“ዲፕሎማት ሠርተፍኬት ያለው ሰላይ ማለት ነው”

0
1964

በዘመናችን ስለ ኢትዮጵያ ሽንጣቸውን ገትረው ከሚከራከሩ መካከል ከግንባር ቀደሞቹ ጎን የሚሰለፉ ናቸው። በተለይ በአባይ እና በታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ጉዳይ ላይ ከግንባታው መነሻ ጀምሮ ያላቸውን አመለካከት በተለያዩ የአገር ውስጥም ሆኑ በዓለም ዐቀፍ ሚዲያዎች ላይ ሲያንጻባርቁ ቆይተዋል። የግድቡ መገንባትን የሚቃወሙትን ለመርታት የሚናገሩበትን ቋንቋ ተጠቅመው በተለያዩ አገራት በመገኘትም ሞግተዋል።
እኚህ አንጋፋ ምሁር በተለያዩ ዓለም ዐቀፍ ዩኒቨርሲቲዎች በማስተማር አንቱታን ያተረፉ ናቸው። የተለያዩ የጥናት ጽሑፎችንም ያሳተሙት እኚህ ኢትዮጵያዊ፤ አደም ካሚል ፋሪስ (ረዳት ፕሮፌሰር) ይባላሉ። ወቅታዊውን የዲፕሎማሲ ሁኔታ እንዲሁም ከምዕራቡና ከአረቡ ዓለም ጋር ስላለን ግንኙነት ከአዲስ ማለዳው ቢኒያም ዓሊ ጋር ተከታዩን ቆይታ አድርገዋል።

ራስዎን ቢያስተዋውቁን?

አደም ካሚል ፋሪስ እባላለሁ። በእስላማዊ ቅርሶች ዙሪያ የጥናት ምርምር ባለሞያ እና ረዳት ፕሮፌሰር ነኝ። በግል እስካሁን 33 የሚሆኑ ጥናቶችን ሠርቻለሁ። ከእነሱ ሰባቱ ታትመዋል፣ ቀሪዎቹ አልታተሙም። በብዛት ትኩረት የማደርገው የኢትዮ አረብ የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት ላይ ነው። የኢትዮጵያን ታሪክ በሙስሊሙና በአረቡ ዓለም ምን ይመስላል? ኢትዮጵያ ከመካከለኛው ምሥራቅ ጋር ግንኙነቷና ኃይሏ ምን ዓይነት ነው? በታሪክ፣ በቅርስ፣ በሥልጣኔ ያላትን ቦታና የመሳሰሉትን ነው የምዳስሰው።

ምክንያቱም፣ የእኛ 90 በመቶ የሚሆነው የችግሮቻችን ምንጮች በአረብኛ ቋንቋ የተዘጋጁ ናቸው። እኔም ትምህርቴን ያካሄድኩት በአረብኛ ስለሆነ፣ ያንን ተጠቅሜ ከተጻፈውና ከተዘጋጀው አምጥቼ ኢትዮጵያን እየተረጎምኩና እያስተረጎምኩ ለመመገብ እየሞከርኩ ነው ያለሁት።

ዋናው ኢትዮጵያን በኢንቨስትመንትና በቱሪዝም ብሎም በንግድ ከመካከለኛው ምሥራቅ ጋር እንዴት አድርገን አገናኝተን ድህነትንና ኋላ ቀርነትን፣ መሃይምነትን፣ ሕገወጥ ፍልሰትን ለመቅረፍ እንችላለን የሚለው ላይ ነው የማተኩረው።

እስካሁን የት የት አገልግለዋል፣ አሁንስ የት ነው የሚያገለግሉት?

አሁን በውጭ አገር ነው ትምህርት የምሰጠው። በካናዳ፣ አሜሪካ፣ ሞሮኮ፣ ኢሜሬትስ፣ ኩዌት የመሳሰሉት ጋር ነው የማገለግለው። በአገር ውስጥ በሚዲያ ተሳትፎ ነው በብዛት የምታወቀው። እስካሁን በሕይወቴ 368 ጊዜ በረራ አድርጌያለሁ። የፋይናንስ መረጃውንም እውቀቱንም በዓለም ዙሪያ ዐይቻለሁ። እንደኢትዮጵያ ቆንጆ አየር ያለው ቆላ ወይናደጋና ደጋን የያዘ የትም ቦታ አጋጥሞኝ አያውቅም። በሕይወቴ እስካሁን 447 ጊዜ ቃለመጠይቅ ሰጥቻለሁ። በተለይ በአረቡ ዓለም በአልጀዚራ፣ በኣይን፣ በኢቢኤስና በመሳሰሉ የዜና አውታሮች ላይ ነው ትኩረት የምሰጠው።

