ድርድሩ የጦርነቱ መቋጫ ወይስ…!

0
2354

በመንግሥትና ትግራይን ያስተዳድር በነበረው ሕወሓት መካከል የነበረው ግንኙነት እየሻከረ መጥቶ ወደለየለት ጦርነት ከተቀየረ ድፍን ኹለት ዓመት ሊሞላው ቀናት ቀርተውታል።

ጦርነቱ ከመቀስቀሱ በፊትም ሆነ በይፋ ከተጀመረ አንስቶ ልዩነቱ በሰላማዊ መንገድ እንዲፈታ የተለያዩ አካላት ቢጠይቁም ውጤታማ ሳይሆን ቀርቷል። በተለያዩ ግንባሮች አልፎ አልፎ በሚካሄዱ ውጊያዎች ለኹለት ጊዜ ተቋርጦ የነበረው ጦርነት፣ ከኹለት ወራት በፊት ለሦስተኛ ጊዜ እንደ አዲስ ተፋፍሞ አቅጣጫው እየተቀየረ ይመስላል።

የፌዴራል መንግሥቱ ከኹለት ዓመት ቆይታ በኋላ መልሶ ትላላቅ የትግራይ ከተሞችን በቁጥጥሩ ስር ማስገባቱን ተከትሎ ለመደራደር ቅድመ ሁኔታዎች ቀርተው ፊት ለፊት በደቡብ አፍሪካ ከሰሞኑ ለመነጋገር ተገናኝተዋል። መንግሥት ከድርድሩ ምን ሊያተርፍ እንደሚችል፣ የሕወሓት ባለሥልጣናት ፍላጎትና መጨረሻም ምን ሊሆን እንደሚችል የአዲስ ማለዳው መርሻ ጥሩነህ ባለሙያ አነጋግሮ የሐተታ ዘ ማለዳ ርዕሰ ጉዳይ አድርጎታል።

የሰሜኑ የኢትዮጵያ ጦርነት ከመጀመሩ አስቀድሞ በፌዴራል መንግሥት እና በሕዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ (ሕወሓት) መካከል የተፈጠረው ልዩነት በሰላማዊ ንግግር እልባት እንዲያገኝ የብዙዎች መሻት ነበር። የተፈጠረው ልዩነት ወደ ጦርነት ከማምራቱ አስቀድሞ ሰላማዊ መፍትሔ ይበጃል ያሉ፣ የአገር ሽማግሌዎች ኹለቱን ኃይሎች ለማቀራረብ ያደረጉት ጥረት ባለመሳካቱ ልዩነቱ ወደ ጦርነት አምርቶ ኹለት ዓመት አስቆጥሯል።

ጦርነቱ ከተጀመረ በኋላም ቢሆን፣ አፍሪካ ኅብረትን ጨምሮ በተለያዩ ዓለም ዐቀፍ ተቋማትና አገሮች ኹለቱ ኃይሎች ጦርነት አቁመው ልዩነታቸውን በድርድር እንዲፈቱ ጥረት ሲያደርጉ ነበር። ከብዙ ጥረት በኋላ የጦርነቱ ዋና ተዋንያን የሆኑት የፌዴራል መንግሥት እና ሕወሓት ለመጀመሪያ ጊዜ በአፍሪካ ኅብረት አደራዳሪነት ጥቅምት 15/2015 ደቡብ አፍሪካ ላይ ድርድር ጀምረዋል።

በአፍሪካ ኅብረት ጥላ ስር የተጀመረው ድርድር ለኹለት ዓመት የዘለቀው የሰሜኑ ጦርነት በትግራይ፣ በአፋርና በአማራ ክልል ከፍተኛ ሰብዓዊና ቁሳዊ ኪሳራ ካደረሰ በኋላ በብዙ ጥረት የተሳካ ነው። ጦርነቱ ከተካሄደባቸው ሦስቱ ክልሎች በተጨማሪ፣ ኢትዮጵያን እንደ አገር ለዘርፈ ብዙ ኪሳራ የዳረገ ነው። ምንም እንኳን ድርድሩ ከብዙ ጥረት በኋላ የተጀመረ ቢሆንም፣ የሕወሓትና የፌዴራል መንግሥት የሚያካሂዱት ጦርነት አሁንም እንደቀጠለ ነው።

