“ያልነገርኩህ” አስቀያሚው እውነት

0
1502

በየቀኑ በምትመላለስበት መሥሪያ ቤት አኳኋኗ ለብዙዎች ተለዋዋጭና ግራ አጋቢ ቢሆንም ምክንያቱን በግልጽ ያወቀ ሰው አልነበረም፤ እርሷም ብትሆን። በኋላ ግን በቤተሰቧ ይልቁንም ባሳደጓትና አብልጣ በምትወዳቸው አባቷ ምክንያት ወደ ሕክምና እንድትሔድ ይደረጋል። “አዕምሮዬን ልታከም” ብሎ ሕክምና መሔድ ቀርቶ ልታከም ብሎ ማሰቡ ራሱ ጭንቀት ይፈጥራልና በቀላሉ አልሔደችም። መሔዷ ግን ጥሩ መፍትሔን ሰጥቷታል፤ ይህንንም ተከትሎ በሕይወቷ የታዩ ለውጦች ፊልሙን ገንብተውታል። የዳንኤል በየነ “ያልነገርኩህ” ፊልም።

ያልነገርኩህ ፊልም መስከረም 29/2012 ነበር በዓለም ሲኒማ በድምቀት የተመረቀው። በእርግጥ ምርቃቱ ፊልሙ ለዕይታ እንደሚቀርብ ማብሰሪያ ሳይሆን በዓለም የአዕምሮ ጤና ቀን መከበሩን ምክንያት ያደረገ ነው። ፊልሙ ከወር በኋላ ለዕይታ እንደሚቀርብ አዲስ ማለዳ ከፊልሙ ደራሲና ዳይሬክተር ዳንኤል በየነ ጋር ባደረገችው ቆይታ ለማወቅ ተችሏል።

ታድያ ፊልሙ ስለምንድን ነው? ለተመልካቹ ምን ይዟል? የአገራችን የፊልም ዘርፍስ በጉዳዩ ላይ ምን ሠርቷል? የሚሉ ሐሳቦችም ከፊልም ባለሙያው ጋር የተነሱ ጉዳዮች ናቸው።

የአዕምሮ ጤና በፊልሞች
የአዕምሮ ጤና መታወክ ያጋጠማቸው ሰዎች ከሕመሙ በተጓዳኝ ከማኅበረሰበቡ የሚፈጠርባቸው ተጽዕኖ ቀላል አይደለም። ብዙዎቻችን በምንንቀሳቀስበት አካባቢና በየአቅራቢያችን አንድ የማኅበረሰቡ አካል ሆነን ካለማወቅ ያደረስነው ተጽዕኖም ጥቂት አይሆንም። ከአንድ ዓመት በፊት ቢቢሲ አማርኛ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሳይካትሪ ትምህርት ዘርፍ ክፍል አሶሺየት ፕሮፌሰር እንዲሁም አማኑኤል ሆስፒታል ለ12 ዓመታት ሐኪም ሆነው ያገለገሉትን ዶክተር ዮናስ ባሕረ-ጥበብ አነጋግረው ባስነበቡት ዘገባ፤ ከባድ የሚባል የአዕምሮ ሕመም ያለባቸው ሰዎች መደብደብ፣ መንገላታት፣ መታሰር እንዲሁም ከማኅበረሰቡ መገለል ይደርስባቸዋል።

መፍትሔዎችም ከመንፈሳዊ ቦታዎች የሚፈልጉ ሲበዙ ወደ ሕክምና የሚያመሩት ጥቂት መሆናቸውም በዘገባው ተጠቅሷል። ከዛም ባለፈ አንድ ሰው የአዕምሮ ሕመም አለበት ተብሎ መድኀኒት ፍለጋው የሚጀመረው ሕሙማኑ በራሳቸው ወይም በሰዎች ላይ ጉዳት ማድረስ ሲጀምሩ እንደሆነም የአዕምሮ ሐኪሙ አስረድተዋል። ጉዳቱ ይደርስብናል ብለው የፈሩ ደግሞ ከቤታቸው ያርቃሉ አልያም ያስሯቸዋል። ዶክተሩ እንዳሉት ታድያ፤ “ይሔ የሚሆነው ለአዕምሮ ሕሙማኑ ኀላፊነት የሚወስዱ ተቋማት እንዲሁም የመንግሥት አካላት ስለሌሉ ነው።”

