የኢትዮጵያ እና የግብጽ ፍጥጫ

0
1310

ለዘመናት ግብጽንና ኢትዮጵያን ሲያወያይ፣ ሲያነጋግር ብሎም ጦር ሲያማዝዝ የከረመው ነገረ አባይ፤ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ደግሞ መልኩን ቀይሮ የወንዙን ተፋሰስ መሰረት አድርጋ ኢትዮጵያ እየገነባች ያለችው ታላቁን የሕዳሴ ግድብን ማዕከል አድርጓል። በአገራቱ መካከል በተናጠልና እንዲሁም ሱዳንን በማካተት የሦስትዮች ውይይትና ድርድር ሲደርጉ በርካታ ዓመታት ተቆጥረዋል።

ኢትዮጵያ የሕዳሴ ግድብ ግንባታን የግብጽ የውስጥ ፖለቲካ በአመጽ በሚታመስበት ወቅት በመጀመሪያ በከፍተኛ ምስጢር በመያዝና በኋላ ላይም ይፋ በማድረግ መጀመሯ ይታወቃል፤ አሁን ግንባታው 68 በመቶ ደርሷል። ግብጽ በበኩሏ የኢትዮጵያን የውስጥ ጸጥታና ደኅነት መዳከም እንደ ጥሩ አጋጣሚ በመጠቀም በተደጋጋሚ የኢትዮጵያን እጅ ለመጠምዘዝ ሳታሰልስ ሞክራለች። በመሆኑም የኹለቱ አገራት ግንኙነት በመጠራጠር እና ባለመተማመን የተሞላ ቢሆንም የዲፕሎማሲ ካባ ለብሶ ግንኙነታቸው እስካሁን ቀጥሏል።

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ መንግሥት ለሕዳሴ ግድብ ላይ በወሰደው የማስተካከያ እርምጃዎች ግንባታውን በመፋጠን ላይ መገኘቱ ያሳሰባት ግብጽ ኢትዮጵያ ላይ ጫና በመፍጠር የሦስተኛ አገር አደራዳሪነትን የሙጢኝ ብላለች። በሌላም በኩል ፕሬዘዳንት አልሲሲ በአገር ውስጥ የገጠማቸውን ተቃውሞ ለማስቀየሻነት የተጠቀሙት ካርድ የአባይ ወንዝ ጉዳይ እንደሆነ የአደባባይ ሚስጢር ነው።

የአዲስ ማለዳው ሳምሶን ብርሃኔ ይህንን የኢትዮጵያንና የግብጽን በሕዳሴው ዙሪያ የሚደርጉትን ወቅታዊ ውይይት/ድርድር የሐተታ ዘ ማለዳ ጉዳይ አደርጎታል። መጽሐፍት በማገላበጥ፣ በየጊዜው የተሠሩ ዘገባዎች በመመልከት፣ ፖለቲከኞችንና በጉዳዩ ዙሪያ ጥናት ያደረጉ ባለሙያዎች በማነጋገር ከታሪካዊ ደራው በመነሳት የኢትዮጵያንና የግብጽን የዓመታት ሕዳሴ ግድብን ድርድርና አቋም ያስቃኘናል። በተጨማሪም መፍትሔ ናቸው የተብለው የቀረቡ ምክረ ሐሳቦችንም አካትቷል።

ልክ የዛሬ ስምንት ዓመት ገደማ ነበር ግብጽ በውስጥ ጉዳይ በታመሰችበት ወቅት ነበር ኢትዮጵያ በዜጎቿም ሆነ በዓለም አገራት ዘንድ ያልተጠበቀ ነገር ይዛ ከተፍ ያለችው። ግብጽን ከሦስት ዐሥርት ዓመታት በላይ የመሩት ሆስኒ ሙባረክ መንበረ ሥልጣን በሕዝባዊ ቁጣ ግብዓተ መሬቱ ሊፈጸም አፋፍ ላይ በነበረበት ወቅት ኢትዮጵያ የሚለኒየም ግድብ ግንባታን ይፋ ያደረገችው። በርግጥ ግድቡ ለደኅንነት ሲባል ፕሮጀክት ኤክስ በሚል ሥያሜ እንደሚገነባ በወቅቱ ጠቅላይ ሚኒስቴር መለስ ዜናዊ እና ጥቂት ከፍተኛ ባለሥልጣናት ያውቁ የነበረ ቢሆንም ይፋ ይሆናል ብሎ የጠበቁት ግን በጣም ጥቂት ነበሩ።

የግድቡ መሰረት ድንጋይ ሲቀመጥ ገና የኢትዮጵያ ኹለተኛ ሚሊኒየም ከተገባደደ ሦስት ዓመት ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ሥሙም ሚሊኒየም ግድብ ተባለ፤ ነገር ግን በ2003 አሁንም ሥያሜው ሆኖ የዘለቀውን ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ተብሎ እንዲጠራ የተወሰነው። በተመሳሳይ ዓመት ነበር ለዓመታት በኢትዮጵያውያን የተዘፈነለት አባይ ወደ ጥቅም እንዲውል ግንባታ የተጀመረው። ታዲያ በወቅቱ ግድቡ ወደ 80 ቢሊዮን ብር ይፈጃል ተብሎ የተገመተ የነበረ ሲሆን በስድስት ዓመታት ውስጥ ልክ የዛሬ ኹለት ዓመት ይጠናቀቃል ተብሎ ተጠብቆ ነበር።

በተለይም ግድቡ ሲጀመር የሚፈጀው አጠቃላይ ወጪ (4 ነጥብ 8 ቢሊዮን ዶላር) የነበረ ሲሆን ይህም በወቅቱ የነበረውን የኢትዮጵያ አጠቃላይ ምርት 15 በመቶ እና አጠቃላይ በጀት 60 በመቶ አካባቢ መሆኑ አገሪቷ ገንዘቡን ከየት ማግኘት ትችላለች የሚለው የብዙዎች ጥያቄ ነበር። ይህንን የተረዳችው ግብጽ ምንም እንኳን ጊዜው በውስጣዊ ጉዳዮች ታምሳ የነበረበት ወቅት ቢሆንም ኢትዮጵያ ከሌሎች አበዳሪዎች ገንዘብ እንዳታገኝ ደፋ ቀና እያለች ነበር። እንደ ዓለም ባንክ ያሉ ተቋማት ላይ ያላትን ጥሩ ተሰሚነት ዜጎቿ በባንኩ ከፍተኛ ደረጃ ላይ ከመሆናቸው ጋር ተዳምሮ ግድቡ የገንዘብ ድጋፍ እንዳያገኝ ግብጽ ያደረገችው እንቅስቃሴ ተሳክቶላታል ቢባል ማጋነን አይሆንም። ይህ ዓይነቱ እንቅስቃሴ በቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስቴር መለስ ስትመራ የነበረችውን ኢትዮጵያ እንኳንስ ሊያደክማት እንደውም እንድትጠናከር አድርጎት አልፏል።

