“ልርዳ ብለሽ መጥተሽ የማይቀበልሽ ያለበት አገር እዚህ ነው”

0
1965

ፍሬሕይወት ደርሶ ይባላሉ። ትውልዳቸው ጎንደር ሲሆን ገና የ16 ዓመት አዳጊ እያሉ ነው ከአገር ወጥተው መኖሪያቸውን በአሜሪካ ያደረጉት። በውጪ አገር ቆይታቸውም የነርሲንግ ትምህርትን የተከታተሉ ሲሆን፣ በካንሰር እና ኤችአይቪ ዙሪያ ከ30 ዓመት በላይ በተለያየ መልክ ሠርተዋል፣ አገራቸውንም አገልግለዋል።

ከ10 ዓመታት በፊት በእድሜ ታናሻቸው የምትሆን እህታቸው ዓለምፀሐይን በጡት ካንሰር የተነሳ ማጣታቸው በጉዳዩ ላይ የበለጠ ትኩረት እንዲሰጡ አድርጓቸዋል። ይልቁንም በኢትዮጵያ በጡት ካንሰር ዙሪያ ያለው ግንዛቤ ማነስና የእህታቸውን ጤና በሚከታተሉበት ጊዜ ሌሎች ሴቶች ኢትዮጵያዊያት የሚጋፈጡትን ችግር መመልከት ችለዋል።

ከዛም አልፈው እህታቸው በበሽታው የተነሳ ሕይወታቸው ሲያልፍ፣ ‹በእርሷ ሥም ሌሎች መረዳት አለባቸው› በማለት ዓለምፀሐይ የጡት ካንሰር ፋውንዴሽንን መሠረቱ። በዚህም ለብዙ ሴቶች ለመድረስ ግብ ይዘው ተነሱ። ይኸው በአትላንታ ጆርጂያ የተመሠረተው ፋውንዴሽን አዲስ አበባ ላይ ከኹለት ዓመት በፊት ነበር ፒነክ ሐውስን በመክፈት እንቅስቃሴውን የጀመረው።

ፋውንዴሽኑ ‹ፒንክ ሐውስስ በሚለውና በርካታ የጡት እንዲሁም የማሕጸን ካንሰር ሕሙማን ሴቶችን በተለያየ መልክ እያስተናገደ ይገኛል። በየዓመቱም የእግር ጉዞ ዝግጅት የሚያዘጋጅ ሲሆን፣ ዘንድሮም ለሦስተኛ ጊዜ የፊታችን ጥምቅት 20/2015 ይካሄዳል። ይህንን ዝግጅት ብሎም ፋውንዴሽኑ እየሰጠ ያለውን አገልግሎት በሚመለከት የአዲስ ማለዳዋ ሊድያ ተስፋዬ ከፋውንዴሽኑ መሥራች ፍሬሕይወት ደርሶ ጋር ተከታዩን ቆይታ አድርገዋል።

‹ፒንክ ሀውስ› ሥሙን እንዴትና በምን የተነሳ አገኘ?

እንደሚታወቀው የጡት ካንሰርን የሚገልጸው ምልክት ሮዝ (ፒንክ) ቀለም ያለው ሪበን ነው። ልክ ቀይ ሪበን የኤችአይቪ እንደሆነ ሁሉ ማለት ነው።

ከዛ ወደ ፒንክ ሐውስ ስንመጣ፣ ቤቱ ያንን እንዲወክልልን ለማድረግ ሮዝ ቀለም ቀብተነዋል። እናም ሥሙን ፒንክ ሐውስ ያልነው የጡት ካንሰር ታማሚ ሴቶች መጠለያ ማለት ነው፤ በእኛ ትርጓሜ። እንዳልኩት ግን በዓለም ዐቀፍ ደረጃ ሮዝ (ፒንክ) ሪበን የጡት ካንሰር መለያና ግንዛቤ መስጫ ነው።

ይህን መጠለያ ለመመሥረት መነሻ የሆናችሁ ምን ነበር? በመጠለያውስ ምን ምን አገልግሎቶች ይሰጣሉ?

