በአዲሱ ቤተ መንግሥት ግንባታ ዙሪያ የሚገኙ ነዋሪዎች ቤታችን ያለማስጠንቀቂያ እየፈረሰብን ነው አሉ

0
2321

“የጫካ ፕሮጀክት” ከተሰኘው የአዲሱ ቤተ መንግሥት ግንባታ ጋር በተገናኘ፣ በዙሪያው የሚኖሩ በርካታ ዜጎች መኖሪያ ቤታችን በድንገት እየፈረሰብን ነው ሲሉ ቅሬታቸውን ለአዲስ ማለዳ ገለጹ።

በዚህም ከፈረንሳይ እስከ የካ አባዶ ባለው ቦታ የሚገኙ የመዲናዋ ነዋሪዎች እስካሁን 100 የሚጠጉ አባዎራዎች በድንገት ቤታቸውን እንደፈረሰ ተናግረዋል። ከሰሞኑ በድንገት ቤታቸው የፈረሰባቸው የአካባቢው ነዋሪዎች ቤታቸው የፈረሰው ያለ ምንም ቅድመ ማስጠንቀቂያ ነው ብለዋል።

በአካባቢው የአየር ላይ ካርታ አለን የሚሉ ባለቤቶች፣ “ቤታችን መቼ እንደሚያፈርስ ስንጠይቅ፣ አንናገርም በሌሊት መጥተን ነው የምናፈርሰው” የሚል ምላሽ ከመንግሥት አካላት እንደደረሳቸው ተናግረዋል።

በየካ ክፍለ ከተማ ከፈረንሳይ እስከ የካ አባዶ ባለው ቦታ፣ ለጊዜው ቤታቸው ያልፈረሰባቸው የአካባቢው ነዋሪዎች “ቤታችን በድንገት ይፈርሳል በሚል” ከፍተኛ ስጋት ውስጥ ነን ሲሉ ጠቁመዋል።

“የጫካ ፕሮጀክት” የተባለው የቤተ መንግሥት ግንባታ ይፋ ሲደረግ፣ የጠቅላይ ሚኒስቴር ጽሕፈት ቤት እንዲሁም ከክፍለ ከተማው ጋር ተወያይተን መግባባት ላይ ተደርሶ የነበረ ቢሆንም፣ አሁን እየተደረገ ያለው ግን ከዚህ ውጭ ነው ሲሉም ቅሬታ አቅራቢዎች ተናግረዋል። “እኛ እንደማንፈናቀል ይልቅስ ባለንበት እንደምንለማ ነበር የተነገረን፣ ይሁን እንጂ በድንገት መጥተው ነው ቤታችን እያፈረሱ ሜዳ ላይ እየበተኑን ያሉት” ሲሉ ቤታቸው በድንገት የፈረሰባቸቨው ሰዎች ተናግረዋል።

ፕሮጀክቱ ወደ ተግባር ሲገባ ደረጃ በደረጃ ትነሳላችሁ በሚል የእያንዳንዳችን ቤት ተለክቶ፣ ንብረታችንም፣ ተቆጥሮ ኹሉም ነገር ተመዝግቦ ነበር የሚሉት ነዋሪዎቹ፣ ይህ ሲሆን በመንግሥት ተስፋ አድርገን እየኖርን ባለበት ነው ድንገት ቤታችን እየፈረሰ ያለው የሚል ቅሬታቸውን አሰምተዋል።

በዚህ ሁኔታ ልጆቻችንን እንዴት ነው የምናስተምረው ያሉት ነዋሪዎች፣ ቤታችንንስ በአንዴ ማፍረስ ከመንግሥት የሚጠበቅ ተግባር ነው ወይ ሲሉ ጠይቀዋል።

የፖሊስ አባላት እንዲሁም የወረዳና ክፍለ ከተማ አካላት የተካተቱበት ቤታችንን የሚያፈርስ ግብረ ኃይል አለ ሲሉም ነዋሪዎቹ ጠቁመዋል። አፍራሽ ግብረ ኃይል የተባሉት አካላት በጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ቀድሞ የተገባልንን ቃል ስንነግራቸው አናውቅም የሚል ምላሽ ከመስጠት ውጭ ሌላ ምክንያት አይሰጡንም ብለዋል።

በፕሮጀክቱ የተነሳ ቤታችን እንደማይፈርስና እንደማንፈናቀል ሰብስበው ሲያወያዩን ወደነበሩት የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ሚኒስትር ዴኤታ ዓለምፀሐይ ጳውሎስ ኮሚቴ አዋቅርን ስንልክም፣ “የሉም” በሚል ምክንያት ችግራችን እየተሰማ አይደለም ብለዋል።

ለተለያዩ የመንግሥት አካላት ቅሬታችንን ስናቀርብ አንዳንዶች አናውቅም ይሉናል የሚሉት ነዋሪዎቹ፣ ‹‹ፕሮጀክቱን እኛም እንደግፈዋለን። ግን ሕዝብ የማይጎዳ እንዲሁም ልጆቻችንን ከትምህርት ቤት የማያስቀር ሊሆን ይገባል›› ብለዋል።

‹‹እኛም ዜጋ ነን›› የሚሉት ቤታቸው የፈረሰባቸው ነዋሪዎች፣ ቤታችን የጨረቃ ነው ከተባለ መፍረስ የነበረበት አሁን በድንገት ሳይሆን ከጅምሩ ነበር ይላሉ። መብራትና ውሃ የመሳሰሉ መሠረተ ልማቶችንም መንግሥት ሲያቀርብልን ነበር ያሉት ነዋሪዎቹ፣ በቦታው ላይ ከ20 ዓመት በላይ የኖረ ብዙ አባወራ መኖሩን አስታውሰዋል። ቤታቸው በድንገት የፈረሰባቸው ነዋሪዎች ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታ ቤት አልባ መሆናቸው ለከፋ ችግር እንዳጋለጣቸው ተናግረዋል።

ነዋሪዎቹ የጠቅላይ ሚኒስቴር ፅህፈት ቤት በፕሮጀክቱ የተነሳ ጉዳት እንደማይደርስባቸው ቃል እንደገባላቸው እና ጉዳዩም በቀጥታ እንደሚመለከተው ቢገልጹም፣ የፅህፈት ቤቱ ሚኒስቴር ዴኤታ አለምጸሐይ ጳውሎስ “ስለዚህ ጉዳይ የሚመለከተው ወረዳና ክፍለ ከተማ ነው” ብለዋል፡፡ አክለውም የጠቅላይ ሚኒስቴር ጽህፈት ቤት አይመለከተውም ሲሉ ለአዲስ ማለዳ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡


ቅጽ 4 ቁጥር 208 ጥቅምት 19 2015

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here