አሳሳቢ እየሆነ የመጣው የአየር ንብረት ለውጥ

0
1330

‹‹የዓለማችን ሙቀት እየጨመረ ነው። በረዶ እየቀለጠ፣ የባህር ከፍታም እየጨመረ ነው። በርካታ ብዝኀ ሕይወት እየጠፋ ነው። ወደፊት የማናገኛቸው የእንስሳትና የእጽዋት ዝርያዎች ብዙ ናቸው። የዚህ ኹሉ ምክንያት የአየር ንብረት ለውጥ እና የኢንዱስትሪ መስፋፋት መሆኑ ግልጽ ነው። ስለዚህ የአየር ንብረት ለውጥ የመብላትና ያለመብላት፣ የመኖርና ያለመኖር ጉዳይ ሆኗል።›› ይህ የአየር ንብረት ለውጥ ባለሙያዎች ዕይታ ነው።

ፕላስቲኮች ተመልሰው ጥቅም ላይ የሚውሉበት መንገድ ላይ በትኩረት ካልተሠራ፣ ተመራማሪዎች የተለያዩ የመፍትሔ ሐሳቦች የያዙ የምርምር ውጤቶችን ካላስተዋወቁ፣ መንግሥትም የተለያዩና ጠንከር ያሉ የፖሊሲ አማራጮችን ካልተገበረ እንዲሁም ዜጎች ግንዛቤ አግኝተው የበኩላቸውን ድርሻ ካላበረከቱ ዓለም እየገዘፈ የሚሄድ አደጋ ይጠብቃታል ነው የሚሉት ምሁራኑ።

የዓለማችን የአየር ንብረት ለውጥ በዚህ ከቀጠለ የሰው ልጅን ከምድረ ገጽ ሊያጠፋ እንደሚችል ከወራት በፊት በካምብሪጅ ዩኒቨርሲቲ አንድ ጥናት ይፋ ተደርጓል።

የአየር ንብረት ለውጥን መከላከል ካልተቻለ ሊደርስ የሚችለውን ጥፋት መገመት እንደማይቻል ባለሙያዎች ያነሳሉ። የዓለም የዱር እንስሳት ፈንድ የዘንድሮ ሪፖርት እንደሚያሳየው፣ የዓለም የዱር እንስሳት መጠን 69 በመቶ ቀንሷል። 83 በመቶ የዓለም የምንጭ ውሃ እንዲሁ።

ዓለም ከፍተኛ የሆነ የብዝኀ ሕይወት ውድመት ያጋጠማት ሲሆን፣ ቀዳሚ (94 በመቶ) ውድመት የተከሰተው በላቲን አሜሪካ መሆኑ ተገልጿል። በመቀጠል በአፍሪካ 60 በመቶ፣ በእስያ 55 በመቶ፣ በሰሜን አሜሪካ 20 በመቶ እንዲሁም በአውሮፓ 18 በመቶ የብዝኀ ሕይወት ውድመት ተከስቷል ይላል ተቋሙ።

ይህም ጥፋት በብዙዎች ዘንድ የወደፊቱን ጊዜ አስፈሪነት የሚያሳይ ያልታሰበ አደጋ ተብሏል።

በቅርቡ በአየር ንብረት ለውጥ ላይ ትኩረቱን አድርጎ ለጋዜጠኞች በተዘጋጀ ውይይት ላይ ተገኝተው ሐሳብ ያቀረቡት የአየር ንብረት ለውጥ ቅነሳ ባለሙያ ስምረት ተረፈ፣ የዓለም ጤና ድርጅትን መረጃ ዋቢ አድርገው እንደገለጹት፣ 230 ሚሊዮን የሚጠጉ አፍሪካዊያን በውሃ እጥረት ስቃይ ውስጥ ይኖራሉ።

ይህ ቁጥር በፈረንጆች 2030 ወደ 460 ሚሊዮን ከፍ እንደሚል አስገንዝበው፣ በአየር ንብረት ለውጥ ሳቢያ በተለይ ወደ አፍሪካ ትልቅ ችግር እየመጣ ለመሆኑ በርካታ ማሳያዎች አሉ በማለት ያስረዳሉ።

በፈረንጆች 2019 በዓለም ላይ በአየር ንብረት ለውጥ ክፉኛ ከተጠቁ አገራት አምስቱ ከአፍሪካ ነበሩ የሚሉት ባለሙያዋ፣ በአኅጉሪቱ ከሚሞቱ ሦስት ሰዎች አንዱ በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት በመጣ ችግር ወይም በሽታ ሳቢያ መሆኑን ሳይጠቅሱ አላለፉም።

ስለሆነም፣ አፍሪካ በአየር ንብረት ለውጥ ቀዳሚ ተጠቂ ሆና ሳለ ከዓለምም ይሁን ከራሷ ለጉዳዩ የተሰጠው ትኩረት እጅግ አናሳ መሆኑን ይገልጻሉ።

ለአፍሪካ ለምን የተለየ ትኩረት ያሻል?