ዓለምፀሐይ የጡት ካንሰር ፋውንዴሽን ሲመሠረት፣ አንደኛም ኹለተኛና ሦስተኛም ዓላማው ግንዛቤ መፍጠር፣ ሰዎችን ማስተማር ነው። ሌላው ደግሞ ሰዎች የሚጠለሉበትን ቤት ማዘጋጀት ነው።

ከ10 ዓመት በፊት ስንጀምር አሁን እንዳለው ይሆናል ብለን አስበን አልነበረም። ግን የሆነ ቤት ያስፈልጋል፤ ያ ቤት ደግሞ ሰዎች የሚመጡና የሚማማሩበት፣ የምክር አገልግሎት የሚያገኙበት፣ እርስ በእርሳቸው የሚነጋገሩበት ይሆናል ብለን ነበር ያሰብነው። በኋላ ስናሻሽለው፣ ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ጨረር (የጨረር ሕክምና) እየጠበቁ በረንዳ ላይ፣ ሳሩ ላይ ወይም ዛፉ ስር የሚተኙ ሴቶችን ስናይ ነው እንደመጠለያ ይሁን ብለን የወሰንነው።

ይህም ከገጠር የሚመጡ እህቶቻችን ዛፍ ስር የሚተኙት፣ በረንዳ ላይ በቀን 300 ብር እየከፈሉ፣ ሌሊት ተኝተው ደግሞ ገንዘባቸውን ሲወስዱባቸው፣ አንዳንዴም መኝታ ሲያጡና ወደመጡበት ተመልሰው ሕክምና ሳያገኙ ሕይወታቸው ሲያልፍ፤ ያንን ሁሉ ተመለከትን። እናም ፍላጎቱ በጣም ከፍተኛ መሆኑን ስናውቅ ነው ቤት ተከራይተን (በ40 ሺሕ ብር) በስድሰት አልጋ የጀመርነው።

ከዛም በሦስት ወር ውስጥ፣ ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ከጡት አልፎ የማሕጸን ጫፍ ካንሰር ሕሙማንን ተቀበሉልን እርዱልን፤ ምክንያቱም እነርሱም ማረፊያ በማጣት እየተመለሱ እየሞቱ ነውና አለን። እሺ ነው ያልናቸው። እናም የጡት እና የማሕጸንን እኩል መቀበል ጀመርን። የአልጋ ቁጥርም ጨመርን። አሁን በአንድ ጊዜ 31 አስታማሚና ታማሚን እንቀበላለን። በድምሩም ከአራት ሺሕ ሰው በላይ ረድተናል።

ሕሙማኑ ይመጣሉ፣ ሕክምናቸውን እስኪጨርሱ ይቆያሉ። ቅዳሜ በየሳምንቱ የማማከር አገልግሎት አለ። የሥነልቦና እና ሥነ አእምሮ ባለሞያዎችና ሐኪሞች ይመጣሉ። የትዳር ማማከር ድረስ ይሰጣቸዋል። ምክንያቱም፣ የጡትና የማሕጸን ካንሰር ትዳር ላይ በጣም ተጽእኖ አለው። ገንዘብ ላይ ብቻ ሳይሆን ባልና ሚስት በጣም የሚዳከሙበትና እስከ መለያየት የሚፈተኑበት በሽታ ነው፤ በተለይ ገጠር። ከገጠር ባል እርሻውን ወይም ንግዱን ትቶ ነው የሚመጣው፣ እናት ዘጠኝ ወር ልጇን ትታ፣ ሦስት አራት ልጆቿን ለጎረቤት ሰጥታ ትመጣለች።

