ግንደበረት እና አቡና ግንደበረት ከአዲስ አበባ በስተምዕራብ 190 ኪሎ ሜትር ገደማ ርቀት ላይ በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ሸዋ ዞን የሚገኙ ወረዳዎች ናቸው። ከዓመታት በፊት ለኹለት ከመከፈሉ በፊት ግንደበረት አንድ ወረዳ ነበር። በደቡብ ከጀልዱ ወረዳ ጋር፣ በደቡብ ምዕራብ አቅጣጫ ከአምቦ ጋር፣ በምዕራብ ከሆሮ ጉዱሩ ወለጋ በሚለየው የጉደር ወንዝ ይዋሰናል። በሰሜንና ሰሜናዊ ምዕራብ በኩል ከአማራ ክልል ጎጃም በሚለየው የአባይ ወንዝ ይዋሰናል። በምሥራቅ ደግሞ ከኦሮሚያ ሰሜን ሸዋ ዞን ከሚለየው የሙገር ወንዝ የሚዋሰን፣ በወይና ደጋማ አካባቢ የተከበበ ደጋማ ስፍራ ያለው ነው፤ ግንደበረት።
የአቡና ግንደበረት ዋና ከተማ ቀላጤ ስትባል የግንደበረት ደግሞ ካቺሲ ትባላለች። እነዚህ ኹለት ወረዳዎች ባለፉት አራት ዓመታት ገደማ በምዕራብ ኦሮሚያ ሰፍኖ ያለው የሰላም እጦት ማዕበል ደርሷቸው፣ ኑሯቸው በጭንቅ ከሆነ ሦስተኛ ዓመት መያዛቸውን ነዋሪዎች ይናገራሉ።
የግንደበረት ካቺሲ ከተማ ነዋሪ የሆኑት ዋቆ ገማቹ (ለዚህ ዘገባ ሲባል ሥማቸው የተቀየረ) እንደሚሉት፣ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሽብርተኝነት የተፈረጀው ኦነግ ሸኔ ወደ አካባቢው ከገባ ሦስት ዓመታትን እያስቆጠረ ነው። በአሁን ሰዓት ከወረዳው ቀበሌዎች መንግሥት የሚያስተዳድረው አሥሩን ብቻ ሲሆን የተቀሩትን 23 በተለይ ገጠራማ ቀበሌዎችን የሚቆጣጠረው ኦነግ ሸኔ ነው።
ቀደም ሲል የነበሩ መረጃዎች እንደሚያሳዩት፣ ኹለቱ ግንደበረት ወረዳዎች ከሕወሓት ኢሕአዴግ ዘመን ጀምሮ የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) ከፍተኛ ሕዝባዊ ድጋፍ ከነበሩት አካባቢዎች አንዱ ነው። ብዙ ጊዜ በሚደረጉ የተቃውሞ ሰልፎች ላይም የኦነግ ሥም ገኖ ይወጣ እንደነበር መረጃዎች ያሳያሉ።
ሌላኛው በግንደበረት ወረዳ ነዋሪ እና የመንግሥት ሠራተኛ ጃርሶ ጎበና (ለዚህ ዘገባ ሲባል ሥማቸው የተቀየረ) እንደሚሉት፣ የኦነግ ሸኔ ኃይል ከኹለት ዓመት በፊት መጀመሪያ ወደ ወረዳው ሲገባ በርካታ ገጠራማ አካባቢዎች በደስታ ተቀብለውት ነበር። አፍታም ሳይቆይ ግን ኃይሉ ኅብረተሰቡን ትጥቅ ማስፈታትና ኢኮኖሚያዊ ጫናዎችን ማድረግ ጀምሯል። ሰዎችን እያገተ ከመቶ ሺሕ ብሮች እስከ ሚሊዮን ይጠይቃል። ገበሬውም የሸኔን ታጣቂዎች በመመገብ ተሰላችቷል ይላሉ። በመንግሥት ኃይልና በሸኔ ታጣቂዎች መካከል የሚደረገው ጦርነትና መገፋፋትም የሕዝቡን ኑሮ እጅጉን እንደጎዳው ይናገራሉ።
