የሕግ ጉድለቶችን ሞልቶ ክፍተቶችን ያመጣው የጦር መሣሪያ አዋጅ

0
1632

ኢትዮጵያ እስከ 2012 ድረስ የተሟላ የጦር መሣሪያ አስተዳደርና ቁጥጥር ሕግ እንዳልነበራት ባለሙያዎች ያናገራሉ። ይህ ሁኔታ በተለይ በፖለቲካው አስተዳደር ሪፎርም በተደረገ ማግሥት የተፈጠረውን አለመረጋጋትና የሰላም እጦት ተከትሎ የጦር መሣሪያዎች ዝውውር ከፍተኛ ሥጋት መፍጠሩ የሚታወቅ ነው። ሌላው ቀርቶ በየጊዜው ብዛት ያላቸው የጦር መሣሪያዎች በሕገ ወጥ መንገድ ሲዘዋወሩ የመያዛቸው ዜና የዕለት ተዕለት ሆኖ ነበር።

በዚህ መልኩ የሚዘዋወሩት ጦር መሣሪያዎች ደግሞ ከቀላል ሽጉጦች እስከ ከባድ የቡድን መሣሪያዎች የሚደርሱ ናቸው። ይህ ሁኔታ በአገራችን የተለያዩ አካባቢዎች አሁንም ድረስ ለሚስተዋለው እልቂትና የሰላም እጦት አስተዋጽዖ እንደሚያደርግ እሙን ነው።

ይህንን ግንዛቤ ውስጥ በማስገባት በ2012 በፍትሕ ሚኒስቴር ተዘጋጅቶ የቀረበው ረቂቅ ሕግ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የጦር መሣሪያ አስተዳደርና ቁጥጥር አዋጅ 1177/2012  ተብሎ ጸድቆ በሥራ ላይ ይገኛል። አዋጁ በርካታ የሕግ ጉድለቶችን የመሙላቱን ያህል የራሱን አወዛጋቢ የሕግ ክፍተቶች ደግሞ መያዙን ባለሙያዎች ያናገራሉ።

በጉዳዩ ላይ ከአዲስ ማለዳ ለቀረበላቸው ጥያቄ አስተያየታቸውን የሰጡት በፌዴራል ፍርድ ቤቶች ጠበቃ እና የሕግ አማካሪ አቤል አበበ፣ አዋጁ ሦስት ዋና ዋና ጉዳዮችን ታሳቢ በማድረግ የወጣ ነው ይላሉ።

የጦር መሣሪያ አስተዳደርን እና ቁጥጥርን የሚገዛ አዋጅ የኅብረተሰቡን ሰላምና ጸጥታ እንዲሁም መብትና ደኅንነትን ለማስጠበቅ አስፈላጊ መሆኑ አንደኛው ሲሆን፣ ዘርፉን የሚመለከቱ እና በሥራ ላይ ባሉ ሕጎች ያልተሸፈኑ ክፍተቶችን መሙላትና ኢትዮጵያ በዘርፉ የፈረመቻቸውን ዓለም ዐቀፍ ማእቀፎች እና ፕሮቶኮሎችን ተፈጻሚ ማድረግ ደግሞ ኹለተኛው ነው ይላሉ። አቤል እንደ አብነትም፣ አስገዳጅ የሆነውና ኢትዮጵያን ጨምሮ 11 አገራት የፈረሙት የናይሮቢ ፕሮቶኮል አካባቢያዊ ስምምነትን ይጠቅሳሉ።

በሦስተኛነት ይህን አዋጅ አስፈላጊ ያደረገውና ከአዋጁ መግቢያ ላይም የሚነበበው ደግሞ ግለሰቦች የታጠቋቸውን የጦር መሣሪያዎች ለኅብረተሰቡ ሰላምና ጸጥታ መጠበቅ ማዋል የሚችሉበትን ሁኔታ ማመቻቸት ነው።

