የስሚንቶ አከፋፋዮች የትርፍ ህዳግ አምስት በመቶ እንዲሆን ተወሰነ

0
2207

የስሚንቶ አከፋፋዮች የትርፍ ህዳግ አምስት በመቶ እንዲሆን መወሰኑን አዲስ ማለዳ የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር ለክልሎችና ከተማ አስተዳደር ንግድ ቢሮዎች ከላከው ደብዳቤ ተመልክታለች።

ከፋብሪካዎች የበር መሸጫ ዋጋ በመነሳትም በክልል ለሚኖሩ ሽያጮች የዋጋ ተመን ለማውጣት የሚያግዝ የዋጋ ግንባታ አሠራርን ንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር ለክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች በላከው ደብዳቤ አሳውቋል።

በዚህም መሠረት የአንድ ኩንታል ስሚንቶ የትራንስፖርት መጓጓዣ 50 ሳንቲም በኪሎ ሜትር፣ የአንድ ኩንታል ስሚንቶ የመጫኛ እንዲሁም የማውረጃ የነጠላ ዋጋ 10 ብር በድምሩም 20 ብር፣ የመጋዘን ኪራይ እና ሌሎች ተገቢ የሆኑ ወጪዎችን በኩንታል ታሳቢ ማድረግ እንደሚቻል በደብዳቤው ተገልጿል። የፋብሪካዎች የበር መሸጫ ዋጋ ላይ ይህንን የዋጋ ግንባታ አሠራርን የተከተሉ ወጪዎችን በመደመር የአከፋፋዮች የትርፍ ህዳግ ደግሞ ከአጠቃላይ ወጪው አምስት በመቶ እንዲሆን ተወስኗል።

የስሚንቶ ፋብሪካዎች የአንድ ኩንታል ስሚንቶን የበር መሸጫ ዋጋ በንግድና ቀጣናዊ ሚኒስቴር ተወስኖ ከመስከረም 5/2015 ጀምሮ በሥራ ላይ የዋለ ሲሆን፣ በዚህም መሠረት ዳንጎቴ ስሚንቶ 549.49 ብር፣ ደርባ ስሚንቶ 590.59 ብር፣ ሀበሻ ስሚንቶ 683.44 ብር፣ ሙገር ስሚንቶ 643.95 ብር፣ ናሽናል ስሚንቶ 561.39 ብር፣ ኢትዮ ስሚንቶ 595.66 ብር፣ ኩዩ ስሚንቶ 628.10 ብር፣ ፓዮኔር ስሚንቶ 510.04 ብር፣ ካፒታል ስሚንቶ 633.38 ብር፣ ኢስት ስሚንቶ 506.99 ብር እንዲሆን መወሰኑ የሚታወስ ነው።

ይህንንም ማስፈጸም የክልልና የከተማ አስተዳደር ንግድ ቢሮዎች ኃላፊነት ሲሆን፣ በዚሁ የዋጋ ግንባታ አሰራር መሠረት በእያንዳንዱ የመሸጫ ቦታ የሚኖረው ዋጋ እንዲወሰን ሚኒስቴሩ ለንግድ ቢሮዎች በላከው ደብዳቤ አሳስቧል። ይህን በመከታተልም ሳምንታዊ የጽሑፍ ሪፖርት የክልልና የከተማ አስተዳደር ንግድ ቢሮዎች ለንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር እንዲልኩ ተመላክቷል።

የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር፣ በአገር ዐቀፍ ደረጃ እያደገ በመጣው የግንባታ ዘርፍ እና በሌሎችም ልዩ ልዩ ምክንያቶች በስሚንቶ ምርት አቅርቦትና ፍላጎት መካከል ያለው ልዩነት እየሰፋ መምጣቱን አመላክቶ፣ በገበያ ላይ የተከሰተው የስሚንቶ ምርት እጥረት የሚያሳድረውን ጫና ለመቋቋምና ፍትሐዊ የስሚንቶ ክፍፍል እንዲኖር ለማስቻል ይረዳል ያለውን የስሚንቶ ግብይትና ስርጭት መመሪያ ቁጥር 908/2014ን ተግባራዊ ማድረጉ ይታወሳል።

በዚህ መመሪያ መሠረትም በክልልና ከተማ አስተዳደር ንግድ ቢሮዎች ስሚንቶ እንዲያከፋፍሉ የተፈቀደላቸው አከፋፋዮች ብቻ በዚህ የዋጋ ግንባታ አሠራር መሠረት በሚተመንላቸው ዋጋ ስሚንቶውን ለሽያጭ የሚያቀርቡ ይሆናል።

በመመሪያው መሠረት ለሕዝብ ከፍተኛ ጠቀሜታ ያላቸው ሜጋ ፕሮጀክቶች ከስሚንቶ አምራች ፋብሪካዎች በቀጥታ ግዢ የሚፈጽሙ ሲሆን፣ ለአንድ ጊዜ ለግል ወይም ለቤተሰብ ፍጆታ ስሚንቶ አከፋፋዮች እንዲሸጡ የተፈቀደው ከፍተኛ የስሚንቶ መጠን ደግሞ 15 ኩንታል እንዲሆን ንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር ይፋ ባደረገው የሕዝብ ማስታወቂያ ማሳወቁ የሚታወስ ነው።

ስሚንቶ አምራች ፋብሪካዎች መንግሥት የመሸጫ ዋጋ ተመን ማውጣቱን ተከትሎ ቅሬታቸውን እየገለጹ ነው። የስሚንቶ ምርት አቅርቦት እጥረት በኮንስትራክሽን ዘርፉ ከፍተኛ ጫና የፈጠረ ሲሆን፣ የስሚንቶ ገበያውን መንግሥት ቢቆጣጠረውም ችግሩ አልተቀረፈም።


ቅጽ 4 ቁጥር 205 መስከረም 28 2015

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here