ትልቁ በዚህ 11 ዓመት ያደረኩት ግድቡን በተመለከተ ከግብፆች ጋራ ተሟግቻለሁ። እነሱ ጋር በነበረኝ ቆይታ ስለማውቃቸው፣ የቋንቋቸውም ተናጋሪ ስለሆንኩና ኹለተኛ ዲግሪዬንም የሠራሁት እዛው ስለሆነ. የግብፆችን ሐሳብ ከመነሻ እስከመጨረሻው ስለማውቀው፣ ከተማሪዎቼ ከመሐመድ አልአሩሲና ከጀማል በሽር ጋር ሆነን ትልቅ ትግል አካሂደናል።

ኢትዮጵያ አሁን ያለችበትን ወቅታዊ ሁኔታ እንዴት ያዩታል?

ኢትዮጵያ የረጅም ጊዜ ታሪኳን ስናይ እጅግ በጣም አኩሪ ታሪክ ያላት አገር ናት። ከጣሊያን የአምስት ዓመት ቆይታ ውጭ ለቅኝ ገዢዎች ያልተበገረች፣ ሁሉም ተሸንፈው የወጡባት አገር ነች። ኢትዮጵያ የተባበሩት መንግሥታት ሲመሠረት በ1945 ከመሥራቾቹ አንዷ ነች። በ1963 የአፍሪካ ኅብረት ሲመሠረትም ከመሥራቾቹ አንዷ ነበረች።

ስለዚህ፣ በኹለት ቦታ ላይ ትልቅ ክብር አላት። በአፍሪካ ደረጃ የጥቁሮች መብት እንዲከበር በር የከፈተች በመሆኗ በጥቁሮች ዘንድ በመላው ዓለም ክብር አላት። ከአድዋ ዘመቻ በፊት ጥቁሮች የመሸነፍ አመኔታ ወይም አመለካከት ነበራቸው። ነጭ የበላይ ጥቁር የበታች ነው ብለው አምነው የተቀበሉት አመለካከት ነበር። የአድዋ ዘመቻ አዲስ ምዕራፍ ከፍቷል። ጥቁሮች ነጮችን ማሸነፍ እንደሚችሉ ያሳየ ነበር ማለት እንችላለን። ከዛ ጊዜ በኋላ ነው በቅኝ ግዛት ወድቀው የነበሩ አፍሪካዊያን ተንቀሳቅሰው ነፃነታቸውን ለማግኘት ጥረት ያደረጉት ማለት እንችላለን።

የኢትዮጵያ ተሳትፎ በተባበሩት መንግሥታም ሆነ በአፍሪካ ኅብረት በኩል የአፍሪካዊያን መብት እንዲከበር ትልቅ ትግል አካሂዳለች። በንቅናቄው የተነሱትን በማሠልጠን፣ በማዘጋጀትና በማሰማራት ትልቅ ኃላፊነት ተወጥታለች። ማንዴላ ለዚህ ትልቁ ምሳሌ ነው። ከዚህ አንፃር አፍሪካውያን ነፃነታቸውን ካገኙ በኋላ ለአገራቸው መለያ ባንዲራ ሲመርጡ እንኳን ከኢትዮጵያ ቀለም ነው የወሰዱት። ስለዚህ በጥቁሩ ዓለም ቅልቅ ቦታ አላት ማለት ነው።

ከእምነት አንፃር ከመጣህ ደግሞ ኢትዮጵያ የሚለው ቃል በኦሪት 37 ጊዜ ተጠቅሷል። በሙስሊሙ ዓለም የመጣህ እንደሆነ ደግሞ፣ ሐበሻ የሚለው ቋንቋ ልዩ ክብር አለው። ምክንያቱም ለእስልምና ቁርዓን ሕገመንግሥት እንደመሆኑ፣ በቁርዓን ላይ ከ30 ጊዜ በላይ ተመዝግቦ እናገኘዋለን። ኢትዮጵያን የሚያሞግሱ 23 አንቀፆች እናገኛለን። የነብዩ 27 ቃላት ሐበሻን ያሞግሳሉ።