ይህን ነገር የጥበብ ዘርፉም የተረዳው አይመስልም። በአዕምሮ ጤና ዙሪያ የተሠራው “ያልነገርኩህ” ፊልም ደረሲና ዳይሬክተር ዳንኤል በየነ እንደሚለው፤ ፊልም ሕዝብ ከፍሎ እየገባ ማየት የጀመረበት ጊዜ ጀምሮ ብዙ ተመልካች የነበረው የፍቅር አልያም አስቂኝ ዘውግ ያለው ፊልም ነው። ማኅበራዊ ጉዳዮችን የሚያነሱ ፊልሞችም ጥቂቶች ናቸው ይላል። ይሁንና “ፊልም የሕይወት ነጸብራቅ በመሆኑ የማያነሳቸው ጉዳዮች የሉም፤ ፊልሞች በሁሉም አቅጣጫ ሊሠሩ ይችላሉ” ብሏል።

ማኅበራዊ ጉዳይ ላይ ትኩረት ያደረገና ተጽዕኖ መፍጠር የቻለ ፊልምን መሥራትን በተመለከተም፤ በአገራችን የቴዎድሮስ ተሾመ “ቀዛቃዛ ወላፈን” የተሰኘው ፊልም ተጠቃሽ ነው፤ በዳንኤል ዕይታ። ይህ ፊልም ኤች አይ ቪ ላይ አተኩሮ የተሠራና ለተመልካች እያዝናና ትልቅ መልእክት ያስተላለፈ በመሆኑ በቫይረሱ ዙሪያ ግንዛቤ ለመስጠት አግዟል ሲልም ያክላል።

ከአዕምሮ ጤና ጋር በተያያዘ ግን ፊልሞች በዚህ ደረጃ እንኳ እንዳልተሠሩ ዳንኤል ያወሳል። በዚህም ላይ ኢትዮጵያ ውስጥ በአዕምሮ ጤና ዙሪያ የተሠሩ ፊልሞች ቢኖሩም እንኳ አሉታዊ ጎናቸው ያመዘነ ነው። ይልቁንም ከአዕምሮ ጤና መታወክ ጋር የሚፈጥሯቸውን ገጸ ባሕርያት ማዝናኛ እና ማሳቂያ ያደርጓቸዋል። ይህ በመሆኑና ግንዛቤ የሚሰጡ ባለመሆናቸው የአዕምሮ ሕመምንና ሕሙማንን በአካል ወይም በእውኑ ዓለም የሚመለከት የፊልም ተመልካችም አውቆትም ይሁን ሳያውቀው በፊልሞች ላይ በሚመለከተው መልኩ የሚያስተናግድ ወይም ግብረ መልስ የሚሰጥ አድርጎታል።

ይህንን የተገነዘቡት የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ሥነ አዕምሮ ትምህርት ክፍል እና የአዕምሮ ጤና ክብካቤ ማኅበር ከካናዳ ሥነ አዕምሮ ዩኒቨርስቲ ጋር በመተባበር አንድ ሥልጠና አዘጋጅተውም ነበር። በዚህ ሥልጠና ላይ ተሳታፊ የነበረው ዳንኤልም ቀድሞ በቆየበት የፊልም ጥበብ ዘርፍ በጉዳዮ ላይ አስተዋጽዖ ማድረግን መሠረት አድርጎ፤ ከሰማውና ካየው ተነስቶ “ያልነገርኩህ” ፊልምን ሊያዘጋጅ እንደቻለ ለአዲስ ማለዳ ገልጿል።