ጠበቃ አቤል አበበ ቀደም ሲል በዳኝነት እና በፌዴራል ዐቃቤ ሕግነት ለዓመታት ሲሠሩ የነበሩ እንደመሆናቸው የሕግ ባለሙያዎችን በተግባር ሲፈትኑ የነበሩ ክፍተቶችን የሸፈነ መሆኑን ይናገራሉ።

ለአብነትም ከዚህ በፊት የጦር መሣሪያን ትርጉም በምልዓት የያዘ፣ ሕገ ወጥ የጦር መሣሪያ ይዘው የተገኙ ሰዎችን ለመዳኘት፣ መሣሪያን በመሸጥ ተግባር ላይ የተገኙ ሰዎችን ቅጣት፣ ሕጋዊ ፈቃድ ያለው ሰው የታጠቀውን መሣሪያ መሸጥ የሚችልበትን ሕጋዊ አሠራር በመደንገግ ሕገ ወጥ የመሣሪያ ዝውውርን ለመከላከል እና መሰል ሁኔታዎችን በሚመለከት የነበሩ የሕግ ክፍተቶችን ወይም የአዋጆች አለመኖርን ክፍተት በሚገባ መሸፈኑን ይገልጻሉ።

የጦር መሣሪያን ትርጉም አሟልቶ ማስቀመጡን በሚመለከት ግን እንደ አቤል አገላለጽ አዋጁ ለአፈጻጸም አስቸጋሪ የሆኑ ክፍተቶች እንደሚታዩበት ይናገራሉ። ይህም ከአዋጁ ክፍተቶች እንደ አንዱ ሊወሰድ ይችላል ይላሉ። የጦር መሣሪያ አስተዳደርና ቁጥጥር አዋጅ 1177/2012   አንቀጽ ኹለት ላይ የጦር መሣሪያ ተብለው የሚለዩትን ምንነቶች ይዘረዝራል።

በዚህ አንቀጽ መሠረት ከጦር መሣሪያ ጋር ተያያዥነት ያላቸው ዕቃዎች ተዘርዝረው እንደ ጦር መሣሪያ ተተርጉመው ይገኛሉ። በዚህ ውስጥ ጥይት፣ የጦር መሣሪያ ማንገቻ፣ መፍቻና የመሳሰሉት ሁሉ እንደ አንድ የጦር መሣሪያ ሊቆጠሩ በሚችሉበት ሁኔታ ተተርጉመው ይገኛል።

ይህ ሁኔታ በአፈጻጸም ላይ ችግር የሚፈጥረው እንዴት ነው ለሚለው ጥያቄ አቤል እንደሚከተለው ይመልሳሉ።

አዋጁ አንድ ሕገ ወጥ የጦር መሣሪያን ይዞ በተገኘ ሰው እና ኹለት እና ከዚያ በላይ ሕገ ወጥ የጦር መሣሪያን ይዞ በተገኘ ሰው ላይ የሚተላለፈውን ቅጣት በተለያየ መልኩ ይደነግጋል። በአንቀጽ 22 ንዑስ አንቀጽ 2 መሠረት አንድ ሰው በጦር መሣሪያነት ከተተረጎሙት ዕቃዎች  አዋጁ በሚከለክልበት መንገድ አንድ ይዞ ሲገኝ ከአንድ እስከ ሦስት ዓመት በሚደርስ እስራትና በገንዘብ የሚቀጣ ሲሆን፣ በዚሁ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ 3 ላይ ደግሞ የጦር መሣሪያው ብዛት ያለው ሲሆን፣ ማለትም በአዋጁ ድንጋጌ መሠረት ኹለትና ከዚያ በላይ ሲሆን ደግሞ እስከ ኻያ ዓመት በሚደርስ እስራትና ገንዘብ ይቀጣል።

ታድያ አንድ ሰው አንድ ሽጉጥና አንድ ጥይት ይዞ ቢገኝ ወይም የጦር መሣሪያ ተያያዥ እቃዎችን ይዞ ቢገኝ አዋጁ ብዙ የጦር መሣሪያ ይዞ እንደተገኘ በመቁጠር እስከ ኻያ ዓመት ሊደርስ በሚችል እስራት ሊቀጣ የሚችልበትን ሁኔታ ፈጥሯል ይላሉ።

