አርሂቡ አፍሪካ

0
1003

ኢትዮጵያ የቡና መገኛ ከመሆኗ አንጻር ማምረት ከጀመረች አንስቶ ከፍተኛ የሆነ የምርት እድገትም ሆነ የስርጭት መሻሻልን እንዳላሳየች ይታያል። ዓለም ቡናን እያደር መጠቀሟን ስትጨምር አፍሪካ ግን ዝቅተኛ ተጠቃሚ ሆና ትታወቃለች። አፍሪካዊያን የቡና ተጠቃሚነታቸውን እንዲጨምሩ በየአገራቱ የተለያዩ ሥራዎች እየተጀመሩ ቢሆንም በቂ አለመሆኑ ይነገራል። አፍሪካዊያን ቡና ጠጪዎች ቁጥር እየጨመረ መምጣቱን ተከትሎ ኢትዮጵያ በምን መንገድ መጠቀም እንደምትችል በማንሳት ስንታየሁ ግርማ ይህን ሐሳብ አስፍረዋል።

ሕይወቴን በቡና ስኒ ለካሁ። – ቲ.ኤስ.ኤል የዘፈነው ነው።

በዓለም አስደናቂው የኢትዮጵያ መለያ የሆነው ቡና በዘጠነኛው ክፍለ ዘመን በአገራችን ተገኘ። ከዛም ወደ አረቡ ዓለም ተሻገረ፡፤ በመቀጠል በባሪያ ንግድ እና በቅኝ ገዢዎች አማካይነት በሦሰተኛው ዓለም እየተመረተ አወሮጳ እየተላከ የቡና መጠጣት ባህል ተፈጠረ።

ቡና የምዕራቡ ዓለምን ከመጠጥ ሱሰኝነት በማላቀቅ ባለውለታ ነው። ለምሳሌ በመካከለኛው ክፍለ ዘመን በእንግሊዝ መጠጥ ከቁርስ ጋር ሳይቀር እየቀረበ በየዓመቱ በአማካይ እስከ 70 ጋሎኖች ይጠጡ እንደነበረ መረጃዎች ያሳያሉ። ይሁንና ቡና መጥቶ እንግሊዝን ጨዋ እና ነፃ አገር አደረጋት።

ከቅርብ ዓመታት ወዲህ የቡና ባህል በአፍሪካ እያደገ ነው። ምንም እንኳ አፍሪካ ለዓለም ከሚቀርበው 13 በመቶ ብታበረክትም፣ እና የቡና መገኛ አኅጉር ብትሆንም፣ ከሌላው ዓለም ጋር ሲወዳደር የአፍሪካዊያን ቡና የመጠጣት ባህል የተፈለገውን ያህል አይደለ፤ ከኢትዮጵያ በስተቀር። አፍሪካዊያን ከሚያመርቱት ምርት አብዛኛውን ለዓለም ገበያ የምታቀርብ ፍጆታዋ በጣም ትንሽ ነበር። አሁን ግን በመጠኑም ቢሆን ሁኔታዎች እየተለወጡ ነው።

የአፍሪካ መንግሥታት የአገር ውስጥ የቡና ፍጆታን እያበረታቱ ነው። ለምሳሌ፣ ካሜሩን «የቡና ፌስቲቫል» የሚል ኹነት በማዘጋጀት በሁሉም የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ቡና መጠጣትን እያስተዋወቀች ነው።

በደቡብ አፍሪካም ከፋስት ፉዱ እና ወደ ቤት ተወስደው ከሚጠቀሙበት መጠጦች ውስጥ በየዓመቱ በአማካይ 2.8ቱ የቡና ሱቆች ይሸፍናሉ። የቡና ኢንዱስትሪውም በዓመት በአማካይ በ7.1 በመቶ እያደገ ነው። የቡና መጠጣት አብዮት በደቡብ አፍሪካ እየተካሄደ ነው ይላሉ ተንታኞች።

በናይጄሪያም ውስጥ የመካከለኛው ኅብረተሰብ ክፍል እያደገ በመምጣቱ እንደ አውሮፓዊያን አቆጣጠር በ2010 እና 2015 በናይጄሪያ ቡና መጠጣት በ20 በመቶ እያደገ ነው።