የ”ያልነገርኩህ” መነሻዎች
“ከሥልጠናው ውስጥ ትኩረቴን የሳበው አዕምሮ ጤና ሕሙማን ላይ የሚደረሰው መገለል ነው” ይላል ዳንኤል። የአዕምሮ ሕሙማን አደባባይ ላይ የወጡም ሆነ ያልወጡ፣ ጸበል ቦታ በሰንሰለት ታስረው ያሉም አሉ። እነዚህ ሰዎች ከሰማይ የወረዱ ሳይሆኑ አንድ ወቅት የራሳቸው ቤትና ቤተሰብ የነበራው ናቸው፤ ይህም ማንም ሰው ሕመሙ እንደማያጋጥመው ዋስትና የማይሰጠው ጉዳይ እንዲሆን ያደርገዋል።

ታድያ የአዕምሮ ሕሙማን በተለይም መንገድ ላይ ያሉት ሕይወታቸው የሚያልፈው በረሃብ ምክንያት ነው። ለምን ቢባል ማን ቀርቦ ምግብ ሰጥቷቸው? ማኅበረሰቡም ይሸሻቸዋል፤ እነርሱም ለምኖ እንደሚበላ የኔ ቢጤ ምግብ ስጡኝ ብለው አይጠይቁም። ይህ በሥልጠናው ወቅት ጥናትን መሠረት አድርጎ የቀረበ ሐሳብ የበለጠ መንፈሱን እንዳስጨነቀውና እንዳሳዘነው ዳንኤል ያስታውሳል።

ከዛም ባለፈ ደግሞ የአዕምሮ ሕመም እንዳለባቸው አውቀው ነገር ግን መገለሉን ፈርተው ሳይናገሩ ሥራቸውን እየሠሩና ከሰው መካከል እየተንቀሳቀሱ የሚኖሩ ሰዎችም አሉ። ለእህት ለወንድም ቀርቶ ለትዳር አጋር እንኳ ሕመማቸውን ሳይናገሩ ሕክምና እየተከታተሉና መድኀኒት እየወሰዱ የሚኖሩ ማለት ነው። ይህም ለፊልሙ ቀጥተኛ መነሻ ሆኖ ገጸ ባሕሪ ግንባታ ላይም ግብዓት የሆነ ሐሳብ ሆኖ ፊልሙ ተሠርቷል።

ዳንኤል እንዳለውም በተጨማሪም ያገኘው እውነተኛ ታሪክ የበለጠ ያገዘው ነው። “ይህን ሐሳብ ይዤ ሳለ አንድ እውነተኛ ታሪክ አገኘሁ፤ በዚህ ሕይወት ውስጥ ያለፈች ባንክ ውስጥ የምትሠራ ሴት ናት። እናም የዚህችን ሴት እውነተኛ ታሪክ መሠረት አድርጌ ያሰባሰብኳቸውንና ከሕክምና ባለሙያዎች ያገኘሁትን ሐሳብ አጣምሬ የፊልሙን ጽሑፍ አዘጋጀሁ” ዳንኤል እንደተናገረው።

በፊልሙ ላይ አንጋፋ እንዲሁም አዳዲስ ተዋንያን ተሳትፈዋል። ፊልሙን በአዕምሮ ጤና ክብካቤ ማኅበር ወጪው ሲሸፈን አብዛኖቹ ተዋንያን በአነስተኛ ክፍያ እንደሠሩና ማኅበራዊ ግዴታቸውን እንዳስቀደሙ ዳንኤል ገልጿል። ከዛ ውጪ ወጪው ይበልጥ ወደ ፕሮዳክሽኑ ያተኮረና ፊልሙም ጥራቱንና ደረጃውን ጠብቆ የተሠራ መሆኑን ጠቅሷል። ዳኝነቱ ለተመልካች የሚተው ሆኖ፤ ማጀቢያ ሙዚቃ ለራሱ ለብቻ (ኦሪጅናል) መሠራቱንም አንስቷል።

