የኢትዮጵያ ዲፕሎማሲ በስሜትና በብልሃት ጎዳና

0
1332

የኢትዮጵያ ዓለም ዐቀፍ ግንኙነት ጉዳዮች ከዲፕሎማቶቿ አልፎ የሁሉም ዜጋ አጀንዳ የሚሆኑበት አጋጣሚ እየተበራከተ መጥቷል። አንዳንዴ በሰልፎች ላይ የተለያዩ መፈክሮች ከዚህ አንጻር ይስተጋባሉ። ይዘታቸው አሉታዊም አዎንታዊም ነው፤ ፉከራና ነቀፋም አልጠፋቸውም።

ሌላ ጊዜ አንዳንድ የክልል ፕሬዝዳንቶችና ሚኒስትሮችም በሕዝባዊ መድረኮች ብሎም በመገናኛ ብዙኀን በሚያደርጓቸው ንግግሮችና በሚያወጧቸው ጽሑፎችም አንዳንድ አገራትን ሲዘልፉ ይስተዋላል። የአክቲቪስቶችና ተጽዕኖ ፈጣሪ ሰዎች የማኅበራዊ ሚዲያ ድምጾችም በተመሳሳይ ይዘቶች ይስተዋላሉ።

የእነዚህ ሁኔታዎች ድምር ውጤት በዲፕሎማሲው መድረክ ተጽዕኖ አለው? ከኖረውስ አሉታዊ ወይስ አዎንታዊ? ኢትዮጵያ የዓለም ዐቀፉ ማኅበረሰብ ትኩረት በሆነችበት በዚህ ወቅት የዜጎች እና ተጽዕኖ ፈጣሪ ግለሰቦች የዘርፉ ተሳትፎስ ምን መምሰል አለበት?

እነዚህንና ተያያዥ ጥያቄዎችን ይዛ አዲስ ማለዳ ያነጋገረቻቸው የዘርፉ አዋቂዎች ሁኔታውን በተለያየ መንገድ ተንትነውታል። በደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ሳይንስና ዓለም ዐቀፍ ግንኙነቶች መምህር ዳምጠው ተሰማ (ረ/ፕሮፌሰር) በተለይ የምዕራቡ ዓለም የዲፕሎማሲያዊ ስለላ (ኢንተለጀንስ) አሠራር 80 በመቶ መረጃ የሚሰበስቡት ከአደባባይ ምንጮች ነው ይላሉ። ይህም መሪዎች ወይም ፖለቲከኞች እና የአገሪቱ ተጽዕኖ ፈጣሪዎች በተለያዩ መድረኮችና ብዙኀን መገናኛዎች የሚያድርጓቸውን ንግግሮች፤ በማኅበራዊ ሚዲያዎች ወይም በሕዝባዊ ሰልፎች በስፋት ተደራሽ የሆኑ መልእክቶችን ይጨምራል።

ከእነዚህ ግምገማዎች በመነሳት አገራት የብሔራዊ ጥቅማቸውን ጉዳይ ያሰላሉ፣ አቋምም ሊይዙ ይችላሉ። ይህም ከዛ አገር መንግሥት ጋር በሚኖራቸው ግንኙነት ላይ አሉታዊ ወይም አዎንታዊ ውጤት ሊያስከትል ይችላል ይላሉ።

የባለሥልጣናትን ጨምሮ መደበኛ የዲፕሎማሲ መድረክ ባልሆነ መንገድ የሚሰሙ ሕዝባዊ አስተያየቶች ከአገር ውስጥ ፍጆታነት አልፈው አዎንታዊ በሆነ መንገድ የአንድ ሌላ አገርን የውጪ ግንኙነት ፖሊሲ ማስቀየር ላይ እምብዛም ተጽዕኖ የላቸውም የሚሉት ደግሞ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በዘርፉ የፒ ኤች ዲ ተማሪ የሆኑት የዓለም ዐቀፍ ግንኙነቶች ባለሙያ ጉተማ ዳንኤል ናቸው።

እንደ ጉተማ አገላለጽ፣ እነዚህ ሕዝባዊ አስተያየቶችና ከመደበኛው ዲፕሎማሲ መስክ ውጪ ያሉ ባለሥልጣናት የሚያስተጋቧቸው መልእክቶች፣ አሉታዊ በሆነ መንገድ ግን ሌሎች አገራት ከአገሪቱ ጋር ያላቸውን ግንኙነት ሊጎዳ ይችላል ይላሉ። ይህ የሚሆነውም መንግሥታት መደበኛ በሆነው የዲፕሎማሲ መስክ ለማለት የከበዳቸውን በእነዚህ ኢ-መደበኛ መንገዶች እያስተጋቡ እንደሆነ የሚወሰድ በመሆኑ ነው።   በአብዛኛው በኢ-መደበኛ መንገዶች የሚንጸባረቁ አቋሞች በዘፈቀደ የሚመጡ ሳይሆን ታስቦበት እና ተሠርቶበት ሕዝብ እንደዛ እንዲያስብ ተደርጎ ነው ተብሎ የሚወሰድ በመሆኑ ነው ይላሉ።

