በ1920ዎቹ በተደረጉ ምርምርና ሙከራዎች ለዓለም የተዋወቀው ቴሌቪዥን፣ ከኹለተኛው የዓለም ጦርነት ማግስት ጀምሮ በጥቁርና ነጭ ቀለማት በታጀቡ ምስሎች ተወስኖ በስፋት ለዓለም የቴክኖሎጂ በረከት ሆነ። ለአሜሪካና እንግሊዝ ሕዝቦችም እንደ ቀዳሚ የሐሳብ ማንሸራሸሪያነት ማገልገሉን ተያያዘው።
በሀምሳዎቹ መጨረሻ ደግሞ ቴክኖሎጂው ከጥቁርና ነጭ ቀለማት አለፍ ብሎ በርከት ያሉ ቀለማትን በማበርከት የዕይታ ልኩን ከፍ አደረገ። ከዛ ዘመን ጀምሮ መሻሻሉን ያላቆመው ቴክኖሎጂው፣ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየዘመነና የሚያሳየው ምስል ጥራትም ከፍ እያለ መጥቷል።
ቴሌቪዥን የኢትዮጵያን ምድር የረገጠውና አገሪቱም የቴሌቪዥን ጣቢያ ባለቤት የሆነችው ቴክኖሎጂው በመገናኛ መሣሪያነት ለዓለም ከተዋወቀ ከጥቂት ዓመታት በኋላ ነበር። ከ1948 ጀምሮ ቴሌቪዥንን በአገሪቱ ለማስተዋወቅ የተለያዩ ሙከራዎች ተደርገዋል። የመጀመሪያው ሙከራ የቀዳማዊ አጼ ኃይለሥላሴን የዘውድ በዓል አስመልክቶ በአሮጌው አውሮፕላን ማረፊያ (ብሥራተ-ገብርኤል) አካባቢ ተዘጋጅቶ በነበረው ኤግዚቢሽን ላይ የእንግሊዙ የሚዲያ ተቋም ቢቢሲ ያቀረበው ፕሮግራም ነበር።
ቀጥሎም በ1952/53 ደጃዝማች ዳንኤል አበበ የግል ቴሌቪዥን ጣቢያ ለማቋቋም ለሚኒስትሮች ምክር ቤት ጥያቄ አቅርበው የነበረ ቢሆንም፣ ጥያቄው በምክር ቤቱ ተቀባይነትን አጣ። የብሥራተ-ወንጌል ሬዲዮ ጣቢያና የቴሌኮምዩኒኬሽን ባለሥልጣንም ተመሳሳይ ጥያቄ አቅርበው ውድቅ ተደረገባቸው።
የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን
በእንግሊዙ ቶምሰን ኩባንያና በፊሊፕስ ኢትዮጵያ በቀረበ ምክረ ሐሳብ ምክንያት በኢትዮጵያ መንግሥት የተመደበለትን 247 ሺሕ ብር በጀት በመጠቀም የኢትዮጵያ የመጀመሪያው ቴሌቪዥን ጣቢያ ጥቅምት 11 ቀን 1957 የአፍሪካ አንድነት ድርጅት መሥራች ስብሰባን በቀጥታ በማስተላለፍ “የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን” በሚል ሥያሜ ሥራ ጀመረ። ተጠሪነቱም ለኢትዮጵያ መንግሥት የማስታወቂያ ሚኒስቴር ሆኖ ሲቋቋም፣ ሥራውን ለማለማመድ በኃላፊነት በተሾሙት እንግሊዛዊ ጂ. ዋትሶንና በሳሙኤል ፈረንጅ ምክትል ኃላፊነት ይመራ ነበር።
ጥቅምት 23 ቀን 1957 የኢትዮጵያ ቴሌቪዥንን በይፋ መርቀው የከፈቱት አጼ ኃይለሥላሴ በወቅቱ ባደረጉት ንግግር ”የቴሌቪዥን ጣቢያ አገልግሎት ለመጀመሪያ ጊዜ አነስተኛ ቢሆንም፣ ወደፊት ድርጅቱ ተስፋፍቶ የሚሰጠው ጥቅም መላውን ሕዝባችንን እንደሚያዳርስ ተስፋ አለን።” ብለው ነበር። የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ለሰዓታት ብቻ በሚተላለፍ ስርጭት አገልግሎት መስጠት ቢጀምርም፣ በአሁኑ ሰዓት የ24 ሰዓት ስርጭት ያላቸው ሦስት የቴሌቪዥን ጣቢያዎች አሉት።