በርግጥ፤ ይህንን የተረዳው የኢትዮጵያ መንግሥት በዚያን ወቅት ነበር በራስ አቅም እንደሚገነባ እና ያልተቆጠበ የሕዝብ ድጋፍ እንደሚያስፈልገው ይፋ ያደረገው፤ ሕዝቡም ታዲያ አላመነታም። ከተማሪ አንስቶ እስከ ትላልቅ አገር በቀል ድርጅቶች፤ ደሞዛቸውን ከዕለት ጉርሳቸው የማያልፈው አስተማሪዎችና ሌሎች የመንግሥት ሠራተኞች፤ ባላቸው አቅም ለግድቡ ቦንድ በመግዛት አገራዊ ግዴታቸውን ተወጥተዋል። እስካሁንም ከተሸጠው ቦንድ በተገኘው ገቢ እንዲሁም ከመንግሥት ካዝና በወጣ ወጪ ወደ 100 ቢሊዮን ብር ገደማ ግድቡ ላይ ፈሰስ ተደርጓል። ነገር ግን ይጠናቀቃል በተባለበት ወቅት ያለመጠናቀቁ ካልተጠበቀው የግድቡ ሥራ አስኪያጅ የነበሩት ስመኘው በቀለ ሞት እንዲሁም የግድቡ ግንባታ በስፋት ሲሳተፍ የነበረው ሜቴክ በደካማ አስተዳደር የተነሳ በሙስና መዘፈቁ ጋር ተዳምሮ ኅብረተሰቡ በግድቡ ላይ ያለው እምነት እንዲሸረሸር ምክንያት ሆኗል።

ምን ይኼ ብቻ! በአገሪቷ ውስጥ ያለው አለመረጋጋት እና በክልሎች እና የብሔር ብሔረሰቦች ግጭት መስፋፋት ግድቡ በኅብረተሰቡ ዘንድ ያለው ተነጋጋሪነት እንዲቀነስ አድርጎታል ሲሉ ባለሙያዎች ይሞግታሉ። ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ደግሞ በግብጽ በኩል እየተነሱ ያሉ ጥያቄዎች ጉዳዩ ውስብስብ ከማድረጉም በላይ የግብጽ ባለሥልጣናትም ሆነ ቀላል የማይባሉ ዜጎቿ ሌት ተቀን ግንባታውን ለማዘግየት ደፋ ቀነና ቢሉም በኢትዮጵያውያን ፖለቲከኞችም ሆነ በመደበኛ መገናኛ ብዙኀን  ከጉዳዩን ግዝፈት አኳያ የተሰጠው ትኩረት እምብዛም ነው። ይህ ግብጽ በግድቡ ግንባታ ዙሪያ በሚደረጉ ውይይቶችም ሆነ ድርድሮች ላይ ያላትን ተፅዕኖ ከፍ እንዳያደርገው እንዳያደርግ ባለሙያዎች ስጋታቸውን ያጋራሉ። በተለይም በኢትዮጵያውያን መካከል የከረረውን አለመስማማት ግብፆች እንዳይጠቀሙበት ከፍተኛ ስጋት ያለ ሲሆን ጠቅላይ ሚኒስቴር ዐቢይ  አሕመድ ወደ ሥልጣን ከመጡ ለግድቡ የተሰጠው ትኩረት ማነስ ችግር ይፈጥራል ያሉም አልጠፉም።

የግብጽ ፍራቻ ምን ይሆን?

ከዘመናዊት ኢትዮጵያ ምስረታ አንስቶ የነበሩ መሪዎች ከሚያመሳስላቸው ጉዳዮች አንዱ አባይ ላይ ፍትሐዊ ጥቅም አገሪቷ እንድታገኝ ማድረግ ላይ ያላቸው አቋም ነው። ከአጼ ምኒሊክ ዘመነ መንግሥት አንስቶ ተግባራዊ ካደረጉት እስከ መለስ ዜናዊ ድረስ የኢትዮጵያን ጥቅም ለማስከበር በርካታ ጥረቶች ተደርገዋል። ይህን ማድረግ ግን መቼም ቢሆን ቀላል አልነበረም። ለምን የሚል ጥያቄ ሊነሳ ይችላል። ለዚህም መልሱ በቀላሉ ግብጽ የአባይ (ናይል) ስጦታ ነች ከሚለው ብሒል ጋር ይያዛል። በተለይም ወደ 100 ሚሊዮን የሚጠጋ ሕዝብ ያላት ግብጽ ዜጎቿ የሚመገቡት ስንዴም ሆነ የሚጠጡት ወሃ ከአባይ የፈለቀ ነው። ሲፈጥራትም በረሃማ የሆነችውን ግብጽ ያለ አባይ (በውጭ ሥሙ ናይል) ማሰብ አይቻልም። በአገሪቷ ያሉ የመስኖ እርሻዎችም ሆነ ኤልክትሪክ አገልግሎት ያለማቋረጥ ማግኘት የሚፈልጉት ፋብሪካዎች የአባይ ውጤቶች ናቸው ቢባል አይገርምም።

ታዲያ ከጥንት ጊዜ ጀምሮ ወንዙን ከመነሻው አንስቶ ለመቆጣጠር ከ17ኛው ክፍለ ዘመን አንስቶ ግብፆች ኢትዮጵያን እና ሱዳንን ለመወረር የተለያዩ ጥረቶች አድርጋለች። ይህ ባለመሳካቱ፤ ወንዙ እንዳይገደብ ፍራቻ በተለያዩ ጊዜያት ስጦታዎችና የእጅ መንሻዎችን ወደ ጥንታዊ ኢትዮጵያ ነገስታቶች በመላክ ምስጋና ታቀርብ ነበር። ነገር ግን በ19ኛው ክፍለ ዘመን መባቻ ላይ ከእንግሊዝ ከፍተኛ ድጋፍ ታገኝ የነበረችው ግብጽ የላይኛው ተፋሰስ አገራትን በቁጥጥሯ ሥር ለማድረግ ካላት ፍላጎት የተነሳ የናይልን 85 በመቶ ውሃ መነሻ የሆነችውን ኢትዮጵያን ለመውረር ጦሯን አሰልፋ የነበረ ነበር። በወቅቱ በአጼ ዮሃንስ ትመራ የነበረችው ኢትዮጵያ በአሉላ አባነጋ በተመራ ጦር የግብጽ ሠራዊት በጉንደት እና ጉራ (የአሁኗ ኤርትራ) ማሸነፍ ችለው እንደነበርም የታሪክ ድርሳናት ያሳያሉ።