የጦርነቱ ተፋላሚ ወገኖች የኢትዮጵያ መንግሥት እና ሕወሓት ከተለያዩ አካላት ሲቀርብላቸው የነበረውን የድርድር ጥያቄ መቀበላቸውን ማሳወቃቸውን ተከትሎ፣ ከወራት በኋላ በደቡብ አፍሪካ የተጀመረው ድርድር እስከ ነገ እሁድ ድረስ እንደሚቀጥል አፍሪካ ኅብረት አስታውቋል።

የደቡብ አፍሪካው ድርድር በአፍሪካ ኅብረት መሪነት የሚካሄድ ቢሆንም፣ የምሥራቅ አፍሪካ በይነ መንግሥታት ድርድት (ኢጋድ)፣ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት(ተመድ) እና የአሜሪካ መንግሥት በአፍሪካ ኅብረት ጥላ ስር በሚካሄደው የሰላም ሂደት ላይ በታዛቢነት ተሳታፊ መሆናቸውን የአፍሪካ ኅብረት ድርድሩ በተጀመረበት እለት ባወጣው መግለጫ አስታውቋል። ኅብረቱ ድርድሩ መጀመሩን ባበሰረበት መግለጫ፣ ድርድሩን እንዲመሩ የኅብረቱ የምሥራቅ አፍሪካ ልዩ መልዕክተኛ ኦሊሴንጉ ኦባሳንጆ፣ የቀድሞው የኬኒያ ፕሬዝደንት ዑህሩ ኬኒያታ እና የቀድሞዋ የደቡብ አፍሪካ ምክትል ፕሬዝደንት ፋምዚሌ ምላምቦ ንግኩሳን መሰየሙን ይፋ አድርጓል።

ኅብረቱ ተፋላሚ ኃይሎችን ለማደራደር ከአንድ ዓመት በላይ ያስቆጠረ ጥረት ሲያደርግ መቆየቱ የሚታወስ ሲሆን፣ የኅብረቱ የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ ኦሊሴንጉን ኦባሳንጆ በተደጋጋሚ የፌዴራል መንግሥትንና የሕወሓትን ባለሥልጣናት በተናጠል ሲያነጋግሩ ቆይተዋል። ከአፍሪካ ኅብረት ጥረት በተጨማሪ የአሜሪካ ልዩ መልዕክተኛ አምባሳደር ማይክ ሐመር ከመቀሌ አዲስ አበባ እየተመላለሱ ኹለቱን ኃይሎች በተናጠል ሲያነጋግሩ ነበር።

በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ እየገባች ነው የሚል ብርቱ ትችት ከኢትዮጵያ መንግሥት የሚቀርብባት አሜሪካ በድርድሩ ላይ በልዩ መልዕክተኛዋ ማይክ ሐመር ተሰይማ የድርድር ሂደቱን እየታዘበች  መሆኑ ተሰምቷል።

ከተጀመረ ኹለት ዓመት ሊሞላው አምስት ቀናት የቀሩትን የሰሜኑ የኢትዮጵያ ጦርነት መቋጫ እንዲያገኝ ከብዙ ጥረት በኋላ የተጀመረው የመጀመሪያው ይፋዊ ድርድር ውጤት፣ ለኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላምም ሆነ ለአፍሪካ ቀንድ መረጋጋት ወሳኝ መሆኑ እየተነገረ ይገኛል። በአፍሪካ ኅብረት አደራዳሪነት በፌዴራሉ መንግሥት እና በሕወሓት መካከል የሚደረገው ድርድር ፍሬ አፍርቶ ለጦርነቱ መቋጫ ይሆን ዘንድ የብዙዎች ምኞት ነው። ጦርነቱን በሰላም ለመቋጨት ድርድር ቢጀመርም፣ ኹለቱ ኃይሎች የተኩስ አቁም አዋጅም ይሁን ሌላ ጦርነቱን የማቆም ስምምነት ላይ እስካሁን አልደረሱም።

የጦርነቱ ዳራ

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ወደ ሥልጣን ከመጡበት ከመጋቢት 2010 ጀምሮ መንግሥታቸውን በአዲስ አደረጃጀት መተካታቸውን ተከትሎ፣ በሕወሓት እና በፌዴራል መንግሥት መካከል ልዩነት መፈጠሩ የሚታወስ ነው።

