የነዳጅ ዋጋ ግስጋሴ

0
2084

ገረመ ጌጤነህ በደብረ ብርሃን ከተማ በሸቀጣ ሸቀጥ ንድግ ላይ የተሰማሩ ነጋዴ ናቸው። የተሰማሩበት የንግድ ዘርፍ ከጭነት ትራንስፖርት ሰጪ ተሽከርካሪ ጋር በቀጥታ የተገናኘ መሆኑን ይገልጻሉ። በዚህም የታለመ የነዳጅ ድጎማ መተግበር ከተጀመረ በኋላ፣ ሸቀጣ ሸቀጥ ከአዲስ አበባ ወደ ደብረ ብርሃን ለማጓጓዥ የሚያወጡት የመኪና ኪራይ ወጪ መጨመሩን ይናገራሉ።

‹ሳልወድ በግድ እያንዳንዷ ሸቀጥ ላይ የትራንስፖርት ጭማሪ ወጪውን የሚያካክስ ጭማሪ ማድረጌ አይቀርም› የሚሉት ነጋዴው፣ ‹መንግሥት የዋጋ ጭማሪ አታድርጉ የሚለው ማስፈራሪያ ከእውነታው ጋር የማይጣጣም ነው› ይሉታል።

መንግሥት የነዳጅ ምርቶችን የማቅረብ እና የመሸጫ ዋጋ የመተመን ሥልጣን ያለው ሲሆን፣ በዚህም የነዳጅ ምርቶችን የመሸጫ ዋጋ በየወሩ ይከልሳል። የነዳጅ ዋጋ በየወሩ እንደየሁኔታው የሚከለስ ቢሆንም፣ አብዛኛውን ወራት ከአውሮፕላን ነዳጅ ውጭ ያሉት የነዳጅ ምርቶች ባሉበት ዋጋ እረግተው እንዲቆዩ ሲደረግ መቆየቱ የሚታወስ ነው።

ይሁን እንጂ መንግሥት ለነዳጅ ድጎማ በየዓመቱ የማወጣው ወጪ ከጊዜ ወደ ጊዜ ከአቅሜ በላይ እየሆነ ነው በሚል፣ የታለመ የነዳጅ ድጎማ ከሰኔ 29/2014 ጀምሮ ተግባራዊ አድርጓል። ተግባራዊ የተደረገው የነዳጅ ድጎማ ለሕዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪ ተሽከርካሪዎች የሚሰጥ ሲሆን፣ 160 ሺሕ በላይ ተሽከርካሪዎች በድጎማው ተጠቃሚ ሆነዋል ተብሏል።

የታለመ የነዳጅ ድጎማ ተጠቃሚ እንዲሆኑ የተለዩ የሕዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪ ተሽከርካሪዎች የነዳጅ ድጎማ ተጠቃሚ ለመሆን አስፈላጊ መረጃዎችን በመስጠት በኢትዮ ቴሌኮም የሽያጭ ማእከላት በኩል ተመዝግበው አገልግሎት እያገኙ ነው ተብሏል። ከሰኔ 29/2014 ጀምሮ ተግባራዊ በመደረግ ላይ የሚገኘው የታለመ የነዳጅ ድጎማን ተከትሎ የተደረገው የነዳጅ ምርቶች የመሸጫ ዋጋ እንደገና ከሦስት ወር በኋላ የዋጋ ማስተካከያ ተደርጎበታል።

የኹለተኛ ዙር የታለመ ድጎማና የችርቻሮ መሸጫ ዋጋ ጭማሪን በተመለከተ የንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር በሰጠው መገለጫ፣ በዓለም ገበያ የነዳጅ ዋጋ በመስከረም ወር መጠነኛ መረጋጋት ያሳየ ቢሆንም፣ በኢትዮጵያ በሥራ ላይ ካለው ዋጋ ጋር ሲነጻጸር ልዩነቱ አሁንም ሰፊ እንደሆነ ቀጥሏል ብሏል። በዚህም ልዩነቱን ለማጥበብ የነዳጅ ምርቶች የችርቻሮ መሸጫ ዋጋ የዓለም ገበያን በሚያንጸባርቅ ሁኔታ ማስተካከያ እንዲደረግ የሚኒስትሮች ምክር ቤት በሰጠው ውሳኔ መሠረት፣ በመስከረም ወር የነበረውን የዓለም የነዳጅ ዋጋ መነሻ ተደርጎ የተሰላውና ከመስከረም 18/2015 ጀምሮ ሥራ ላይ የሚውል የነዳጅ ውጤቶች መሸጫ ዋጋ ማሻሻያ ተግባራዊ ተደርጓል።

በማሻሻያው መሠረት የመስከረም ወር በዓለም ገበያ የነበረውን የነዳጅ ውጤቶች አማካይ ዋጋ በመውሰድ መንግሥት የነዳጅ ዋጋን ለማረጋጋት ያደረገውን የ50 በመቶ የታክስ ቅናሽ መነሻ በማድረግ በተደረገው የዋጋ ክለሳ ጥናት መሠረት፣ በሥሌት የተደረሰበት የአንድ ሊትር የነጭ ናፍጣ የችርቻሮ መሸጫ ዋጋ አንድ ሊትር 81.6 ብር የደረሰ ሲሆን፣ የቤንዚን ደግሞ 66.22 በሊትር ሆኗል።