ይህ በኹለቱ አገራት መካከል የተደረገው የመጨረሻ ጦርነት ተደርጎም ሊወሰድ ይችላል። ይሁን እንጂ፤ የአውሮፓውያን አገራት ቅኝ ግዛት በአፍሪካ ማብቃቱን ተከትሎ በምሥራቅ አፍሪካ ያሉ ሉአላዊ የሆኑ የናይል ተፋሰስ አገራት መፈጠራቸው በጉዳዩ ዙሪያ ያለውን ሹክቻ የበለጠ ሊያወሳስበው ችሏል። ከዚህም ባሻገር በጦርነት ብትሸነፍም እንኳን ግብጽ በቀጥታ ሆነ በተዘዋዋሪ ኢትዮጵያ ላይ ተፅዕኖ ለማድረግ ብዙ ሙከራዎችን አድርጋለች። ከነዚህም መካከል ኢትዮጵያ ከዓለም ዐቀፍ ተቋማት የምታገኘውን የፋይናንስ ምንጭ እንዲደርቅ የምታደርገው ጫና እና የዐመፅ ቡድኖችን መደገፍ ይገኝበታል። ዲፕሎማትና የታሪክ ተመራማሪ የሆኑት ግርማ ባልቻ ይህንን በቅርበት ካጠኑት መካከል ናቸው። “ኢትዮጵያን ማተራመስ እና በሌላ ችግሮች እንድትጠመድ ማድረግ የግብጽ ዋነኛ ፖሊሲ” ነው የሚሉት ግርማ ይህንን ተግባራዊ ማድረግ የአገሪቷ ዋነኛ አጀንዳ እንደሆነ ያነሳሉ።

ከዚህ አለፍ ብሎ፤ ማስፈራሪያ አዘል ንግግሮችም በማድረግ ግብጽ ትታወቃለች። ለአብነትም በ1979 የግብጽ ፕሬዝደንት የነበሩት አንዋር ሳዳት አገራቸው ከእስራኤል ጋር የገባችውን ጦርነት እንዲቆም ካደረጉ በኋላ “ወደፊት ግብጽን ወደ ጦርነት ሊከታት የሚችል ነገር ቢኖር ውሃ ነው” ሲሉ ተደምጠው ነበር። በተጨማሪ በ1980ዎቹ መጀመሪያ “ኢትዮጵያ በናይል ወሃ ላይ ያለንን መብት ለመገደብ ማንኛውንም ዓይነት እርምጃ ለመውስድ ከሞከረች ከጦርነት ውጪ ሌላ ምንም አማራጭ የለንም” ብለው የነበረ ሲሆን በ1988 የግብጽ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የነበሩት ቡትሮስ ቡትሮስ ጋሊ (በኋላም የተባበሩት መንግሥታት ዋና ፀሐፊ) ቀጣዩ በመካከለኛው ምሥራቅ  የሚኖረው ጦርነት በናይል ዙሪያ ይሆናል ሲሉ ተደምጠው ነበር።

ይህ ዓይነቱ ኢትዮጵያ ላይ በተለያዩ መንገዶች ጫና የማድረግ የግብጽ ስትራቴጂ የማይካዱ እውነታዎችን ጥሎ አልፏል።

አንደኛው፤ ኹለቱ አገራት እንደ ጠላት እንዲተያዩ እና በኢትዮጵያ ሕዝብ ዘንድ ቁጭት እንዲኖር፤ ሌላኛው ደግሞ ግብጽ ከማንም የናይል ተፋሰስ አገራት በላይ የበለጠ በወንዙ ላይ ከፍተኛ ኀይል እንዲኖራትና ገናና አድርጓት አልፏል። ታዲያ ይህንንም ላለማጣት ኢትዮጵያን ያላሳተፈ ስምምነት እስከማድረግ ግብጽ ደርሳ ነበር። በተለይም ግብጽን በቅኝ ግዛት ገዝታ ከነበረችው እንግሊዝ ጋር በመሆን በ1902 ከዚያም በ1929 ከሱዳን ጋር የፈረመቻቸው አጨቃጫቂ እና ኢትዮጵያን ያላሳተፉ በአባይ ዙሪያ ከተፈረሙ ስምምነቶቿ መካከል ይጠቀሳሉ። በኋላም አገራቶቹ ከቅኝ ግዛት ነፃ ከወጡ በኋላ ስምምነቱ በ1959 ሊታደስ ችሏል።

የናይልን 85 በመቶ ድርሻ ያላትን ኢትዮጵያን ባላካተተው ይህ ስምምነት መሰረት ግብጽ በየዓመቱ 55 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር ውሃ ማግኘት የምትችል ሲሆን ሱዳን 18 ነጥብ 5 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር ውሃ ታገኛለች። በተጨማሪ ስምምነቱ ግብጽ የላይኛው ተፋሰስ አገራት ፈቃድ ባታገኝም እንኳን የተለያዩ የውሃ ፕሮጀክቶችን ማካሔድ እንድትችል እና በገባር ወንዞች ላይ የሚተገበሩ ፕሮጀክቶች ተፈፃሚነት ላይ ድምፅን በድምፅ የመሻር መብት ሰጥቷል። ታዲያ ይህ ስምምነት ፈራሚ ያልነበሩትን የላይኛው ተፋሰስ አገራትን የሆኑትን ታንዛኒያ ፣ ቡሩንዲ፣ ኡጋንዳ እና ኬንያ እንዲሁም የወንዙ ዋነኛ ምንጭ የሆነችውንና ስምምነቱ እንደማትቀበል ለዓለም ይፋ ያደረገችውን ኢትዮጵያን አስከፍቷል። ይሁን እንጂ ስምምነቱ ተፈፃሚ እንዲሆን ግብጽ ከታላቁ ሕዳሴ ግድብም ግንባታ ከመጀመሩ በፊትም ሆነ በኋላ ስትወተውት ነበር።

በግድቡ ዙሪያ ግብጽ ተቀዛቅዛ የነበረችበት ወቅት ቢኖር በአገር ውስጥ ጉዳይ ተወጥራ በነበረችበት ከ2009 እስከ 2010 (እ.ኤ.አ.) ድረስ ነበር ቢባል ማጋነን አይሆንም። በሙስና፣ በሥራ አጥነት እንዲሁም በአምባገነናዊ አገዛዝ ተማረው የነበሩት ግብፃውያን በአረብ አገራት የነበረውን ሕዝባዊ እንቅስቃሴን መሰረት ካደረገ ለውጥ በመማር ለሦስት ዐሥርት ዓመታት በሥልጣን ላይ በነበሩት ሆስኒ ሙባረክ ይመራ የነበረውን መንግሥት ከሥልጣን እንዲወርድ አድርገዋል። ታዲያ ይህ ከ1960ዎቹ አንስቶ በአባይ ወንዝ ላይ ግድብ ለመገንባት አቅዳ ለነበረችው ኢትዮጵያ ጥሩ አጋጣሚ የፈጠረ ሲሆን ከዚያም ሆስኒን ሙባረክን ተክተው የመጡት ሙሐመድ ሙርሲ በመፈንቅለ መንግሥት መነሳታቸው ለኢትዮጵያ ጥሩ አጋጣሚ ፈጥሮ አልፏል።

