የፀጥታ መዋቅሩ ሲፈተሽ

0
527

ከእንድ ሳምንት በፈት በተለይ በኦሮሚያ ክልል በሚገኙ የተለያዩ ከተሞች በተከሰቱ ግጭቶች ህይወታቸውን ካጡ 78 ግለሰቦች አንዱ የሆነው እና ለቤተሰቡም የመጨረሻ ልጅ የነበረው ሰመረዲን ኑሪ በጫት ንግድ ላይ ተሰማርቶ የሚኖር እና ቤተሰብ አስተዳዳሪም ነበር። ከፖሊስ በተተኮሰ ጥይት ህይወቱ ያለፈው ወጣቱ ከፖሊሶች ጋር ከዚህ ቀደም ግጭት እንደነበረው እና ቤተሰቦቹም የህልፈቱ ምክኒያት ከዚህ ቀደም አንድ የተጣላው ፖሊስ በያዘው ቂም ነው ብለው ያምናሉ።
የ29 አመት ወጣቱ በአዳማ ከተማ ቀበሌ 07 በሚገኝ የጫት መሸጫ ሱቁ ውስጥ ከህልፈቱ ከአንድ ወር በፊት ከአንድ ሰው ጋር ተጋጭቶ የነበረ ሲሆን አንገቱን በምላጭ ተቆርጦ እንደነበርም የሟች ወንድም ይናገራሉ። ነገር ግን ፖሊስ ሰመረዲን ታክሞ እስኪመጣ ተጠርጣሪውን ለቆ እንደጠበቀው እና እርሱን ጥፋተኛ በማድረግም ለእስር ሲፈልጉት እንደነበር ያስታውሳል።

በአዳማ ከተማ የነበረው ግጭት ከጥቅምት 12ቱ ክስተት ባሻገር ቀድም ያሉ ቁርሾዎች አባባሽ ምክኒያቶች እንደነበሩ አዲስ ማለዳ ያነጋገረቻቸው ነዋሪዎች ይናገራሉ።
የኦ ኤም ኤን ሚዲያ ዋና ስራ አስፈፃሚ ጃዋር መሃመድ ከሰኞ ጥቅምት 11 ለ ማክሰኞ አጥቢያ መንግስት ያሰማራላቸው የግል ጠባቂዎች ለእርሳቸው ሳያሳውቁ ለቀው እንዲወጡ መታዘዛቸውን በማህበራዊ ገፃቸው አጋርተዋል። ‹‹ማንኛውም ታጥቆ በዚህ ጭለማ ወደ መኖሪያ ግቢያችን ለጥቃት የሚንቀሳቀስ ግለሰበም ሆነ ቡድን ላይ የጥበቃ አካሉ ሕጋዊ መብቱን ተጠቅሞ የመከላከል እርምጃ እንደሚወስድ ሊታወቅ ይገባል›› በማለት የማስጠንቀቂያ መልክት አስተላልፈዋል።

ይሀንን ተከትሎ አዳማ ከተማን ጨምሮ በመላው ኦሮሚያ ዋና ዋና መንገዶች በድንጋይ ተዘግተው ሰልፎች የተካሄዱ ሲሆን በእለቱ የከፋ ግጭቶች አልታዩም ነበር። ይልቁንም በማግስቱ ሮብ ከቀትር በኋላ ጃዋር በመኖሪያ ቤታቸው ጋዜጣዊ መግለጫ የሰጡ ሲሆን ይህንን ተከትሎ መንገዶች መከፈት ጀምረዋል።

በአዳማ ከተማም የተዘጋውን መንገድ ክፈቱ የሚሉ ወጣቶች እና መንገዱን በዘጉት ወጣቶች መካከል ግጭት መፈጠሩን አዲስ ማለዳ ያነጋገረቻቸው ነዋሪዎች የገለጹ ሲሆን ተመሳሳይ ግጭቶችም በቢሾፍቱ ከተማ ተከስተዋል።