ይህ ሁሉ የምክክር አገልግሎት ሊሰጥበት ይገባል፤ አስታማሚዎችም ራሱ ይህን አገልግሎት ያገኛሉ። ትምህርታቸውን ትተው ለማስታመም የሚመጡ ልጆችና አዳጊዎች አሉ። እንዲህ ያሉ ልጆችንም ለብቻ የምክክር አገልግሎት እንዲያገኙ ይደረጋል።

ከዛ ውጪ አሁን ጎንደር ላይ ኹለተኛ ቤት ከፍተናል። የጎንደሩ የአልጋው ቁጥር ጥቂት ነው፣ ቤቷም አነስ ያለች ናት። አሁን ግን ኹለት ሺሕ ካሬ ሜትር ቦታ ሰጥተውናል። በ2015 መጨረሻ ትልቅ ፒንክ ሐውስ ሠርተን የራሳችን ቤት እንገባለን ብዬ አስባለሁ፤ ከእግዚአብሔር ጋር። እስከዛ ግን የጎንደር ዩኒቨርሲቲ የቤት ኪራይ እየከፈለልን እዛ ተቀምጠናል።

በዛም ልክ እንደ አዲስ አበባ ሁሉ ከገጠር ያሉ እህቶች ሲመጡ መጠለያ የላቸውምና ማረፊያ ይሆናቸዋል፤ አንደኛው እሱ ነው። እንደገና የሴቶችና የሕጻናት ቢሮው በከተማዋ ያሉ ስድስት ክፍለ ከተማዎች ላይ የሚያስተምሩ ሰዎች መርጠውልን፣ በየሳምንቱ ሥልጠና እየሰጠናቸው ሄደው ማኅበረሰቡን እንዲያስምሩ እያደረግን ነው። ዶክተሮችና ነርሶች ደግሞ በጡት ካንሰር ላይ ያለንን ግንዛቤና እውቀት አዳብሩልን ብለው ጠይቀውን ትምህርቶችን ሰጥተናል።

ከዛው ባለፈ ጎንደር ዩኒቨርሲቲ 400 አባላት ያለው የሴት መምህራን ማኅበር አለ። ከእነሱም ፈቃደኛ ለሆኑና ፍላጎት ላላቸው ሥልጠና ሰጥተናል። እናም እነዚህ ሁሉ ከፒንክ ሐውስ አገልግሎት ባለፈ የምንሠራቸው ሥራዎች ናቸው።

ብዙውን ጊዜ እንዲህ ያሉ እንቅስቃሴዎች በከተማ ብቻ በተለይም በአዲስ አበባ ተወስነው ነው የሚታዩት። እናንተስ ይህን በተመለከተ ምን አስተዋላችሁ?

በጣም ትክክል ነሽ! አሁን ብቻ ሳይሆን ከዚህ ቀደም በኤችአይቪ ዙሪያ የአሠልጣኞች ሥልጠና ትምህርት ነበርና ያንን ለማስተማር ስንመጣ፣ ሁሉ ነገር አዲስ አበባ ነው፤ ከዛ አለፍ ሲል አዳማ ነው። ሁሉም ነገር የሚመጣው ወደ ዋናው ከተማ ነው። ክፍለ አገር ያሉ ሴቶች ተረስተዋል፣ ክፍለ አገር ያለ ሰው ተረስቷል። እንደሚታወቀው ከኢትዮጵያ 70 በመቶ በላይ ሕዝብ ገጠር ነው የሚኖረው፣ አርሶአደር ነው። ነገር ግን አብዛኛው ሕዝብ የሚኖርበት ቦታ ሄዶ የመሥራት ነገሩ የጠበበ ነው። ለዚህም ነው የክፍለ አገር ሴቶች መጥተው እዚህ (አዲስ አበባ) የሚታከሙት። እነሱም የነቁ፣ ገንዘብ ያላቸውና ባሎቻቸው ፈቃደኛ ሆነው ‹አሞሻል፣ ሐኪም ቤት ልውሰድሽ› ብለው የሚያመጧቸው ናቸው።