ይሁን እንጂ፤ ግብጽ ምንም እንኳን በአገር ውስጥ ጉዳይ ቀላል የማይባል ፈተና ቢገጥማትም በፕሬዝዳንት ሙርሲ በተጠራ በቀጥታ በቴሌቭዥን ስርጭት በቀረበ ውይይት ላይ የግብጽ ከፍተኛ ባለሥልጣናት ግድቡን በቦምብ ለማጥቃት ወይም ኢትዮጵያ ላይ ወታደራዊ ጥቃት ለመሰንዘር ሐሳብ ሰንዝረው ነበር። በተጨማሪ በመረጃ ጠላፊዎች በ2012 (እ.ኤ.አ.) አፈትልኮ የወጣ መረጃ እንደሚያሳየው የግብጽ ባለሥልጣናት ከሱዳን የመንግሥት ሥራ ኀላፊዎች ጋር በተለዋወጡት ኢሜል ግድቡን ኩስቲ በተባለች ቦታ አነስተኛ የአየር ኀይል ማዕከል በመገንባት በቦምብ ግድቡን ለማፈራረስ አስበው ነበር። በርግጥ ይህ ዓይነቱ ማስፈራሪያ የጥቂቶች ምኞት ሆኖ ቢያልፍም የግብጽ አብዮት ወቅት በናይል ዙሪያ የተፈጠረው ክስተት እንደ ማስተማሪያም ተደርጎ በቅርቡ ሕይወታቸው ያለፈውና ሙርሲን አስወግደው ሥልጣን በያዙት የአሁኑ ግብጽ ፕሬዝደንት ሙሐመድ አል ሲሲ ተነስቶ ነበር።

የዛሬ ሦስት ሳምንት ገደማ ነበር አል ሲሲ የአገራቸው የጦር ኀይል ባዘጋጀው የባሕል ሴሚናር ላይ ተገኝተው በ2011 (እ.ኤ.አ.) የነበረው አብዮት ባይነሳ ኖሮ በሕዳሴ ግድብ ግንባታ ዙሪያ ኢትዮጵያ ጋር የምናደረገው ውይይት አርኪ ይሆን ነበር ያሉት።

በርግጥ አልሲሲ ዕድለኛ ከማይባሉት የግብጽ መሪዎች ይመደባሉ ቢባል። ምክንያቱም በእርሳቸው የሥልጣን ዘመን ነበር ከፍተኛ ድርሻ የሚይዘው የሕዳሴ ግድብ ግንባታ የተካሔደው። በተለይ በ2015 (እ.ኤ.አ.) ከኢትዮጵያ ጋር የተፈራረሙት አጠቃላይ የማዕቀፍ ስምምነት በአንዳንድ ፖለቲከኞችና አክቲቪስቶች ዘንድ የግብጽን ፍላጎት አሳልፎ የሰጠ ነው በሚል ወቀሳ ሲሰነዘርባቸው ነበር።

በናይል ዙሪያ የተደረጉ ስምምነቶች

በ1929 እና በ1959 (እ.ኤ.አ.) በግብጽ እና በሱዳን መካከል የተደረጉ ስምምነቶችን ተከትሎ የበይ ተመልካች የሆኑት ኢትዮጵያ እና ሌሎች የላይኛው ተፋሰስ አገራት የሕዝብ  ቁጥራቸው መጨመሩ ናይልን ለልማት ለማዋል ያላቸው ፍላጎት እንዲያድግ ምክንያት ሆኗል። ግብጽ በበኩሏ እነዚህን ስምምነቶች በመጥቀስ ያለ እኔ አንዳች ፈቃድ ሳታገኙ መሥራት አትችሉም በማለት ብትወተውትም ይህ ዓይነቱ አቋም በላይኛው ተፋሰስ አገራት ዘንድ ሊወደድ አልቻለም።  እንደ ታንዛኒያ ያሉ አገራት ሉዓላዊነታቸውን ባወጁ ማግስት ያለቅት የተለጠጠውን የግብጽን መብት በፅኑ ተቃውመው ነበር። ለአብነትም፤ በ1960ዎቹ መባቻ የቀድሞዋ ታንጋኒካ (አሁን ደግሞ ታንዛኒያ) መሪ የነበሩት ጁሊየስ ኔሬሬ በናይል አጠቃቀም ላይ የወጡ ሕጎች የእርሱንም ሆነ የላይኛው ተፋሰስ አገራትን ፍላጎት የሚጋፋ እና አገራቱም በወንዙ ላይ የሚያደርጉት ስምምነት በግብጽ ፍላጎት ላይ የተመሰረተ እንዲሆን ምክንያት ነው ሲሉ ተችተው የነበረ ሲሆን የአገሮቹን ሉዓላዊነት የሚጋፋ ነው ሲሉ አማረው ነበር።

በተመሳሳይ ሌሎች የአባይ ተፋሰስ አገራት የግብጽን አቋም በመቃወም አዲስ የሕግ ማዕቀፍ ያስፈልጋል ሲሉ ጠይቀው ነበረ። ይህንን ወደ ተግባር ለመቀየር ቀላል አለመሆኑ ከአገራቱ ውስጣዊ ችግር ጋር ተዳምሮ ለኹለት ዐሥርት ዓመታት በወንዙ ዙሪያ የሚደረጉ ውይይቶች አነስተኛ የነበረ ሲሆን እና የወጣም ሕጋዊ ማዕቀፍ አልነበረም። ነገር ግን፤ የአውሮፓውያን ኹለተኛ ሚሊኒየም ሊገባደድ ዓመት ሲቀረው በ1999 (እ.ኤ.አ.)፡- ኢትዮጵያን ጨምሮ ዘጠኙ የተፋሰስ አገራት ወንዙን ፍትሐዊ በሆነ መንገድ ለመጠቀም ‘የናይል ተፋሰስ ኢኒሼቲቭን’ አቋቁመዋል። ከዚያም በኢኒሼቲቩ አስተባባሪነት የዓባይን ወንዝ ፍትሐዊ እና ምክንያታዊ በሆነ መንገድ ለመጠቀም የናይል ተፋሰስ ትብብር የሚል የሕግ ማዕቀፍ የተዘጋጀ ሲሆን ሰባት አገራት ተፈፃሚ እንዲሆን ተስማምተዋል። ኬኒያ፣ ብሩንዲ፣ ሩዋንዳ፣ ታንዛኒያ እና ኡጋንዳ ከፈረሙት አገራት መካከል ሲሆኑ ኤርትራ በራሷ ፍላጎት ታዛቢ በመሆኗ እና ግብጽና ሱዳን የስምምነቱን አንቀፅ 14(ለ)ን በመቃወማቸው አንፈርምም ብለው ነበር።

የውሃ ደኅንነቴን ይጎዳል በማለት ግብጽ እና ሱዳን አንቀፅ 14(ለ) የተቃወሙበት ዋነኛ ምክንያት ቀደም ብለው የወጡ ስምምነቶች ተፈፃሚ ሊሆኑ ይገባሉ በማለታቸው ሲሆን ለዚህም ማረጋገጫ ይሆን ዘንድ የኹለቱን አገራት ጥቅም እና መብት ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ የሚያሳድር ተግባር ውስጥ የላይኛው ተፋሰስ አገራት እንዳይገቡ በሚያስገድድ ሌላ አንቀፅ ይተካ ብለው ነበር። ይባስ ብሎ፤ በናይል ላይ ድምፅን በድምፅ የመሻር መብት ሊኖረን ይገባል ብለው ላነሱት ጥያቄ የታችኛው ተፋሰስ አገራት ጆሮ ዳባ ልበስ ማለታቸውን ተከትሎ ግብጽ እና ሱዳን ከኢንሼቲቩ ራሳቸው ሊያገሉ ችለዋል። ይሁን እንጂ ሱዳን ከጥቂት ዓመታት በኋላ  ወደ አባልነት ስትመለስ ግብጽ ግን የቀረበላትን ጥሪ አልቀበለም በማለት አሻፈረኝ ብላ ቆይታለች።