በመጀመሪያው ዙር የታለመ የነዳጅ ድጎማ ጭማሪ መሠረት፣ ቤንዚን በሊትር 47 ብር ከ83 ሳንቲም፣ ነጭ ናፍጣ በሊትር 49 ብር ከ02 ሳንቲም፣ ኬሮሲን በሊትር 49 ብር ከ02 ሳንቲም፣ ቀላል ጥቁር ናፍጣ በሊትር 53 ብር ከ10 ሳንቲም፣ ከባድ ጥቁር ናፍጣ በሊትር 52 ብር ከ37 ሳንቲም፣ የአውሮፕላን ነዳጅ በሊትር 98 ብር ከ83 ሳንቲም ነበር።

ከሦስት ወር በኋላ ተሻሽሎ ተግባራዊ በመደረግ ላይ የሚገኘው በኹለተኛው ዙር የታለመ የነዳጅ ድጎማ ማሻሻያ መሠረት፣ አንድ ሊትር ቤንዚን 57.05 ብር፣ ነጭ ናፍ 59.90 ብር እንዲሁም ኬሮሲን 59.90 ብር እንዲሆን ተደርጓል። በመጀመሪያው ዙር ተፈጻሚ በሆነው የታለመ የነዳጅ ድጎማ የነበረው የዋጋ ጭማሪ አሁን ላይ ተግባራዊ ከተደረገው ኹለተኛ ዙር የዋጋ ማሻሻያ ጋር ሲነጻጻር እስከ 20 በመቶ የሚደርስ ልዩነት አሳይቷል።

በኹለተኛው ዙር የታለመ የነዳጅ ድጎማ የዋጋ ማስተካከያ  ጭማሪ የተደረገባቸው ቤኒዚን፣ ነጭ ናፍጣና ኬሮሲን ሲሆኑ፣ የአውሮፕላን ነዳጅ፣ ቀላል ጥቁር ናፍጣ እና ከባድ ጥቁር ናፍጣ ባለፈው ወር የመሸጫ ዋጋ እንደሚቀጥሉ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ይፋ አድርጓል።

ለሕዝብ ትራንስፖርት ተሽከርካሪዎች ወይም የታለመ ድጎማ ተጠቃሚ ተሽከርካሪዎች 15 በመቶ በመንግሥት እንዲደጎሙና ቀሪውን 10 በመቶ እንዲከፍሉ በማድረግ የድጎማ መጠኑን በቴሌ ብር አማካኝነት ተመላሽ እንዲሆንላቸው ይደረጋል።

መንግሥት ተግባራዊ እያደረገ በሚገኘው የታለመ የነዳጅ ድጎማ ያልተካተቱ ተሽከርካሪዎች፣ የንግድ እና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር ባወጣው የነዳጅ ምርቶች የመሸጫ ዋጋ ነዳጅ ይገዛሉ። የዋጋ ንረት የማኅበረሰቡ ችግር እየሆነ በመጣበት ሁኔታ፣ ተደርቦ የመጣው መንግሥት ይፋ ያደረገው የታለመ የነዳጅ ድጎማን መንግሥት በበጎ ሁኔታ ቢያየውም፣ የምጣኔ ሀብት ባለሙያዎች የኑሮ ውድነት አባባሽ ምክንያት እንዳይሆን ስጋታቸውን ይገልጻሉ።

የነዳጅ ምርቶች የመሸጫ ዋጋ ጭማሪን ተከትሎ በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ በሌሎች ምርቶች እና አገልግሎቶች ላይ የዋጋ ጭማሪ ማስከተሉ፣ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየናረ በመጣው የዋጋ ግሽበት ላይ ሌላ አቀጣጣይ ምክንያት እንደሚሆን በኢትዮጵያ የፖሊሲ ጥናት ኢንስቲትዩት ተመራማሪ ክፍሉ ደገፉ (ዶ/ር) ይገልጻሉ።

‹‹የነዳጅ ዋጋ መጨመር ዋነኛ የዋጋ ግሽበት አቀጣጣይ ነው›› የሚሉት ክፍሉ፣ መንግሥት የዋጋ ጭማሪውን ካለው ወቅታዊ ኹኔታ አንጻር ያለበትን ጫና ለመቀነስ ያደረገው ቢሆንም፣ የሚያስከትለው አሉታዊ ተጽዕኖ ቀላል አለመሆኑን ጠቁመዋል።

በኢትዮጵያ ገበያ የዋጋ ግሽበት ከጊዜ ወደ ጊዜ እያሻቀበ መምጣቱን የኢትዮጵያ ስታትስቲክስ አገልግሎት በየወሩ የሚያወጣው ሪፖርት ያመላክታል። በኢትዮጵያ የሚታየው የዋጋ ግሽበት በአንድ ምርት ላይ የመሸጫ ዋጋ ጭማሪ ሲደረግ የሌሎች ምርቶች መሸጫ ዋጋ አብሮ ማደጉ የተለመደ እየሆነ የመጣ ጉዳይ ነው።

የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር የነዳጅ ምርቶች መሸጫ የዋጋ ማስተካከያ ካደረገ በኋላ፣ ‹‹መንግሥት በየወቅቱ የሚያደርገውን የነዳጅ ዋጋ ማስተካከያ ተከትሎ በሸቀጦች እና በመሰል ምርቶች ላይ ጭማሪ በሚያደርጉ አካላት ላይ እርምጃ ይወሰዳል።›› ብሏል። ይሁን እንጂ የመንግሥት ማስፈራሪያ ከእውነታው ያፈነገጠ መሆኑን ከምጣኔ ሀብት ባለሙያዎች እስከ ነጋዴዎች እየገለጹ ነው።

የምጣኔ ሀብት ባለሙያዎች፣ በኢትዮጵያ የሚታየው የዋጋ ግሽበት በአንድ ምርት የዋጋ መጨመር ላይ ሰበብ አድርጎ የሚከስት መሆኑን ብዙ ጊዜ ሲገልጹ ይደመጣል። የነዳጅ ዋጋ ጭማሪ በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ የሚነካቸው ምርቶች እና አገልግሎቶች ላይ የዋጋ ጭማሪ ለማድረግ አስገዳጅ እንደሚሆንም ስጋታቸውን አስቀድመው ሲገልጹ ነበር።

ባለሙያዎቹ እንደሚሉት ከሆነ፣ መሠረታዊ የሆነውን የነዳጅ ድጎማን ማንሳት ባለው የኑሮ ውድነት ላይ ‹እየነደደ ባለ እሳት ላይ ነዳጅ ማርከፍከፍ› እንዳይሆን ስጋት አላቸው።

የሕዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪ ተብለው ድጎማ ውስጥ ከተካተቱት ተሽከርካሪዎች ውጪ የሚገኙት፣ በተለይ የጭነት አገልግሎት የሚሰጡ ተሽከርካሪዎች በነዳጅ ዋጋ መጨመር ምክንያት የሚሰጡት የአገልግሎት ክፍያ ከጨመረ በሚያጓጉዙት ምርት ላይ የዋጋ ጭማሪ እንዲከሰት አስገዳጅ እንደሚሆን ባለሙያዎች ያነሳሉ።

ለገበያ የሚቀርቡ ምርቶች የትራንስፖርት ዋጋ ሲጨምር በትራንስፖርት ተጓጉዘው ለገበያ የሚቀርቡ ምርቶች እንደመሆናቸው፣ መሸጫ ዋጋቸው መጨመሩ የማይቀር መሆኑን አስቀድመው ባለሙያዎች ሲገልጹ ነበር።

በታለመ የነዳጅ ድጎማው መሠረት የሕዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪ ተሽከርካሪዎች ዕለታዊ የነዳጅ ፍጆታ ተመድቦላቸዋል። በዚህም ለባለ ሦስት እግር (ባጃጅ) በቀን ሰባት ሊትር፣ ለባለ ኮድ አንድ እና ሦስት የከተማ ሚኒባስ ታክሲዎች በቀን 25 ሊትር፣ ለአነስተኛ አገር አቋራጭ የሕዝብ ማመላለሻ ተሽከርካሪዎች በቀን 65 ሊትር፣ ለመለስተኛ አገር አቋራጭ የሕዝብ ማመላለሻ ተሽከርካሪዎች በቀን 94 ሊትር፣ ለከተማ ሕዝብ ማመላለሻ አውቶብስ በቀን 102 ሊትር፣ ለፐብሊክ አውቶብስ 25 ሊትርና ለአገር አቋራጭ አውቶብስ 65 ሊትር ዕለታዊ ፍጆታ ተመድቦላቸዋል።

የሕዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪ ተሽከርካሪዎች ዓመታዊ የነዳጅ ፍጆታ ተቀራራቢ የሊትር መጠን ግምት በጥናት መለየቱና እያንዳንዱ ተሽከርካሪ የሚጠቀመውን የነዳጅ መጠን ያገናዘበ ስሌት በመቀመጡ፣ ተሽከርካሪዎቹ ያለ ብክነት የታለመ የነዳጅ ድጎማን ጥቅም ላይ እንዲያውሉ የሚያግዝ ነው ተብሏል።

በታለመው የነዳጅ ድጎማ ተጠቃሚ የሆኑ የሕዝብ ትራንስፖርት ተሽከርካሪዎች ተብለው የተመደቡ ብቻ በተቀመጠላቸው እለታዊ የነዳጅ ፍጆታ ዝርዝር መሠረት እለታዊ የነዳጅ መጠን ማግኘት እንደሚችሉ የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴር ይፋ ማድረጉ የሚታወስ ነው።


ቅጽ 4 ቁጥር 205 መስከረም 28 2015

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here