አሁንስ ለኦነግ ሸኔ ሕዝቡ ያለው ድጋፍ ምን ይመስላል ስትል አዲስ ማለዳ ላቀረበችው ጥያቄ የግንደበረትም ሆነ አቡና ግንደበረት ነዋሪዎች በሰጡት ምላሽ፣ ሕዝቡ አሁን የሚያደርገው ቢጠፋው እንጂ ለሸኔ ቀድሞም በነበረው ድጋፍ እጅጉን ስለ መጸጸቱ ይናገራሉ።
የሆነው ሆኖ የመንግሥት ኃይሎችና የኦነግ ሸኔ ኃይል በተደጋጋሚ ውጊያዎችን ማድረጋቸውን፣ ነገር ግን እስካሁን ኅብረተሰቡ ሙሉ በሙሉ ነጻ አለመውጣቱን እና በኹለቱም ወረዳዎች ሰፊው የገጠሩ አካባቢ በሸኔ ኃይሎች ስር መሆኑን ነው ነዋሪዎች የሚናገሩት። የሸኔ ታጣቂዎች ግለሰቦች ገንዘብ እንዲሰጡ፣ ጦር መሣርያ ካላቸው እንዲያስረክቡ ይጠይቃሉ፣ እምቢ ያለው ላይ ደግሞ እስከ መግደል የሚደርስ እርምጃ ይወስዳሉ፡፡ በዚህ መልኩ ታፍነው የተወሰዱ፣ የሞቱና ከደረሰባቸው ዘረፋ የተነሳ ሕይወታቸውን በራሳቸው ያጠፉ ነዋሪዎች መኖራቸውንም ይናገራሉ።
ከዚህ ሁሉ ብለው ደግሞ አቅም ያላቸውና የቻሉት ከኹለቱም ወረዳዎች ጨርቄን ማቄን ሳይሉ የሸሹ ሰዎች ቁጥር ቀላል እንዳልሆነም ይናገራሉ። ይህ ሁሉ ተዳምሮ የአካባቢውን ልማትና እድገት ወደ ኋላ ከመጎተቱ ባሻገር፣ ለዛሬውም ቢሆን ኑሮን የማይቀመስ እንዳደረገባቸው ነዋሪዎች ይናገራሉ።
በአቡና ግንደበረት ቀላጤ ከተማ ነዋሪ የሆኑት ሰላም ሞቲ (ለዘገባው ሲባል ሥማቸው የተቀየረ) አንድ ኪሎ ሽንኩርት እስከ አንድ መቶ ብር እየገዙ መሆናቸውን ይናገራሉ። እንደ ሳሙና፣ ዘይት፣ ጨውና ሌሎች ወረዳው የማያመርታቸው እና ከአዲስ አበባ የሚቀርቡ ሸቀጣ ሸቀጦች ዋጋ ከሚታሰበው በላይ እንደናረ ይጠቅሳሉ።
ይህ ሁኔታ ለግንደበረትም ተመሳሳይ ሲሆን፣ የካቺሲ ነዋሪ የሆኑት ዋቆ እንደሚሉት ሩብ ኪሎ የሚመዝን ጥሬ ጨው በኩባያ መለኪያ እስከ ሠላሳ በር እየተሸጠ ነው። አምስት ሊትር ዘይትም አይገኝም እንጂ ሲገኝ ካቺሲ እስከ አንድ ሺሕ አምስት መቶ ብር በአማካይ ይሸጣል፡፡ አቅርቦቱ ሲኖር እና ይብሱን ሲጠፋ በአንድና ኹለት መቶ ብሮች ከፍ ወይም ዝቅ ሊል ይችላል ይላሉ።