የጠቅላይ ሚኒስትሩ አዲስ አመራር፣ ኢትዮጵያን በበላይነት ለ27 ዓመት በመራው ሕወሓት ላይ ከጊዜ ወደ ጊዜ እያየለ የመጣ ቅሬታ መፍጠሩን ተከትሎ፣ በፌዴራል መንግሥት እና በወቅቱ የትግራይ ክልል መንግሥት በነበረው በሕወሓት መካከል ልዩነቱ በግልጽ ጎልቶ ወደ ጦርነት ከተቀየረ ኹለት ዓመት ሊሞላው አምስት ቀናት ቀርተውታል።

የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ወደ ሥልጣን መምጣት በሕወሓት እና በፌዴራል መንግሥት መካከል ልዩነት እንዲፈጠር ያደረገ የመጀመሪያው ፈር ቀዳጅ ክስተት እንደሆነ ብዙዎች ይስማማሉ። ሕወሓት የጠቅላይ ሚኒስትሩን ወደ ሥልጣን መምጣት ከጅምሩ የተቀበለው ቢመስልም፣ የኋላ ኋላ ግን እያፈገፈገ መምጣቱ የሚታወስ ነው። ቡድኑን እንዲያፈገፍግ ካደረጉት መነሻዎች የወቅቱ አዲስ ጠቅላይ ሚኒስትር አስተዳደር ከተለመደው የተለየ አካሄድ መከተሉ እንደነበር የሚታወስ ነው።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወደ ሥልጣን እንደመጡ በፈጠሩት አዲስ የመነቃቃት ወኔ፣ መላው አገሪቷን እየተዘዋወሩ ከሕዝብ ጋር እየተወያዩና አዲስ መንገድ እያስተዋወቁ በነበረበት ጊዜ መቀሌ ላይ ጥሩ የሚባል አቀባበል አግኝተው ነበር። ይሁን እንጂ፣ የጠቅላይ ሚኒስትሩ አስተዳደር የሚያደርጋቸው የተቋማትና የአመራር ለውጦች በሕወሓት በኩል ቅሬታን የፈጠሩ ነበሩ።

የሕወሓት እና የጠቅላይ ሚኒስትሩ አስተዳደር በልዩነት እየተጓተቱ የመጨረሻው ምዕራፍ ላይ እንዲደርሱ ካደረጉ ዋና ዋና ክስተቶች አንዱ፣ ትግራይ ውስጥ የሚገኘው የኢትዮጵያ ጦር ወደ ማዕከል እንዲንቀሳቀስ የፌዴራል መንግሥቱ ፍላጎት ቢኖርም፣ በክልሉ መንግሥት በኩል ጦሩ ከትግራይ እንዳይወጣ ክልከላ ተደርጎበት ነበር። በዚህም የኢትዮጵያ ጦር ለመንቀሳቀስ ሲሞክር ከነበረባቸው ከተሞች እንዳያልፍ ሲታገድ እንደነበር የሚታወስ ነው።

አዲሱ አስተዳደር ተቋማት ላይ የሚያደርገው ለውጥም ሕወሓትን ያስኮረፈ ነበር። በተለይ የቀድሞው ሜቴክ የአሁኑ ኢትዮ ኢንጅነሪንግ አመራሮች በሙስና ወንጀል ተጠርጥረው መያዛቸው፣ ቡድኑ ‹‹በትግራይ ተወላጆች ላይ ያነጣጠረ ውንጀላ ነው›› በማለት የልዩነት ጎራውን አሰፋው።

የልዩነት ጎራው እያደገ በመጣበት ሁኔታ፣ የጠቅላይ ሚኒስትሩ አስተዳደር የኢትዮጵያን ፖለቲካ በቀዳሚነት የሚዘውሩትን ድርጅቶች አክስሞ ወደ አንድ ለማምጣት ውጥን በያዘበት ጊዜ ሕወሓት ውህደቱን አልተቀበለም ነበር። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወደ ሥልጣን ከመጡ ጀምሮ ውህድ ፓርቲ የመመሥረት ዕቅዱን ተግባራዊ ለማድረግ ተንቀሳቀሱ።

ኢሕአዴግን ከመሠረቱት እና የአድራጊ ፈጣሪነት ሚናውን ከፊት ሆኖ ለ27 ዓመታት ሲዘውር የቆየው ሕዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ (ሕወሓት) ብልጽግና የተባለውን ውህድ ፓርቲ ሳይቀላቀል ቀረ። ከውህድ ፓርቲነት ራሱን ያገለለው ፓርቲ ተቃዋሚ በመሆን ጉዞውን ጀመረ።