“ያልነገርኩህ” ፊልም በሚቀጥለው አንድ ወር ውስጥ በተመረጡ ሲኒማ ቤቶች ለዕይታ ሲቀርብ በአገራችን ከሰላሳ በላይ በሆኑ ከፍተኛ የመንግሥት የትምህርት ተቋማት በነጻ እንዲታይ እቅድና በጀት ተይዟል። በተጨማሪም ፊልሙ ዓለም ዐቀፍ በሆኑ ሦስት ፊልም ፌስቲቫሎች ላይ ለመቅረብ ታጭቷል። አንደኛው የአዕምሮ ጤና ላይ ብቻ ያተኮሩ ፊልሞች የሚቀርቡበት ፌስቲቫል ነው። ይህም ስኮቲሽ ኢንተርናሽናል ሜንታል ሔልዝ ፈልም ፌስቲቫል ሲባል፤ በስኮትላንድ የሚካሔድ ነው።
ኹለተኛው ቶሮንቶ ላይ ራንዴቩ የሚባል ፊልም ፌስቲቫል ነው፤ ይህም የአዕምሮ ጤና ላይ ያተኮረ ሲሆን፤ ሦስተኛው ፓን አፍሪካን የሚባል አሜሪካ ሎስ አንጀለስ የሚዘጋጅ ነው። “ያልነገርኩህ” ፊልምም በዚህ ፌስቲቫል ላይም ሊታይ እንደታጨ ነው ዳንኤል የገለጸው።

ከዚህ ቀደም የተሠሩ ፊልሞች
ምንም እንኳን ከአዕምሮ ጤና ጋር በተያያዘ የተነቀፉ፣ የተወገዙና ያከራከሩ፤ የጤና ባለሙያዎችን ያስቆጡ የፊልም ሥራዎች ቢኖሩም በአንጻሩ ጥሩ መልዕክትን ያስተላለፉ እንዳሉ ዳንኤል ያነሳል። ለምሳሌም የብርሃኔ ጌታቸው (ሐረግ) “ኅርየት”፣ በቴዎድሮስ ፈቃዱ ተጽፎ በተስፋዬ ክንፈ ዳይሬክት የተደረገው “አብሮ አበድ” እንዲሁም ዳንኤል በየነ ራሱ ያዘጋጀው “የመሃን ምጥ” እና ቀደም ብሎ የሠራው የመጀመሪያ ፊልሙ “መንታ ነፍስ” የሚጠቀሱ ናቸው።
በዚሁ ውስጥ “መባ” የተሰኘው የቅድስት ይልማ ፊልም አለ። ነገር ግን ይህ ፊልም ለዕይታ በቀረበበት ጊዜ የአዕምሮ ሕመምን በተመለከተ ያለውን የአመለካከት ችግር የሚያባብስ በሚል በተለያዩ የሕክምና ባለሙያዎች ቅሬታ የተነሳበት እንደነበር ይታወሳል። ይህም ምን አልባት የሕመሙን አሉታዊ ጎን ካሳዩት መካከል የሚጠቀስ ሳይሆን አልቀረም።

ዳንኤል በበኩሉ በአዕምሮ ጤና ክብካቤ ማኅበር በኩል ካገኘው ሥልጠና ቀደም ብሎም በ2000 ለመጀመሪያ ጊዜ የሠራው “መንታ ነፍስ” ፊልም ከአዕምሮ ጤና ጋር የተያያዘ ነበር። ይህም እርሱ በጉዳዩ ላይ ቀደም ብሎ ትኩረት ይሰጥ ስለነበር እንደሆነ ነው ለአዲስ ማለዳ የገለጸው።
“በፊትም ሥነ ልቦናዊ (‘ሳይኮሎጂካል ትሪለር’) ፊልምን ማየት እመርጣለሁ። “ዘ ብዩቲፉል ማይንድ” በብዙ መልኩ ሕይወቴን የቀየረው ፊልም ነው፤ ታሪክ ነገራውና መሰል የፊልሙ አሠራር ተጽዕኖ ሳይፈጥርብኝ አልቀረም” ብሏል።

