ግጭት አስወጋጅ ዘጋቢነት

0
825

በፍቃዱ ኃይሉ ወቅታዊውን የኢትዮጵያ ኹኔታ ታሳቢ አድርገው እና ሮስ ሀዋርድ የፃፉት ‘ግጭት አስወጋጅ አዘጋገብ መመሪያ’ የሚል ጽሑፍ ተንተርሰው ፥ የግጭት አስወጋጅ ዘገባ ምንነትን እንዲሁም በዘገባ ወቅት መደረግ ስላለባቸው እና ስለሌለባቸው መሰረታዊ ነጥቦችን ዘርዝረው አብራርተዋል።

 

“ለዘጋቢዎች ለውጥ ዜና ነው። እናም ለውጥ ሲኖር፥ አለመግባባት እና ግጭትም ይኖራል። ለውጡን በሚፈልጉት እና በማይፈልጉት መካከል ግጭት አለ፤ የበለጠ ለውጥ በሚፈልጉ እና በሚቃወሙ መካከልም ግጭት አለ። ስለሆነም ጋዜጠኞች በየዕለት ሥራቸው ከእነዚህ ግጭቶች ጋር ይጋፈጣሉ። ነገር ግን ብዙ ጋዜጠኞች ስለግጭት እምብዛም አያውቁም። የግጭቶችን ሥረ መሠረት ወይም ግጭቶች እንዴት እንደሚቋጩ ብዙም አያውቁም።” – ሮስ ሀዋርድ

ለጋዜጠኞች ብዙ ጊዜ ወሳኙ ጉዳይ የተረጋገጠ እና ለማንም ወገንተኛ ያልሆነ (accurate and impartial) ዜና ማግኘት ብቻ በቂ ሆኖ ነው የሚታያቸው። ነገር ግን ሚዲያዎች እና ዜናዎች ተደራሲዎች ጋር ሲደርሱ የሚፈጥሩት ተፅዕኖ አለ። ተፅዕኖ ባይኖራቸው ኖሮ እንደ ሸቀጥ ተቆጥረው ገበያ አይወጡም ነበር። ሆኖም፣ ልክ እንደ ሕክምና እና ትምህርት አገልግሎት ሁሉ በጣም ጥንቃቄ የሚሻ አገልግሎት ነው – የዜና አቅርቦት ጉዳይ።

አዲስ ማለዳ ጋዜጣ እነሆ 52ተኛ ዕትሟን ከእጃችሁ በዛሬው ዕለት አስገብታለች። እነኾ በኅትመት አንድ ዓመት ሞላት ማለት ነው። ይህንን አስመልክቼ መጻፍ የፈለግኩት ስለ ግጭት አስወጋጅ ዘጋቢነት ነው። አዲስ ማለዳ የኢትዮጵያን ወቅታዊ፣ ፖለቲካዊ ሁኔታ ያገናዘበ፣ ግጭትን አስወጋጅ ነገር ግን የተጣራ መረጃ ሰጪ፣ ከአራጋቢነት ሞጋችነትን የመረጠች እና ለዚሁም የአቅሟን እየሞከረች ያለች ጋዜጣነቷን ብዙዎች ይመሰክራሉ ብዬ እገምታለሁ። ሆኖም የዚህ ጽሑፍ ዓላማ ግን ጋዜጣዋን ለማንቆለጳጰስ ሳይሆን የግጭት አስወጋጅ (conflict-sensitive) ዘገባን ምንነት እና በወቅታዊው የኢትዮጵያ ኹኔታ ያለውን አስፈላጊነት አጋጣሚውን በመጠቀም ማውጋት ነው። ግጭት አስወጋጅ ዘጋቢነት ለአዲስ ማለዳ ብቻ ሳይሆን፣ ኀላፊነት ለሚሰማቸው የግል እና የመንግሥት፣ ነጻ እና የሕዝብ ብዙኀን መገናኛዎች በሙሉ ጠቃሚ ነው።

በዚህ ርዕሰ ጉዳይ የረዥም ጊዜ ዕውቀት ያካበቱት ሮስ ሀዋርድ ለጋዜጠኞች ‘ግጭት አስወጋጅ አዘጋገብ መመሪያ’ አሳትመዋል። ለዚህ ጽሑፍ እንደ ዐቢይ ግብዓት የተጠቀምኩት የእርሳቸውን መጽሐፍ ነው።