በዚህም የተነሳ የተፋሰሱ አገራት ውሃውን ፍትሐዊና ምክንያታዊ በሆነ መንገድ መጠቀም አንዲችሉ እንዲሁም የእርስ በእርስ ግንኙነታቸውን ያጠናክሩ ዘንድ የናይል ተፋሰስ ኮሚሽን ሊያቋቁሙ ተስኖቸዋል። በሌላ በኩል የአባል አገራት እንቅስቃሴ መቀዛቀዙ እና ከለጋሾች የሚገኘው ድጋፍ መቀነሱ ኢንሼቲቩ ያዳከመው ቢሆንም አሁንም የአየር ንብረት ለውጥ እና ሌሎች ናይል ወንዝ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ሊያሳድሩ የሚችሉ ጉዳዮች ላይ በማተኮር ምርምሮችን ያካሒዳል።

ምንም እንኳን የኢንሼቲቩ ድክመት እና ግብጽ ወደ ቀድሞ አባልነቷ መመለሰ አለመቻሏ ለኢትዮጵያ ትልቅ ተግዳሮት ሆኖ ቢቆይም የታላቁ ሕዳሴ ግድብን ግንባታ ከመጀመር ምንም ነገር ሊያቆማት ግን አልቻለም። ምንም እንኳን ኹለቱም የታችኛው ተፋሰስ አገራት የግድቡ ግንባታ እንዲቆም በተደጋጋሚ ጫና ቢያደርጉም ኢትዮጵያ ግን ጥያቄዎች ችላ ግድቡን መገንባቷን ቀጥላለች።

በተጨማሪ ግብጽ  የማገኘው የውሃ መጠን ይቀንሳል በማለት ተቃውሞዋን ብትገልፅም በፍሰት አኳያ ግድቡ ሊያመጣው የሚችለው አሉታዊ ተፅዕኖ በጥናት አልተረጋገጠም። ይሁን እንጂ፤ የዛሬ ስድስት ዓመት ባለሙያዎች ጠቅሶ አልጀዚራ እንደዘገበው ግድቡ ወደ ግብጽ  የሚፈሰውን ውሃ በ11 እስከ 19 ቢሊየን ሜትር ኪዮብ ሊቀንሰው ይችላል። ይህ ከሆነ ደግሞ የአስዋን ግድብ ኤልክትሪክ የማመንጨት ኃይል በ100 ሜጋዋት ሊቀነስው እንደሚችል በግብጽ  ሚዲያዎች በስፋት ሲወራ ይታያል። ይሁን እንጂ፤ የኢትዮጵያ መንግስት በተደጋጋሚ ባወጣው መግለጫ የግድቡ አሉታዊ ተፅዕኖ ማወቅ የሚቻለው በገለልተኛ ተቋም በሚደረገው ጥናት እንደሆነ ገልጿል።

አባይ የበረሃው ሲሳይ

ኢትዮጵያ ለብዙ ምዕተ ዓመታት ናይል በግብጽ ቁጥጥር ሥር መውደቁን ስትቃወም ቆይታለች። በንጉስ ላል ይበላ ዘመን (ላሊበላ) አባይን ለመገደብ ኢትዮጵያ ዝታ እንደነበር የታሪክ ድርሳናት ያሳያሉ። ከዚያም በ20ኛው ክፍለ ዘመን አጋማሽ ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ በሥልጣን ላይ በነበሩበት ወቅት ለግብጽ በተፃፈ ድብዳቤ ላይ ኢትዮጵያ ከጎረቤት አገራት ጋር ወንዙን ለመጋራት ዝግጁነታቸውን ተገልፆ የነበረ ሲሆን የኢትዮጵያ ተጠቃሚነት ሊረጋገጥ እንደሚገባም ሰፍሮ ነበር። ምንም እንኳን ወንዙን መጋራት የግብጽ ፍላጎት ያልነበረ ቢሆንም የቀዝቃዛው ጦርነት የፈጠረውን አጋጣሚ በመጠቀም ግብጽ ከሶቪየት ኅብረት ጋር አጋርነት በመፍጠሯ አሜሪካም ለዚህ ምላሽ ለኢትዮጵያ ጂኦሎጂያዊ ጥናት አድርጋለች። ጥናቱም የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስቴር መለስ የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ከማስጀመራቸው ቀደም ብሎ ለተደረጉ ጥናቶች እና ለቦታ መለየት ሥራዎች ግብዓት ሆኖ ነበር።

በኹለት ተራሮች መካከል ላይ ያረፈው የታላቁ ሕዳሴ ግድብ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ከአዲስ አበባ 700 ኪሎ ሜትር ርቀት በጉባ ወረዳ የሚገኝ ሲሆን 145 ሜትር ከፍታ እና 1 ነጥብ 8 ኪሎ ሜትር ርዝመት አለው። 1 ሺሕ 680 ስኩዌር ኪሎ ሜትር ላይ ያረፈው ግድቡ የሚይዘው የውሃ መጠን 74 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር ይሆናል። ግድቡ ሲጠናቀቅ ከሚያመነጨው የኤሌክትሪክ ኀይል  በተጨማሪ 500 ሺሕ ሔክታር በላይ መሬት በመስኖ ማልማት ከማስቻሉም በላይ ከ10 ቶን በላይ ዓሣን ማምረት ያስችላል። ከ40 በላይ ደሴቶች ይኖሩታል ተብሎ የሚጠበቀው ግድቡ የውሃ ላይ ትራንስፖርት እና የተለያዩ የቱሪዝም አገልግሎቶች ይሰጣል ተብሎ ይጠበቃል።  እነዚህን ቀልብ የሚስቡ ቁጥሮች ግድቡን በብዙዎች ዘንድ ተጠባቂ ቢያደርጉትም እንደታሰበው በጊዜው ለማጠናቀቅ አልተቻለም። በአሁኑ ወቅት የግድቡ አጠቃላይ አፈፃፀም 68 በመቶ የደረሰ ሲሆን ከሲቪል ሥራዎቹ በስተቀር ሌሎች ግንባታዎች በጣም ዘግይተዋል።

የግድቡ ግንባታ ከጀመረ በኋላ በአራት ዓመት ውስጥ ኹለት ጄኔሬተሮች በመትከል ኀይል ለማመንጨት ታቅዶ የነበረ ቢሆንም  ከስምንት ዓመታት በኋላ ይህንን ማድረግ አልተቻለም። ለዚህም እንደ ዋነኛ ምክንያት ተደርጎ በመንግሥት የሚነሱ ኹለት ምክንያቶች ናቸው።