ከዚሁም አንፃር ሐበሾችን አትንኩብኝ ብለው ኑዛዜ ያስተላለፉት ከራሳቸው ሳይሆን ፈጣሪ ከሚጠቁማቸው ነው። ይህ በብቸኝነት የኢትዮጵያ ንብረት ነው ማለት እንችላለን። ስለዚህ፣ በሙስሊሙ ዓለም ኢትዮጵያ ልዩ ክብር አላት። በሌላ በኩል የነጃሺ የነቢላል አገር በመሆኗ በእስልምና ታሪክ ልዩ ከበሬታን ተጎናፅፋለች።

በጥቁሮችና በሙስሊሙ ዓለም በቢሊዮን የሚቆጠር ሕዝብ ኢትዮጵያን ያከብራል። እኛ በዋናነት ይህን ያለንን ክብር ወደ ኢንቨስትመንት ወደ ቱሪዝም ለመቀየር ችለናል ወይ ብለን መጠየቅ አለብን። ለእስከ አሁኑ ጥፋቱ የማን ነው የሚለውን በዚህች አገር ያለፉ መሪዎች ግንዛቤ ውስጥ ይክተቱት። በዚህ አጋጣሚ እንደኢትዮጵያዊ መገንዘብ ያለብን፣ የእኛ ጉዳይ የሚታረሰው የሚዘራው የሚሰበሰበው የሚቦካው የሚጋገረውም 80 በመቶ በዓረብኛ ነው። ስለዚህ ይህን ተከታትለን በእኛ ላይ ምን እየተሠራ ነው ብለን ማሰብ ያለብን። የግድቡን ምሳሌ ለዚህ ማንሳት እንችላለን።

በግድቡ የተነሳ የግብፆች አቋም ከጥንት ጀምሮ እስካሁን ድረስ ምን ይመስል ነበር? ግብፆችን ስንል ከእኛ ቀጥሎ በምዕራቡ ዓለም ኹለተኛ ደረጃን የያዙ ናቸው። 10 ሚሊዮን ስደተኞች በመላው ዓለም አሏቸው። ወደ 350 ሺሕ የሚሆኑ መሃንዲሶች ወይም ሐኪሞች በውጭ አገር የተሰማሩ አሏቸው። በየትኛውም ዓለም ስትሄድ በዓለም ዐቀፍ ተቋምም ቢሆን ግብፆች የሌሉበት የለም። ስለዚህ፣ የግድቡ ነገር ሲነሳ ግብፆች በእነሱ አመለካከት፣ “ከሰማይ የመጣ የእኛ ትሩፋት ነው” የሚል እምነት አላቸው። የተለያዩ የግብፅ መሪዎችን ከተመለከትን ለኢትዮጵያ ጥሩ አመለካከት የላቸውም።

ግብፅ ውስጥ አራት ሺሕ ሚዲያዎች አሉ። እኛ ግድቡን መገንባት ከጀመርን ወዲህ ወደ 28 የሚሆኑ ጋዜጠኞች ተሳትፈው ትልቅ ትግል ሲያካሂዱ ነበር። ግድቡን እንዳንሠራ ያላደረጉት ሙከራ የለም። ሙከራቸው ሁሉ ከሽፎ ግድቡ ከአንድ እስከ ሦስት ዙር ድረስ ሙሌቱ ሊካሄድ ችሏል።

ሌላው እኛ ከግምት ያላስገባነው የሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት ሦስት ጊዜ የተነሳበት ምክንያት ከግድቡ ሙሌት ጋር የተያያዘ ነው። ቁጥር አንዱ ጦርነት የመጀመሪያው ሙሌት በተካሄደ በኹለተኛው ቀን ነው የተጀመረው። ቁጥር ኹለትም ሆነ ሦስት የተቀሰቀሰውም ከግድቡ ሙሌት ጋር በተገናኘ ነው። ስለዚህ ከጀርባው ማን አለ የሚለው በደንብ አድርጎ ሊጠና ሊታሰብ የሚገባ ነው። ይህ ዲፕሎማቶቻችንን የሚመለከት ነው።

