በጎዳና ተዳዳሪው ላይ አስገድዶ መድፈር ወንጀል የፈጸመው ፖሊስ ተፈረደበት

0
786

በልደታ ክፍለ ከተማ ወረዳ 9 በተለምዶ ቆጬ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ እድሜው 15 የሚጠጋ የጎዳና ተዳዳሪን በቁጥጥር ስር እንደዋለ በማስመሰል ወደ ጣቢያ በመውሰድ እና በገጀራ በማስፈራራት አስገድዶ የደረፈው ፖሊስ በ9 ዓመት ጽኑ እስራት ተቀጣ።

መጋቢት 3 ቀን 2011 ከሌሊቱ ሰባት ሰዓት ላይ በወረዳው በሚገኝ አንድ የማህበረሰብ አቀፍ የፖሊስ አገልግሎት መስጫ ቢሮ በቅርብ ርቀት ላይ ከሚገኝ በረንዳ ከተኙ ሦስት የጎዳና ተዳዳሪዎች መካከል፣ የግል ተበዳይን ከእንቅልፉ ቀስቅሶ የወሰደው የፖሊስ ባልደረባ የደንብ ልብሱን ለብሶም እንደነበር የፌደራሉ የመጀመሪያ ፍርድ ቤት የልደታ ምድብ ችሎት የሰማው የምስክርነት ቃል ያስረዳል።

‹‹እስረኛ ነህ፣ አስርሃለሁ›› የሚል ሰበብ በመስጠት የግለ ተበዳይ በጎዳና ላይ ያሉትን ልብሶቹን እንዳይዝ በማሳሰብ ለጥሎ ወደ ጣቢያው ይዞት ይሄዳል። የታዘዘውን የተቀበለው የጎዳና ተዳዳሪ ወደ ፖሊሱ የመኝታ ስፈራ ይዞት እንደሄደ እና ጓደኞቹም እንዳይከተሉት ማድረጉን በምስክረነቱ ገልጿል።

‹‹የፖሊስ አልጋ ላይ ተኛ ብሎ ካስተኛኝ በኋላ እርሱም የፖሊስ ልብሱን አውልቆ ተኛ፣ እኔም ማንኮራፋት ጀመርኩ›› ሲል የ15 ዓመቱ የግል ተበዳይ የምስክርነት ቃሉን ለፍርድ ቤቱ ሰጥቷል። በእንቅልፉ መሃልም ጥቃት እያደረሰበት እንደሆነ አውቆ በጩኸት የድረሱልኝ ጥሪውን ለማሰማት ቢሞክርም በብርድ ልብሱ እንዳፈነው እና በገጀራም እንዳስፈራራው ገልጿል። ፖሊስ በሰበሰበሰው የማስረጃ ዝርዝር ላይም ገጀራውን ጨምሮ የግል ተበዳይ የጠቀሳቸው ቁሳቁሶች በፎቶ ተነስተው ከመዝገቡ ጋር ተያይዘው ለፍርድ ቤቱ መቅረባቸውን አዲስ ማለዳ አረጋግጣለች።

ሌሊቱን ሙሉ ሦስት ጊዜ ተመሳሳይ ጥቃት እንደደረሰበት የተናገረው ታዳጊው፣ ድምፅ አሰምቶ ሰዎች እንዳይደርሱለት እንኳ በቅርብ ሰው እንዳልነበረና በዛም ላይ ፖሊሱ ከፍራሽ ስር የሚያወጣው ገጀራ ተስፋ እንዳስቆረጠው ተናግሯል።

ተበዳይ ቶሎ ወደ ፖሊስ ከማመልከት ይልቅ ጉዳዩን ለቅርብ ጓደኛው የነገረ ቢሆንም ጉዳዩ የአካባቢው ነዋሪዎች ጆሮ በመድረሱ ወደ ሕክምና እንዲሔድና ለፖሊስም እንደሚያመለክት ሆኗል። ቃሉን ሊሰጥ ወደ ፖሊስ ጣቢያ ባቀናበት ወቅት ጥቃቱን ከፈጸመበት ፖሊስ ጋር የተገናኙ ሲሆን ለምን እንደመጣ በጠየቀውም ወቅት ‹‹ፍርፋሪ ለማግኘት መጥቼ ነው›› ብሎ እውነቱን በመደበቅና ቃሉን ለተቀበለቸው ፖሊስም በመልክ ለይቶ ማሳየቱን የክስ ታሪኩ ያስረዳል።

ወዲያውኑ በቁጥጥር ስር የዋለው ፖሊሱ፣ በፍርድ ሒደቱ ላይ ሕግ ለማስከበር የተሰጠውን ሥልጣኑን ያለአግባብ መጠቀሙ፣ የተለየ ጭካኔ ማሳየቱ እና ወንጀሉ በሌሊት መፈጸሙ ማክበጃ ሆነው ቀርበው የነበረ ቢሆንም፤ ፖሊሱ ከዚህ ቀደም ክስ የሌለበት እንዲሁም ቤተሰብ አስተዳዳሪ መሆኑን በማስረዳቱ ቅጣቱን ሊያቀልለት እንደቻለ የክስ መዝገቡ ያስረዳል። ይሁንና ወንጀሉ ከ3 ዓመት እስከ እስከ 13 ዓመት ጽኑ እስራት የሚያስቀጣ ነው።

ችሎቱም ጥቅምት 13 ቀን 2012 በዋለው ችሎት፤ ተከሳሽ በፈጸመው ለአካለ መጠን ባልደረሱ ልጆች ላይ የሚፈጸም የግብረሰዶም ጥቃት ወንጀል የተከሰሰ ሲሆን በ9 ዓመት ጽኑ እስራት እንዲቀጣ ወስኖበታል።

በጉዳዩ ላይ አስተያየታቸውን ለአዲስ ማለዳ ያካፈሉት በሕጻናትና ሴቶች ጉዳይ ሚኒስቴር የሕጻናት የድጋፍ አገልግሎትና ኢንስፔክሽን ዳይሬክተር ተወካይ በለጠ ዳኜ በበሉላቸው፣ የተፈጸመውን ጥቃት እንደ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤት እንደሚቃወሙ አነስተዋል። መሥሪያ ቤቱ እንዲህ ባሉ ጥቃቶች ላይ እርምጃ የመውሰድ ሥልጣን ባይኖረውም ጉዳዩ ትኩረት እንዲያገኝ ከሚመለከታቸው ጋር በመተባበርም መሠራት አለበትም ብለዋል።

ጎዳና ተዳዳሪ ሕጻናትና ልጆችን መጠበቅና መደገፍ ከባድና አስቸጋሪ መሆኑን አያይዘው ያነሱት በለጠ፣ ይህንን ለማስቀረት ያለው አማራጭ ህጻናት ጎዳና ላይ እንዳይወጡ መከላከልና የወጡትም እንዲመለሱ ማድረግ ነው ብለዋል። በሕግ እርምጃ ሊወሰድባቸው የሚገቡትንም ትኩረት ሰጥቶ ሕግ ማስከበር ያስፈልጋል ሲሉም አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ በአሁኑ ሰዓት በብዛት ጎዳና ተዳዳሪ ይወጡባቸዋል በተባሉት አራት ክልሎች ማለትም ደቡብ ኢትዮጵያ ክልል፣ አማራ፣ ትግራይ እና ኦሮሚያ እንዲሁም የተለዩ 12 ዞኖችና 36 ወረዳዎች ላይ እየሠራ መሆኑን ገልጸዋል።

ቅጽ 1 ቁጥር 51 ጥቅምት 15 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here