የግድቡ ግንባታን ለማፋጠን በመጀመሪያ በትይዩ የጥናት ዲዛይን እየተሠራለት የቅድመ ኮንስትራክሽን ሥራዎችን ለማካሔድ ታስቦ የነበረ ቢሆንም ወንዙ በሚሔድበት ቦይ ላይ ልል የሆነ ድንጋይና

ጥልቀት ያለው የልል ድንጋይ ሸለቆ በማጋጠሙ ምክንያት ግንባታውን ለሦስት ዓመታት አዘግይቷል።

ኹለተኛው ለግድቡ መዘግየት ዋነኛ ምክንያት የሆነው የብረታብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን (ሜቴክ) ሲሆን

ኮርፖሬሽኑ ሥራውን በተያለት ወቅትና የጥራት ደረጃ ማጠናቀቅ ባለመቻሉ ከ2009 በኋላ ላጋጠመው መዘግየት

ከፍተኛ አስተዋጽዖ እንዳደረገ መረጃዎች ያሳያሉ። ይህ ሜቴክ የሠራቸው የግንባታ ሥራዎች አብዛኞቹ የክህሎትና

የልምድ ችግር የነበረበት ከመሆኑ ጋር ተዳምሮ አገሪቷን ለተጨማሪ ወጪ የዳረገ ሲሆን በተፈጠረው ስህተት የተነሳ የተበላሹ ሥራዎችን ዳግም ለማከናወን ተጨማሪ ጊዜ ሊጠይቅ ችሏል።

በተጨማሪ ግድቡ በተለያዩ ችግሮች ውስጥ ተዘፍቆ ቆየቶ የነበረ ቢሆንም መረጃው ለዓመታት መደብቁ እና የሜቴክ ሥራዎች መዘግየትን አስመልክቶ ሲወጡ የነበሩ አሉታዊ መረጃዎች በኅብረተሰቡ ዘንድ ጥርጣሬ እንዲፈጠር እና የሕዝብ ድጋፍ እንዲቀንስ ምክንያት ሆኗል። ለአብነትም የሕዳሴ ግድብ ቦንድ ሽያጭ ኹለት ዕጥፍ ቅናሽ በባለፈው በጀት ዓመት አሳይቶ አንድ ቢሊዮን ብር ደርሷል።

ይሁን እንጂ ጠቅላይ ሚኒስቴር ዐቢይ  ወደ ሥልጣን ከወጡ ጥቂት ወራት በኋላ ለሜቴክ ተሰጥተው የነበሩ የግንባታ ሥራዎች እንደ ንዑስ ኮንትራክተርነት ሆነው ሲሠሩ ለነበሩ ኮንትራክተሮች የተላለፈ ሲሆን ከፈረንሳይ፣ ጀርመንና ሌሎች በዓለም ላይ ከታወቁ ከአምስት ኮንትራክተሮች ጋር ሰባት ኮንትራቶች ተፈርመው ወደ ሥራ ተገብቷል። ይህንንም ተከትሎ የግድቡ ግንባታ ከ2010 እስከ 2011 አጋማሽ ከፍተኛ መዘግየት የነበረ ቢሆንም በቅርቡ ግንባታው በፍጥነት ለማካሄድ የተለያዩ ጥረቶች እየተደረጉ ነው። የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኀይል  በባለፈው ወር አጋማሽ ያወጣው ሪፖርት እንደሚያመለክተው በኤሌክትሮ ሜካኒካል ሥራዎች መዘግዬት የተነሳ ተቀዛቅዞ የቆዬው የዋናው ግድብ የኮንክሪት ሙሌት ግንባታ የተጀመረ ሲሆን የኀይል  ማመንጫ፣ የስዊች ያርድ፣ የጎርፍ ማስተንፈሻ እና የኮርቻ ቅርፅ ግድብ የሲቪል

ሥራዎች በሙሉ አቅም እየተከናወኑ ነው። ኮርቻ ቅርፅ ግድቡ ግንባታ 96 በመቶ፣  የጎርፍ ማስተንፈሻ 96 በመቶ፣ የኀይል  ማመንጫ ክፍል 70 በመቶ እንዲሁም የዋናው ግድብ የኮንክሪት ሙሌት 80 በመቶ የግንባታ አፈፃፀም አሳይቷል።

ነገር ግን ምንም እንኳን የተለያዩ ማስተካከያ እርምጃዎች ቢወሰዱም የጠቅላይ ሚኒስቴር ዐቢይ  አሕመድ መንግሥት ከትችት ሊያመልጥ አልቻለም።

የመጀመሪያው እና የብዙዎች ትኩረትን የሳበው የግድቡ የማመንጨት አቅም እንዲቀነስ የተላለፈው ወሳኔ አንዱ ነው። በተለያዩ የሚዲያ አውታሮች ከነሐሴ አንስቶ ስለ ውሳኔው ቢወራም ኢትዮጵያ ኤልክትሪክ ኀይልም ሆነ የግድቡ ግንባታ ሥራ ኀላፊዎች ሐሰት ነው በማለት ሲሞግቱ ቆይተው ነበር። ማስተባበያው ብዙም ሊቆይ አልቻለም።

የመሰኖ እና ኢነርጂ ሚኒስቴር የሆኑት ስለሺ በቀለ (ዶ/ር) ምንም እንኳን ስለመቀነሱ በተለያዩ ጊዜያት ሲጠየቁ ሐሰት ነው ብለው የነበረ ቢሆንም የግድቡ የማመንጨት ኀይል  ከ6 ሺሕ 500 ሜጋ ዋት ወደ 5 ሺሕ 150 ሜጋ ዋት እንዲቀነስ መደረጉን አምነዋል። ታዲያ ይህንን የተመለከቱ ባለሙያዎች ይህ ዓይነቱ ውሳኔ የኢትዮጵያ ጥቅም የሚነካ ነው ቢሉም መንግሥት በበኩሉ የአንድ የውኃ ኀይል  ማመንጫ ግድብ የማመንጨት አቅም የሚወሰነው ግድቡ በሚይዘው የውሃ መጠን እና ውሃው ከተርባይን ማዕከል በሚኖረው ከፍታ ላይ መሆኑን በመጥቀስ የተርባይኖች ቁጥር እንዲቀንስ መወሰኑ ምንም ዓይነት ለውጥ እንደማያመጣ ሞግተዋል።

