ለምን ጸጉረ ልውጥ?

0
1324

“ሲቄ” የሚለው የኦሮምኛ ቃል ‹አለንጋ› የሚል ትርጉም አለው። በገዳ ትውፊታዊ አስተዳደር ውስጥ በባሏ ጥቃት የደረሰባት ሚስት፣ ከሌሎች ሴቶች ጋር በመሆን ባሏ ላይ የካሣ ውሳኔ የምታሳልፍበት ስርዓት ሲቄ ይባላል።

በአዲስ ማለዳ በጥቅምት 19 ቀን 2015 ላይ በወጣው 208ኛ ዕትም የሲቄ አምድ ላይ ‹ፀጉረ ልውጥ› የሚል ርዕስ ያለው አንድ ጽሑፍ አንብቤ ነበር። በተለያየ ምክንያት በቶሎ አስተያየቴን ለመስጠት አልቻልኩም ነበር። ነገር ግን ‹ከመቅረት መዘግየት› ብዬ በጉዳዩ ላይ ያለኝን ምልከታ ላካፍል ወደድኩ።

ጽሑፉ መነሻው የውጭ ምንዛሬ ክልከላ ከተደረገባቸው የውጪ ምርቶች መካከል የሆኑ የሴቶች መዋቢያዎቻ ጋር የተገናኘ ነው። የጽሑፉ አዘጋጅ ደስታ ሽርካ (ደስታ ጠማኙ)፣ ከውጪ የሚመጡ መዋቢያዎች እገዳ የተጣለባቸው መሆኑ ሴቶች ‹አርቴፊሻል› መጠቀም ትተው ወደ‹ራሳቸው› እንዲመለሱ ያደርጋል የሚል ነው። ቢያንስ እኔ የተረዳሁት በዛ መንገድ ነው።

በጽሑፉ ላይ አንዳንድ መላምትና ሴቶችን በአንድነት የሚጠቀልሉ የሚመስሉ ነጥቦችን ተቀምጠዋል። ለምሳሌ ‹አብዛኞቹ ሴቶች በሚባል መልኩ እነዚህን መዋቢያና ማጌጫዎች ይጠቀማሉ። ለተለያዩ ዝግጅቶችም ያለእነዚህ መዋቢያዎች እንቅስቃሴ የማያደርጉ ሴቶችም በርካታ ናቸው።› የሚሉ ገለጻዎች አሉ። እነዚህ ትክክል ሆነው አልተሰሙኝም። እነዚህን ገለጻዎች ለመጠቀምም ጥናቶች አስፈላጊ መሆናቸውን አምናለሁ።

ጸሐፊው አያይዘው፤ ‹‹እገዳው ስጋት ውስጥ መክተቱ አሳዛኙ ነገር ቢሆንም፣ አገር ውስጥ የሚመረቱትን መዋቢያዎች እንዲሁም የራስን የተፈጥሮ ፀጉር የመጠቀም እድልንም ይዞ መጥቷል። ይህንንም መልካም አጋጣሚ በሚገባ መጠቀም ያስፈልጋል።›› ይላሉ።

እዚህ ላይ አንድ ልንስማማ የምንችልበት ነጥብ አገር ውስጥ ለሚመረቱ መዋቢያዎች እድል ይከፍታል የሚለውን ነው። በበኩሌ የመዋቢያ ምርቶች ተጠቃሚ ባልሆንም፣ ምርቶቹ ለአገር ቤቷ እህቴ የሚሆኑ ናቸው ወይ? ጉዳቱስ ምን ያህል ነው? አጠቃቀሙን በተመለከተስ ያለው መረዳት እንዴት ነው? የሚሉ ጉዳዮች ናቸው ትኩረት ሊያገኙ የሚገባው።

በአገርኛ የቀደሙ እናቶች ውበታቸውን የሚጠብቁባቸው፣ አሁንም ከከተማ ራቅ ባሉ አካባቢዎች ያሉ እህቶቻችን የሚዋቡባቸው ብዙ መንገዶች አሉ። እነዚህን ወደዘመናዊ ማምጣትና ከቆዳችን አንጻር ሊስማማ የሚችለውን ማዘጋጀቱ ተመራጭ ነው ብዬ አምናለሁ። ንቅሳትን እንኳ ስንመለከት በአገራችን የኖረ ቢሆንም፣ ዘመናዊው ሲመጣ የነበረው ሲታፈርበትና ሲናቅ፤ ዘመነኛው ሲደነቅ ታዝበናል። እናም ነባሩን ዘመናዊ ማድረጉ ጠቃሚ ነው።

በተረፈው ግን የተለያዩ የውበት ቁሰቁሶችን የሚጠቀሙ ሴቶች እውነተኛ መልካቸው የማይታይ፣ የቅርብ ቤተሰቦቻቸው እስኪረሷቸው ድረስ የሆኑ ተደርጎ መቀመጣቸው ትክክል አይመስለኝም። ‹ጠዋት፣ ከሰዓትና ማታ መልካቸው ይቀያየራል። ተፈጥሮን በሰው ሠራሽ ተክተዋል። ዘላለማዊ መልክን በጊዜያዊ ቀይረዋል› የሚለው በጽሑፉ የተጠቀሰ ነጥብም አያስማማንም።

በአጠቃላይ አስቀድሞ እንዳልኩት፣ ለውበት ተብለው ከውጪ የሚመጡ ማናቸውንም ነገሮች የምንጠቀምበት መንገድ ላይ የውበት ጉዳይ ባለሞያዎች የሚኖራቸው አስተያየት እንዳለ ሆኖ፣ ግን በጸሐፊው የተሰጠው አስተያየት አግባብ ነው ብዬ አላምንም። ዕይታቸውንና ጉዳዩን ለውይይት ማምጣታቸውን ግን አከብራለሁ።


ቅጽ 5 ቁጥር 210 ኅዳር 3 2015

 

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here