ባሎቻቸው ያልፈቀዱላቸው አይመጡም፣ ከቤታቸው አይወጡም። ፀበል አልያም የባህል መድኃኒት እያሉ ነው የሚቆዩት፤ እንደዛ እንደሆነ የመጡት ይነግሩናል። ባሎቻቸው ስላልፈቀዱ፣ አቅም ስለሌላቸው፣ እርሻ ትተው መምጣት ስለማይችሉ፣ ብቻቸውን ወደ ከተማ መምጣት ስለማይችሉ ተደብቀው እዛው ይሞታሉ። የክፍለ አገሩ የከፋ የሚሆነው፣ እንደ ከተማ ሴቶች እድል የተመቻቸላቸው አይደሉም። ባልሽ እንኳ እንቢ ቢልሽ፣ ታክሲ ጠርተሽ ወይም ጓደኛሽን ጠርተሽ እዚህ ከተማ ትታከሚያለሽ።

ገጠር ግን እንደዛ ማድረግ አይቻልም፣ ባል መፍቀድ አለበት። ባል ከሌለ የሆነ የደረሰ ልጅ ወይም የሆነ ቤተሰብ/እህት ወንድም መኖር አለበት። እባክህ ውሰደኝ የምትለው ሰው ያስፈልጋታል። ያም ሰው አንዴ ሊወስዳት ይችላል፤ ኹለተኛ ጊዜ ግን አያመጣትም። ምክንያቱም የሚቀመጥበት ቦታ የለውም፣ ምግቡ ሆቴሉ ውድ ነው፤ መድኃኒቱም እንደዛው። ስለዛ ይሰለቻሉ። ካንሰር አለ ሲባል ደግሞ ነገ ለምሞት ነገር ገንዘቡን ልጆቼ ቢያድጉብት ይሻላል ይላሉ። እኔ እንደዛ ያለች እናት ገጥማኛለች። እኔ መሞቴ ካልቀረ ለምን ገንዘቤን ጨርሳለሁ ያለች፤ ባለቤቷም እንደዛ ያላት።

እና ከከተማ ውጪ በገጠር የሚሠራ ሥራ በጣም አስፈላጊ ነው። አስፈላጊነቱንም ሁሉም ያውቃል፤ ግን ለመሥራት ደፍሮ የሚሄድ የለም። ሁሉም ነገር ከተማ ውስጥ ነው።

ጎንደር የዛሬ ኹለት ዓመት የእግር ጉዞ እናደርጋለን ብለን ስንሄድ፣ ከጎንደር ዩኒቨርሲቲ ዶክተር አስራት ‹ይህኮ በጣም የምንፈልገው ነው። ለምንድን ነው ሁሉም ነገር መሀል ከተማ ብቻ የሚሆነው። ሴቶቻችን ከሕክምና እየተመለሱ እየሞቱብን፤ ዶክተሮችም እየተቸገሩ ነው› አሉን።

ካንሰር አለብሽ ሲባሉ ለእነሱ አንደኛ የሞት ፍርድ እንደመስማት ነው። ኹለተኛ ሕክምናው መመላለስ አለው ሲባሉና የሚወስደው ጊዜ ሲነገራቸው፣ ‹አይ ባሌ እርሻውን ትቶ ሊመጣ ነው? ልጄን ለማን ትቼ ነው የምመጣው? መጥቼ የት አርፋለሁ?› ብለው ተመርምረው በሽታውን አውቀው ብቻ የሚሄዱና የማይመለሱ አሉ። ዶክተሮችም ‹እባካችሁ ፈልጉልን፣ ቀጠሮዋ ቢደርስም ተመልሳ ያልመጣች ሴት አለች› ብለው ይጠይቁናል።