ኹለቱ ኃይሎች ወዳልተፈለገ ግጭት ውስጥ እንዲገቡ ካደረጓቸው ዋና ምክንያቶች መካከል፣ የኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ኢሕአዴግ) መክሰም እና የብልጽግና ፓርቲ ውልደት ይገኝበታል። ኢሕአዴግን አክስሞ አዲስ ፓርቲ መመሥረቱ ለሦስቱ ነባር አውራ ፓርቲዎች ማለትም ለአማራ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (አዴፓ)፣ ለኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኦዴፓ) እና ለደቡብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ደኢሕዴን) እና ሌሎች ከዛ በፊት አጋር ተብለው አብረው ለሚሠሩ ድርጅቶች ቀላል ቢሆንም፣ በሕወሓት በኩል ግን ተቀባይነት አላገኘም።

የኢሕአዴግ ክስመት እና የብልጽግና ውልደት ሕወሓትን ከቀደሙት ጊዜያት በላይ ወደ መቀሌ እንዲከትም እና የተናጠል ሐሳብ እንዲያራምድ እንዳደረገው ይታመናል። ለዚህም እንደማሳያነት ኅዳር 11/2012 ከሕወሓት ውጪ በተደረገ የያኔው የኢሕአዴግ ምክር ቤት ስብሰባ ምክር ቤቱ ውህደቱን በሙሉ ድምጽ ያጸደቀ ሲሆን፣ ኅዳር 21 ቀን 2012 ውህደቱን የተቀበሉት ፓርቲዎች ተፈራርመው ብልጽግና ፓርቲ በይፋ ተመሠረተ። ኅዳር 24 ፓርቲው ለብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የእውቅና ጥያቄ አቅርቦ ቦርዱ ታኅሳስ 15/2012 ለብልጽግና ፓርቲ እውቅና መስጠቱ ይታወሳል።

ይህንኑ ተከትሎ የቀድሞዋ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ ኬሪያ ኢብራሒም ሥልጣናቸውን በገዛ ፈቃዳቸው ለቀው መቀሌ መግባታቸውን ሰኔ 2012 መቀሌ ሆነው በሰጡት መግለጫ ማብሰራቸው የሚታወስ ነው። የኬሪያ ከአፈ-ጉባኤነት ለቀው ወደ መቀሌ መሔድ እና ሕወሓት ፌዴራል ላይ የሚገኙ አባሎቹን ሥራ ለቀው ወደ መቀሌ እንዲመጡ መጠየቁ የቡድኑን ወደ መቀሌ የማቅናት ጉዳይ ያጠናከረ ነበር።

ኬሪያ በወቅቱ ሥልጣናቸውን የለቀቁት ስድስተኛውን አገራዊ ምርጫ ማካሄድ እንደማይችል የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ማሳወቁን ተከትሎ፣ ምርጫውን ለማራዘም በወቅቱ የተቀመጠውን አማራጭ የሕገ-መንግሥት ትርጉም ይሰጥ ውሳኔ እና ትርጉም ለመሥጠት እየተሄደበት ያለውን መንገድ ባለመደገፋቸው መሆኑን አብራርተው ነበር።

“በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ” እንዲሉ የሕወሓት እና የፌዴራል መንግሥቱ ልዩነት ከነበረበት ደረጃ ከፍ እንዲል የሚያደርግ ሌላ ክስተት ተፈጠረ። ይሄውም ዓለምን ያሸበረው ኮቪድ-19 ሲሆን፣ በሽታው ወደ ኢትዮጵያ የገባው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ስድስተኛውን አገራዊ ምርጫ ለማካሄድ በዝግጅት ላይ በነበረበት ወቅት ነበር። በዚህም በሽታው ወደ ኢትዮጵያ መግባቱን ተከትሎ ምርጫ ቦርድ ምርጫ ማካሄድ እንደማይችል መጠየቁን ተከትሎ ነበር ምርጫው እንዲራዘም የተወሰነው።

የሕገ መንግሥት ትርጉምን እና ምርጫ መራዘምን በወቅቱ አምርሮ የተቃወመው ሕወሓት፣ የራሱን ክልላዊ የተናጠል አካሄድ መከተል ጀምሮ ነበር። በዚህም ስድስተኛውን አገራዊ ምርጫ ኮቪድ-19 እያለም ቢሆን፣ በመደበኛ ጊዜው በክልል ደረጃ አካሂዳለሁ በማለት የክልሉን ምርጫ አስፈጻሚ አዋቅሮ ዝግጅት ጀመረ።