አሁን ላይ የኤሌክትሪክ አገልግሎት በሚያገኙ የኢትዮጵያ ክፍሎች የቴሌቪዥን ተደራሽነት ከፍ ያለ ሲሆን፣ ከመደበኛ የአንቴና ስርጭቶች ባለፈም በሳተላይት ስርጭታቸውን ለሕዝብ የሚያደርሱ ጣቢያዎች ተበራክተዋል።
የቴሌቪዥን ባለቤትነትና የፍቃድ ክፍያ በኢትዮጵያ
የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን በአዋጅ ቁጥር 20/1967 በተሰጠው ሥልጣን መሠረት ዓመታዊ የቴሌቪዥን ፍቃድ ክፍያዎችን ከግለሰቦች ይሰበስባል።
ቴሌቪዥን ከገዙ 15 ዓመታትን እንዳስቆጠሩ የተናገሩት ሥማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁ አስተያየት ሰጪ እንደሚሉት፣ ቴሌቪዥኑን ከገዙ ከስምንት ዓመት በኋላ ፍቃድ ያወጡበት ቢሆንም ዓመታዊ ክፍያውን ግን ለኹለት ዓመታት ብቻ እንደከፈሉ ተናግረዋል። እንደ ምክንያት ሲያነሱም ለስምንት ዓመታት ያህል የቴሌቪዥን ባለቤትነት የምስክር ወረቀት እንደሚያስፈልግ አላውቅም ነበር ብለዋል። ይሁንና ላለፉት ስድስት ዓመታት የሳተላይት ቴሌቪዥን ጣቢያዎችን ስለሚጠቀሙ ዓመታዊ ክፍያ መክፈል እንደሌለባቸው እንደሚያምኑ ተናግረዋል።
ወሰንሰገድ ገብሩ የሚባሉ አስተያየት ሰጪ ደግሞ ቴሌቪዥን ሲገዙ የቴሌቪዥን ፍቃድ እንዳወጡ ተናግረው፣ በየዓመቱም የሚጠበቅባቸውን 60 ብር በአግባቡ እየከፈሉ እንደሚገኙ ገልጸዋል። ‹‹ዓመታዊ ክፍያውን የምከፍለው ማንም አስገድዶኝ ሳይሆን ብዙ ጊዜ ማታወቂያዎችን አዳምጥ ስለነበር ነው›› ብለዋል።
የሚያውቋቸው በርካታ ሰዎችም ይህን ክፍያ እንደማይከፍሉ የተናገሩት ወሰንሰገድ፣ ዓመት ሙሉ ለሚታይ ቴሌቪዥን 60 ብር መክፈል ምንም ማለት እንዳልሆነ ተናግረው፣ “የቄሳርን ለቄሳር፣ የእግዚአብሔርን ለእግዚአብሔር” የሚለውን የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅስ አስታውሰዋል።
ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ የሳተላይት ቴሌቪዥን አገልግሎት እየተስፋፋ መምጣቱ የሚታወቅ ሲሆን፣ ኅብረተሰቡ በርካታ የቴሌቪዥን ቻናል ምርጫዎችን አግኝቷል። በዚህም ምክንያት የመደበኛ አንቴና ስርጭት ያለውን የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን በሳተላይትም ስርጭቱ ማግኘት የሚቻልበት አጋጣሚ ተፈጥሯል። ይህን አጋጣሚም የቴሌቪዥን ዓመታዊ የአገልግሎት ክፍያን ላለመክፈል እንደ ምክንያትነት የሚያነሱ ግለሰቦች አሉ።