ስለ ዳንኤል
ዳንኤል የመጀመሪያ ዲግሪውን ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ በቢዝነስ አድሚንስትሬሽን አግኝቷል። ሥራውን የጀመረውም ባንክ ውስጥ ሲሆን በባንክ ለዐሥር ዓመት አገልግሏል። “በዛ ቆይታዬ ፊልም መሥራት እፈልግ ነበር። ዩኒቨርሲቲ ከመግባቴም በፊት ብዙ ፊልም እከታተል ነበር፤ መጽሐፍትንም አነባለሁ። በተለይ ልብ ወለድ መጻሕፍትን ሳነብ በዐይነ ሕሊናዬ እስላቸው ነበር። ይህም ወደ ፊልም አቅርቦኛል” ሲል ያስታውሳል።

ቀስ በቀስ ፊልም እንዴት እንደሚሠራ እያወቀና እየተረዳ ሲሔድ ታድያ መሥራት እንደሚችል በማመን ወደ ሥራው ገባ። ቀድሞም ክርኤቲቭ የፊልም ሙያ ማሠልጠኛ በመግባት መነሻ የሚሆነውን ትምህርት ወሰደ። ከዚህ በኋላ ነው የመጀመሪያ ፊልሙን “መንታ ነፍስ” ሠርቶና አጠናቆ፤ በራሱ ፕሮድዩስ አድርጎ በ2000 ለዕይታ ያበቃው።

የመጀመሪያ ፊልሙ ራሱን ችሎለት፤ ወጪውንም ሸፍኖለታል፤ አላሳፈረውም። “ያ ፊልም በመላው ኢትዮጵያ ታይቷል። ፊልም ሠሪ መሆን እንደምችልም ያረጋገጥኩበት ፊልም ነው” ሲል ነው ዳንኤል የገለጸው። ነገሩ የተሻለ ዕድልን ይዞለት የመጣም ይመስላል። “ያኔውኑ ለዓለም ዐቀፍ ፊልም ፌስቲቫል ፊልሙን ላኩኝ፤ የዛኔውኑ ደውለውልኝ ፊልሙ ተመርጧል መጥተህ አሳይ ተባልኩኝ” አለ፤ ይህም ልምዱን እንዲያሰፋ እድል የፈጠረለት ሲሆን በሎስ አንጀለስ የተካሔደ የፊልም ፌስቲቫል ነው።

ዳንኤል መለስ ብሎ እንዲህ አስታውሷል፤ “በፌስቲቫሉ ከ167 ፊልሞች አካባቢ ነበር በማጣሪያው ያለፉት የተደረጉት። በአንድ ጊዜ 4 ፊልሞች በተለያዩ ክፍሎች ነበር የሚታዩት፤ አንድ ፊልም አቅራቢ ሰው ገብቶ ፊልሙን እንዲያይለት ለማድረግ በር ላይ ሆኖ ታሪኩን በመንገር ማሳመን ይጠበቃል። እኔም በማሳመኔ ብዙ ሰው አየልኝ፤ እናም ዓለም ዐቀፍ ምርጥ የተመልካቶች ሽልማት (‘ኢንተርናሽናል ቤስት ኦድየንስ አዋርድ’) አስገኝቶኛል።”

በአሜሪካ አምስት ወር ቆይቷል። በዛው የመቅረትና ያለመቅረት ጉዳዮም ፈትኖት እንደነበር ያስታውሳል። የተለያዩና ብዙ ሰዎችንም አማክሯል። ሁሉም ታድያ ፊልም መሥራት ከፈለገ አገሩ መመለስ እንዳለበት ነገሩት። “ስለዚህ አገሬ መመለስን መረጥኩ፤ ሕልሜ በፊልሙ ስኬት ማግኘት እንጂ አሜሪካ መኖር አይደለም ብዬ ነው የማስበው” ሲል ገልጾታል።