ይህ በእንዲህ እያለ የልዩነት ደረጃው እያደገና በሐሳብ ልዩነት ላይ የተመሠረተው ፍትጊያ ወደ ተግባር መቀየር ጀመረ። ሕወሓት በፌዴራሉ መንግሥት ሕገ-ወጥ ነው የተባለውን ምርጫ ጳጉሜ 4/2012 በይፋ በማካሄድ ማሸነፉን አበሰረ። አሸነፍኩ ማለቱን ተከትሎ ለሚቀጥሉት አምስት ዓመታት የትግራይ ክልል መንግሥት ሆኖ እንደሚቆይ በይፋ አወጀ። ከመስከረም 25/2012 በኋላ የፌዴራል መንግሥቱ ሕጋዊ እውቅናና ውክልና እንደሌለው በመግለጽ ለማዕከላዊው መንግሥት ተገዢ እንደማይሆን አስታወቀ።

በዚህ ሂደት የፌዴራል መንግሥቱ የትግራይ ክልል ሕገወጥ ምርጫ በማካሄዱ ሕገ ወጥ ቡድን እንደሆነ በማወጅ ወደ ትግራይ ክልል የሚላከውን በጀት በወረዳዎችና በከተሞች ደረጃ እንደሚያሰራጭ አስታወቀ። በኹለቱ ፓርቲዎች መካከል ያለው ልዩነት እያደገ ሄዶ አንዱ ሌላውን ‹ሕገ ወጥ ቡድን› በሚል ሲካሰሱ ነበር።

ችግሩ እየተባባሰ በመግፋቱ የፌዴራል መንግሥት ለትግራይ ክልል የሚሰጠውን በጀት ለክልሉ ሕገ ወጥ መዋቅር እንደማይሰጥ ከወሰነበት ቀን ጀምሮ፣ ሕወሓት ‹‹የፌዴራል መንግሥት በትግራይ ሕዝብ ላይ ጦርነት እንዳወጀ እንቆጥረዋለን›› በማለት ከውይይት ይልቅ ወደ ጦርነት የሚያመሩ መግለጫዎችን በተደጋጋሚ ሲያወጣ ነበር።

ሕወሓት ጳጉሜ 4/2012 ባካሄደው ክልላዊ ምርጫ አሸነፍኩ ማለቱን ተከትሎ የወቅቱ የክልሉ ፕሬዝዳንት የነበሩት ደብረጽዮን ገ/ሚካኤል (ዶ/ር) ጥቅምት 23/2013 በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ፣ የፌዴራል መንግሥት በትግራይ ሕዝብ ላይ ተደጋጋሚ በደል መፈጸሙን በመግለጽ፣ አሁን ላይ ያለው የመጨረሻ አማራጭ እንደ ሕዝብ መዋጋት መሆኑን በይፋ ተናግረው ነበር። ደብረጽዮን በመግለጫቸው ‹ከመንገዳችን የሚያደናቅፈንን ኃይል ውጊያ እንገጥማለን› በማለት የተፈራውን ጦርነት ለመቀስቀስ ጉትጎታ አድርገዋል።

‹‹የምንገጥመው ውጊያ የሕዝብ ውጊያ ነው የሚሆነው። ድሉ የእኛ ነው፤ ድሮም የእኛ ነበር፤ አሁንም አሸናፊዎች እኛ ነን›› ሲሉም የጦርነት አሸናፊነታቸውን አረጋግጠው ነበር። ፕሬዝዳንቱ አክለውም፣ ‹‹የፈለገው መሣሪያ አያሸንፈንም። እንደ ትግራይ ተዘጋጅተናል፤ እንገጥማለን›› ሲሉ የጦርነት ነጋሪቱን ጎስመዋል። ይህ በሆነ በማግስቱ ማክሰኞ ጥቅምት 24/2013 ሌሊት ላይ በትግራይ ክልል ርዕሰ መዲና በሆነችው መቀሌ ላይ ያልታሰበ እና መላ ኢትዮጵያዊያንን ያስደነገጠ ድርጊት ተፈጽሞ ማደሩን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ጥቅምት 25/2013 በብሔራዊ ቴሌቪዥን ጣቢያ ብቅ ብለው አረዱ።

