ተሰርቆ የተገኘው ሕጻን

0
1578

ሠሞኑን በማኅበራዊ ድረ ገፅ መነጋገሪያ ከነበሩ በርካታ ጉዳዮች መካከል የአንድ ሕጻን መጥፋትና መገኘት አንዱ ነበር። ሕጻኑ የጠፋው ከቤት ወጥቶ በራሱ ሄዶ ሳይሆን፣ አንዲት ለቤት ሠራተኛነት የተቀጠረች ሴት ሰርቃ ስለወሰደችው ነው።

ምስሉ በማኅበራዊ ድረ ገፅ ከተሰረቀ ቀን አንስቶ ሲዘዋወር የነበረው ሕጻንን ገና ከተቀጠረች አጭር ጊዜ የሆናት የቤት ሠራተኛ ሱቅ ይዤው ሊሂድ ብላ ይዛው ወጥታ በዛው ሰርቃው መጥፋቷ ነበር የተነገረው። ይህን አሳዛኝ ታሪክ የሰሙ የጊዜውን አስከፊነት፣ ሰውን ምን ያህል ለማመን ከባድ እንደሆነ እያመላከቱ ቤተሰቡን ሲያስተዛዝኑ ነበር።

የሕጻኑ መሰረቅ እረፍት የነሳቸው የማኅበረሰብ ክፍሎች ከዚህ ቀደም እንደሚሰማው ሞቶ እንዳይገኝ ስጋቱ ቢኖራቸውም ከማፈላለግ አልቦዘኑም ነበር። የቤተሰብም ልብ ስለማያርፍ በየተገኘው አጋጣሚ የተሰረቀው ልጅ ምስልም አብሮ ሲዟዟር ሰንብቷል።

ይህ የመሰረቅ ወሬ ከተሰራጨ ከ11 ቀናት በኋላ ግን መልካም ወሬ ተሰምቷል። ክፍለ ሃገር በፖሊስ ክትትል ተገኝቷል የሚል አስደሳች ዜና መሰራጨቱን ተከትሎ ብዙዎች በደስታ ምስሉን ደጋግመው ሲቀባበሉት ውለዋል። ለቤተሰቡ የሚሰጠው ደስታ ምን ያህል ከፍተኛ እንደሚሆን መገመት ቢቻልም፣ ኅብረተሰቡ ይህን ያህል በልጁ መገኘት መደሰቱ ለየት ያለ ግምትም አሰጥቶ ነበር።

እንደማኅበረሰብ ልጁ አይገኝ ይሆናል የሚለው ግምታችን ሚዛን በመድፋቱ ነው እንዲህ እጅግ ሰውን ያስደሰተው የሚል ሐሳብ ተደምጧል። ኅብረተሰቡ ስለ ሥነምግባር ምን ያህል ተስፋው እንደወረደ የሚያመላክት ነው ቢባልም፣ ይገኛል ብለው ያሰቡና ተስፋ ሳይቆርጡ የጠበቁ ደግሞ ቢያንስ ስለምግባራችን ያላቸው አመለካከት ጨርሶ እንዳልተበላሸ ማሳያ እንደሆኑ ያቀረቡም ነበሩ።

ያም ተባለ ይህ፣ የሕጻኑ መገኘት ያላስደሰተው የለም። ነገር ግን በራሱ ጠፍቶ የተገኘ ይመስል፣ ክፍለ አገር ተገኘ ብቻ ብሎ ከቤተሰቡ ጋር ሲቀላቀል የሚያሳይን ምስል ማሰራጨቱ በቂ አይደለም ያሉ ነበሩ።

ዋናው አስተማሪ መሆን ያለበት ልጅ ጠፍቶ መገኘት እንደሚችል ብቻ አይደለም ይላሉ። ይልቁንም፣ ሰርቃ የወሰደችው የቤት ሠራተኛ መስላ የተቀጠረችውና ይዛው የጠፋችው ሴት እጣ ፋንታ መታወቅ እንዳለበት የወተወቱ በርካታ ናቸው።

ለሌሎች ማስተማሪያ እንዲሆን እንዴት እንደተገኘም ሆነ ሰራቂዋ በምን ሁኔታ ላይ እንዳለችና በኋላም ምን ውሳኔ እንደተላለፈባት ይፋ መደረግ እንዳለበት አስተያየታቸውን የሰጡ አሉ። የተሰረቀውን ሕጻን ለማግኘት ምስሉን ማሰራጨቱ የጠቀመውን ያህል፣ የሰራቂዋንም ምስል አፈላልጎ እኩል በኩል አሰራጭቶ እንድትያዝ ማድረጉ ምን ያህል ጠቃሚ እንደሚሆን ማሳወቅ ያስፈልጋል። እንዲህ ዓይነት ወንጀሎች ከተፈፀሙ በኋላ መረባረቡ አስፈላጊ ቢሆንም፣ በተመሳሳይ ደግሞ እንዳይፈፀምም መተጋገዝ ይገባል።


ቅጽ 4 ቁጥር 208 ጥቅምት 19 2015

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here