ዳምጠው በበኩላቸው፣ ዲፕሎማሲ ዓላማው ጠቅለል ሲል ጠላትን መቀነስ እና ወዳጅን ማብዛት ሲሆን፣ ይህን በማድረግም የአንድ አገር ሕዝብ ሊያሳካው የሚፈልገውን ርዕይ ወይም እንዲኖረው የሚፈልገውን ስኬት ከግብ ለማድረስ የሚያስፈልጉ የኢኮኖሚ፣ የሳይንስና ቴክኖሎጂ እንዲሁም መሰል ጥቅሞችን ማስገኘት ነው ይላሉ።

ያለፉ ቁርሾዎችም ሆኑ ሌሎች ሁኔታዎች እንደ ግለሰባዊ ግንኙነት ብዙም ተጽዕኖ ሳያደርጉበት አገራዊ ሕልውናን ለማስጠበቅ፣ የግዛት አንድነትን ለማስከበር፣ ደኅንነት፣ የኢኮኖሚ ልማትን ለመሰሉ ብሔራዊ ፍላጎቶች ሊጠቅም የሚችልን የትኛውንም አካል ወዳጅ ማድረግ የአሁናዊ ዲፕሎማሲ ተግባር መሆኑን ዳምጠው ይናገራሉ። ይህ ሁኔታም መንግሥታት ቋሚ የሚባል ወዳጅም ሆነ ጠላት እንደሌለ አስበው እንዲንቀሳቀሱ ያደርጋቸዋል።

በመሆኑም፣ ዲፕሎማሲ በየዘርፉ ከስሜት ይልቅ በምክንያታዊነት ላይ ተመሥርቶ የሚካሔድ ነው ይላሉ። ከኢ-መደበኛ አሠራሮች ይልቅ ታስቦ እና ታቅዶ የሚሠራባቸው መደበኛ የዲፕሎማሲ ተቋማትና የሰው ኃይል የሚያስፈልጉትም ለዚሁ መሆኑን ይናገራሉ። ከዚህ መደበኛ መንገድ ውጪ የአገሪቱን የውጪ ግንኙነት በሚመለከት የሚስተጋቡ ድምጾች በአግባቡ ካልተመሩ የሚፈለገውን ውጤት ሊያስቱ እንደሚችሉ ያሰምሩበታል።

የፖለቲካ ሳይንስና ዓለም ዐቀፍ ግንኙነቶች ባለሙያ ረቡማ ደጀኔ ደግሞ፣ በኢትዮጵያ የተከሰተውን ጦርነትና የሰላም እጦት ተከትሎ ኢትዮጵያ የዓለም ዐቀፉ ማኅበረሰብ ትኩረት መሆኗን በማውሳት ይጀምራሉ። እንዲህ ባለው የቀውስ ወቅት የዲፕሎማሲና ዓለም ዐቀፍ ግንኙነት ሥራዎቻችን በጥንቃቄ መታየት አለባቸው ይላሉ። ረቡማ እንደሚሉት በተለይ የምዕራቡ ዓለም ኢትዮጵያን በሚመለከት እያራመደ ያለው አቋም በአመዛኙ ፍትሐዊነት የጎደለው እና ከስሁት ትንታኔዎች የሚመነጭ አቋም መሆኑን ያወሳሉ።

አሜሪካም ሆነች እንደ አየርላንድ ያሉ አገራት ኢትዮጵያን በሚመለከት እያራመዱት ያለው አቋም ከተናጥል ይልቅ የምዕራቡን ዓለም የፖሊሲ አቅጣጫን የሚወክል ነው ያሉት ረቡማ፣ ምዕራባዊያኑ በአንድ አገር ውስጥ ቀውስ ባጋጠመ ቁጥር ማእቀብ እና ጣልቃ ገብነትን እንደ ዋና መሣርያ አድርገው ይወስዳሉ። ይህ ዓይነቱ እርምጃ ስህተት ለመሆኑ የእስካሁኑ የሶርያ፣ ደቡብ ሱዳን እና መሰል ቀውሶች ላይ ካደረጉት እርምጃ መመልከት ይቻላል ይላሉ።