ሀዋርድ “ማኅበረሰቦች በነውጥ አዘል ግጭቶች ሲታመሱ፥ ጋዜጠኝነት ፈተና ውስጥ ይወድቃል” ይላሉ። “ተቀናቃኝ ወገኖች ብዙኀን መገናኛዎችን መቆጣጠር ይፈልጋሉ። መረጃዎች ደግሞ የማይታመኑ ወይም የጠለሉ [የተቆረጡ/የተቀጠሉ] ሊሆኑ ይችላሉ። የግል የአደጋ ስጋቶችም አሉ። ስለሆነም ‘መልካም ጋዜጠኝነት’ የሚያስፈልገው የዚህ ጊዜ ነው።”

የግጭት መነሾዎችን መረዳት
ሮስ ሀዋርድ የትም ዓለም ላይ ይሁን የት፣ የግጭቶች ሁሉ መነሻዎች ጥቂት እና ተመሳሳይ ናቸው ይላሉ። እነዚህንም በአምስት ያስቀምጧቸዋል።
አንደኛ፣ የሀብት እጥረት አለ፣ በዚያ ላይ ደግሞ ፍትሐዊ ክፍፍል የሌለ ሲሆን (ይህ ምግብን፣ መጠለያን፣ የሥራ ዕድልን፣ መሬትን ይጨምራል)፤ ኹለተኛ፣ ግጭት ውስጥ በገቡት አካላት መካከል ምንም ዓይነት ንግግር/ምክክር የለም፣ ወይም በቂ አይደለም፤ ሦስተኛ፣ ግጭት ውስጥ የገቡት አካላት አንደኛው ስለሌላው የተዛባ አመለካከት አለው፤ አራተኛ፣ መልሥ ያላገኙ ብሶቶች ካለፈው ጊዜ ተወርሰዋል፤ እና አምስተኛ፣ የሥልጣን ክፍፍል ችግር አለ።

እውነትም የኢትዮጵያን ወቅታዊ የፖለቲካ ግጭት ምክንያቶች ጠልቀን ስንመለከታቸው ከነዚህ አምስት ማዕቀፎች ውስጥ አይወጡም። እንዲያውም በነዚህ ውስጥ ተበታትነው እናገኛቸዋለን።

ባሕላዊ እና መዋቅራዊ ነውጦች
ነውጥ አዘል ግጭቶች የሚከሰቱባቸው የተለያዩ መንገዶች አሉ። ሀዋርድ ባሕላዊ እና መዋቅራዊ ነውጦች ብለው ነው የሚከፍሏቸው። ባሕላዊ ነውጦች የሚባሉት በስዕል፣ በንግግር ወይም በእምነት የሚገለጽ የነውጥ ፍቅር ወይም ዓይነት ነው። ለምሳሌ የጥላቻ ንግግር፣ የዘርጥላቻ (‘ዜኖፎቢያ’)፣ ስለ ቀድሞ የጦር ጀግኖች የተጻፉ የማያስማሙ ትርክቶች፣ ጦርነቶችን በሃይማኖት ሥም ዕውቅና የመስጠት ችግሮች፣ እና ስርዓተ ፆታዊ መድልዖ ናቸው።

በሌላ በኩል፣ መዋቅራዊ ነውጦች የሚሏቸው በሕግ ወይም በትውፊት የሚደገፉ እና ነውጡ ሲከሰት በቸልታ የሚታለፍ ወይም የሚፈቀድ ዓይነት ሲሆን ነው። መዋቅራዊ ነውጦች ከሚገለጹባቸው መንገዶች ውስጥ ተቋማዊ ፆተኝነት ወይም ዘረኝነት፣ ቅኝ አገዛዝ፣ የበዛ የጉልበት/ሀብት ብዝበዛ፣ ድህነት፣ ሙስናና ቤተዘመዳዊነት እንዲሁም መዋቅራዊ የክፍፍል-ሰፈራ (ሴግሪጌሽን) ናቸው።

ጋዜጠኞች እነዚህን ባሕላዊ እና መዋቅራዊ ነውጦች በአግባቡ ከተረዱ በባሕል፣ በትውፊት፣ በሕግ ወይም በስርዓት ሥም ተሸሽጎ የሚመጣ ግጭት ሊያስከትል የሚችል ማንኛውንም ዓይነት ክስተት፣ ንግግር ወይም መረጃ በአግባቡ ማቅረብ ይችላሉ።