በተጨማሪ አዲስ ማለዳ ያነጋገረቻቸው አንድ ሥማቸው እንዳይጠቀስ የሚፈልጉ ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣን እንደገለፁት የግድቡ የማመንጨት አቅም መቀነሱ በአንድ ወቅት ከፍተኛ መጠን ያለው ኤሌክትሪክ ከማመንጨት ይልቅ ዓመቱን በሙሉ ያለማቋረጥ እንዲያመነጭ እንደሚያደርገው ገልፀዋል። አዲስ ማለዳ ባደረገችው ተጨማሪ ማጣራት ከዚህ ቀደም የግድቡ የማመንጨት መጠን ከ5250 ሜጋዋት ኹለቴ በተደረገ ማስተካከያ ወደ 6450 ሜጋዋት እንዲያድግ በተደረገበት ወቅት የቴክኒክ ኮሚቴ አባላት እና ተደራዳሪ ባለሙያዎች ተቃውመው የነበረ ሲሆን የመጠኑ መጨመር በሳይንሳዊ አገላለፅ ከቤዝ ሎድ ፓወር ፕላንት (ዓመቱን ሙሉ የማያቋርጥ ኀይል  ከሚያቀርብ የኀይል  ጣቢያ) ወደ ፒክ ሎድ ፓወር ፕላንት (በዓመት አንዴ ከፍተኛ ፍሰት ሲኖር ፍላጎት መሰረት አድርጎ ኀይል  ወደ የሚያቀርብ የኀይል  ጣቢያ) የተደረገ ሽግግር ነበር። አንድ ጉዳዩን በቅርብ የሚከታተሉና መንግሥት እያደረገ ባለው ውይይት ላይ የተሳተፉ ባለሙያ እንደገለጹት ጠቅላይ ሚኒስቴር ዐቢይ የግድቡ የማመንጨት መጠን እንዲቀንስ በመፍቀዳቸው ሊመሰገኑ እንደሚገባ እና በግድቡ ዙሪያ በመውሰድ ላይ ካሉት አዎንታዊ የማስተካከያ እርምጃዎች መካከል የሚጠቀስ ነው።

የጂኦፖለቲካል ጉዳዮች ተንታኝ የሆኑት ያየሰው ሽመልስ በዚህ ሐሳብ አይስማሙም። እንደ እርሳቸው አገላለፅ የተርባይኖች መጠንና የግድቡ የማመንጨት አቅም እንዲቀንስ እንዲሁም የግድቡ ውሃ ሙሌት እንዲራዘም መወሰኑ የጠቅላይ ሚኒስቴር ዐቢይ አስተዳደር ግብጽ ለዓመታት ስታነሳ የነበረቻቸው ጥያቄዎች በቀላሉ ይሁንታ እየሰጠ መሆኑን ማሳያ ነው ይላሉ።

በተጨማሪም አሜሪካ እና ዓለም ባንክ ሱዳን፣ ኢትዮጵያ እና ግብጽ በግድቡ ዙሪያ በሚያደርጉት ውይይት ላይ መግባታቸው የአገሪቷ የመደራደር አቅም ማሽቆልቆሉን ማሳያ ነው ይላሉ ያየሰው። ነገር ግን በውሃ ፖለቲካ ከፍተኛ ልምድ ያካበቱት ያዕቆብ አርሳኖ (ዶ/ር) ኢትዮጵያ ሦስተኛ ወገን በተገኘበት በግድቡ ዙሪያ የፖለቲካ ውይይት እንዲደረግ መፍቀዷ ስህተት አይደለም ይላሉ። ውይይት ምንጊዜም ቢሆን ሦስተኛ ወገን በተገኘበት መደረጉ ምንም አይነት ተፅዕኖ አያመጣም ያሉት ያዕቆብ ድርድሩ ላይ ሦስተኛ ወገን እንዳይገባ ያላትን አቋም ኢትዮጵያ እስካልቀየረች ድረስ ችግር የለውም ብለዋል።

ስለ ጉዳዩ ለውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ነቢያት ጌታቸው አዲስ ማለዳ ጥያቄ ያቀረበች ሲሆን ድርድሩ ላይ ሦስተኛ ወገን እንደማይገባ ማረጋገጫ ሰጥተዋል። በሚቀጥለው ሳምንት በዋሽንግተን አሜሪካ በኢትዮጵያ፣ ሱዳን እና ግብጽ  የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች መካከል ውይይት እንደሚደረግ የገለፁት ነቢያት ይህም በቴክኒክ ኮሚቴውም ሆነ በሦስቱ አገራት ከፍተኛ አመራሮች መካከል የሚደረገው ድርድር ላይ ተፅዕኖ እንደማያሳድር ተናግረዋል። ጠቅላይ ሚኒስቴር ዐብይ አሕመድ ግብጽ  የቴክኒክ ድርድሩ ላይ ያላት እምነት እንዲያድግ አድርገዋል ብለዋል፤ ነቢያት።

በቅርቡ ያገረሸው በግድቡ ዙሪያ ያለው አለመግባባት

የሕዳሴ ግድብ ከጀመረበት ዕለት አንስቶ ትልቁ የግብጽ  ፍራቻ ኢትዮጵያ ውሃ ሙሌት ከጀመረች የሚፈሰው የውሃ መጠን እንዳይቀንስ ማድረግ ነው። በተለይም ለአገሪቷ ደኅንነት ቅርብ የሆኑት የግብጽ  ሚዲያዎች ግድቡ ትልቅ ስጋት እንደሆነ በመግለፅ የሚያወጡት ዘገባ ግብፃውያን ስለ ግድቡ እና ስለ ኢትዮጵያ የልማት ግቦች ያላቸው አመለካከት የተነሽዋረረ እንዲሆን አድርጎታል። የግብጽ ፕሬዝደንት የሆኑት አልሲሲም ቢሆን ይህንን ክፍተት ሲጠቀሙበት ይስተዋላል። ወደ ሥልጣን ከመጡበት ጊዜ አንስቶ በቅርቡ እስከተነሳው የሕዝብ አመፅ እና ተቃውሞ ለማብረድ ግድቡን ለመቀስቀስ እና የአገራቸውን ፖለቲከ ለማረጋጋት ሲጠቀሙበት ይስተዋላል። ምንም እንኳን ከዚህ በኋላ የግድቡን ግንባታ ማስቆም የማይቻል ነገር ቢሆንም እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ2015 አገራቸው ከሱዳን እና ኢትዮጵያ ጋር የተፈራረሙት የስምምነት መርህ መግለጫ ተፈፃሚ እንዲሆን ሲወተውቱ ይስተዋላል።

በስምምነቱ መሰረት ግድቡ ጉልህ ተፅዕኖ እንደማያሳድር ኢትዮጵያ ቃል ብትገባም በግብጽ በኩል ያለው ፍላጎት በየጊዜው ሲለዋወጥ ተስተውሏል። ከዚህ ቀደም በግብጽ ዲፕሎማት የነበሩት ግርማ ይህንን ከተገነዘቡት መካከል ናቸው። “ምንም እንኳን ኢትዮጵያ ፍትሐዊ ጥቅም ታገኝ ዘንድ በሦስቱ አገራት ስምምነት መሰረት በውሃ ሙሌት እና አለቃቀቅን በተመለከተ ያሉ አለመግባባቶችን ለመፍታት በገልለተኛው ቴክኒክ ኮሚቴ እንዲፈታ ብትፈልግም በግብጽ  በኩል ችግሮቹን በፖለቲካ ዐይን የማየት ችግር አለ” ይላሉ ግርማ። የግድቡ ግንባታ በተፈጥሯዊ እንዲሁም ሌሎች ሊያመጣቸው የሚችለውን ጉዳት ለማጥናት ከሦስቱም አገሮች ኮሚቴ ተቋቁሞ ከዚያም ቢ.አር.ኤል እና አርቴሊያ የተባሉ ኹለት የፈረንሳይ ኩባንያዎች የማጣራት ሥራ ተሰጥቷቸዋል።

