የ70 በ 30 የከፍተኛ ትምህርት ምጣኔ ተቀየረ

0
844

መንግሥት ለዓመታት ሲተገብር የነበረው እና ከተለያዩ አካላት ትችት ሲቀርበበት የቆየው የ70 በመቶ የተፈጥሮ ሳይንስ እንዲሁም 30 በመቶ የማህበራዊ ሳይንስ ምጣኔ በያዝነው ዓመት በ 55 በመቶ እና 45 በመቶ በሚል ተቀየረ።

በቋንቋ ትምህርቶች እና በቢዝነስ ነክ ትምህርቶች ላይ ያለው ፍላጎት ላለፉት ኹለት ዓመታት እየጨመረ በመምጣቱ በዚህ ዓመት ወደ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ከገቡ ተማሪዎች መካከል 55 በመቶው ወደ ተፈጥሮ ሳይንስ ሲገባ 45 በመቶው ወደ ማህበራዊ እንዲገባ ምክንያት እንደሆነ በሳይንስ እና ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ሚኒስትር ዴኤታ የሆኑት ሳሙኤል ክፍሌ ለአዲስ ማለዳ አረጋግጠዋል።

የቀደመው ቀመር ሲዘጃግ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ውስጥ ኢንዱስትሪው ከፍተኛ ቀጣሪ ይሆናል በሚል መንግሥት ያቀደውን እቅድ ተከትሎ እንደነበር የተናገሩት ሳሙኤል፣ በሒደት ግን ኢኮኖሚው የተባለውን የሰው ኀይል ባለመቅጠሩ የተማሪዎች ፍላጎት መቀየሩን ተናግረዋል። የትምህርት ፍኖተ ካርታው በሚሻሻልበት ወቅትም ይህ ምጣኔ ላይ ሰፊ ጥናት ተደርጎ የማህበራዊ ሳይንስ የትምህርት ዘርፎች ላይ ፍላጎት መጨመሩ በመረጋገጡ መንግሥትም ለመጣው የፍላጎት ለውጥ ምላሽ መስጠቱን ጨምረው ተናግረዋል።

የትምህርት ስርዓትን አቅጣጫ በጥቅሉ የሚያሳይ ጠቋሚ ሆኖ በያዝነው 2012 ወደ ሥራ የገባው ትምህርት ፍኖተ ካርታ በሚተገበርበት በ10 ዓመት ውስጥ፣ የሚፈለገው የሰው ኀይል በምን መልክ ተቀርጾ መውጣት አለበት የሚለውን እና ከኢትዮጵያ የልማት አቅጣጫ ጋር የትምህርት ሥርዓቱን ማቀናጀት ዓላማ ያደረገ ነው።
በዚህ ፍኖተ ካርታ ላይ የተሳተፉት እና ሂደቱን በማስተባበር ከፍተኛ ሚና የነበራቸው፤ በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ በልዩ ፍላጎት ትምህርት ክፍል ኀላፊ የዓለም ሎሬት ጥሩሰው ተፈራ (ፕሮፌሰር) ‹‹የበፊቱ ፖሊስ ትክክል አልነበረም፣ ከገበያው ጋር የማይስማማ እና የተመረቀውን ተማሪ ይቀጥራሉ የተባሉ ትልልቅ ፐሮጀክቶች ሳይሳኩ በመቅረታቸው ከተፈጥሮ ሳይንስ ተማሪዎች መካከል ከፍተኛ ተማሪዎች ሲመረቁበት የነበረውን የኢንጂነሪንግ ተመራቂዎች ሥራ አጥ ያደረገ ቀመር ነበር›› ሲሉ ለአዲስ ማለድ አስተያየታቸውን ገልጸዋል።

እንደ ጥሩሰው ገለጻ፣ ሥራ ፈላጊ እንጂ ሥራ ፈጣሪ መፍጠር ያልቻው ቀመር ገበያውን መሰረት አድረጎ እንዲሻሻል የፍኖተ ካርታው ሲዘጋጅ የተደረጉት ጥናቶች ጠቁመዋል። ‹‹የአካውንቲንግ፣ ማኔጅመንት አንዲሁም ሌሎች ተመሳሳይ የአገልግሎት ዘርፉ ላይ ተፈላጊነት ያላቸው ትምህርቶች በገበያው ላይ ብልጫ አሳይተዋል›› ያሉት ፕሮፌሰሩ ‹‹ነገር ግን ይህም በተከታተይ በሚደረጉ ጥናቶች ገበያውን ካልፈተሽን በአንዳንድ መስኮች እጥረት የሚፈጠር ሲሆን በአንዳንዱ ደግሞ ሥራ አጥ መፍጠራችን አይቀርም›› ሲሉ ቀመሩ ተራማጅ እንጂ ሕግ መሆን እንደሌለበት አስረድተዋል።

ኢትዮጵያ ስትገለገልበት የቆየችው የትምህርትና ሥልጠና ፖሊሲ በተለይም የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ተደራሽነት እንዲሁም ከፍተኛ የትምህርት ተቋማትን በየአካባቢው በመክፈት እና መሰል ጉዳዮች ላይ በተሠሩትን ሥራዎች ስኬታማ እንደነበር ጥሩሰው ለአዲስ ማለዳ አስረድተዋል።

ፍኖተ ካርታው የመምህርነት ሙያን ጨምሮ ከዚህ ቀደም በውጪ አገራት ተጽዕኖ ስር የነበሩት የትምህርት ሥርዓቶችን በተመለከተ አገር በቀል እውቀትን ለመጠቀምም የሚያስችል ነውም ብለዋል። በተለይም በእደ ጥበብ፣ በሕግ፣ በጤና እና መሰል ጉዳዮች አገር በቀል እውቀት ከግምት ከቷል የተባለው ፍኖተ ካርታው እነዚህን እውቀቶች በቅጡ በማጥናት ወደ ስርዓተ ትምህርት የሚገቡበት መንገድ መፈለግ አለበት በሚል ከታች ጀምሮ እንዲሰጥ እንደሚያደረግም አክለው ገልጸው ነበር።

ቅጽ 1 ቁጥር 51 ጥቅምት 15 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here