጀል የመደገፍ ድርጊት ሰለባ እንዳይሆኑ ለማድረግ እየተሠራ መሆኑ ተገልጿል።

ቅጽ 1 ቁጥር 51 ጥቅምት 15 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here