የሚዲያዎች ሚና
ብዙ ጋዜጠኞች የዕለት ሥራቸውን ከመሥራታቸው እና በዜና ክፍል የሚጠበቅባቸውን ዜና ከማቅረብ ውጪ ኀላፊነት ያለባቸው አይመስላቸውም። በረዥም ጊዜ የማኅበረሰቡን ዕጣ ፈንታ በመቅረፅ ረገድ ያላቸውን ሚናም ቆም ብለው የሚያጤኑት ጥቂቶች ብቻ ናቸው። ይሁን እንጂ እነሱ አለማስተዋላቸው ማኅበረ-ፖለቲካዊ ኩነቶችን በመዘወር ረገድ የሚያሳርፉትን ተፅዕኖ አይቀንሰውም ወይም አያስቀረውም።

ከነዚህ ሚናዎቻቸው መካከል በተለይም ግጭትን በሚመለከት ሚዲያዎች የመነጋገሪያ መድረክ የመሆን ዕድላቸው ሰፊ ነው። ሆኖም ይህንን ሚናቸውን ባለማስተዋል የአንዱ ወገን ብቻ መናገሪያ መድረክ የሚሆኑበት አጋጣሚ በርካታ ነው። ይህንን ለማስወገድ፣ በጥንቃቄ ሚናቸውን አስተካክለው መበየን ይችላሉ። ማለትም፣ ለሁለቱም ግጭት ላይ ላሉ (ከላይ አይነጋገሩም ላልናቸው ወደ ግጭት እየገቡ ያሉ ወይም የገቡ) ወገኖች የመመላለሺያ ወይም የመነጋገሪያ መድረክ መፍጠር ይችላሉ። በተጨማሪም ስለጉዳዩ ማስተማሪያ፣ በተቀናቃኝ ወገኖች መካከል መተማመንን የማሳደጊያ፣ የተዛቡ ግንዛቤዎችን የማረሚያ፣ ግጭቱ የሚያሳድረውን ጉዳት በሰዎች ማሳያነት የማስረጃ፣ ግጭት ውስጥ ያሉ ወገኖች አንዱ የሌላውን እንዲያውቅ የማድረጊያ፣ የታመቁ ብሶቶችን የማስተንፈሺያ፣ ግጭቱን በጤናማ መንገድ ሥያሜ በመስጠት የማስረጃ፣ ሥምምነቶችን የማበረታቻ፣ መፍትሔ የማፈላለጊያ እና የተዛቡ የኀይል ሚዛኖች እንዲታረሙ የማበረታቻ ሚናን መጫወት ይችላሉ።
ለዚህም ጋዜጠኞች ጥሬ ሐቅ እና አስተያየቶችን ቀምረው ከመዘገብ ባለፈ ግጭቶችን መተንተን እና መረዳት መቻል አለባቸው።

መልካም ጋዜጠኝነት
ሀዋርድ ግጭት አስወጋጅ ጋዜጠኝነት መልካም ጋዜጠኝነት ነው ይሉታል። ጋዜጠኞች ምንም እንኳን መልካም ጋዜጠኛ የመሆን ግዴታ ባይኖርባቸውም መልካም ጋዜጠኛ በመሆን ማኅበራዊ የሞራል ግዴታቸውን መወጣት ይችላሉ። መልካም ጋዜጠኝነት አንዱን ወግኖ ሌላውን ማጥቃት አይደለም፤ መንግሥትን ወይም ሌላ ኀይለኛ ቡድንን ማገዝም አይደለም። መልካም ጋዜጠኝነት ግጭትን ባለመዘገብ ሐቁን መሸሸግም አይደለም፤ መልካም ጋዜጠኝነት ግጭትን በሐቅ ላይ ተመሥርተው ሲዘግቡ በዚያውም መፍትሔውን ማመላከት መቻል ማለት ነው።

መልካም ጋዜጠኞች የማያደርጓቸው ነገሮች አሉ ይላሉ ሮስ ሀዋርድ። እነዚህም “ሥም የማጥፋት ዘመቻ፣ የሌሎችን ዘገባ መከተል ወይም መድገም፣ ሌሎችን አደጋ ወይም ድንጋጤ ላይ መጣል፣ ሙስና ተቀብሎ መዘገብ የመሳሰሉት ናቸው”። በተመሣሣይ መልካም ጋዜጠኞች የሚያደርጓቸውንም ዘርዝረዋል። እነዚህም፣ “የተጣራ መረጃ ማቅረብ፣ ወገንተኝነትን ማስወገድ፣ በኀላፊነት ስሜት መዘገብ እና ፍረጃን መቀነስ ናቸው”።