እንደ ባለሙያዋ ገለጻ፣ የአኅጉሪቱ ዋና የኢኮኖሚ ምሰሶ ግብርና በመሆኑ፣ የማኅበረሰቡ የቤት ግንባታ ወይም አሠራር ከአየር ንብረት ለውጥ ጋር የተያያዘ ባለመሆኑ እንዲሁም የአየር ንብረት ለውጥን የመከላከልና የመቋቋም አቅማችን በጣም ዝቅተኛ በመሆኑ፣ ዓለምም ሆነ አኅጉሪቱ በዚህ ጉዳይ የተለየ ትኩረት ሊኖራቸው ይገባል ባይ ናቸው።

ዓለም በሙሉ ለአየር ንብረት ለውጥ ችግር ተጋላጭ ቢሆንም፣ አፍሪካ ግን የተለየ ተጠቂ ናት ይላሉ። ዝቅተኛ የቴክኖሎጂ አቅም፣ ደካማ የፖለቲካ ሥርዓት፣ ደካማ ምጣኔ ሀብት እንዲሁም ደካማ ተቋማትና ሌሎች ምክንያቶች ተደማምረው የአፍሪካ የመከላከልና የመቋቋም አቅም የወረደ እንዲሆን አድርጎታል ነው የሚሉት።

በቅርቡ አውሮፓ ውስጥ በ500 ዓመት ውስጥ ያልተከሰተ እጅግ አስከፊ የሆነ ድርቅ ተከስቷል። ነገር ግን የመከላከልና የመቋቋም አቅማቸው ከፍተኛ በመሆኑ የችግሩን ግዝፈት ያህል ሳይወራለትና ሳይታወቅ ቀርቷል ሲሉም አክለዋል።

የአየር ንብረት ለውጥ ድርድር

ከተጀመረ 28 ዓመታትን ያስቆጠረውና በኮሮና ቫይረስ ምክንያት ለአንድ ዓመት ተቋርጦ የነበረው  የዓለም የአየር ንብረት ለውጥ ድርድር ጉባኤ (COP 27) የዘንድሮው በግብፅ ይካሄዳል።

በዚህ ጉባኤም በበለጸጉ አገራት ከፍተኛ የበካይ ጋዝ ልቀት የተነሳ ዘርፈ ብዙ የአየር ንብረት ለውጥ ወለድ ችግሮችን እየተጋፈጠች የምትገኘው አፍሪካ ዋና ተደራዳሪ በመሆን ጠቃሚ ውሳኔዎችን እንደምታስወስን ተስፋ ተጥሎበታል። ኢትዮጵያም በዚህ ጉባኤ ትልቅ ሚና እንዲኖራትና ይህን ለማሳካትም ከወዲሁ አስፈላጊ ዝግጅቶች መደረግ እንዳለባቸው ተመላክቷል።

በዚህ ጉባኤ የበርካታ አገራት መሪዎች ተገኝተው፣ ባለፈው ጉባኤ የተወሰኑ ውሳኔዎችን አፈጻጸም ይገመግማሉ። አዳዲስ የመፍትሔ ውሳኔዎችን ይወስናሉ። እርስ በእርስ የተለያዩ ድርድሮችን ያካሂዳሉ።

ከኹሉም ጉባኤዎች እንግሊዝ ውስጥ የተካሄደው 26ኛው ላይ ጠቃሚ ውሳኔዎች የተወሰኑ ሲሆን፣ ከዚህም አገራት በካርበን ልቀት ቅነሳ ላይ ለመሥራት ትብብር የፈጠሩበት እንደሆነ ይነሳል።

በዚህ ጉባኤ ተሳታፊ የነበሩ ኢትዮጵያዊያን የአየር ንብረት ለውጥ ባለሙያዎች እንዳስረዱት ከሆነ፣ እስከ ፈረንጆች 2025 የአደጉ አገራት ለአየር ንብረት ለውጥ መከላከያ የሚሆን ብለው ቃል ከገቡት 100 ቢሊዮን ዶላር እጥፍ እንለግሳለን ብለው ነበር።