‹‹ፖሊስ ሱቅ ዝጉ ሲለን ነበር፣ መንግሰት ሃገር ተረጋግቷል ብሎ መግለጫ እየሰጠ እኛ ሰፈር ያሉ ፖሊሶች ግን ዳቦ ቤት ካልዘጋችሁ ሲሉ ተመልክቻለሁ›› ሲሉ አንድ ነዋሪ ተናግረዋል። በቢሾፍቱ ከተማም ፖሊስ ጣቢያ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ፖሊሶች እየተመለከቱ የንግድ ቤቶችቻቸውን መዝጋት ያልፈለጉ ነጋዴዎችን ሲደበድቡ ፖሊስ ቢመለከትም ምንም ጥበቃ እንዳላደረገላቸው ይናገራሉ።

በቢሾፍቱም ሆነ በአዳማ ከተማ አዲስ ማለዳ ያነጋገረቻቸው ሰዎች እንደሚሉት መከላከለያ ወደ ከተሞቹ ሲገባ ‹‹አቀባበል›› የተደረገለት ሲሆን ይህም በተለይ የከተሞቹ የፖሊስ ሃይሎች ነገሩን ከማረጋጋት ይልቅ የማባባስ አዝማሚያ ስለታየባቸው መከላከያ ግን ገለልተኛ ሆኖ ያረጋጋል በሚል ተስፋ እንደሆነ ይናገራሉ። በቢሾፍቱ መንገድ መዝጋት የተጀመረው ከፖሊስ ጣቢያው ፊት ለፊት ጀምሮ እንደነበረም ይነዋሪዎች ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

በአዳማ ከተማ በተፈጠረው ግጭት በሶማሊ ክልል እና በኦሮሚያ ክልል አዋሳኝ ቦታዎች ተፈጥረው በነበሩ ግጭቶች አማካኝነት የተፈናቀሉ ነዋሪዎች መኖሪያ ካምፕ ላይ የሰደረሰው ጥቃት ነው። ባሳለፍነው ሳምንት ግጭቱ ከመቀስቀሱ ቀደም ብሎ ከምስራቁ የአገሪቱ ክፍል ከመጡት ነዋሪዎች እና የከተማዋ ነዋሪዎች መካከል ተደጋጋሚ ግጭቶች ሲከሰቱ እንደነበር አዲስ ማለዳ የሰበሰበችው መረጃ ያሳያል።

በተለይም ሰፊ የሆነ የባህል ልዩነት በመኖሩ አንዲሁም ቁጥራቸው ቀላል የማይባሉት ተፈናቃዮች አሁንም ከፍተኛ የስራ አጥነት ችግር ስለተጋረጠባቸው አለመግባባቶች በተደጋጋሚ እንደሚከሰቱ ነዋሪዎቹ ገልፀዋል።

‹‹የነዋሪዎቹ ግዜአዊ መኖሪያ ምንጃርን እና አዳማን በሚያገናኘው ቀጨማ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ የተሰራ ስለሆነ አንዳንዴ የኮቴ ገንዘብ ክፈሉን ብለው ይጠይቃሉ›› ሲሉ ይገልጻሉ። ‹‹በቀጨማ አካባቢ ከሚገኙ ሶስት የኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያናት ምእመናን ጋርም ተጋጭተው ስለሚያውቁ የቆየ ቂም አለ።››
አዲስ ማለዳ ከምንጮቿ ማረጋገጥ እንደቻለችውም በዚሁ ቀጨማ ተብሎ በሚጠራው የከተማዋ አካባቢ የታጠቁ ግለሰቦች ወደ ከተማው ገብተው ነበር።
‹‹ባለፈው ሳምንት የተከሰቱ ግጭቶች መባባስም በአብዛኛው የቆየ ቂም ሲሆን አሁንም የእርቅ ሂደት ተብሎ የተጀመረው ነገር የከተማውን ነዋሪ ያገለለ እና የመንግስት ካድሬዎች እና ቄሮዎችን ብቻ ያሰተፈ በመሆኑ የመገለል ስሜት ከመፍጠሩ ባሻገር የግጭቱን መሰረት ያላወቀ ነው›› ሲሉ ነዋሪው ስለስጋቱ ይናራሉ።