የእኛም ድክመት ዓረብኛ የሚችሉ ዲፕሎማቶች አልመደብንም። ከጥንት ጀምሮ ለድርጅት ታማኝነትን መለኪያ አድርገን ነው የሄድነው፣ እንደመሪዎች ማለቴ ነው። ያ ደግሞ ትልቅ ስህተት ነው። ዲፕሎማት ሠርተፍኬት ያለው ሰላይ ማለት ነው። ይህ ስለሆነም በሄደበት በቋንቋቸው መከታተል፣ ማንበብና መጻፍ ካልቻለ አገሩን እንዴት አድርጎ ነው ሊጠቅም የሚችለው? ይህ ድክመት ነበረብን። ለዚህ ነው ምዕራባውያን ወደመካከለኛው ምሥራቅ ዲፕሎማቶችን ሲመድቡ አረብኛ የሚችሉን የሚሾሙት። እኛ ጋር ትልቁ ምሳሌ የሩሲያ አምባሳደር ነው፣ አማርኛን አቀላጥፎ የሚናገር ነው።

ከዚህ አንፃር አገሪቷ ላይ ሊያስከትል የሚችለው ጥቅም ታይቶ ችግሩን አስወግደን ጫናውን መከላከል ያልቻልንበት ጊዜ ነበር። አሁን ግን ከዛ አጀንዳ የወጣን ይመስለኛል። አሁን ያንን ችግር በመረዳት ዲፕሎማሲያችን ተሻሽሎ ይታያል። ውጭ ጉዳይ ባወጣው እቅድ  መሠረት ችግሩ የሚቀረፍ ይመስለኛል። ስለዚህ ከወቅታዊው ሁኔታ አንጻር ብዙ ትግል ይጠይቀናል።

አሁን ግድቡ ከሞላ ጎደል ስለተሞላ የሚደፈርበት ሁኔታ የለም። ይህንን ግድብ ማፍረስ አለብን ተብሎ  በሳውዲ ድጋፍ አውሮፕላን ገዝተው ነበር። 4 ቢሊዮን ዶላር ወጪ አድርገው የገዙት አውሮፕላን 2 ሺሕ ኪሎሜትር ምንም ነዳጅ ሳይጨምር ይሄዳል። ይህ የተገዛው ግድቡን በደረቁ ለመምታት ነበር። ባልተጠበቀ ሁኔታ ሙሌቱ በፈጣሪ ኃይል በሦስት ዙር ወደ 22 ቢሊዮን ሜትር ኪዩብ ስለተሞላ አያሳስብም።

ግብፆቹ ባመኑት እንኳን 18.6 ቢሊዮን ሜትር ኪዩብ ውሃን ግድቡ ስለያዘ አሁን ባለው ሁኔታ ሊመታ አይችልም። ይህንን እነሱም አምነው ተቀብለዋል። እነሱም መረጃዎችን ስለሚያሰባስቡ ጉዳዩን በደንብ የሚያጠኑ ባለሙያዎችም ስለመደቡ ያውቁታል። አሁን ባለው ሁኔታ ግድቡ ቢመታ የተቀበረ ፈንጂ እንደማለት ስለሆነ ይፈነዳና ከሱዳን 20 ሚሊዮን ሕዝብን ጠራርጎ ይወስዳል። ከ7 ሰዓት በኋላም አስዋን ግድብ ደርሶ አደጋ ያመጣል። ስለዚህ፣ አማራጩ ምንድን ነው የሚለውን በጥናት አስቀምጠው ወቅታዊውን ሁኔታ ተጠቅመው የኢትዮጵያ ውስጣዊ አንድነቷን ማተረማመስና መከፋፈል የሚለውን እየሠሩበት ነው።

በዚህ ጉዳይ ላይ እኛ ምን ያህል ክትትል አድርገናል የሚለው የአስተዳደሩም የፖለቲካውም ሥራ ይመስለኛል። ችግራችን የሚቦካውና የሚጋገረው በአረብኛ ነው። ያንን መከታተል የቤት ሥራ ይሆናል ማለት ነው።

በዲፕሎማሲው መስክ ለውጥ ተደረገ ከተባለ ወዲህ ምን ተጨባጭ ለውጥ ተገኝቷል ይላሉ?