ፍረጃን መቀነሻ ጥቁምታዎች
ብዙ ጋዜጠኞች እንደ ብዙኀን ዜጎች ሁሉ የየራሳቸው ፍረጃዎችን ስለተለያዩ ሰዎች፣ የፖለቲካ ድርጅቶች፣ የማኅበረሰብ ክፍሎች በልቦናቸው ይዘው ነው የሚዞሩት። ነገር ግን ዘገባዎችን በሚሠሩባቸው ጊዜያት ከነዚህ ፍረጃዎች መላቀቅ አለባቸው። ሀዋርድ ይህንን ለማድረግ የሚቻልባቸው የሚሏቸው ጥቆማዎች አሏቸው።
ጋዜጠኞች ዘገባቸው ላይ ስለማኅበረሰብ ክፍሎች ወይም ቡድኖች ያሏቸው ፍረጃዎች እንዳይገቡባቸው ራሳቸውን በየጊዜው እነዚህን ጥያቄዎች ሊጠይቁ ይገባል። ይህ ዜና አስፈላጊ ነው? ብዙኀን ከዚህ ምን ይጠቀማሉ? ለምን እና እንዴት? ይህ ዜና የሚሆነው ስሌሎቹ ወገኖች ስለሆነ ብቻ ነው? ጥሬ ሐቆቹ እውነት ቢሆኑም እንኳን፥ ይህ ዘገባ ፍረጃን ያበረታታ ይሆን? በተለየ መንገድ ሊዘገብ ይችላል? በቂ የተለያዩ ድምፆች ዘገባው ላይ ተካትተዋል? የተለያዩ ባለሙያዎች እና ተራ ዜጎች በበቂ ሁኔታ መጠየቅ ያለባቸው ጥያቄዎች ሁሉ ቀርበውላቸዋል? ሰዎችን የሚያናድዱ ወይም ፍረጃ ያለባቸው ቃላት ወይም አስተያየቶች ዘገባው ውስጥ ተካትተዋል? እነዚህ አስተያየቶች በሌሎች ሰዎች አስተያየት ሚዛን እንዲያገኙ ተደርጓል? በወንጀል ዘገባ ወቅት፣ የወንጀል ፈፃሚውን ወይም ተጎጂውን ዘር ወይም ባሕል ይሆን እየዘገብን ያለነው?

ግጭት አስወጋጅ ዘገባ
ግጭት አስወጋጅ ዘገባዎች ግጭት ውስጥ ያሉ ወገኖች ለማባበል የሚዘጋጁ ዘገባዎች አይደሉም። እውነታውን የሚሸሽጉም አይደሉም። ነገር ግን እውነታውን ግጭት እንዲቀሰቅስ ወይም እንዲያባብስ ሳይሆን፥ እንዲፈታ አድርገው የሚያቀርቡ ዘገባዎች ናቸው።

ስለሆነም በግጭት አስወጋጅ ጋዜጠኝነት ሥራ ውስጥ ጥሬ ሐቅ አይበቃም። ከዚህ ባሻገር ዘጋቢዎች የሚከተሉትን ነጥቦች ማረጋገጥ ይኖርባቸዋል። ግጭትን በግጭቱ ከተሳተፉት ወገኖች አንፃር ብቻ አለመመልከት፣ የግጭቱን ምንነት ለመናገር በልኂቃኑ ንግግር ላይ ብቻ አለመመርኮዝ፣ በግጭት ውስጥ ያሉ አካላትን ምን ሊያስማማቸው እንደሚችል ጠይቆ መዘገብ፣ የአንድ ወገን ጉዳት እና ስጋት ላይ ብቻ አለማተኮር፣ ጥቃትን ሳያሳንሱ ነገር ግን በስሜት የሚነዳ አተራረክን ማስወገድ፣ ወገንተኛ ቃላትን (እንደ አክራሪ፣ አሸባሪ፣ ፅንፈኛ… ያሉ ቃላትን) አለመጠቀም፣ አስተያየትን እንደ ሐቅ አለማቅረብ፣ ከአንድ ወገን ልኂቃን ብቻ መፍትሔ እንዲመጣ አለመጠበቅ ወሳኝ የግችጥ አስወጋጅ ጋዜጠኝነት መርሖዎች ናቸው።