በማለዳ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ የተሰማው ዜና፣ ‹‹ሕወሓት በትግራይ በሚገኘው የመከላከያ ካምፕ ላይ ጥቃት አድርሷል። ሰሜን እዝንም ለመዝረፍ ሙከራ አድርጓል›› የሚል ነበር። ሕወሓት ያልተፈለገ ጦርነት መጀመሩን የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ መከላከያ በአካባቢው “የሕግ የማስከበር ሥራ” እንዲሠራ ትዕዛዝ መሰጠቱን አሳውቀው ነበር። በቃላት ጦርነት የገነገነው የኹለቱ ኃይሎች ልዩነት ከጥቅምት 24 ሌሊት ጀምሮ ወደ ኃይል ፍልሚያ መቀየሩ የሚታወስ ነው።

የጦርነቱ ጉዞ

ጥቅምት 24/2013 በይፋ የተጀመረው ጦርነት በፌዴራል መንግሥት በኩል “የሕግ ማስከበር ዘመቻ” የሚል ሥያሜ የተሰጠው ሲሆን፣ መንግሥትም ተገዶ የገባበት ጦርነት መሆኑን ሲገልጽ ነበር። መንግሥት ወደ ትግራይ ክልል መከላከያ ሠራዊት ማሰማራቱን ተከትሎ የሕግ ማስከበር ዘመቻው በ17 ቀን መጠናቀቁን ቢገልጽም፣ ጦርነቱ ግን ለስምንት ወራት በክልሉ ቆይቷል።

ጦርነቱ ለስምንት ወራት በትግራይ ክልል ተወስኖ ቢቆይም፣ መከላከያ ሠራዊት ሰኔ 21/2013 ክልሉን ለቆ መውጣቱን ተከትሎ ሕወሓት በ15 ቀን ልዩነት ወደ አማራ እና አፋር ክልል ዘልቆ በመግባት እስከ ደብረ ሲና ድረስ ዘልቆ ነበር። ሕወሓት በአማራ እና አፋር ክልሎች ላይ ባደረገው ማጥቃት  በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ከማፈናቀል ለተለያዩ ሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ሰለባ እንዲሆኑ ምክንያት ሆኖ ለአምስት ወራት ዘልቋል። ሕወሓት በኹለቱ ክልሎች ለአምስት ወራት በቆየባቸው ጊዜያት የደረሱ ሰብዓዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ሥነ ልቦናዊ እና ፖለቲካዊ ችግሮች አስከፊ ነበሩ።

ይሁን እንጂ፣ ከአምስት ወራት በኋላ የፌዴራል መንግሥት ሕወሓትን ከክልሎቹ ለማስወጣት የተጠናከረ የማጥቃት ዘመቻ ማድረጉን ተከትሎ ሕወሓት ከአማራ እና ከአፋር ክልሎች እንዲወጣ ተደርጓል። በተደርገው የማጥቃት ዘመቻ ሕወሓት የያዛቸውን አካባቢዎች ለቆ ወደ ትግራይ ሲመለስ መከላከያ የማጥቃት እርምጃውን አስቀጥሎ ሕወሓትን ተከትሎ ወደ ትግራይ እንዳይገባ በፌዴራል መንግሥት በኩል ውሳኔ ተሰጥቶ ነበር።

ከአምስት ቀናት በኋላ ኹለት ዓመት የሚደፍነው ጦርነት፣ መነሻውን በትግራይ ክልል ያድርግ እንጂ፣ በአማራ እና በአፋር ክልል መስፋፋቱን ተከትሎ የዜጎችን ሞት፣ ርሀብ፣ መፈናቀልና ቁሳዊ ኪሳራን በስፋት አስከትሏል።

ሕወሓት ወደ ትግራይ ክልል ከተመለሰ እና የፌዴራል መንግሥት ኃይሎች ወደ ትግራይ ክልል እንዳይገቡ በመንግሥት ትዕዛዝ ከተሰጣቸው በኋላ፣ ጦርነቱ አልፎ አልፎ ከሚሰሙ ውጊያዎች ወጪ ለወራት በፍጥጫ ቆይቷል። ይሁን እንጂ በፍጥጫ ላይ የነበረው ተለዋዋጭ ጦርነት ነሐሴ 18/2014 ለሦስተኛ ጊዜ ተቀስቅሷል።

