ፀጉረ ልውጥ

“ሲቄ” የሚለው የኦሮምኛ ቃል ‹አለንጋ› የሚል ትርጉም አለው። በገዳ ትውፊታዊ አስተዳደር ውስጥ በባሏ ጥቃት የደረሰባት ሚስት፣ ከሌሎች ሴቶች ጋር በመሆን ባሏ ላይ የካሣ ውሳኔ የምታሳልፍበት ስርዓት ሲቄ ይባላል።

ሰሞኑን መንግስት ወደ አገር ውስጥ እንዳይገቡ ወይም የዶላር ምንዛሬ አንዳይሰጥባቸው የተባሉ የምግብ፣ የመጠጥ፣ የውበት መጠበቂያዎችና ሌሎችም መገልገያ ቁሳቁሶች የአብዛኛው ሰው መነጋገሪያ አጀንዳዎች ነበሩ። አንድ ነገር ሲታገድ የራሱ የሆነ ችግር ይዞ እንደሚመጣ ኹሉ ይዞ የሚመጣቸውም በረከቶችና መልካም እድሎች ይኖራሉ።

በተለይ በአሁኑ ሰዓት ከላይ ከተዘረዘሩት ውስጥ ሴቶች የሚጠቀሙባቸው የውበት መጠበቂያዎች ሰው ሰራሽ ፀጉሮች መነጋገሪያ ናቸው። አብዛኞቹ ሴቶች በሚባል መልኩ እነዚህን መዋቢያና ማጌጫዎች ይጠቀማሉ። ለተለያዩ ዝግጅቶችም ያለነዚህ መዋቢያዎች እንቅስቃሴ የማያደርጉ ሴቶችም በርካታ ናቸው። አሁን ግን በእገዳው ምክንያት በርካታ ሴቶች ስጋት ውስጥ መሆናቸውም ግልጽ ነው። እገዳው ስጋት ውስጥ መክተቱ አሳዛኙ ነገር ቢሆንም፣ አገር ውስጥ የሚመረቱትን መዋቢያዎች እንዲሁም የራስን የተፈጥሮ ፀጉር የመጠቀም እድልንም ይዞ መጥቷል። ይህንንም መልካም አጋጣሚ በሚገባ መጠቀም ያስፈልጋል።

ኢትዮጵያዊያን በተፈጥሮ ውቦች ነን። ምንም መኳኳል የማያስፈልገን፣  የማንም ፀጉር የማያሻን፣  ተፈጥሮ ራሷ የኳለችን ቆንጆዎች ።  በተጨማሪም በተፈጥሮ የሚገኙ በርካታ መዋቢያዎችም የታደልን ህዝቦች ነን። ከበርካታ ዓመታት በፊት ሴቶች የተፈጥሮ መዋቢያዎችን በሚጠቀሙበት ጊዜም ምን ያህል ውቦች እንደነበሩ አያቶቻችንን መጠየቅ ብቻ በቂ ነው። አሁን ግን ኹሉም ነገር በሰው ሰራሽ  ስለተተካ የእህቶቻችንም መልክ ሰው ሰራሽ ሆኗል። ፊታቸውም ሌላ ለምዷል። ጠዋት ሌላ መልክ፣ ከሰዓት ሌላ፣ ማታም የሌላ መልክ ባለቤት ሆነዋል። ተፈጥሮን በሰው ሰራሽ ተክተዋል። ዘላለማዊ መልክን በጊዜያዊ መልክ ቀይረዋል።

ጊዜው አሁን ነው። ወደ ማንነትና ወደ ራስ መልክ የመመለሻው ጊዜ አሁን ነው። ይህን ክስተት ተከትሎ ወጪን በመቀነስ የነበረ ውበትን ማጉላት ይቻላል። ከሰው መልክ ወደ ራስ መልክ፣ ከሰው ፀጉር ወደ ራስ ፀጉር የመመለሻው ጊዜ አሁን ነው። ፍቅረኛና ባልን በእውነተኛ መልክ መቅረቢያው ጊዜ አሁን ነው። ድሮ በልጅነታችሁ ወቅት ወንድምሽ የሚያውቀውን ያን ውብ መልክ ዳግም የምታሳይበት ወቅት አሁን ነው። ያኔ አባትሽ ፀጉርሽን እየዳበሰ ፍቅሩን ሲግልጽልሽ የምታገኚውን ደስታ መልሰሽ የምታገኚው አሁን ነው።

ጉዞ ወደ ማንነት። ጉዞ ወደ ሐበሻነት። ሴቶች የራስን መልክ በራስ ለመፈለግ ጉዞ ሊጀምሩ ይገባል። ለፊታቸውና ለራሳቸው ሌላ ፊትና ራስ ወደ ማይፈልጉበት መንገድ ሊሄዱ ይገባል። በራስ ፀጉር ራስን መሸፈን ያስፈልጋል። የራስን ፊት በራስ መልክ መጠቀም ያዋጣል። የራስ ነገር የራስ ነው። ለሰው ሰራሽ ነገር ፊት መስጠት ሊቆም ይገባል። የራስ ያልሆነን ነገር የራስ አስመስሎ በመኖር ፀጉረ ልውጥ መሆን ይበቃል። ጉዞ የራስን መልክ ይዞ።

ደስታ ሽርካ (ደስታ ጠማኙ)


ቅጽ 4 ቁጥር 208 ጥቅምት 19 2015

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here