ግጭቱ ከመፈጠሩ ከሳምንት በፊት የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ(ዶ/ር) መደመር የተሰኘ መጽሃፍ በተመረቀበት ወቅት ወጣቶች ከተለያዩ ከተሞች መጥተው በአዳማ ከተማ የምርቃት ስነስርአት ላይ የተሳተፉ ሲሆን በተመሳሳይም ዐቢይ የኖቤል ሽልማትን በማሸነፋቸው አማካኝት ሰልፍ መካሄዱን ነዋሪዎች ይናገራሉ።
ከሁለት ሳምንት በኋላ ግን በተመሳሳይ በተለምዶ ኤፍ ኤስ አር ተብሎ በሚጠራው መኪና ተጭነው የሚመጡት ወጣቶች መፅኃፉን በማቃጠል እና ጠቅላይ ሚኒሰቴሩ ስልጣናቸውን እንዲለቁ በማሰማት መለወጡን አዲስ ማለዳ ነጋገረቻቸው ነዋሪዎች ይናገራሉ።

‹‹እነዚህን ህፃናት ከሌላ አካባቢ ትራንስፖርት አዘጋጅተው በማምጣት እና ምግብ በማቅረብም የሚያንገላቷቸው ሰዎች እንዳሉ ስለምንመለከት ለልጆቹ እናዝናለን›› ሲሉ አንድ ነዋሪ ገልጸዋል።

አምቦ
በቢሾፍቱ እና አዳማ ከነበረው ግጭት ለየት የሚለው የአምቦ ከተማ ተቃውሞ ሮብ ጥቅምት 12 የተደረገ ሲሆን በተቃውሞ ሰልፉ ላይም የኦሮሚያ ክልል ልዩ ፖሊስ እና በአምቦ ከተማ ፖሊስ መካከል የተፈጠረ ግጭት ነበር።

ኢሕአዴግ ወደ ስልጣን ከመጣበት ግዜ ጀምሮ ተቃውሞ የማያጣት አምቦ ለአንድ አመት ከመንፈቅ መንግሰት ላይ የከፋ ተቃውሞ ሳታሰማ መቆየቷን ነዋሪዎቿ ይናገራሉ።

‹‹በአምቦ ከተማ ነዋሪዎች ያለማቋረጥ ለአመታት ሲያሰሙ በነበረው ተቃውሞ በመላው ኢትዮጵያ ያሉ ሰዎች ምን ነክቷቸው ነው ይሉን ነበር፣ ኦሮሚያ ውስጥ ጨምሮ›› ይላሉ የከተገማዋ ነዋሪ። ‹‹ነገር ግን የተቃውሞ መንገዱ እየተቀጣጠለ ሲመጣ በአንቦም እየተባባሰ የዴሞክራሲው ጥያቄ ተፋፍሞ ነበር። የዐቢይ አህመድን ወደ ስልጣን መምጣት ተከትሎ ግን ህዝቡ ጥያቄዬ ተመልሶልኛል ብሎ በዝምታ ተቀምጦ ነበር።››

ከዚህ ቀደም በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ህይወታቸው ላለፉ የክልሉ የፖሊስ አባት ወገኖቻችን ናቸው በሚል ሰልፍ እንደነበር ነገር ግን እንደዚህ ቀደሙ ትምህርት ቤቶች ተዘግተው እና የእለት ተለት እንቅስቃሴ ተዘግቶ እንደማያውቅ ግን ነዋሪው ይናገራሉ። ‹‹ከረጅም አመታት በኋላ ግን ያለፈው የትምህርት ዘመን ዩኒቨርሲቲ እንዲሁም በከተማው ባሉ ትምህርት ቤቶች ትምህርት ሳይቆራረጥ ለመጀመሪያ ግዜ የተገባደደበት አመት ነበር›› ሲሉ ያስታውሳሉ።