ግድቡን ያለምነውም የሠራነውም በራሳችን ወጪ ነው። ግብፆች ይሠሩታል የሚል ግምት አልነበራቸውም። ግን የኢትዮጵያ ሕዝብ ከሊስትሮ እስከ መንግሥት ሠራተኛ ከኪሱ አዋጥቶ ድህነትንና ኋላቀርነትን ለመቅረፍ አልሞ አስቦ የሠራው ነው። ይህ ማለት በ21ኛው ክፍለ ዘመን እኛም መኖር አለብን፣ የኤሌክትሪክ ተጠቃሚም መሆን አለብን፣ በመስኖ መጠቀም እንፈልጋለን። የ65 እና የ77 ረሃብ ትልቁ ትምህርት ነው። ያን ጊዜ ኢትዮጵያ የረሃብ አገር ተብላ ነው በአረቡ ዓለም የተሰየመችው።

ችግሩ የአስተዳደር ችግር ነበር። አሁን ግን ችግራችንን በማወቅ ግድቡን ሠርተን ወደ መስኖ ነው የምናተኩረው። አሁን ብልጭታዎች አሉ። የስንዴውም ይሁን የሩዝ ምርቱ ከእኛ ተርፎ ወደ ውጭ እንልካለን እስከማለት ደርሰናል። ይህ ትልቅ ለውጥ ነው። ይህን እንዴት አድርገን ማዳበር አለብን የሚለው ነገር ነው የቤት ሥራ መሆን ያለበት። ስለዚህ ይህን ካደረግን ድህነቱም ኋላቀርነቱም ይቀረፋል። ሕገወጥ ፍልሰቱም ይቀራል።

አሁን ወደ ውጭ አገር መሰደድ መሄድ ያከተመበት ጊዜ ላይ ነው የምንገኘው። ምክንያቱም ለምሳሌ በሕገወጥ ፍልሰት ወደ ሳውዲ የሄዱት ከ102 ሺሕ በላይ ኢትዮጵያውያን ነበሩ። ከእነሱ እስካሁን 70 ሺሕ መልሰናል። ቀሪዎቹ በጉዞ ላይ ነው ይሉት።

አሁን ወደ ውጭ ወደኢምሬት፣ ሳውዲ፣ ኩዌት መሄድ አይቻልም። አውሮፓ ራሷ፣ በተለይ በሩሲያና በዩክሬን መካከል ባለው ጦርነት በትልቅ ውጥንቅጥ ውስጥ ነው ያለችው። ምናልባት ከኹለት ሳምንት በኋላ የአውሮፓ ከተሞች ከዜሮ በታች ወደ 35 ዲግሪ ሴንቲግሬድ ቅዝቃዜው የሚወርድበት ወቅት ነው። ይህ በሚሆንበት ሁኔታ ወደእነሱ መሰደድ ያከተመበት ሁኔታ ነው ያለው። ወደደቡብ አፍሪካ መሄዱም ለማክተሙ በማላዊ ኢትዮጵያውያኑ ላይ የደረሰው ግፍ እና በደል አመላካች ነው።

ስለዚህ፣ ያለን አማራጭ ኑሮ ውድነትንም ሆነ ሥራ አጥነትን በመቅረፍ በመስኖ በመጠቀም፣ ኩታ ገጠም እርሻን በማዳበር ውጤቱን እያየነው ያለነውን ተግባር ማዳበር ነው። ወንዞቻችንን እና ሐይቆቻችንን መለወጥ እንችላለን። አንድ ግድብ አይደለም 100 ግድብ መሥራት እንችላለን። ይህን ግብፆችም የመሰከሩት ነው። 12 ወንዞች 8 ሐይቆች አሉን። እነሱን የምንጠቀምበትን ሥልት እንደመንግሥትም እንደሕዝብም ለመንደፍ ማተኮር ያለብን ይመስለኛል።

ዋናው ኢትዮጵያን እንዴት ያውቋታል የሚለው ሲሆን፣ በዚህ ጉዳይ ሚዲያውም በሰፊው መሥራት ይኖርበታል። መሪዎችም በዚህ ላይ ማተኮር አለባቸው። የሃይማኖት ድርጅቶች ከቤተክርስቲያንና ከመስጂድ ወጥተው ምሳሌ መሆን አለባቸው። ዝም ብለው ለምዕመናኑ በሳምንት ወይም ለበዓላት ትምህርት መስጠት ሳይሆን፣ ወደታች ወርደው አርዓያ መሆን አለባቸው።