እናም የእኛ እዛ መሄድ አንደኛ እዛ ያሉትን ለመጥቀም ነው። አዲስ አበባ ለጨረር ሂዱ ሲባሉ ‹መሀል አገር አንሄድም። ምክንያቱም ቋንቋችንን አይረዱም። የት እንገባለን፣ ገንዘብስ የት እናገኛለን!› ይሉና ይቀራሉ፤ እዚህ መዳን ሲችሉ። አሁን ያደረግነው ጎንደር ያሉ ነርሶችና አዲስ አበባ ያሉት ነርሶች ተነጋግረው እዚህ እንዲመጡ ይደረጋል። እኛም በዚህ ላይ አግዘን መጥተው ሕክምና እንዲከታተሉ እናደርጋለን።

ከአዲስ አበባ ቀጥሎ ጎንደር ከተማ የተመረጠችበት የተለየ ምክንያት ይኖር ይሆን?

ድርጅቱን ሲያውቁት ባህርዳር እንዲሁም ጅማ ኑልን ብለው ጠይቀውናል። ቀጣይ ከተሞች እነሱ ናቸው። ጎንደርን የመረጥንበት በእርግጥ ምክንያት አለ። እህቴ (ዓለምፀሐይ) ተወልዳ ያደገችው፣ በኋላም የኖረችውና ታምማ ያረፈችው ጎንደር ነው። እኔ ብወለድበትም ጎንደር አይደለም ያደግሁት፤ እና ግን ብዙ ችግር እንዳለ፣ ብዙ ሴቶች እያለቁ እንደሆነ ነግራኛለች። እኛ የእግር ጉዞም ያደረግሁት ግንዛቤ እንዲሰጥ እንጂ ፒንክ ሐውስ ለመክፈት እቅድ አልነበረም። ከእግር ጉዞው በኋላ ግን ዶክተሩ (ዶክተር አስራት) ሲያነጋግረኝ፣ ከመጣችሁ እኛ እንረዳችኋለን አለን። እሺ ብለን መጣን። ከዛም ወዲያው ነው ቤት የፈለግነው። ቤት አገኘን፤ በስድስት አልጋ ጀመርን። ፍራሽና አልጋ የሰጠን ዩኒቨርሲቲው ነው። ብርድ ልብስና የቤት እቃ ብቻ ነው የገዛነው። የቤት ኪራይም እስከ አሁን አንከፍልም፤ እነሱ (ዩኒቨርሲቲው) ናቸው የሚከፍሉት።

በዚህ ሥራ በነበራችሁ ቆይታ የግንዛቤ ችግር ያለው ከበሽታው መንስኤ ላይ ነው? ከሕክምናው ጋር ይያያዛል ወይስ አይድንም የሚለው አመለካከት ነው?

ካለፉት አራት ዓመታት ወዲህ ጥሩ ለውጦች ዐይተናል። የጡት ካንሰር ምንድን ነው? ምልክቶቹ ምንድናቸው? ለምሳሌ ከጡት ደም የቀላቀለ ፈሳሽ ሲወጣ፣ ወደ ውስጥ ስርጉድ ያለ ነገር፣ የጡት ጫፍ ወደ ውስጥ ሲገባ፣ ጡት ሳይታሰብ ትልቅ ሲሆን፣ የጡት ጫፍ ቀይ ሲሆን የመሳሰሉ ምልክቶችን ብዙዎች አያውቁም። ብብት ስር ያበጠ ነገርም እንደዛው።

የእኔ እህት ብብቷ ስር እብጠት ሲኖር፣ በአጋጣሚ የሌላ እህታችንን ሰርግ ታዘጋጅ ነበርና፣ ‹የሰርጉ ሥራ ነው ያሳመመኝ› ብላ ቆየችበት። ግን ካንሰር ነው።