እንደ ረቡማ አገላለጽ፣ እንዲህ ላለው የምዕራባዊያን ኢ-ፍትሐዊ አካሔድ አስተዋጽኦ ያደረጉ ከሚመስሉ ሁኔታዎች አንዱ አገራቱ ውሳኔዎቻቸው በጠራ ትንታኔ ላይ አለመመሥረቱ ነው። ኢትዮጵያን በሚመለከትም የተመድ የጸጥታው ምክር ቤት በተደጋጋሚ ስብሰባ ማድረጉን እና የአሜሪካ መንግሥት ያስተላለፋቸውን ውሳኔዎች እንደ አብነት ያነሳሉ። ማእቀቦችና ውሳኔዎቹ ከዚህ በፊት በሌሎች በርካታ አገራት ላይ እንደተደረጉት የሚባለውን ተፈላጊ ውጤት ከማምጣት ይልቅ ውስብስብ የሆነውን ቀውስ የበለጠ የሚያባብስ ነው ይላሉ።

የአሜሪካ መንግሥት በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ ባቀረበው ኤች አር 6600 የውሳኔ ሐሳብ ጉዳይም እንደ መነሻ ምክንያትነት ከተጠቀሱ ጉዳዮች አንዱ፣ የኢትዮጵያ ባለሥልጣናት በተለያዩ መድረኮች ያደረጓቸው ንግግሮች መሆናቸውን ይጠቅሳሉ፡፡ እንዲህ ባሉ የቀውስ ጊዜያት ሰፊ ተደራሽነት ሊኖራቸው በሚችል ሕዝባዊ መድረኮችም ሆኑ በአንዳንድ ባለ ሥልጣናት የሚስተጋቡ መልእክቶች በዲፕሎማሲው መድረክ እንደ ግብዓትነት ሊወሰዱ የሚችሉ መሆናቸውን አጽንዖት ይሰጣሉ።

በመሆኑም፣ ስሜት መር የሆኑ አስተያየቶች እና የብሽሽቅ የሚመስሉ ንግግሮች በኢትዮጵያ ዲፕሎማሲና ዓለም ዐቀፍ ግንኙነቶች ውስጥ ፋይዳ የሌላቸው መሆኑን ተረድቶ ምክንያታዊ የሆኑ ትክክለኛ ጥያቄና ፍላጎቶቻችንን ማንጻባረቅ እንደሚገባ ያሰምሩበታል።

አሁን አሁን ከዲፕሎማሲያዊ ሽኩቻዎችና ጫናዎች የተነሳ የምዕራቡ ዓለም በሕዝባዊ አስተያየቶች በከፍተኛ አሉታዊነት ሲነሳ ይስተዋላል። ይሁን እንጂ ኢትዮጵያ ከዳግማዊ አፄ ምኒልክ ዘመን ጀምሮ ገለልተኛ የዲፕሎማሲ (Non-Alignment) መንገድን እንደምትከተል የገለጹት ፕሮፌሰር ዳምጠው፣ ይኼው ሁኔታ በቀዳማዊ አፄ ኃይለሥላሴ ዘመነ መንግሥት ይበልጡን በመደበኛ አቋም የተገለጸ እንደሆነ ይናገራሉ።

በደርግ ዘመን ግን ሥርዓቱ ካነገበው ርዕዮተ ዓለም የተነሳ ወደ ምሥራቁ ክንፍ የማዘንበል ሁኔታ ነበር። ድኅረ ደርግ እና አሁን ባለንበት ሁኔታም ኢትዮጵያ ከዚኽኛው ጎራ ናት ተብሎ የሚያስፈርጅ የዲፕሎማሲ አቅጣጫ እንደሌላት ይናገራሉ።

እንደ ጉተማ አገላለጽ ግን፣ ከቀዳማዊ አፄ ኃይለሥላሴ ዘመነ መንግሥት ጀምሮ የኢትዮጵያ የውጪ ግንኙነት ከማንም ጋር ያልወገነ ነው የሚባለው በመርህ ደረጃ ይኑር እንጂ የንጉሡ ዘመን አካሔድ ወደ ምዕራቡ ዓለም ያደላ ነው። ደርግ ደግሞ ይበልጥ ወደ ምሥራቁ ጎራ ያመዘነ ነው። አሁናዊው ዓለም ግን ምሥራቅና ምእራብ ብቻ ተብሎ ለመክፈል አሰላለፉ የተመቸ አይደለም። አሁናዊውን የኢትዮጵያ የዲፕሎማሲ መንገድ ጉተማ ‹ፕራግማቲክ› የሚባለው አካሔድ የበለጠ ይገልጸዋል ይላሉ።