በኢትዮጵያ በርካታ የቴሌቪዥን ጣቢያዎች አሉ የሚሉት እስከዳር ድሪባ ደግሞ፣ የቴሌቪዥን ባለቤትነት የምስክር ወረቀት ለምን እንደሚያስፈልገው አላውቅም ብለዋል። እንደ ሌሎች የቤት እቃዎች ቴሌቪዥንም አገልግሎት ይሰጣል ያሉት እስከዳር፣ አሁን ባሉ ቴክኖሎጂዎች የቴሌቪዥንን አገልግሎት የሚተኩ ስልክና ኮምፕዩተሮች እንዳሉ ተናግረዋል። እስከዳር ሲያክሉም፣ የሚከፈለው ክፍያ ብዙ ሆኖ ሳይሆን ስለማያሳምነኝ አልከፍልም ብለዋል።
በቴሌቪዥን፣ የቴሌቪዥን ፍቃድ አውጡና የአገልግሎት ክፍያ ክፈሉ የሚሉ ማስታወቂያዎችን እንደሚሰሙ የተናገሩት እስከዳር፣ ቤታቸው ድረስ መጥቶ ፍቃድ አውጡ ያላቸው አካል ግን እንደሌለ ተናግረዋል።
ከኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ውጭ ከኅብረተሰቡ በፍቃደኝነት መዋጮ ገንዘብ የሚሰበስቡ ጣቢያዎች እንዳሉ ቢታወቅም፣ በአስገዳጅ ሁኔታ የፍቃድ ክፍያ ለመሰብሰብ ፍቃድ ያለው ግን የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን ነው።
የእንግሊዝ ተሞክሮ
በእንግሊዝ የቴሌቪዥን ፍቃድ ክፍያ ብሔራዊ የሆነው ቢቢሲን ለማጠናከርና ቋሚ የገቢ ምንጭ ይሆነው ዘንድ የሚከፈል ክፍያ እንደሆነ ይታመናል። ይህም ጣቢያው ለየትኛውም አካል ዓላማ መስፈጸሚያ ሳይሆን ራሱን ችሎ እንዲተዳደር ለማድረግ ነው። ምንም እንኳን በጣቢያው ሽፋን በሚያገኙ ዓለም ዐቀፍ ጉዳዮች ላይ የወገንተኝነት ጥያቄ ሲነሳበት ቢሰማም፣ ለአገሬው ነዋሪ ሚዛናዊ እንዲሆን ታስቦ ይህ የገቢ ምንጭ እንደተዘጋጀለትም መረጃዎች ያሳያሉ።
ከገንዘብ ምንጮች ፖለቲካዊ እሳቤ ጫና የጸዳ ሚዲያን ለመፍጠር እንዲህ ዓይነቱ የገቢ መሰብሰቢያ አማራጭ የተሻለ እንደሆነ ምሁራን ይናገራሉ። በእንዲህ ዓይነት የገቢ ምንጮች የሚተዳደሩ መገናኛ ብዙኀንም ሕዝባዊ እንዲሆኑ የሚጠበቅ ሲሆን፣ በእንግሊዝ አገር ማንኛውም የቴሌቪዥን እንዲሁም በማኅበራዊ ሚዲያ የቴሌቪዥን ስርጭቶችን የሚከታተል ተመልካች ለቢቢሲ በዓመት 159 ፓውንድ እንዲከፍል ይጠበቅበታል።
ጥቁርና ነጭ ቴሌቪዥን የሚጠቀም ሰውም 53.5 ፓውንድ እንዲከፍል ይገደዳል። እ.ኤ.አ በ2019 ይፋ በሆነ ሪፖርትም ቢቢሲ ከዚሁ የቴሌቪዥን ፍቃድ ክፍያ 3.7 ቢሊዮን ፓውንድ ክፍያ የሰበሰበ ሲሆን፣ ይህም የዓመታዊ ገቢውን 76 በመቶ መሆኑ ነው።
እድሜያቸው ከ75 ዓመት በላይ የሆኑ ሰዎች ነጻ የቴሌቪዥን ፍቃድ የሚያገኙ ሲሆን፣ ለዐይነ ስውራን ደግሞ የፍቃድ ክፍያው በግማሽ ቀንሶ 79.5 ፓውንድ ብቻ እንዲከፍሉ ይደረጋል።