ጥናቶች እንደሚያሳዩት በዛው በአውሮፓዊያን አቆጣጠር በ2020 ናይጄሪያውያን አንድ ሺሕ ቶን ቡና ይጠጣሉ ተብሎ ይገመታል። ይህንን ፍጆታ ደግሞ የናይጄሪያ የቡና ምርት አይሸፍንም። ይህንን እድል ኢትዮጵያ ልትጠቀምበት ትችላለች። የአሜሪካ የግብርና ምርት መምሪያ እንደገመተው፣ ኢትዮጵያ በ2022 /2023 በኢትዮጵያ 495 ሺሕ ሜትሪክ ቡና በማምረት ሪከርድ የሆነ ምርት በማምረት ኤክስፖርቱም ሪከርድ እንደሚሆን ተንብይዋል።

ከአፍሪካ አብዛኛው የሮብስታ ቡና አምራች አገራት የሆነችውም ዩጋንዳ፣ የአገር ውስጥ ፍጆታዋን በ20 በመቶ በአማካይ በማሳደግ ኢኮኖሚዋን በከፍተኛ ሁኔታ ማሳደግ ትችላለች። የዩጋንዳም የቡና ባለሥልጣን የአገር ውስጥ ፍጆታን ለማበረታታት ንቅናቄ ጀምሯል። ይህም በሳምንት ውስጥ 20 ሺሕ ስኒ ቡና በነጻ ማቅረብን ያካትታል።

በጎረቤታችን ኬንያም መካከለኛው ኅብረተሰብ እያደገ በመምጣቱ የኬንያዊያን ቡና የመጠጣት ባህል ለማሳደግ እና ከሻይ ይልቅ ቡናን እንዲጠጡ ለማበረታታት የቡና ሱቆች በማስፋፋትና በማበረታታት የሸማቹን እምነት ለማሳደግ እየጣረች ነው።

ይሁንና እነዚህ ጥረቶች ሁሉ በቂ ሆነው አልተገኙም። ከዚህ በመነሳት ከዳበረው የኢትዮጵያ ቡና የመጠጣት ባህል ልምድ ለመውሰድ አፍሪካዊያን ከኢትዮጵያ የቡና ባህል ልምድ በመቅሰም እና ወደ ራሳቸው ለመውሰድ በአዲስ አበባ መክረዋል።

ምክንያቱ ደግሞ ኢትዮጵያ የቡና መገኛ አገር ብቻ ሳትሆን ለዘመኑ የዳበረ የቡና ባህል ያላት አገር በመሆኗ ነው። መረጃዎች እንደሚያሳዩት ኢትዮጵያ በአማካይ ከምታመርተው የቡና ምርት ከግማሽ በላይ ለአገር ውስጥ ፍጆታ ታውለዋለች። ይህ ልምድ የኢትዮጵያን ቡና ቀጣይነት ከማረጋገጥ አኳያ መልካም እድል ነው።

በአፍሪካ ከከተሞች መስፋፋት ጋር ተያይዞ ቡና የመጠጣት ባህል በተለይም በመጠኑ እየጨመረ ነው። በከተሞች የቡና ሱቆች እየተስፋፉ ነው። የመካከለኛው ኅብረተሰብ ክፍልም እያደገ ነው። ይህ ደግሞ ለኢትዮጵያ ቡና ኤክስፖርት ማደግ ከፍተኛ እድል ነው።

የዓለም የቡና ገበያ ዋጋ ወሰኖች ባደጉ አገሮች ትንሽ ቡና ቆዪዎች እና ድንበር ተሻጋሪ ኮርፖሬሽኖች ናቸው። ዋጋውን የሚወስኑት እነሱ በመሆናቸው የዓለም አነስተኛ ቡና አብቃይ አርሶ አደሮች ገቢ የምርት ወጪውን እንኳን የሚሸፍን አይደለም። ይሁንና የኢትዮጵያን ቡና ይህንን ስጋት የመቋቋም እድሎች አሉት። እነሱም፤