ሦስተኛው ዙር ጦርነት የተቀሰቀሰው የተለያዩ አካላት ኹለቱን ተፋላሚ ኃይሎች ለማደራደር ያላሰለሰ ጥረት በሚያደርጉበት ወቅት ነበር።

ሦስተኛው ዙር ጦርነት ከተጀመረ ከሦስት ወራት በኋላ የተጀመረው ድርድር የጦርነቱ መቋጫ ይሆናል የሚል ተስፋ ተጥሎበታል።  ይሁን እንጂ የፌዴራል መንግሥት ኃይሎች በሦስተኛው ዙር ጦርነት ወደ ትግራይ ክልል ዘልቀው በመግባት የተለያዩ የክልሉ አካባቢዎችን ተቆጣጥረዋል።

ድርድሩ የተጀመረው መካላከያ የትግራይ ክልል አካል የሆኑት እንደ አክሱም፣ አድዋና ሽሬ የመሳሰሉ አካባቢዎችን ከተቆጣጠረ በኋላ ነው። መንግሥት ወደ ትግራይ ክልል ገብቶ በርካታ አካባቢዎችን ከሕወሓት ነጻ ባወጣበት ሁኔታ የሚካሄደው ድርድር የተለያዩ አመለካከቶች ይንጸባረቁበታል።

ድርድሩ የጦርነቱ መቋጫ ወይስ…?

የፌዴራል መንግሥት ወደ ትግራይ ክልል ዘልቆ በመግባት በሕወሓት ላይ የኃይል የበላይነት ባሳየበት ወቅት የተጀመረው ድርድር ላይ የተለያዩ ሐሳቦች እየተንጸባረቁ ነው። በተለያዩ ወገኖች ከሚንጸባረቁት ሐሳቦች መካከል የፌዴራል መንግሥት በሕወሓት ላይ የኃይል የበላይነት ቢይዝም፣ ዓለም ዐቀፍ ጫናን ለማቅለል የሚያደርገው የዲፕሎማሲ ስልት ነው የሚለው አንዱ ነው። በሌላ በኩል በጦርነት የኃይል የበላይነት የተበለጠውን የሕወሓት አመራሮች ወደ ውጭ ማስመለጫ ወይም “የማርያም መንገድ” ለመስጠት ነው የሚሉም ይገኙበታል።

በጉዳዩ ላይ ከአዲስ ማለዳ ጋር ቆይታ ያደረጉት “የመግባባት ዴሞክራሲ” የተሰኘው መጽሐፍ ደራሲ የሆኑት ፖለቲከኛ አድማሱ ገበየሁ (ፕ/ር)፣ በደቡብ አፍሪካ የተጀመረው ድርድር የፌዴራል መንግሥት በሕወሓት ላይ የኃይል የበላይነት በወሰደበት ሁኔታ መካሄዱ ለሕወሓት ውግንና ያላቸውን የውጭ ጫናዎች ለማቅለል የሚካሄድ ድርድር ነው ይላሉ። ለዚህም እንደ ምክንያት የሚያነሱት መንግሥት ሕወሓትን አሸንፎ ትግራይ ክልል መግባቱንና የሕወሓትን የኃይል መዳከም ነው።

‹‹መንግሥት በትግራይ ክልል ሕዝብን በማረጋጋት ላይ ነው›› የሚሉት ፖለቲከኛው፣ በደቡብ አፍሪካ በመካሄድ ላይ የሚገኘው ድርድር፣ ጦርነቱ በፌዴራል መንግሥት የኃይል የበላይነት እየተመራ ባለበት ሁኔታ መሆኑ፣ ድርድሩ ለሕወሓት አመራሮች “የማርያም መንገድ” ለመስጠት ነው በሚለው ሐሳብ ይስማማሉ። የሕወሓት አቅም መዳከሙን የሚያምኑት አድማሱ፣ አንድ ኃይል በጦርነት ከተሸነፈ ያለው አማራጭ ወደ ድርድር መቅረብና የኃይል የበላይነት በያዘው አካል የተሰጠውን እድል መጠቀም ነው ይላሉ።

እንደ ፖለቲከኛው ገለጻ፤ በፌዴራል መንግሥትና በሕወሓት መካከል እየተደረገ የሚገኘው ድርድር ከዚህ የተለየ አይደለም። በድርድሩ ላይ የምዕራባዊያን ኃይሎች ፍላጎት አለበት የሚሉት ፖለቲከኛው፣ የተጀመረው ድርድር ሕወሓት በጦርነቱ መሸነፉንና ያለው የኃይል ሚዛን በመዳከሙ በድርድሩ አመራሮችን ከሕግ ተጠያቂነት ከማዳን የዘለለ ነገር እንደማይኖረው ያነሳሉ።