ቢቢሲ ማንኛውም የቴሌቪዥን ተጠቃሚ ክፍያውን እንዲከፍል የማስገደድና የመቆጣጠር ሥልጣን የተሰጠው ሲሆን፣ ያለ ፍቃድ ቴሌቪዥን የሚጠቀሙ ግለሰቦችንም በሕግ እንዲጠየቁ የማድረግ ኃላፊነት አለበት።
የአዋጅ ማስተካከያ
የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽንን በቴሌቪዥን ፍቃድ ክፍያ ዙሪያ መረጃ ለመጠየቅ አዲስ ማለዳ ባደረገችው ጥረትም የአዋጅ ማሻሻያ ሥራ ላይ ስላለ ምንም ዓይነት መረጃ ማግኘት ያልተቻለ ቢሆንም፣ የቴሌቪዥን ፍቃድ ክፍያ በበቂ ሁኔታ እየተሰበሰበ እንዳልሆነ የሚያስማማ ጉዳይ ነው።
በ2006 በአዲስ አበባ ከተማ ይገኛሉ ተብሎ ከተገመቱ 1 ሚሊዮን የቴሌቪዥን ባለንብረቶች 13 ሚሊዮን ብር እንደተሰበሰበ የተገለጸ ሲሆን፣ ይህም ሊሰበሰብ ይገባ ከነበረው 60 ሚሊዮን በ47 ሚሊዮን ያነሰ ነው።
ከአዋጁ ምን ዓይነት ማሻሻያዎች ይጠበቃሉ
ከሌሎች አገሮች ተሞክሮ መረዳት እንደሚቻለው ሕዝባዊ መገናኛ ብዙኀንን ለመፍጠር የኅብረተሰቡ ሚና ከፍተኛ ነው። ለዚህም ለመገናኛ ብዙኀን የሥራ ማስኬጃ ክፍያዎችን ለመሸፈን መዋጮ መጠየቁ አይቀርም። በዚህም ምክንያት በሥራ ላይ ያለውን አዋጅ ገምግሞ እርምጃዎች እንደሚወሰዱ ይጠበቃል።
በዚህም የመጀመሪያው ጉዳይ አስገዳጅነት ሊሆን እንደሚችል ይገመታል። ከዓመታት በፊት ለሚዲያ አስተያየታቸውን የሰጡ የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን የወቅቱ የሥራ ኃላፊ፣ በኢትዮጵያ የግል የቴሌቪዥን ጣቢያዎች ሲስፋፉ የዓመታዊ የክፍያ አሰባሰቡ ላይ ለውጥ ሊኖር እንደሚችል ገልጸው ነበር። ምንም እንኳን የተቋቋሙ የቴሌቪዥን ጣቢያዎች ቢበረክቱም የዓመታዊ የቴሌቪዥን ፍቃድ ክፍያ ሰብሳቢዎች ላይ ልዩነት ላይኖር እንደሚችል አስተያየታቸውን ለአዲስ ማለዳ የሰጡ ባለሙያዎች ተናግረዋል። እንደ ምክንያትነትም የቴሌቪዠን ጣቢያዎቹ በአብዛኛው በግለሰቦች የሚመሩና ለንግድ የተቋቋሙ መሆናቸውን ገልጸዋል።
ነጻ ሚዲያን ለመፍጠር የኅብረተሰቡ አስተዋጽኦ እንደሚያስፈልግ የሚጠቅሱ አስተያየት ሰጪዎች እንደዚህ ዓይነት ዓመታዊ ክፍያዎች ሚናቸው ከፍተኛ እንደሆነ ይገልጻሉ።
ሲጠቃለል፤ ዓመታዊ የቴሌቪዥን ፍቃድ ክፍያዎች ከኢትዮጵያ ውጭም ተግባራዊነት ያላቸው ሲሆን፣ የየአገሩን ነባራዊ ሁኔታ ያገናዘቡ አካሄዶችን ይጠቀማሉ። በክፍያው ዙሪያም የአመለካከትና የአተገባበር ችግር እንዳለ ከአስተያየት ሰጪዎች አስተያየቶች ማረጋገጥ የሚቻል ሲሆን፣ አሠራሩን ለማዘመንም ተጨማሪ ሥራዎችን ይጠይቃል።
ቅጽ 4 ቁጥር 208 ጥቅምት 19 2015