ሙያተኝነት ወይስ አርበኝነት?
ግጭት አስተካይ ዘገባዎች በብዛት የሚዘጋጁት የአርበኝነት ሥሜታቸው ከሙያተኝነት ስሜታቸው የበለጠባቸው ሰዎች ነው። አርበኝነት ለወገንተኝነት ያጋልጣል። ወገንተኝነት ደግሞ የሌላውን ወገን ላለመረዳት እንቅፋት ይዳርጋል። ይህ በጋዜጠኞች ሲሆን ደግሞ ችግሩ የከፋ ይሆናል፤ ሌሎችም ሌሎችን እንዳይረዱ ያደርጋል። በኢትዮጵያ መሠረታቸውን የዘውግ አርበኝነት ላይ ያደረጉ ብዙኀን መገናኛዎች እና ጋዜጠኞች ባሉበት አገር ውስጥ ግጭት አስወጋጅ ዘጋቢዎችን ማፍራት በጣም አስቸጋሪ ነው። ሆኖም፣ የሚወግኑለትን ወገን ለማስጠበቅም ቢሆን ግጭቶች እና ነውጦችን ማስወገድ ጠቃሚ እንደሆነ ከግንዛቤ ማስገባት ጠቃሚ ይሆናል።

የዜና ክፍል ብዝኀነት
ብዙዎቹ የኢትዮጵያ የዜና ክፍል አርታዒዎች ስብስብ አንድ ዓይነት የፖለቲካ አመለካከት የያዙ ሰዎች የሚሰባሰቡባቸው በመሆናቸው ምክንያት ግጭት አስወጋጅ ዘገባዎችን መሥራት አስቸጋሪ ይሆንባቸዋል። ብዙዎቹ የዜና ክፍሎች የፆታ፣ የብሔር፣ የሃይማኖት እንዲሁም ሌሎችን በተመለከተ ስብጥራቸው ብዝኀነት ይጎድለዋል። በተጨማሪም ዘገባዎቹ የሚያጣቅሷቸው ሰዎች ከተለያዩ ቡድኖች የመጡ ሰዎች አይደሉም። በዘገባዎቹ የሚጠቀሱባቸው መንገድም አንዱ ቡድን በሌላው ላይ ያለውን ፍረጃ የሚያሳብቁ ናቸው። ይህ ዓይነቱ የብዝኀነት ጉድለት ለግጭት አባባሽ ዘገባ ያጋልጣል።

እንደ ሮስ ሀዋርድ፣ የዜና ክፍሎች ብዝኀነትን በተመለከተ በተደጋጋሚ የሚከተሉትን ጥየቄዎች ማንሳት ይጠበቅባቸዋል። በዘገባችን፣ ስለአንዱ ቡድን የምንዘግበው ስለሌላው ቡድን ከምንዘግበው አንፃር የሕዝብ ብዛቱን የሚመጥን ነው? ስለ ሕዳጣኖች የምንዘግባቸው ዘገባዎች በአንድ ጠርዝ የተሸሸገ ነው? ሌለኞቹ ወገኖች ጋር ከዜና ክፍሉ አባላት መካከል ማን የተሻለ እና ታማኝ ግንኙነት አለው? ከሕዳጣን አካባቢዎች የመጡ ዘጋቢዎች አሉን? አስፈላጊውን ሥልጠናስ አድርገንላቸዋል?

ዜናዎቻችን ብዝኀነትን የጠበቁ ለማድረግ መመሪያዎች አሉን?
በዚህ መልኩ የተዋቀረ የዜና ክፍል እና አርትዖት መርሕ እና የዘጋቢዎች ሥነ ምግባር ደንብ ከተዘጋጀ ብዙኀን መገናኛዎች ከግጭት አባባሽነት አዘቅት ወጥተው ማኅበራዊ ኀላፊነታቸውን አንድ ደረጃ ከፍ ባለ መንገድ ማበርከት ይቻላቸዋል።

በፍቃዱ ኃይሉ የሰብኣዊ መብቶች ተሟጋች እና ጸሐፊ ናቸው። በኢሜይል አድራሻቸው befeqe@yahoo.com ሊገኙ ይችላሉ።

ቅጽ 1 ቁጥር 52 ጥቅምት 22 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here