መንግሥት በሕወሓት ላይ የኃይል የበላይነት ይዟል የሚሉት አድማሱ፣ ጦርነቱ ከዚህ በኋላ የሚቀጥልበት እድል ጠባብ መሆኑን አንስተዋል። መንግሥት ትግራይ ክልል ገብቶ መሠረታዊ አገልግሎት ለማስጀመርና ሕዝባዊ አስተዳደርን ለመመለስ ጥረት እያደረገ ባለበት ሁኔታ የሚደረግ ድርድር፣ የጦርነቱ መቋጫ ነው ማለት እንደማይቻልም ፖለቲከኛው ይገልጻሉ።

ጦርነቱ በፌዴራል መንግሥት የኃይል የበላይነት የሚቋጭበት እድል ሰፊ መሆኑን የሚያምኑት ፖለቲከኛው፣ የጦርነት መጨረሻው ሰላም ስለሆነ የነበሩ ቁርሾዎችን ለመፍታት የሚደረጉ የሰላም ጥረቶች ወደ ሕዝብ ቢዘልቁ የበለጠ ውጤት እንዳለው ጠቁመዋል።

የእርስ በእርስ ጦርነቶችን ለማስቆም የተደረጉ ስምምነቶች ላይ ተመሥርተው የተሠሩ ጥናቶች ውጤት እንደሚያሳዩት ከሆነ፣ ሰላም የሚመጣው በመደራደር ብቻ ሳይሆን ተግባራዊ በማድረግ ጭምር ነው። በዚሁ ጉዳይ ላይ “ድርድር፣ ሰላምና ጦርነት” በሚል መነሻ ርዕስ ስታንፎርድ ዩኒቨርሲቲ በአንድ ወቅት ያቀረበው ጥናት እንደሚያሳየው፣ የእርስ በእርስ ጦርነቶችን ለማስቆም የተባበሩት መንግሥታት ድርጅትና አሜሪካ በአደራዳሪነት የተሳተፉባቸው የሰላም ጥረቶች ተግባራዊነት አነስተኛ ነው።ከኹለተኛው የዓለም ጦርነት ማብቂያ በኋላ በጣም የተለመደ የጦርነት ዓይነት የሆነው የእርስ በርስ ጦርነት፣ በድርድር የመጠናቀቅ ዕድሉ በጣም አናሳ መሆኑን ጥናቶች ያመላክታሉ።

“የመግባባት ዴሞክራሲ” ጸሐፊውና ፖለቲከኛው አድማሱ እንደሚሉት፣ ጦርነቱ በፌዴራል መንግሥት የኃይል የበላይነት የመጠናቀቅ እድሉ ሰፊ ቢሆንም፣ ችግሩን ከመሠረቱ ለመፍታት የሕዝብ ለሕዝብ ንግግሮች አስፈላጊ ናቸው። ‹‹ሕዝብ ለሕዝብ ግጭት የለውም›› የሚሉት አድማሱ፣ ወደ ሰላም ለመቅረብ በትግራይ ክልል መሠረታዊ አገልግሎቶችን በአስቸኳይ ማስጀመርና የመንግሥትና የሕዝቡን ቅርርብ ማጠናከር ተገቢ መሆኑን ጠቁመዋል።

በድርድሩ በተለይ ከዓለም ዐቀፉ ማኅበረሰብ በኩል ለሕወሓት ባለሥልጣናት “የማርያም መንገድ” የመስጠት ፍላጎት ስላለ፣ ኢትዮጵያን በማይጎዳበት ሁኔታ የዓለም ዐቀፉን ማኅበረሰብ ፍላጎት ማስተናገድ እንደሚገባም ጠቁመዋል። ሕወሓት በድርድርም ይሁን በኃይል ተመልሶ ወደ ሥልጣን የሚመጣበት እድል አይታየኝም የሚሉት ፖለቲከኛው፣ በድርድር ሰበብ የወጡ የሕወሓት ባለሥልጣናት በወጡበት እንዲቀሩ የሚደረግበት ሁኔታ እንደሚኖር ጠቁመዋል።


ቅጽ 4 ቁጥር 208 ጥቅምት 19 2015

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here