አንዳንዶች ደግሞ ካንሰር ሲባል ገዳይ ነው፣ መቃብርሽን አዘጋጂ ይላሉ። እኔ ካንሰር ከያዘኝ አራት ዓመቴ ነው። የእኔ ጓደኞችና እኔ ጋር የሚሠሩ ለ16፣14፣7 ዓመት አሉ። ይህን ሕዝቡ ማወቅ አለበት። ካንሰር የያዘው ሰው ሁሉ አይሞትም። የሚድነው ግን ስናውቀው ነው።

አንዳንዶች ካንሰር አለባችሁ ሲባል ሳትነካኪ ፀበል ሂጂ ወይም የባህል ነገር አድርጊ ይላሉ። እኔም አሜሪካ ሆኜ ይህን አድርጊ ነው የተባልኩት። እኔ በዚህ ሥራ ከ30 ዓመት በላይ ቆይቻለሁ። በእግዚአብሔር አምናለሁ፤ ግን ቀዶ ጥገና ሕክምናዬን ከጨረስኩኝ በኋላ ተጨማሪ ፀበል ሄድኩኝ።

አሁን ሰውነታችሁን ዕዩ። በጠዋት ፊታችንን ነው በመስታወት የምናየው፣ ግን ጡታችንንም እንይ። ለውጥ ስናይ፣ የጡት መጠን ከፍተኛ ለውጥ ሲያሳይ፣ እብጠት ሲኖር ወዘተ ማወቅ። ይህን ካወቅሽ በኋላ እንደሚድን ግንዛቤ ይዞ ወደ ሐኪም ጋር መሄድ፤ የሕክምናውን የጎንዮሽ ጉዳት ተረድቶ ሕክምናን መከታተል ተገቢ ነው። ይህንንም ማወቅ ያስፈልጋል።

የፊታችን እሁድ የምታደርጉት የጎዳና ላይ የእግር ጉዞ ለሦስተኛ ጊዜ የሚካሄድ ነው። ይህን የእግር ጉዞ እንድትቀጥሉበት ያስቻላችሁ ያገኛችሁት ጥሩ ውጤት አለ?

ከሦስት ዓመት በፊት በመጀመሪያው 700 የሚሆኑ ሰዎች ነበር የተሳተፉት፤ ስለካንሰር በሰፊው አይወራም ነበር። ከዛ በኋላ ‹ሕዝቡ እንዲህ ያለ ነገር አለ እንዴ?› አለ። ያዘጋጁት ሰዎች ራሳቸው፣ ደኅና መረዳት አላቸው የሚባሉ ሰዎች ናቸው። ነገር ግን ማሞግራም ምን እንደሆነ ወይም በማሞግራም ምርመራ አድርገው አያውቁም። ጡታቸውን በየወሩ መፈተሽ እንዳለባቸውም አያውቁም። ካንሰርን እንደጦር ነበር የሚፈሩት። አሁን ያላቸው ግንዛቤ ግን እንደዛ አይደለም።

ከሕዝብ ደግሞ ያገኘነው ጥቅምት ወር ምንድን ነው የሚለውን፣ እየደወሉ ‹ጡቴ ላይ እብጠት አለ፣ እንምጣ እዩልኝ› የሚለው ቁጥር በዛ። ፒንክ ሐውስ ላይ ምን እንርዳ የሚሉም መጥተዋል። የእግር ጉዞውን በተመለከተ በፊትና አሁን ብለን ለውጡን አጥንተናል። ሕዝቡ ላይ ላለው ግን ጠቅለል ያለ ነገር ነው መናገር የምትችይው። ምክንያቱም ‹ሲጀመር እንዲህ ነበር፣ አሁን ይህን ተምረዋል› የምትይው አይደለም። እናም በመጀመሪያው ጠቅለል ያለ ግንዛቤ ነበር የተፈጠረው።