ዳንኤል ሦስት ፊልሞችን ጽፎ ሲያዘጋጅ “ጽኑ ቃል” የተሰኘውን ፊልም ዳይሬክት በማድረግ ተሳትፎ ነበረው። በድምሩም አራት ፊልሞች ላይ አሻራውን ማሳረፍ ችሏል። ባለፈው ዓመት 2011 ላይም በፊልም ፕሮዳሽን ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ኹለተኛ ዲግሪውን የጨረሰ ሲሆን፤ የመመረቂያ ጽሑፉን የሠራው ከአዕምሮ ጤና ጋር በተያያዘ ነበር።

“በአዕምሮ ጤና ዙሪያ ብዙ መሥራት እፈልጋለሁ። በሌላው ዓለም የፊልም ባለሙያ ዎች የየራሳቸው ዘውግ አላቸው። በአንዱ ላይ መሠልጠን ጥሩ ነውና እኔም ይህን ዘርፍ መርጫለሁ” ዳንኤል ብሏል።

ስለ ኢትዮጵያ ፊልም
የኢትዮጵያ ፊልም ችግር አለበት የሚለው ዳንኤል እነዚህን ችግሮች በኹለት ነጥብ ያስቀምጣቸዋል። “የመጀመሪያው ግንዛቤና እውቀት ማነስ ነው።” እንደ ዳንኤል ገለጻ። በዘመናዊ ተንቀሳቃሽ ስልክ ፊልም እየተሠራ ያለበት ጊዜ መሆኑን አስታውሶ፤ ጉዳዩ ስለ መሣሪያው ብቻ ሳይሆን ትንሹን ታሪክ ፊልም አድርጎ የማውጣት አቅምም ነው ይላል።

ኹለተኛ ያደረገው የስርዓት አለመኖርን ነው። “የፊልም ሥራ ስርዓት አለው፤ እኛ ጋር ግን የለም” ሲል ይጀምራል። በፊልም ሥራ ላይ የሚሳተፍ ሁሉ የየራሱ ድርሻና ተግባራትም የየራሳቸው ከዋኞች ሊኖራቸው ቢገባም ይህ በኢትዮጵያ ፊልሞች ላይ በብዛት አይታይም። ይህ ቢስተካከል ኢትዮጵያ ብዙ ታሪክ ያላት አገር ናት በዛም ላይ ተመልካች በደንብ አለ ባይ ነው። “ሕዝብ ጥሩ ፊልም ከቀረበለት ወጥቶ ያያል። ጥበብ አድናቂና ወዳጅ ነው። ይሔ ጉድለት ስላለ ነው በሚፈለገው መጠን እየሔደ ያልሆነው።”

ዳንኤል በፊልም ሥራ ውስጥ የተለየ ዕይታ አምጥቷል ብሎ የሚያስበውና የሚያደንቀው ተዋናይ ግሩም ኤርምያስን ነው። የፊልም ዳይሬክተር ያሰበውን ወደ ፊልም ማምጣት ፍላጎቱ ሆኖ ሳለ ይህን በአዕምሮ የታሰበን ምስል በማውጣት ብሎም ከዛም በላይ በማሳየት ግሩም ኤርምያስ ጥሩ ምሳሌ እንደሚሆንም ያነሳል።

የዳንኤል መልዕክት ይህ ነው፤ “ፊልም የሚፈልጉትን መናገሪያ ዘዴ ነው። ግን ለበጎ ልንጠቀምበት ይገባል የሚል አመለካከት አለኝ። ይህ ማለት ፊልም ለልማት የሚል አስተሳሰብ ሳይሆን ሐሳብን በአግባቡ ማስተላለፍ የሚቻልበት መንገድ ነው። በተለያዩ ጉዳዮች ላይም መሥራት ይቻላል። ፊልምን የሚተካ ዓውድ ያለ አይመስለኝም፤ ኀይልና አቅም ያለው ነውና ያለአግባብ እንዲባክን መደረግ የለበትም”

ቅጽ 1 ቁጥር 52 ጥቅምት 22 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here