ከኢትዮጵያ ወደ ጅቡቲ የሚላከውን የውሃ መጠን ለማሳደግ እየተሰራ ነው

0
584

ከኢትዮጵያ ወደ ጅቡቲ በቀን የሚላከውን 20ሽሕ ሚትሪክ ኪዮብ የውሃ መጠን ቢያንስ በ50 በመቶ ለማሳደግ እየተሰራ መሆኑን ግንባታውን ያከናወነው እና አሁንም እያስተዳደረው የሚገኘው ቻይናዊው የግንባታ ኩባንያ ሲጅሲኦሲ ለአዲስ ማለዳ አስታወቀ።

ሲጅሲኦሲ ለአዲስ ማለዳ ጨምሮ እንደገለፀው ፕሮጀክቱ ሲጀመር 100ሽሕ ሜትሪክ ኪዮብ ውሃ ወደ ጅቡቲ በየቀኑ ለመላክ ታስቦ የነበረ ቢሆንም የሚፈለገው የኤሌክትሪክ ኃይል ባለመሟላቱ ከታሰበው በታች የውሃ መጠን እየተላከ እንደሚገኝ አስታውቋል።   በሱማሌ ክልል ሽንሌ ዞን ገቢ በተባለ ስፍራ የሚገኘው እና የጅቡቲ መንግስት ከኢትዮጵያ ጋር በገባው ውል መሰረት ለሰላሳ ዓመታት በነፃ 100 ሽሕ ሜትሪክ ኪዮብ ውሃ በቀን ለመላክ የተገነባ ፕሮጀክት እንደሆነም ታውቋል።

አዲስ ማለዳ ግንባታውን ካከናወነው ኩባንያ ሲጅሲኦሲ ያገኘችው መረጃ እንደሚያመለክተው የጅቡቲ ዋና ከተማ ከ15 እስከ 20 በመቶ የሚሆነውን የውሃ ፍጆታ የምታገኘው ከዚሁ ፕሮጀክት ሲሆን፤ የጅቡቲ ኹለተኛ ከተማ ለሆነችው አሊሳቤ ደግሞ ሙሉ በሙሉ የውሃ ምንጭ ይኸው ከኢትዮጵያ የሚሄደው ውሃ እንደሆነ ለማወቅ ተችሏል። የጅቡቲ መንግስት ከቻይናው ኤክዚም ባንክ ባገኘው ድጋፍ የተግነባው ፕሮጀክቱ በፈረንጆች 2015 ተጀምሮ 2017 መጠናቀቁ ተገልጿል። ግንባታው ተጠናቆ ከተመረቀበት ጀምሮ ለኹለት ዓመታት በስራ ላይ እንዳለም አዲስ ማለዳ በስፍራው በመገኘት ለመታዘብ ችላለች።

የውሃው ፕሮጀክት በአካባቢው ለሚኖሩ ማኅበረሰቦችም ንፁህ የመጠጥ ውሃ እንዲያገኙ እንዳስቻላቸው በሲጂሲኦሲ ባልደረባ ዮናታን ጌታቸው ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል። በአካባቢው የሚገኙ ማኅበረሰቦች በአብዛኛው አርብቶ አደር ከመሆናቸው ጋር ተያይዞ እና ከቦታ ቦታ በመዘዋወር የሚኖሩ ሲሆኑ የውሃ መስመሩ ከተዘረጋላቸው ጀምሮ ግን በአንድ ቦታ ተረጋግተው እየኖሩ እንደሚገኙ ዮናታን ገልፀዋል።

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here