‹‹የኦሮሞ መብቶች ተሟጋች የሆኑት ጃዋር መሃመድን መንግስት ዋጋ ለማሳጣት እና መተንፈሻ አካላችንን ለመንካት መሞከሩ ግን በድጋሚ አንቦ እንድትቆጣ አድርጓል›› ሲሉ ስለሰልፉ አላማ ይናገራሉ። ‹‹ነገር ግን ሁሉም ነዋሪ በሰላም ወጥቶ ሰልፉን አከናውኖ ለመመለስ ሲሞክር በከተማው ፖሊስ እና በልዩ ፖሊስ መካከል በተፈጠረው ግጭት በተተኮሰ ግጭት ያለ አግባብ ነፍስ ጠፍቷል። ነገር ግን በአምቦ ከተማ በሃይማኖት እና በብሔር ላይ የተመሰረተ ምንም አይነት ጥቃት አልነበረም፣ ህይወት የጠፋውም በፖሊስ እንጂ በህዝብ የሞተ ሰው የለም›› ሲሉ ይናራሉ።

‹‹ሰልፈኛው የአብይን መንግስት መቃወም ሲጀምር ልዩ ፖሊሶች ጥይት እና አስለቃሽ ጭስ መተኮስ በመጀመራቸው ምክኒያት ጉዳት ደርሷል›› የሚሉት ነዋሪው ‹‹አሁንም ከፀጥታ ሃይሎች በተተኮሰ ጥይት የተጎዱ እና ህክምና ባለማግኘታቸው ምክኒያት የሟች ቁጥር ሊጨምር ይችላል፣ ነዋሪው መዋጮ በማድረግ ልጆቹን ለማሳከም እየሞከረ ነው›› ሲሉ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

‹‹አኔ ዲጄ ነኝ፣ በተለያዩ ዝግጅቶች ላይ ሙዚቃዎችን ሳጫውት እንኳን ትግርኛ ወይ አማርኛ ወይ ሌላ ሙዚቃ ስከፍት ማንም ክፉ ንግግር ተናግሮ አያውቅም፣ የአምቦ ህዝብ የዴሞክራሲ ጥያቄ ይዞ ወጣ እንጂ የጭቆና እና የጥላቻ ወሬ እንኳን አልነበርም›› ሲሉ አንድ ወጣት ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

ድህረ ግጭት
ግጭቶቹ ከረገቡ በኋላ ከ አራት መቶ በላይ ሰዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን የጠቅላይ ሚኒስትሩ የፕሬስ ሴክሪታሪያት ሃላፊ ንጉሱ ጥላሁን ለጋዜጠኞች የሰጡት መግለጫ ያስረዳል። ነገር ግን ከጉዳዩ ጋር ግንኙነት የሌላቸውን ሰዎች የማሰር አዝማሚያ ያላቸው እንቅስቃሴዎች መታየታቸውን በአዳማ ከተማ ያሉ ምጮች ገልፀዋል።

‹‹ሃይለማሪያም ሆስፒታል ሬሳ ለማውጣት የሄዱ ቤተሰቦች፣ የቆሰለ ሰው ያደረሱ ባጃጆች እንዲሁም በግጭቱ የተጎዱ ሰዎች ያለአግባብ ታስረዋል›› ሲሉ አንድ የሟች ቤተሰብ ተናግረዋል። ‹‹መከላከያ ከከተማው ከወጣ ጀምሮ ስጋት ላይ ነን፣ የተለያየ ወሬዎችን እየሰማን ነው›› ሲሉ ስጋታቸውን ገልጸዋል።