ለአዲስ ማለዳ አስተያየታቸውን የሰጡት ሌላኛው በፌዴራል ፍርድ ቤቶች ጠበቃና የሕግ አማካሪ ኤፍሬም አብነትም በአቤል ሐሳብ ይስማማሉ። እንደ ኤፍሬም አገላለጽ የአዋጁ የጦር መሣሪያ ትርጓሜ ለተመሳሳይ ወንጀሎች የተለያየ ቅጣትን ሊያስከትል የሚችል ለትርጉም የተጋለጡ ነጥቦችን የያዘ ነው። ይህ ደግሞ የሕግን ወጥነት እና ፍትሐዊነት መርሆች የሚቃረን ነው ይላሉ።

ኤፍሬም እንደሚሉት የጦር መሣሪያ አስተዳደርና ቁጥጥር አዋጁ ከመውጣቱ በፊት ከወንጀል ሕጉ የጦር መሣሪያን የሚመለከቱ ኹለት አንቀጾች በቀር ሁሉን ዐቀፍ የሆነ የጦር መሣሪያ ሕግ ስላልነበረ ያንን የሸፈነ ነው። ከዚህ በተጨማሪም የዘመኑን የዘርፉን ሁኔታ ግንዛቤ ውስጥ በማስገባት ለስፖርት፣ ለአደን፣ ለቴአትር ዓይነት ተግባራት የሚውሉ የጦር መሣሪያዎችን በማካተት አዳዲስ ድንጋጌዎችን ይዞ መምጣቱ አዋጁ ከሸፈናቸው የዘርፉ ክፍተቶች መካከል ናቸው።

ተፈጻሚነቱ በኢትዮጵያ ውስጥ በሚገኝ ማንኛውም ሰው ላይ እንደሆነ የተደነገገው አዋጁ በአንቀጽ አምስት ጦር መሣሪያ ይዞ መገኘት የተከለከለባቸውን ሥፍራዎች ሲዘረዝር፣ የሕዝቡን ባህል እና ልማድ ግንዛቤ ውስጥ ያላስገቡ ድንጋጌዎች እንዳሉት ባለሙያዎቹ ይናገራሉ። እንደ ምሳሌም በተለይ የአርብቶ አደር እና የሰሜኑን የአገራችን አካባቢዎች ባህል ያነሳሉ።

በዚህ መሠረት እንደዚህ ያሉ የአዋጁ አንቀጾች ቢያንስ አሁን ባለው ነባራዊ የኅብረተሰቡ አኗኗርና ግንዛቤ ለመተግበር የማይቻሉ እንደሆነ ይጠቅሳሉ።

ሌላው የአዋጁ ለአፈጻጸም አስቸጋሪ የሆነ ክፍል ጦር መሣሪያ መሸጥን እና መነገድን በተረጎመበትና ከዚህ ጋር ተያይዞ በሚኖረው የቅጣት እርከን ላይ መሆኑን አቤል ይናገራሉ። አንድ ሰው ብዛት ያለው መሣሪያ ቢሸጥ በአዋጁ አንቀጽ 22 ንዑስ አንቀጽ 3 መሠረት እስከ ኻያ ዓመት በሚደርስ ጽኑ እስራት እና የገንዘብ ቅጣት እንደሚጣልበት አዋጁ ይገልጻል።

ቀደም ሲል የተጠቀሰው የብዛት ትርጉም ጉዳይ እንዳለ ሆኖ በዚሁ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ 1 ላይ እንደሚያመለክተው ደግሞ የጦር መሣሪያ የመነገድ ወንጀልን በሚመለከት የወንጀል ሕጉ አንቀጽ 481 የተጠበቀ መሆኑን ይደነግጋል። ይህ የወንጀል ሕጉ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ 4 በመሣሪያ ንግድ ላይ ተሰማርቶ የተገኘ ሰው ከአምስት እስከ አሥር ዓመት በሚደርስ እስራት እንደሚቀጣ ይገልጻል።

