በመከነው የከፍተኛ ፍርድ ቤት ሕንጻ መገንቢያ ይዞታ ላይ ፓርላማ ጣልቃ እንዲገባ ተጠየቀ

0
1161

ከንቲባዋ በውይይት ቀጠሮ ላይ አልተገኙም

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ባመከነው የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ባለ 19 ወለል ሕንጻ መገንቢያ የይዞታ ማረጋገጫ ካርታ ላይ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጣልቃ እንዲገባ ተጠየቀ።

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሕግ፣ ፍትሕ እና ዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ፣ ከፍተኛ እና ጠቅላይ እንዲሁም የሸሪዓ ፍርድ ቤቶችን የ2015 በጀት ዓመት እቅድ እና የመጀመሪያ ሩብ ዓመት የሥራ ክንውን ላይ ጥቅምት 23/2015 ውይይት እና ግምገማ አካሂዷል። በውይይት መድረኩ ላይ የፌዴራል ከፍተኛ የፍርድ ቤቱ ሕንጻ መገንቢያ ቦታ ካርታ የገጠመው ችግር ላይ ምክር ቤቱ እንዲያግዝ የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ፕሬዝደንት ብርሃነመስቀል ዋጋሪ ጠይቀዋል።

በ2011 በጀት ዓመት ለሕንጻ ግንባታው ሥራ የሚውል 80 ሚሊዮን ብር በጀት ተይዞለት የነበረ ሲሆን፣ ከፍተኛ ፍርድ ቤቱ ቦታውን ተረክቦ ወደ ግንባታ ለመግባት 10 ሚሊዮን ብር የዲዛይን ሥራ ከወጣ በኋላ የይዞታ ማረጋገጫ ካርታው በከተማ አስተዳደር እንዲመክን መደረጉ የሚታወስ ነው። ፍርድ ቤቱ ያለበትን የሕንጻ ችግር ይቀርፋል ተብሎ ተስፋ ተጥሎበት የነበረው ሕንጻ ግንባታ፣ በጀት ከተፈቀደለት በኋላ ካርታው በመምከኑ እስካሁን ድረስ ታጥሮ መቀመጡን ብርሃነመስቀል ለቋሚ ኮሚቴው በሰጡት ማብራሪያ ጠቁመዋል።

ከፍተኛ  ፍርድ ቤቱ ከከተማ አስተዳደሩ ተረክቦት የነበረው ቦታ ካርታ የመከነው፣ የሕንጻ ግንባታውን ወደ ሥራ ለማስገባት የዲዛይን ሥራ አልቆ ተቋራጭ ለመቅጠር ጨረታ የማውጣት ሂደት ደርሶ በነበረበት ጊዜ መሆኑ ተሰምቷል። ከተማ አስተዳደሩ የቦታውን ካርታ ካመከነ በኋላ ከፍተኛ ፍርድ ቤቱና የጠቅላይ ፍርድ ቤት ከፍተኛ አመራሮች ችግሩን በውይይት ለመፍታት ጥረት ማድረጋቸውን ብርሃነመስቀል ተናግረዋል።

የከፍተኛ ፍርድ ቤት ፕሬዝደንቱ ለቋሚ ኮሚቴው በሰጡት ማብራሪያ፣ ችግሩን በውይይት ለመፍታት እና ወደ ክስ ላለማምራት በፍርድ ቤቱ በኩል ጥረት መደረጉን ተናግረዋል። ይሁን እንጂ፣ በጉዳዩ ላይ ውይይት ለማድረግ ተይዞ በነበረ ቀጥሮ ላይ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ ሳይገኙ መቅረታቸውን ፕሬዝዳንቱ አስረድተዋል።

ከተማ አስተዳደሩ ለከፍተኛ ፍርድ ቤቱ የሰጠውን የሕንጻ የግንባታ ሊዝ ውል አቋርጦ ካርታው እንዲመክን ያደረገው፣ በተሰጠው የጊዜ ገደብ ፈጥኖ ወደ ግንባታ ባለመግባቱ መሆኑን እንደ ምክንያት ማስቀመጡ የሚታወስ ነው። አስተዳደሩ የሊዝ ውሉ እንዲቋረጥና ካርታ ማምከኑን መጋቢት 1/2014 ለፍርድ ቤቱ በደብዳቤ አሳውቋል። ከተማ አስተዳደሩ ቦታውን ለራሱ ሕንጻ መገንቢያ ሊጠቀምበት እንዳሰበ ጭምጭምታዎች ሲሰሙ ነበር።

የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት መዓዛ አሸናፊ በበኩላቸው በጉዳዩ ላይ በሰጡት ማብራሪያ፣ “የሕንጻ ግንባታ ላይ የእናንተን ድጋፍ እንፈልጋልን” ሲሉ ተደምጠዋል።

የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በተረከበው 19 ሺሕ ካሬሜትር  ቦታ ላይ ባለ 19 ወለል ሕንጻ ለማስገንባት የይዞታ ማረጋገጫ ካርታ ካገኘ አራት ዓመት አስቆጥሯል። የፍርድ ቤቱ ሕንጻ በዋናነት እስከ 80 ሰው የሚይዙ ትላልቅ የችሎት አዳራሾች፣ መካከለኛ መጠን ያላቸውና እስከ 40 ባለጉዳዮችን የሚያስተናግዱ የችሎት አዳራሾች፣ እንዲሁም 12 ሰዎችን ለማስተናገድ የተዘጋጁ የችሎት አዳራሾች ሊኖሩት እንደሚችሉ በወቅቱ መገለጹ የሚታወስ ነው።

የዳኝነት አገልግሎቱን ዘመናዊ ለማድረግ የሚያስችሉ የመረጃና ተግባቦት ቴክኖሎጂ መሠረተ ልማት ያካተተ እና ዘመኑ የደረሰበትን ወረቀት አልባ የዳኝነት አገልግሎት ታሳቢ ተደርጎ ሊገነባ የታሰበ ሕንጻ ነበር።<


ቅጽ 5 ቁጥር 209 ጥቅምት 26 2015/p>

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here