በዚህ ጉዳይ ከግብፅ ጥሩ ምሳሌ መውሰድ እንችላለን። የግብፅ ክርስቲያኖች ትልቅ ምሳሌዎች ናቸው። በዓመት አንዲት የምትቃጠል ቀን የላቸውም። እኛ ጋር ግን ከ365ቱ 124 ቀን ብቻ ነው የሚሠራው። ግብፆች ያስቀመጡት እዳ 12 ቁጥር ሚስማር ነው። እንዳንነቃ፣ እንዳንነሳ በባህልም፣ በወግም በአመለካከትም አድርገዋል። ወደመጽሐፍ ቅዱስ ብንገባ አትሥራ ሳይሆን ሥራ የሚል ነገር ነው ያለው። እኛ መንቃት ነው ያለብን።

ከግድቡና ከጦርነቱ ድርድር ውጤት አኳያ ምዕራባውያንና ደጋፊዎቻቸው ጋር ያለን ግንኙነት ምን ሊሆን ይችላል?

ምዕራባውያን ምንም ሊያመጡብን አይችሉም። ይህን ማእቀብ የሚሉትን በተመለከተ ትልቁ ትምህርትና ምሳሌ የሚሆነን የኢራን ተሞክሮ ነው። ኢራን በዚህ አራት ዓመት ለአንድ ሺሕ አምስት መቶ በላይ ማዕቀቦች ተጋልጣለች። ያንን ሁሉ ሰብራ ግን የአገሯን ሕዝብ መመገብ የሚችል ኢኮኖሚ ገንብታለች። ምዕራባውያን በተለይ በአሁኑ ጊዜ ከባድ ውጥንቅጥና ችግር ውስጥ ነው ያሉት። ምክንያቱም፣ ከዩክሬንና ሩሲያ ጦርነት ጋር በተገናኘ ከኹለት ተከፍለው ነፍስ ውጪ ነፍስ ግቢ ላይ ናቸው።

የምዕራብ ሚዲያዎችን ብንመለከት ሦስቱ ዙሮች ጦርነቶች በዓለም ዐቀፍ ደረጃ የሚለያዩበትን እናያለን። የመጀመሪያው የጥቅምት 24ቱ ላይ መከላከያ አለቀለት ተብሎ ነበር በዓለም ዙሪያ በተለይ በሱዳኖች የተወራው። ያን ጊዜ ተቀማጭ ነበራቸው፤ ይህችን አገር 27 ዓመት አስተዳድረው ኹሉን ነገር በቁጥጥራቸው ስር አድርገው ነበር።

በዓለም ዐቀፍ ደረጃ ኢትዮጵያ ያገኘችውን ብድር ያስቀመጡት በራሳቸው ሥም ነበር። ስለዚህ የውጭ የጀርባ አጥንታቸው ጠንካራ ነበር ማለት ይቻላል። በሚዲያውም በፖለቲካውም ያላቸውን አቅም ይዘው ሞከሩ፣ ግን ጥቅም አልባ ሆነባቸው። መከላከያችን ከተደፈረ በኋላ ትምህርት ሰጥቶን ፍልሚያው ከ115 ሚሊዮን ኢትዮጵያዊያን ጋር ሆነ። የመንግሥትና የመንግሥት ግጭት አልሆነም። ስለዚህ የኢትዮጵያ ሕዝብ አንድነቱን ያጠናከረበት ሆነ።

ቁጥር ኹለቱ ለእነሱ ጠቃሚ ነበር። ከአማራ ክልልና አፋር የፈለጉትን ዘርፈው ነበር ይዘው የሄዱት። ችግሩ ከመንግሥት ካር ሳይሆን ከአርብቶና አርሶ አደሩ ጋር ነበር ማለት ይቻላል።  ቁጥር ሦስቱ ላይ ሕዝቡ ተምሮ ከመንግሥትና ከሕዝብ በላይ ሲከላከል ነበረ። ሌላው ግንዛቤ ውስጥ መግባት ያለበት እነሱ ናቸው እየመጡ ውጊያ የከፈቱት።  ሌላው አይደለም ወደ እነሱ ሄዶ የዘመተው። የትግራይ ሕዝብ የራሳችን ሕዝብ ቢሆንም መሪዎቹ አሳስተውት ባለፉት ዓመታት ከፍተኛ አደጋ ነው የተከሰተበት። ይህ በሆነበት ሁኔታ ድርድሩ ጠንካራ የዲፕሎማሲ ውጤት ነው ማለት ይቻላል።