አሻሚው ጉዳይ ብዛት ያለው የጦር መሣሪያ መሸጥ እንደ መነገድ ካለመቆጠሩም በላይ የአዋጁ አንቀጽ 22 ንዑስ አንቀጽ 3 የቅጣት እርከን የተጋነነ መሆኑን ይናገራሉ። እንደ ጠበቃ አቤል አበበ አገላለጽ ለምሳሌ አንድ ሰው በአዋጁ ድንጋጌ መሠረት ሕገ ወጥ የሆነ ኹለት የጦር መሣሪያ በቤቱ አስቀምጦ ቢገኝ የሚዳኘው በዚህ አንቀጽ 22 ንዑስ አንቀጽ 3 መሠረት ይሆንና ቅጣቱ ከ8 እስከ 20 ዓመት በሚደርስ እስራትና ከመቶ እስከ ኹለት መቶ ሺሕ ብር ሲቀጣ፤ በዚህ አዋጅ እውቅና በተሰጠው የወንጀል ሕጉ አንቀጽ 481 ድንጋጌ መሠረት ደግሞ በጦር መሣሪያ ንግድ ላይ የተሰማራ ግለሰብ ግን ቢበዛ እስከ አሥር ዓመት በሚደርስ እስራት ብቻ እንደሚቀጣ ይገልጻሉ።

ከዚህ የተነሣ ሕገ ወጥ የጦር መሣሪያ በእጃቸው የተገኘ ሰዎች ቅጣቱ ቀለል ስለሚል መሣሪያውን የያዙት ነግደው ሊያተርፉበት መሆኑን በመናገር በአንጻራዊነት ወንጀሉ ከባድ ቅጣቱ ግን ቀላል በሆነው አንቀጽ ለመዳኘት የሚሹበት ጊዜ እንዳለ አቤል አበበ ይናገራሉ። በዚህ ላይ ያለው ክፍተት ነጋዴ በሚያስብለው ደረጃ በቀጣይነት በጦር መሣሪያ ንግድ ላይ የተሰማራ ሰው ቅጣት፣ ሕገ ወጥ የጦር መሣሪያዎችን በቤቱ አስቀምጦ ከተገኘ ሰው ቅጣት ማነሱ ነው ያሉት ጠበቃ አቤል አበበ፣ ይህ አሥር ዓመትም በራሱ ቀላል ቅጣት ባይሆንም ከሕግ ፍትሐዊነት፣ ተገማችነት እና መሰል ባህርያት ጋር የሚጣረስ ነው ይላሉ።

እነዚህ ክፍተቶች እንዴት ሊፈጠሩ ቻሉ ለሚለው ጥያቄ ኹለቱም ባለሙያዎች በማርቀቅ ሂደት ከሚመጣ የጥንቃቄ ጉድለት ሊሆን እንደሚችል ያምናሉ።

በጉዳዩ ላይ የአዋጁ ባለቤት የሆነውን የፍትሕ ሚኒስቴርን አስተያየት ለማካተት ብንጠይቅም፣ ወትሮ በአዋጆችና ሕግ ጉዳዮች ላይ ማብራርያ በመስጠት ግንዛቤ የመፍጠር ኃላፊነት ያለበት የሚኒስቴሩ ንቃተ ሕግ ቢሮ በዚህኛው አዋጅ ላይ ግን ማብራርያ ለመስጠት ፈቃደኛ አልሆነልንም። ከቢሮ ቢሮ ተንቀሳቅሰን መልስ ለማግኘት ባደረግነው ጥረት የሚኒስቴሩ የሕግ ጥናት፣ ማርቀቅ እና ማጠቃለል ዳይሬክተር ጄነራል አዲስ ጌትነት የጦር መሣሪያ አስተዳደርና ቁጥጥር አዋጁ ከሌሎች በሪፎርሙ ጊዜ ከወጡ ዘጠኝ አዋጆች ጋር ጥናት እየተደረገባቸው መሆኑን ገልጸው፣ ለጊዜው መስጠት የሚችሉት አስተያየትም ይኼው መሆኑን ጠቅሰዋል።


ቅጽ 4 ቁጥር 208 ጥቅምት 19 2015

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here