ይሁን እንጂ በአገራቱ መካከል ያለው ልዩነት ባለመፈታቱ እና ጥናቱን እንዲከታተል የተቋቋመው የሦስትዮሹ የብሔራዊ የቴክኒክ ኮሚቴ እንቅስቃሴ ድክመት ጥናቱ እንደታሰበው የዛሬ ሦስት ዓመት በፊት እንዳይጠናቀቅ እንቅፋት ሆኗል። በቅርቡ የቴክኒክ ኮሚቴ አባላት ከሦስቱም አገራት የውሃ ሚኒስትሮች ጋር ያደረጉት ውይይት ፍሬ ሊያፈራ አልቻለም። ታዲያ በዚህ መሃል ነበር ግብጽ ያልተጠበቀ ምክረ ሐሳብ  ይዛ የቀረበችው። በምክረ ሐሳብ  ላይ የግድቡ የውሃ ሙሌት በሰባት ዓመት ውስጥ እንዲጠናቀቅ ግብጽ  የጠየቀች ሲሆን ኢትዮጵያ በየዓመቱ 40 ቢሊዮን ሜትር ኪዮቢክ ውሃ እንድትለቅላት ጥያቄ አቅርባለች። ከዚህ ቀደም ከነበሩ ምክረ ሐሳቦቿ ይህንን ለየት የሚያደረገው ነገር ቢኖር ግብጽ  የግድቡን የዕለት ተዕለት ሥራዎችን ለመቆጣጠር ጥያቄ ማቅረቧ ነበር። ኢትዮጵያ መልስ ለመስጠት ብዙ ጊዜ አልፈጀባትም።

የውሃ፣ መስኖ እና ኢነርጅ ሚኒስትሩ ስለሺ በቀለ (ዶ/ር) መስከረም 7/2012 መግለጫ በሰጡበት ወቅት በግብጽ  የቀረበው ምክረ ሐሳብ ቀደም ሲል በሦስቱ አገራት መካከል የተፈረመውን የአባይ ውሃ አጠቃቀም የመርህ ስምምነት የጣሰ ነው ብለው የነበረ ሲሆን ኢትዮጵያን አላስፈላጊ እና ጎጂ ግዴታ ላይ ይጥላል ሲሉ ስጋታቸው ገልፀው ነበር። በተጨማሪ ግብጽ  የግድቡ ዓመታዊ  የውሃ ፍስት 40 ቢሊዮን እንዲሆን ያቀረበችው ጥያቄ፤ ኢትዮጵያ የአባይ ውሃን እንዳትጠቀም የሚከለክል ነው ሲሉ ስጋታቸው አጋርተው ነበር።

የተደራዳሪ ቡድኑ አባል እና የሚኒስትሩ አማካሪ ኢንጂነር ጌድዮን አስፋውም በበኩላቸው ኢትዮጵያ በዓመት ልትለቅ የምትችለው ውሃ መጠን ከ29 አስከ 35 ቢሊዮን ሜትር ኪዩብ ብቻ ነው በማለት በዓመት 40 ቢሊዮን ሜትር ኪዩብ ውሃ የመልቀቅ ግዴታ ውስጥ ብትገባ፤ የአየር መለዋወጥን ተከትሎ በሚከሰት ድርቅ የገባችውን ውል መፈፀም ስለማትችል፤ ሐሳቡን ወድቅ መድረጉን ደግፈው ነበር።

መፍትሔ  ሐሳብ

በአሁን ወቅት በመላው ኢትዮጵያ ያለው አለመረጋጋት ግብጽን ከጠቀሟት ነገሮች አንዱ ነው። በተለይም ኢትዮጵያ በውስጣዊ ጉዳዮች ተጠምዳ ግድቡን ለመጠቀም የምታደርገው እንቅስቃሴ እንዲቆም ወይም እንዲቋረጥ ግብጽ ያላሰለሰ ጥረት ስታደርግ ቆይታለች። የኹለቱ አገራትን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት በተመለከተ ጥናት በማድረግ መጽሐፍ የጻፉት ግርማ ይህንን በቅርበት ተከታትለው ከተረዱት መካከል ናቸው።

ምንም እንኳን ግድቡ የኢትዮጵያ ሕዝቦች የአንድነት ማዕከል መሆን ቢገባውም በአገር ውስጥ ያለው ግጭት መቆም አለመቻሉ ግብጽ  በዲፕሎማሲው መስክ ይበልጥ ተሰሚ እንድትሆን እና የኢትዮጵያ መንግሥት ደግሞ በአገር ውስጥ ጉዳይ እንዲጠመድ ምክንያት ሆኗል ሲሉ ግርማ ስጋታቸውን ይገልፃሉ። ስለዚህም ሕዝቡን በማነሳሳት አኳያ መንግሥት ሊሠራ ይገባል ሲሉ ምክራቸውን ለግሰዋል።

የፖለቲካ ምሁር የሆኑት ዲማ ነገዎ (ዶ/ር) በበኩላቸው የአገሪቱ የፖለቲካ ልኂቆች በሌሎች ጉዳዮች ላይ ያላቸው ልዩነት እንደተጠበቀ ሆኖ ታላቁ የሕዳሴ ግድብ አገራዊ ፕሮጀክት እንደመሆኑ መጠን አስፈላጊነቱ ላይ ሊለያዩ የሚችሉበት በቂ ምክንያት ሊኖራቸው አይችልም። ይህንን ማድረግ አለመቻል ግን ለውጭ ተፅዕኖ ሊያጋልጥ እንደሚችል እና የግብጽ ንም ጫና ለመቋቋም አዳጋች እንደሚሆን ስጋታቸው ለአዲስ ማለዳ አጋርተዋል።

የጂኦፖለቲካል ጉዳዮች ተንታኙ ያየሰው ግን ችግሩ አመራር ላይ ነው ሲሉ ያነሳሉ። በተለይም ጠቅላይ ሚኒስቴር ዐብይ ወደ ሥልጣን ከመጡ በኋላ ከቴክኒክ ቡድኑ ጋር የነበረው ግንኙነት መላላቱ እና የተናጠል ውሳኔ መብዛቱ ኢትዮጵያ አደጋ ላይ ሊከታት እንደሚችል ተናግረዋል። ይህንንም ከግምት ውስጥ በማስገባት መንግሥት ባለሙያዎችን ማድመጥ ይኖርበታል ያሉት ያየሰው ከሱዳን፣ ግብጽ  እና ኢትዮጰያ ውጪ ሦስተኛ ወገን በግድቡ ዙሪያ በሚደረጉ ውይይቶች ላይ እንዲኖር መደረግ የለበትም ሲሉ ሞግተዋል።

 

ቅጽ 1 ቁጥር 52 ጥቅምት 22 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here