  1. ኢትዮጵያ ብዛት ያላቸው ልዩ ቡና / Speciality Coffeee ባለቤት በመሆኗ 2/3ኛውን የኢትዮጵያ ቡና ልዩ ቡና ተብሎ የመመደብ ብቃት አለው። ሸማቾች ደግሞ ለልዩ ቡና የተሻለ ክፍያ የመክፈል ልምድ እያዳበሩ ነው።
  2. የኢትዮጵያ ቡና ከ90 በመቶ በላይ ‹ኦርጋኒክ› ተብሎ የሚፈረጅ መሆኑ ከሸማቾች ጤንነት ጋር ተያይዞ ተፈላጊ እየሆነ መምጣቱ እና የተሻለ ክፍያ እያደገ መምጣቱ፤
  3. «ለፍትሐዊ ንግድ» የሚደረግ ንቅናቄ እያደገ መምጣቱ የቡና ቀጣይነት በዓለም በተዛባው የንግድ ሥርዓት ምክንያት አነስተኛ ቡና አብቃይ አርሶ አደሮች እየተጎዱ በመሆኑ ፍትሐዊ ንግድ ንቅናቄ አቀንቃኞች አነስተኛ አምራች አርሶ አደሮች የምርት ወጪያቸውን ለመሸፈን የሚያስችል እና ኑሯቸውን ለመግፋት የሚያስችል ሲስተም እንዲኖር እየጣሩ ነው። በሸማቹም ተቀባይነት እያገኘ ነው። ቡና ጠጪዎች ቡናው የት እንደተመረተ፣ እንዴት እንደተዘጋጀ እና እንደታሸገ በማወቅ የተሻለ ዋጋ ለመክፈል ፍላጎት እያሳዩ ነው።

ከቡና ምርት ጀርባ ያለው አካባቢያዊ፣ ማኅበራዊና የአካባቢ ጉዳዮችን ቡና ጠጪዎች በማወቅ የተሻለ ክፍያ ለመክፈል ፍላጎት እያሳዩ ነው። በድርጊትም እየገለጹ ነው። ኢትዮጵያ ደግሞ ይህንን ስለምታሟላ ለአርሶ አደሮቻቸው ምርጥ እድል ነው። ለዚህም ነው የሚቀጥለው ዓመት የቡና ጣዕም ውድድር አገራችን የምታስተናግደው።

  1. የአፍሪካ ኢኮኖሚ ማደግ በዓለም ላይ በፍጥነት በማደግ ላይ ካሉት አገሮች አብዛኛዎቹ ከአፍሪካ ናቸው። በአፍሪካ ወጣቱ እና መካከለኛው የኅብረተሰብ ክፍል በከፍተኛ ፍጥነት እያደገ ነው። ቡና መጠጣት በአሁኑ ሰዓት የሞደርናይዜሽን እና ሥልጣኔ ምልክት እየሆነ ነው።

ጥናቶች እንደሚያሳዩት በቀን ከኹለት ስኒ ቡና በላይ መጠጣት የእድሜ ጣሪያን በ15 ዓመታት እንደሚጨምር ተረጋግጧል። የእድሜ ጣሪያ ደግሞ ከፍትሐዊ የሀብት ክፍፍል አንዱ ነው። እያደገ የሚመጣውን የአፍሪካ ቡና ፍጆታ ደግሞ ሊሸፍን የሚችለው የረጅም ጊዜ ልምድ ያለው የኢትዮጵያ ቡና ምርት ነው። ስለዚህ ፊታችንን ወደ አፍሪካ ማዞር አለብን።

  1. የኢትዮጵያ የቡና መገኛ አገር በመሆኗ ምርቷ ጥሩ ገጽታ እና መልካም ሥም አዳብሯል። ሸማቾች ደግሞ ከምርቱ በላይ ዋጋ የሚከፍሉት ለመልካም ሥም ነው። ስለዚህ የአፍሪካን ወጣት የበለጠ ቡና መጠጣት በማስተዋወቅ፣ ለምሳሌ ከፕርሚየር ሊግ ክለቦች አንዱን ስፖንሰር በማድረግ ሊሆን ይችላል።

የጽሑፉን አዘጋጅ ስንታየሁ ግርማን በኢሜል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይችላሉ።


ቅጽ 4 ቁጥር 208 ጥቅምት 19 2015

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here