እኛ አገር የሚፈለገው አንድነት፣ ሰላምና መረጋጋት ነው። ይህ ካለ መንግሥት ጋር ግራና ቀኝ ሆኖ ለውጥ ማምጣት ይችላል። መንግሥትን ዛሬ መርጠነው ውጤት ካላመጣ ነገ ለመቀየር ምንም ችግር የለም። የኢትዮጵያ ሕዝብ በዚህ ምንም ችግር የለበትም። ብዙ የተማረ ይመስለኛል። ያለፈውም ምርጫ ጥሩ ምሳሌያችን ነው። ግብጾች ሊፈራርሱ ነው ሲሉ አንድም ደም ሳይፈስ ነው ለውጤት የበቃነው። በታሪካችን አንድነት ካለ ኅብረቱ ካለ ሰብረነው የማንወጣው ምንም ችግር የለም።

አሁን ምንም የሚያሰጋን ነገር የለም። በድርድሩ ሰላም ይፈለጋል፤ በማንኪያ ከሰጡን በአካፋ እንሰጣቸዋለን። ዋናው ነገር የትግራይ ሕዝብ ምን ያህል ጉዳት ተፈጽሞበታል ምን ያህል ለአደጋ ተጋልጧል፣ ሌላው ክልል እየለማ ሲሄድ ወደኋላ መቅረቱ ለኹላችንም የጀርባ ችግር ነው የሚሆነው። ስለዚህ ሰላም ተፈጥሮ ወደልማትና እድገት፣ የፈረሰውን ወደመገንባቱ መሄድ አለብን። ይህን ማድረግ የኹላችን የጋራችን ኃላፊነት ስለሆነ አንድነታችንን አጠናክረን የምንነሳበት ጊዜ ደርሷል።

የውጭ ኃይል ተሞከረ፣ ዋጋ የለውም። ገብተውም የራሳቸውን ጥቅም ለማዳበር ነው እንጂ ሊጠቅሙን አይደለም። እኛን በጣም የሚያሳስበን የሱዳን ሰላም ማጣት ነው። በየቀኑ የሚሆነውን ለሚከታተል የሕዝቡ ጩኸት ሊያሳስበን ነው የሚገባው። ግብፆች ሁኔታውን የፖለቲካ መጠቀሚያ ነበር ያደረጉት። ተቀራርበን ለሰላም መሥራት ይገባናል። ስንወያይና ስንደራደር ጠንካራ ጎናችንን እናጎለብታለን። መከላከያችን በጥሩ ሁኔታ ላይ ነው ያለው፤ ሕዝቡ ነቅቷል።

ኢትዮጵያ ራሷን ችላ፣ የማንንም ጎራ ሳትቀላቀል ገለልተኛ ሆና መቆየት አትችልም ለሚሉ ምን አስተያየት አልዎት?

በተፈጥሮ እንደኢትዮጵያ የታደለ አገር የትም የለም። እዚህች አገር ውስጥ 146 ዓይነት ምርት ማምረት ይቻላል። ገና ያልተነኩ ያልተዳሰሱ ምርቶች አሉ። ኢትዮጵያዊያን ኢትዮጵያን ማወቅ ከቻሉ ከሌላው ዓለም ሳይበደሩ ሳይፈልጉ በራሳቸው ተብቃቅተው መኖር የሚችሉበት በረካ አለ። ተፈጥሮ ያደለችን ማንም ጋር የሌለ ነው።

አብዛኛው አገር አደጋ አይለየውም፣ አንዱ ቃጠሎ ሌላው ማእበልና የተፈጥሮ አደጋ በየጊዜው የሚያሰጋው ነው። አውሮፓም ሆነ ሌላው ውጥንቅጡ የወጣበት አካባቢ ነው። የአረቡን ዓለም እንኳን ብንመለከት፣ ሠሞኑን የተካሄደው የአልጀርስ ስምምነት አለ። ከተሰበሰቡበት ጉዳይ አንዱ የሆነውን የፍልስጤምን ጉዳይ መፍትሔ ሊያመጡ አልቻሉም። በስብሰባው ለመሳተፍ እንኳን አምስት መሪዎች አልቻሉም። እንዲህ የሚሆንበት የሌላው ዓለም የራሱ ጉዳይ ነው። በእኛ ላይ ክፉ ሲያቅዱና ሲያቦኩ የነበሩ ናቸው። ግን ያሰቡት ሁሉ አልተሳካላቸውም። እኛ ለራሳችን እንበቃለን፣ ችግሮቻችንንም በራሳችን እንወጣለን።