በመርህ ከታሰረ ወዳጅነት ይልቅ ብሔራዊ ጥቅምን ለማስጠበቅ በሚያስችሉ ሁኔታዎች ላይ በመመርኮዝ ከሁሉም ጋር ተባብሮ ለመሥራት ክፍት የሆነ ነው ይላሉ። ይህ አካሔድ በተለይ ከፍተኛ ሽኩቻን እያስተናገደ ባለው የዓለም የኃይል አሰላለፍ ውስጥ ጠቃሚ ቢሆንም በመደበኛ ዲፕሎማሲ ዘርፍ ውስንነቶች እንደሚታዩ ይገልጻሉ።

ጉተማ በሰጡት አስተያየት ኢትዮጵያ በአንጻራዊነት ከዚህ ቀደም የተሻለ ጥንካሬ ነበራት ባይ ናቸው። ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ግን በመደበኛው የዲፕሎማሲ አሠራር መሠራት የነበረባቸው ሥራዎች ባለመሠራታቸው የኢትዮጵያ የውጪ ግንኙነት አሁን ድረስ የሚስተዋለው ችግር እንደገጠመው ይናገራሉ። በሕዝብ ክንፍ (ፐብሊክ) ዲፕሎማሲ ዘርፍም ቢሆን መደበኛ በሆነው የዲፕሎማሲ ተቋም በመታገዝ የሚሠሩ ሥራዎች እምብዛም አይስተዋሉም ያሉት ጉተማ፣ ‹‹የሕዝባዊ ዲፕሎማሲያችን ከትዊተር ዘመቻ እና ከተወሰነ ክበብ ያልወጣ በመሆኑ ብዙ ሥራ የሚጠበቅበት ነው›› ይላሉ።

በዚህ ሐሳብ ረቡማም ይስማማሉ። ብዙውን ጊዜ ለችግሮቻችን ከውጪ በተለይ ምዕራባዊያንን ተጠያቂ የማድረግ ችግር አለ የሚሉት ረቡማ፣ ‹‹ከምዕራባዊያን በኩል በእርግጥም በርካታ ችግሮች ቢኖሩም እኛም ደግሞ የሠራናቸውን ስህተቶች መለስ ብሎ ማየት ያስፈልጋል›› ሲሉ አጽንዖት ይሰጣሉ።

ለአብነትም የፖለቲካ ሪፎርም ከተደረገ በኋላ ኢትዮጵያ ከምዕራባዊያን አገራትና ከዓለም ዐቀፍ ተቋማት ጋር የነበራት ግንኙነት ወደ ጠንካራ ትብብርና አዎንታዊነት ተመልሶ የነበረ ሲሆን፣ የሰሜኑ ጦርነት እንደተፈጠረ ግን ይህ ግንኙነት መበላሸቱን እና ማእቀቦችን እስከመጣል እንደደረሰ ግንኙነቱ ፈጣን አሉታዊ ለውጥ እንዳደረገ ይናገራሉ። ‹‹ታድያ ሁኔታዎች እዚህ ደረጃ እንዲደርሱ የሠራናቸው ስህተቶች ምንድን ናቸው፣ ሳንሠራ የቀረናቸው የቤት ሥራዎቻችንስ ምን ነበሩ ብሎ መጠየቅ ይገባል›› ይላሉ።

ሦስቱም ባለሙያዎች የሚስማሙት ዜጎች በአገራቸው የውጪ ግንኙነት ዙርያ ንቁ የሆነ ክትትልና ትኩረት ሲኖራቸው ፋይዳው ብዙ መሆኑን ነው። የአንድ አገር ዜጎች በአገራቸው ሉዓላዊነት እና ብሔራዊ ጥቅሞች ላይ የሚደረጉ ማናቸውም የውጪ ጣልቃ ገብነቶች ላይም ድምጻቸውን ማሰማት እና ማውገዝም ሆነ የመከላከል መብትም ግዴታም አላቸው።

ይሁን እንጂ ዲፕሎማሲና ዓለም ዐቀፍ ግንኙነት የራሱ የሆነ ሜዳና የአጨዋወት ስልትና ሕጎች ያሉት በመሆኑም ሙያዊ የሆነ ክህሎት ይጠይቃል። ከዚህ አንጻር እንደ ሕዝብ በማኅበራዊ ሚዲያዎችም ሆነ በሰልፎች ላይ የሚስተጋቡ መልእክቶች በእውቀት እና ምክንያታዊነት መመራት ይገባቸዋል። የውጪ ግንኙነቱ በቀጥታ ከሚመለከታቸው በመለስ ያሉ ባለሥልጣናትም ስሜታዊ ሆነው በአደባባይ የሚያደርጓቸው ንግግሮች ገደብ ሊኖራቸው ይገባል ይላሉ፤ እስካሁን በዘርፉ የሚስተዋለው ክፍተት ቀላል እንዳልሆነ በማውሳት።


ቅጽ 5 ቁጥር 209 ጥቅምት 26 2015

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here