የዓለምን የሙቀት መጠን በ1 ነጥብ 5 ዲግሪ ሴንቲግሬድ ለመቀነስም እቅድ መቀመጡን ባለሙያዎቹ ይገልጻሉ።

አሜሪካና ቻይና በአየር ንብረት ለውጥ ዙሪያ አብሮ ለመሥራት ስምምነት ላይ መድረሳቸውም የዚህ ጉባኤ ትሩፋት ነበር። ከ100 በላይ የአገራት መሪዎችም (85 በመቶ የዓለም የደን ሽፋን ያለባቸው) የደን ጭፍጨፋን ለማስቆም ቃል ገብተዋል። በተመሳሳይ ከ100 አገራት በላይ መሪዎች የ‹ሚቴን ጋዝ› ልቀትን በ30 በመቶ ለመቀነስ ስምምነት አድርገዋል።

የፋይናንስ ተቋማት በዓመት አንድ ትሪሊዮን ዶላር ወይም እስከ 130 ትሪሊዮን ዶላር በታዳሽ ኃይል ግንባታ እና በአካባቢ ጥበቃ ላይ ለመሥራት ቃል ገብተውም ነበር። ይሁን እንጂ ሩብ ያህልም እንዳልተፈጸመ ባለሙያዎች አመላክተዋል።

የቻይና፣ የሩስያና የብራዚል መሪዎች በጉባኤዎች የማይገኙበት ምክንያት እንዲሁም ህንድ የካርቦን ልቀትን ለመቀነስ ካልሆነ ለማቆም አልስማማም ማለቷ አንዱ እንቅፋት መሆኑ ተነስቷል።

የአየር ንብረት ለውጥን ለመግታት ታስቦ የተዘጋጀው የ2030 (እ.ኤ.አ) እቅድ ካልተተገበረ፣ የዓለም የሙቀት መጠን ከ2 ነጥብ 1 እስከ 2 ነጥብ 4 ዲግሪ ሴንቲግሬድ ከፍ ይላል ተብሏል። የ2030 እቅድ ደግሞ ልፍስፍስ እና ሊተገበር የማይችል መሆኑን ባለሙያዎች ይጠቅሳሉ።

በ21ኛው ጉባኤ ላይ በማደግ ላይ ላሉ አገራት በዓመት 100 ቢሊዮን ዶላር ካሳ እንዲከፈላቸው ተውስኖ የነበረ ቢሆንም፣ እስካሁን የተከፈለው ስምንት በመቶው ብቻ መሆኑ ነው የተገለጸው።

የዓለምን የበካይ ጋዝ ልቀት በየዓመቱ በአራት በመቶ የምትቀንሰው ኮንጎ፣ ለዚሁ የተፈጥሮ ሀብቷ ጥበቃ በርካታ ቢሊዮን ዶላር ቃል የተገባላት ቢሆንም ተግባራዊነቱ ግን ጥያቄ ውስጥ መሆኑ ሳይጠቀስ አላለፈም። ስለሆነም፣ በመጪው ኅዳር ወር በግብጽ በሚካሄደው ጉባኤ እስካሁን የተገቡ ቃልኪዳኖች ተግባራዊ ይደረጋሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ ከባለሙያዎች ተሰምቷል።

ሆኖም ኢትዮጵያን ጨምሮ አፍሪካ በጉባኤው የበለጸጉ አገራት ከፍተኛ የበካይ ጋዝ ልቀት የተነሳ ለደረሰባቸው እና ወደፊትም ለሚደርባቸው ጉዳት ካሳ ክፍያ ነው መጠየቅ ያለባቸው ወይስ የበካይ ጋዝ ልቀታቸውን ለመቀነስ ነው ትኩረት መስጠት ያለባቸው የሚለው ብዙዎችን የሚያከራክር ጉዳይ ነው።

አንዳንዶች አፍሪካ በበለጹጉ አገራት የተነሳ በአየር ንብረት ለውጥ የጉዳት ሰለባ ሆና የኖረችው ከኢንዱስትሪ ዘመን ጀምሮ ነው። በዚህ የተነሳ የምናገኘው ገንዘብ እርዳታ ሳይሆን ተገቢ ካሳ በመሆኑ በጥብቅ መደራደር ይገባል ሲሉ ይከራከራሉ።