የዋጋ ንረቱ በዋናነት በመላው አገሪቱ ከሚስተዋለው ሁኔታ በተጨማሪ የግንደበረቶችን ለየት ያደረገው የትራንስፖርት ጉዳይ ነው። ግንደበረት ከጊንጪ ከተማ በኋላ ያለው ከአንድ መቶ ኪሎ ሜትር ያላነሰ መንገድ ለብዙ ዓመታት ሳይሠራ የቆየና የጠጠር መንገድ ነበር። ከመልክአ ምድሩ አስቸጋሪነት የተነሳ ብዙዎች በትራፊክ አደጋ ሕይወታቸውን ሲያጡ መኖራቸውን እና ወደ አዲስ አበባ ወይም ሌሎች ከተሞች ለመሔድ በታሰበ ቁጥር “በሰላም እንገባ ይሆን” የሚለው የዘመናት ሰቀቀናቸው እንደሆነ ይናገራሉ። ይኸው መንገድ ግንባታው ወደ አስፓልትነት ደረጃ ሊያድግ ተጀምሮ የነበረ ቢሆንም በጸጥታ ችግር ጀልዱ ወረዳ ደርሶ ቆሟል።
በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ እንዲሉ፣ በዚህም ብሶ የወረዳው ዙርያ ገጠራማ አካባቢዎች በኦነግ ሸኔ መያዛቸው ደግሞ ለነጋዴዎች ሁኔታውን አሳሳቢ በማድረጉና ተደጋጋሚ የመታፈን አደጋዎችም በማጋጠማቸው የንግድ መኪኖች መመላለስ ያቋረጡበት ጊዜ ነበር። በአቡና ግንደበረት ነዋሪ የሆኑት ሌንጮ ገረመው (ለዚህ ዘገባ ሲባል ሥማቸው የተቀየረ) እንደሚሉት፣ አሁን ከስንት አንዴ የጭነት መኪኖች ተጠባብቀው፣ ቁጥራቸው በርከት ሲል በመንግሥት ጦር ታጅበው እስከ ጀልዱ ወረዳ ሽኝት ይደረግላቸዋል። ሲመለሱም እንዲሁ ተጠባብቀው እጀባ ተደርጎላቸው ይገባሉ ይላሉ። ይህ ሁኔታ ባለተሽከርካሪዎች የጭነት ዋጋ እንዲጨምሩ ያደረገ ሲሆን፣ በሰላሙ ጊዜ ሃምሳ ብር እንኳን የማይከፈልበት አነስተኛ በሚባለው የሳሙና ካርቶን እስከ ሦስት መቶ ብር ያስከፍላሉ ይላሉ።
ኦነግ ሸኔ በሚቆጣጠራቸው የወረዳው አካባቢዎች ካሉ ትምህርት ቤቶች አገልግሎት መስጠት ያቆሙ መኖራቸውንም ከነዋሪዎች ለማወቅ ተችሏል። ከዚህም የተነሳ በተለይ በካቺሲ የተማሪ ቁጥር እጅግ መብዛቱንም ነዋሪዎቹ ይናገራሉ።
ሥማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ የግንደበረት ወረዳ አስተዳደር ከፍተኛ ኃላፊ በአካባቢው ስላለው ሁኔታ አስተያየታቸውን ለአዲስ ማለዳ ሰጥተዋል። በሰጡት አስተያየትም፣ ነዋሪዎቹ ያነሷቸው ጉዳዮች ከሞላ ጎደል ትክክል ናቸው ይላሉ። ኃላፊው እንደሚሉት፣ የኹለቱ ግንደበረቶች መልክአ ምድራዊ አቀማመጥ በሽብርተኝነት ለተፈረጀው የሸኔ ቡድን አስተዋጽኦ ማድረጉን ይናገራሉ።
ኹለቱ ግንደበረቶች ከአጎራባች አካባቢዎች ጋር የሚዋሰኑባቸው እንደ ሙገር፣ አባይ እና ጉደር ወንዞች፣ የወንዞቹን ተፋሰስ ተከትሎ ያለው ቆላማ እና ደጋማ አካባቢ፣ የመንገድ መሠረተ ልማት አለመኖር እና የአካባቢው ስፋት…ወዘተ የሽብር ቡድኑን ለማጥፋት የሚደረገውን ጥረት ፈታኝ አድርጎት መቆየቱንም ይናገራሉ። የመንግሥት የጸጥታ ኃይል ሲሰማራ አድራሻቸውን በፍጥነት ይቀያይራሉ ይላሉ ኃላፊው።