በኹለተኛው ኹለት ሺሕ በላይ ሰው ነበር የተሳተፈው። ብዙ የሚድያ ሽፋን ነበረው። ብዙ ሰው ከየክፍለ አገር ይደውል ነበር። እንምጣ የሚሉንም ብዙ ነበሩ። ገጠር ያሉ እናቶች ሰምተው፣ አውቀው ንገሩን ማለታቸው፤ ይህ ለእኛ ትልቅ ለውጥ ነው። እና በእግር ጉዞው የተሳታፊ ቁጥርም ጨምሯል። ጥሩ ነው ብለው ሲያስቡና አንድ ነገር ሲገነዘቡ አይደለ የሚጨምረው? ይህ የቁጥር መጨመርም ለውጣችንን የምንለካበት ነው።

ሦስተኛ ሩጫ ስንል፣ ባለፈው ዓመት የሮጡ ሰዎች ‹ዘንድሮ የት ነው ቲሸርት የሚሸጠው?› ብለው መደወላቸው፤ አንዳንድ ከተሞች ‹እኛም ጋር ኑና አዘጋጁ› ብለው መጠየቃቸው ወዘተ ሊጠቀስ ይችላል። ከዛ ውጪ ዶክተሮች ጋር ያለ ግንዛቤ ከፍተኛ ነው። እየደወሉ ‹በምን ልትረዱን ትችላላችሁ? ሰዎች እንልካለን የምክር አገልግሎት እንዲያገኙ አድርጉልን› ይላሉ። ይህ ሁሉ እንዲሆን ያስቻለው የእግር ጉዞው ነው።

ከሌሎች በተለያየ የካንሰር ሕመም እና ግንዛቤ መስጠት ላይ ከሚሠሩ ማኅበራት ጋር ያላችሁ ግንኙነት ምን ይመስላል? ከመንግሥት በኩልስ የምታገኙት ድጋፍ?

ቤት ከማግኘት ጀምሮ ከባድ ነው። ክፍለ አገር ትንሽ ቀለል ይላል። ጎጃም፣ ባህርዳር እና ጅማ ‹ኑ እንጂ እኛ እናዘጋጃለን!› ብለውናል፤ እንደጎንደሩ።

ከሴቶችና ሕጻናት ቢሮ እንዲሁም ከሚኒስቴሩ ጋር እንሠራለን። ግን እንዲገኙልን ስንል የሥራ ኃላፊዎች አይገኙም። እንሠራለን፣ ምን እናግዝ ይላሉ፤ ሐሳቡን ይደግፋሉ፣ የእኛን ሥራ ነው የምትሠሩት ይሉናል። ግን ይህ ነው የምትይው ድጋፍ የለም። የድጋፍ ደብዳቤ ለመጻፍ ራሱ ያመላልሱናል።

ልርዳ ብለሽ መጥተሽ የማይቀበልሽ ያለበት አገር እዚህ ነው። አሁን ትንሽ ለውጥ እያየን ነው። ከሌላ አፍሪካ አገር አኳያ እንኳ ብታይው፣ እርጂኝ ብለው እንኳ ለድርጅትሽና ለሥራሽ ክብር አላቸው። እዚህ እኛ አገር ግን እንደዛ አይደለም። ወደፊት ግንዛቤ ሲኖር ይቀየራል ብዬ አስባለሁ።

ከማኅበራት ጋር በተገናኘ፤ እኔም የሚገርመኝ ያ ነው። ውጪ ያሉ ድርጅቶች ጋር (ካንሰር ላይ የሚሠሩ ባይሆኑም) አብረን እንሠራን። ባለፈው ለምሳሌ ሩጫ ስናዘጋጅ ሁሉም መጥተው፣ በገንዘብም በጉልበትም ተባብረውን ነው። እነሱ ዝግጅት ሲኖራቸውም እኛ አብረን እንሄዳለን።