አክለውም፣ እኛ አቅም ማሳደግ እንጂ የልቀት መጠን መቀነስ አይደለም ያለብን። የአደጉ አገራት ለቅነሳ ነው ሊደግፉን የሚፈልጉት። ለእኛ የበካይ ጋዝ ልቀትን ለማስቆም ወይም ለመቀነስ መስማማት ማለት ደግሞ ኢንዱስትሪ አናስፋፋም ብሎ እንደመወሰን ነው። አንዴ ከወሰንን በኋላ ደግሞ ቆጨኝ ይቀየርልኝ ማለት አይቻልም። ስለሆነም በዚህ መልኩ መደራደር አይገባም ነው የሚሉት።

ከዚህ ይልቅ የመላመድና የመቋቋም አቅምን (adaptation effort) ለማሳደግ መሥራትና ለዚህ ይሆን ዘንድም ከአደጉ አገራት የተገባውን የካሳ ክፍያ በቶሎ ተፈጻሚ እንዲሆን በማድረግ እዚሁ ላይ አጠንክሮ መሥራት ያስፈልጋል ባይ ናቸው።

‹‹ገንዘብ ካገኘን ብለን የምንተወው ጉዳይ አይደለም፣ ከችግሩ አሳሳቢነት የተነሳ አፍሪካም ካሳ መቀበል ብቻ ሳይሆን የበካይ ጋዝ ልቀቷን ለመቀነስ መስማማት አለባት›› የሚሉም አሉ።

በፖላንድ በተካሄደው 24ኛው የአየር ንብረት ለውጥ ድርድር ጉባኤ (COP 24) ላይ ተሳታፊ እንደነበር የገለጸው ጋዜጠና ደምስ መኩሪያ፣ ኢትዮጵያ ከ10 አደገኛ የአየር ንብረት ለውጥ ተጠቂ አገራት መካከል አንዷ መሆኗን አንስቷል።

በዚህም የምርት መቀነስ፣ ቃጠሎ፣ የውሃ እጥረት፣ ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብ፣ በሽታና ድርቅ የአየር ንብረት ለውጥ ችግር የወለዳቸው ናቸው ሲል ያስረዳል።

በኢትዮጵያ ብሎም በአፍሪካ መገናኛ ብዙኀን ዘንድ ጉዳዩ ትኩረት የተነፈገው መሆኑን በመግለጽም፣ ፖላንድ በተካሄደው የድርድር ጉባኤ ከተሳተፉ አንድ ሺሕ በላይ ጋዜጠኞች፣ አራት የምሥራቅ አፍሪካ ጋዜጠኞችን ጨምሮ ከአፍሪካ የሄዱት 30 ብቻ ነበሩ። ይህም በአኅጉሪቱ ጉዳዩ የተሰጠው ትኩረት ምን ያህል ያነሰ መሆኑን ያሳያል ሲል ተናግሯል።

ለመገናኛ ብዙኀን መልካም አጋጣሚዎች

መገናኛ ብዙኀን ትኩረታቸውን አየር ንብረት ለውጥ ላይ አድርገው ተከታታይ ዘገባዎችን ለመሥራት በአሁኑ ወቅት በርከት ያሉ ርዕሰ ጉዳዮች መኖራቸው ተጠቁሟል።

ከእነዚህ መካከል አንዱ በየዓመቱ በርከት ያሉ ችግኞች የሚተከሉበት የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ሆኖ ተጠቅሷል። በዚህም 500 ቢሊዮን ችግኝ መትከል ከተቻለ በከባቢ አየር ውስጥ ያለውን የአማቂ ጋዝ መጠን በአንድ አራተኛ መቀነስ እንደሚቻል ተገልጿል።

በተጨማሪም ከታዳሽ ኃይል ግንባታና ማስፋፋት ጋር ተያይዞ፣ የታላቁ ህዳሴ ግድብ አስተዋፅዖ፣ ከንፋስና ከፀሐይ ኃይል እንዲሁም ከጂኦተርማል የሚገኘው የኃይል መጠን እስከ 60 ሺሕ ሜጋ ዋት በመሆኑ በዚህ ላይ በሰፊው መሥራት ይገባል ነው የተባለው።

ኢትዮጵያ ደን በማልማት የጀመረችው የካርቦን ሽያጭ፣ ከበለጹጉ አገራት የሚገኘው የካሳ ክፍያ እንዲሁም አየር ንብረትን የመላመድና የመቋቋም ጥረት ለመገናኛ ብዙኀን ዋነኛ የዘገባ ትኩረት ሊሆኑ እንደሚችሉ ተመላክቷል።


ቅጽ 4 ቁጥር 208 ጥቅምት 19 2015

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here