የኦነግ ሸኔ ኃይል ሙሉ ወረዳውን ለመቆጣጠር በተደጋጋሚ ጥረት ማድረጉን ነዋሪዎችም የተናገሩ ሲሆን፣ ኃላፊው እንደሚሉት የቡድኑን ሙከራዎች ሁሉ ማክሸፍ ተችሏል ይላሉ። የሽብር ቡድኑ ያስተዳድራቸዋል የተባሉ ቀበሌዎችን በሚመለከት ኃላፊው ጉዳዩን እንደሚከተለው ይገልጻሉ፣ ‹‹የመንግሥት ኃይል ሲሰማራ ከአንዱ ወደ ሌላው ስፍራ ተፈጥሯዊ መልከአ ምድሩን እንደ ምሽግ በመጠቀም በመዘዋወር እንጂ ቋሚ የሆነ አስተዳደር ፈጥረዋል ማለት አይደለም።››
ነገር ግን፣ በገጠሩ ሕዝብ ላይ የሽብር ቡድኑ ከፍተኛ ሰቆቃ እያደረሰ ሲሆን፣ ትላንት አርሶና አርብቶ ‹ብዙዎችን ይመግብ የነበረ ሕዝባችን፣ ሽማግሌዎች ሳይቀሩ ባዶ እጃቸውን ቀርተው ለልመና ተዳርገዋል› ይላሉ ኃላፊው። ከወረዳው አስተዳደር የጸጥታ አካላት በተጨማሪ ከክልልና ከመከላከያ የጸጥታ ኃይሎች ለወረዳው የተላኩ ቢሆንም፣ ቡድኑ እየፈጠረ ካለው አቅም አንጻር ተጨማሪ ኃይል የሚያስፈልግ መሆኑን ኃላፊው ይናገራሉ። ለዚህም ከክልሉ አስተዳደር ጋር እየተነጋገርን ነው ብለዋል።
በካቺሲ ከተማ ከአሥራ ሦስት ሺሕ በላይ ሰዎች ከገጠራማው አካባቢ ተፈናቅለው አሉ ያሉት ኃላፊው፣ እነዚህ ተፈናቃዮች በአብዛኛው በመንግሥት ሠራተኝነት ሕዝብን ሲያገለግሉ የነበሩ ናቸው። የወረዳው አስተዳደር ኃላፊዎች በቁርጠኝነት ከሕዝቡ ጋር ችግሩን እየተጋፈጡ መሆናቸውን ጠቁመው፣ ‹‹ከበጀታችን ቀንሰን እህል በመግዛት የሰውን ሕይወት ለመታደግ ጥረት አድርገናል›› ይላሉ።
የአቡና ግንደበረትና የግንደበረት ነዋሪዎች እንደሚሉት ወረዳዎቻቸው ሰፊ የግብርና ምርት ያላቸው፣ በመአድናት የበለጸጉ እና በርካታ የተፈጥሮ ፀጋ ያላቸው ናቸው። በዚህ እምቅ ሀብቱ ከራሱ ተርፎ ምርቶችን ለሀገር ሲያቀርብ የኖረ ቢሆንም፣ አሁን ግን በሰላም ወጥቶ መግባትም ችግር ስለሆነበት ሕዝቡ ለከፍተኛ ችግር እየተጋለጠ ይገኛል ብለዋል። በታሪካቸው ሰምተዋቸው የማያውቁ በርካታ የጭካኔ ተግባራትን ስለማየታቸውም ይናገራሉ።
ያነጋገርናቸው የኹለቱ ወረዳ ነዋሪዎች በመንግሥት በኩል የሚደረጉ ጥረቶችን በሚመለከት ላቀረብንላቸው ጥያቄ፣ የወረዳውን ሰላምና ጸጥታ ለማረጋገጥ የሚወሰዱ እርምጃዎች ቢኖሩም በቂ አይደሉም ይላሉ። እስከመቼ በዚህ መልኩ እንኖራለን? ዋናው ጥያቄያቸው ነው።
ቅጽ 4 ቁጥር 207 ጥቅምት 12 2015