ኢትዮጵያ ግን ትንሽ ለየት ያለ ነው። ለእኔ ለእኔ የሚል፣ የእኔ ይበልጣል የሚል ነገር ዐይቻለሁ። አንድ ኹለቱን ቀርቤ አውርቻለሁ፤ አብረን እንሠራለን ተባብለናል፤ በምን እንሠራለን የሚለውን ገና አልተወያየንም። እኛ እንደ ድርጅት የጤና ሚኒስቴር ሄደን ‹አንድ የካንሰር ኮንሶርትየም ቢፈጠር። በዛም ሁሉንም በአንድ ጥላ ስር አድርጋችሁ ማኅበረሰቡን በጋራ እንርዳ› ብለን የኹለት ቀን ስብሰባ አድርገን ነበር። እነሱም በጣም ጥሩ ሐሳብ ነው ያሉት። ኹለት ስብሰባ ብቻ አድርገን ቀረ። ግን ተስፋ አልቆርጥም፤ ተመልሼ መሄዴ አይቀርም። ውጤታማ ሥራ መሥራት የሚቻለው አንድ ላይ መሆን ሲቻል ነው።

የእኔ ፍላጎት እዚህም አገር ተቀመጥኩ እዛ አገር፣ እኔም ሠራሁት ሌላ ሰው ይሥራው ዋናው ሴቶች እንዲረዱ ነው። ሴቶች ከመሞት ይዳኑ፣ ልጆቻቸውን ያሳድጉ ነው። ያንን ደግሞ አብረን ብንሠራ ጥሩ ነው፣ አቅማችን እንይ፣ ሳንጠላለፍና ሥራዎችን ሳንደጋግም እንሥራ መባባል አለብን። ግን ኢትዮጵያዊያን ገና ነን፣ እዛ ደረጃ አልደረስንም።

የሚያስተላልፉት መልዕክት ካለዎት እንውሰድ?

ሴቶች ሰውነታችሁን እወቁ። የራሳችሁ አምባሳደር ሁኑ። ምልክቶችን ተረዱ፣ ቶሎ ወደ ሕክምና ሂዱ፣ ከዶክተሮች ጋር ተከራከሩ ‹ይሄ ነገር ለእኔ አዲስ ነው፣ ቀላል ነው ብላችሁ አትዩት› በሏቸው። አንደኛው ዶክተር ቀላል ነው ሲል ኹለተኛው ጋር ሂዱ። ሰውነታችንን የምናወቀው እኛ ነን፣ እነሱ እኛ ከምንነግራቸው ነው የሚያውቁት። እንዲሁም ሴቶች ብቁ መሆንና መረጃ ማግኘት አለባቸው።

ሌላው የአዲስ አበባንና የኢትዮጵያን ሕዝብ ማመስገን እፈልጋለሁ። የተወሰኑ ሰዎች ቢሆንም መጥተው የሚረዱልንና ያዩልን እግዚአብሔር ይስጥልን። ያልመጡትም ግንዛቤ ስላጠራቸው ይሆናል፤ እንደገና እንሞክራለን።

የእኛን ሕልም እውን ያደረጉልን፣ ከእኛ ጋር ሆነው የሚያዘጋጁት የድሮ የሊሴ ተማሪዎች ናቸው። ይህን የእግር ጉዞ ለሦስተኛ ጊዜ ከእኛ ጋር ሆነው የሚያዘጋጁት እነሱ ናቸው። አቅም፣ እውቀትና ኔትወርክም ስላላቸው ለእኛ ከብዶን የነበረው ለእነሱ ቀላል ነበር። ሦስተኛ ዓመት እንድንደርስ ከእኛ ጋር ሆነው ገንዘብም በመርዳት፣ ሩጫውን በማዘጋጀት፣ ጎናችሁ አለን በማለት፣ ከአዲስ ሰው ጋር በማስተዋወቅ አግዘውናል። ጥቂት ሰዎች ቢሆንም በማስተባበር ላይ የሚታዩት፣ ከጀርባ ሺሕ ሰው አለና የረዱንን እናመሠግናለን። ከዛም እናንተን ጨምሮ ሚድያውን እናመሠግናለን።


ቅጽ 4 ቁጥር 208 ጥቅምት 19 2015

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here