ዓለም በተለያየ ጎራ በተሰለፈበት ሁኔታ እኛ ጥቅም እስካለን ድረስ ከማንም ጋር መዛመድ እንችላለን። የዘላለም ጠላትና ወዳጅ የለም። ከጥቅማችን አንጻር ዲፕሎማሲያችን በሳል መሆን አለበት። በዚህ መንገድ መንቀሳቀስ እንችላለን። ይህ በሆነበት ሁኔታ ኢትዮጵያ ለችግር ትጋለጣለች የሚል ስጋት የለኝም። የማንም ተለጣፊም አትሆንም።

ሌላው ዓለም ከገባበት ለመውጣት እየተቸገረ ነው። የሱማሌን፣ የየመንን ጉዳይ በምናይበት ሁኔታ እኛ በሰላም እየተጓዝን መሆኑን መመልከት ይቻላል። ስለዚህ የዓለም መሣሪያ አምራቾች በየትኛውም ዓለም በተለይ በአፍሪካ ቀንድ ውዝግብ ተነስቶ መጠቀም የሚፈልጉ ነጋዴዎች ሊኖሩ ይችላሉ። እኛ ግን በራሳችን ተነስተን ወደልማታችን ገብተን ረሃብን ድህነትን ከቀረፍን በሰላም እንኖራለን።

በሰላም የማያኖር እርስ በእርስ መፈራረጅ እንዲህም በአንዳንድ ባለሥልጣናት የሚደረጉ ዘርንና ሐይማኖትን መሠረት ያደረጉ የጥላቻ ንግግሮችን እንዴት ይመለከቷቸዋል?

እንዲህ ዓይነት ነገሮች ቦታ ሊኖራቸው አይገባም። ተግባሮቹ ከሰሜኑ ጦርነት ጋር የተያያዙ ናቸው። ከግብፆች ጋርም የተያያዘ ነው። ግብፆች ቀደም ብዬ እንደተናገርኩት የግድቡን ግንባታ ማስቆም ሲያቅታቸው፣ ኢትዮጵያን በብሔር፣ በጎሳ፣ በአመለካከት መከፋፈሉ ነው የሚበጀው የሚለውን ጥናታቸውን በሰፊው እያንጸባረቁ ነው የሚገኙት። አሁን እየታየ ያለው ከእነሱ ቫይረስ የመጣ ይመስለኛል።

አንዳንድ መሪዎች አፋቸው ይዘልና ያልተጠበቀ ሁኔታ ይከሰታል። ይህች አገር የማንም አይደለችም፣ የኢትዮጵያዊያን አገር ነች። አይሁድን ክርስትናንና እስልምናን በየዘመኑ አስተናግዳ አሻራቸውን አሳርፈዋል። የየትኛውም ተከታይ ይሁን፣ ይህ ሕዝብ ከመካከለኛው ምሥራቅ የወረደለትን መመሪያ ተግባራዊ እያደረገ የሚኖር ነው።

ቅኝ ባለመገዛታችን እምነታችን፣ ባሕላችን፣ ቅርሳችን፣ ታሪካችንና ወጋችን አልተበከለም። ይህ ቢሆንም፣ ዛሬ የመጡ መሪዎች ትርፍ ቃላትን ለፖለቲካ እንጠቀምበታለን ብለው የሚያካሂዱት ከሆነ ዋጋ የለውም። የሐይማኖት፣ የአመለካከት፣ የብሔርና የቋንቋ ጉዳይ እዚህ አገር አይሠራም። በአንድነት በኢትዮጵያዊነት ተባብረን ከሄድን ግን ይህችን የጋራችን አገር ስለሆነች አማራጭም ስለሌለን እናሳድጋታለን።

ተሰዶ ለመኖርም ጊዜው ምቹ ስላልሆነ ተከባብሮ መኖሩ አስፈላጊ ነው። ትርፍ ቃላትን የሚሰጡ መሪዎች ከስህተታቸው ታርመው ጎንበስ ብለው ይቅርታ ጠይቀው መጓዝ ነው ያለባቸው። ይህ ካልሆነ ራሱ በራሱ ይፈነግላቸዋል። በትክክል የማይመሩና የማያስተዳድሩ ከሆነ ዛሬ የኢትዮጵያ ሕዝብ በጣም ነቅቷል።


ቅጽ 5 ቁጥር 209 ጥቅምት 26 2015

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here