መፍትሄው?
የቀድሞ የመከላከያ የአየር ሃይል አዛዥ እና በአሁኑ ወቅት የሰላም እና ደህንነት ጉዳዮች ተንታኝ የሆኑት ሜጀር ጄነራል አበበ ተክለ ሃይማኖት ‹‹መከላከያ በዲሲፕሊን ጉዳዮች ላይ የማይደራደር ሰራዊት ነው›› ሲሉ ስለቀድሞ ቤታቸው ይናገራሉ። ነገር ግን ባልሰለጠነበት የውስጥ ጉዳዮች ተይዞ የሰለጠነበትን አላማ እንዳያዳክመው ያላቸውን ስጋት ይገልጻሉ።

‹‹መከላከያ በክልሎች መካከል ከአቅም በላይ ችግር ሲኖር እና ከፍተኛ ትጥቅ ያለው ሃይል ካለ ነው በሃገር ውስጥ ያሉ ችግሮችን ለመፍታት ናው የሚሰለጥነው›› ሲሉ ይጀምራሉ።

‹‹ሰራዊቱ ስራው አገርን ከወራሪ አካል መከላከል እንጂ በየቦታው እሳት ሲለኮስ እየዞረ ለማጥፋ ባለመሆኑ ተረጋግቶ እና የወደፊቱን እያሰበ እንዳይዘጋጅ በማድረግ ሊያዳክመው ስለሚችል ቆም ብሎ ማሳብ ያስፈልጋል›› ሲሉ ሜጀር ጄነራሉ ለአዲስ ማለዳ አስረድተዋል።

‹‹የተፈጠሩት ሁኔታዎች በከተማ ጉዳዮች ላይ ያተኮረ ስልጠና ለሰለጠነው ፖሊስ እንኳን ያስቸገረ የሆነበት ምክኒያት በተለይ ፖለቲካዊ መፍትሄዎች የሚስፈልጋቸው ችግሮች ከስር መሰረታቸው መፍታት እንደሚያስፈልግ አመላካች ነው›› ይላሉ።

በከተማ ፖሊስ እና በልዩ ፖሊስ ላይ ታይተዋል የተባሉትን የዲሲፕሊን ግድፈቶች በግል እንዳላጣሩ የገለጹት ሜ/ጀ አበበ ‹‹ይህ ከስልጠና፣ ከሞራል፣ ከትጥቅ፣ ከደመወዝ እና ከኑሮ ጋር እንገሚገናኝ መገመት ግን ቀላል ነው›› ይላሉ።

ነገር ግን ፖሊሶቹ ዞረው የሚኖሩት በማህበረሰቡ ውስጥ በመሆኑ እና ህብረተሰቡ የፖለቲካ ቀውስ እንደ አንድ ነዋሪ ሊሰማቸው ስለሚችል መንግስት የፖለቲካ ቀውሱን ትኩረት ሰጥቶ ሊሰራበት እንደሚገባ እና የፖሊስ ስልጠናዎችም ትኩረት እንደሚፈልጉ ያሳስባሉ።

የሟች ሰመረዲን ቤተሰቦችም እርቅ ስላለ ቀበሌ ኑ እንደሚባሉ ጠቅሰው ‹‹ልጃችንን የገደለው ፖሊስ ዱላውን ይዞ በበራችን ነው የሚያልፈው፣ በዛ ላይ ከሀዘን ተነስተን ከማን ጋር ነው ሄደን የምንታረቀው›› ሲሉም ጥያቄ ያነሳሉ።

በጉዳዩ ላይ ለአዲስ ማለዳ ማብራሪያ የሰጡት የሰብአዊ መብት ኮሚሽን ኮሚሽነር ዳንኤል በቀለ(ዶ/ር) ጉዳዩን በቅርበት እንደሚከታተሉት እና የህግ ፈፃሚ አካላት ስራቸውን እንዲሰሩ ግዜ ከመስጠት ባሻገር ኮሚሽኑ ግን የራሱን ምርመራ በማድረግ በቅርቡ የጥናት ውጤቱን ይፋ እንደሚደርግ ተናግረዋል።

ቅጽ 1 ቁጥር 52 ጥቅምት 22 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here