ከሰሞኑ መነጋገሪያ ከነበሩና የብዙዎችን ትኩረት ከሳቡ አገራዊ ጉዳዮች ባሻገር፣ ለበርካታ ቀልድ በር የከፈተ የባለሥልጣን ሙገሳ አጀንዳ ሆኖ ቆይቶ ነበር። የአዲስ አበባ ከንቲባ በአንድ መድረክ የተንቆለጳጰሱበት አጋጣሚ ነው መነጋገሪያ የነበረው።
ከንቲባዋ የተሞገሱት በቃላት ድርደራና ዜማ በአንድ እውቅ ድምጻዊ መሆኑ ነው ሰውን ሊያነጋግር የበቃው። የተገናኙበት መድረክ ምን ይሁን ወይም መቼ የተከናወነ እንደሆነ አብዛኛው ኅብረተሰብ የጠየቀ ባይሆንም፣ የተዜመበትን ምስል ቀንጭቦ በማንሸራሸር ለብዙዎች ፌዝ ምክንያት ሆኗል።
የከንቲባዋ አድናቂ አንጋፋው አርቲስት ስለሺ ደምሴ (ጋሽ አበራ ሞላ) መሆናቸው ነው እንጂ፣ ብዙ ሊባል በተቻለ እያሉ ሂደቱን ሳያብጠለጥሉ እግረ መንገዳቸውን የሚያደንቁትን ሰው የተቹ በርካቶች ነበሩ።
ከግጥሙና ዜማው ማጠር አኳያ ያን ያህል ትኩረት ለምን ሳበ ለሚሉ ምላሹ የተጠቀሟቸው ቃላት እንደሆኑ የተናገሩ አሉ። ‹ስንት የአፍሪካ ኅብረት መሥራቾች እያሉ ከንቲባዋን ‹አፍሪካ ኅብረት መሠረት ሆነች› ማለታቸው አሽሙር እንዳይሆን ያሉ ቢኖሩም፣ ሌሎቹን ስንኞች ግን ለማሸሞርም ሆነ ወርቁን ለማውጣት ያስቸገራቸው ይመስላል።
አብዛኛው ሙገሳውን ያየ ሰው የሰጠው አስተያየት ተመሳሳይ መሆኑ ግርምትን ያጫረባቸው በርካቶች ናቸው። የሙገሳው አገላለጽ ያልተገባ ነው ያሉትም ‹ኮንዶሚኒየምና መሬት ለማግኘት ይሆን!› የሚል ይዘት ያለው ቀልድ አዘል ትችት ሰንዝረዋል። አንዳንዶች ይህ የሚያመለክተው ባለሥልጣናቱ የሕዝብ ሀብትን እንደፈለጉ ላደነቃቸው ሁሉ ይሰጣሉ የሚል የሕዝብ አደገኛ አመለካከት እንዳለ የሚያሳይ ነው ይላሉ።
እውነቱን የሚያውቅ ያውቀዋል እንደሚባለው፣ ባለሥልጣናቱ እንደቀደሙ ነገሥታት ዐይኑ ላማራቸው እንደፈለጉ ይሰጣሉ የሚለው ምልከታ ባይኖር ኖሮ አስተያየታቸው ምን እንደሚሆን ለመገመት ያስቸግራል። አድናቆታቸው በሥራቸው እንደሆነ የሚገልጽ ስንኝ ቢሆንም፣ ደጋፊዎቻቸው እንኳን ለመከላከል እንዳይመቻቸው ያደረገ አቀራረብ እንዳለው የጠቆሙም አሉ።
አድናቂ የነበሩት አርቲስት ታዳሚው በጭብጨባ እንዲያጅባቸው ደጋግመው የጠየቁ ቢመስልም፣ ጀምሮ ወዲያው ከሚያቋርጠው አኳያ ከልቡ አምኖበት ያስጨረሳቸው ምን ያህሉ እንደሚሆን ምስሉ ያስረዳል። በይሉኝታ ከኹለት የማይበልጥ ጭብጨባ ያሰሙት ሙገሳውን እንዲያቆሙ ለመረበሽ ይሁን እንዲቀጥሉበት ለመገፋፋት ባይለይም፣ አብዛኛው ደስተኛ እንዳልነበረ የገለጹ አሉ።
ከንቲባዋ ከመርሃ ግብሩ በኋላም ሆነ ዘግይተው ምን እንዳሏቸው የተባለ ነገር ባይኖርም፣ ለወደፊት እሳቸው በሚኖሩበት መድረክ ላይ አይገኙም የሚል መላምት ያስቀመጡ አሉ። ለጠቅላይ ሚኒስትሩም ያዘጋጁት ግጥም ይኖራል በማለት መድረክ እንዲመቻችላቸው የጠየቁም ነበሩ።
በሌላ በኩል ሙገሳውንም ሆነ ሽንገላውን ፈልገውም ይሁን ፈርተውት፣ ለወደፊት የሚቀጥሯቸው ባለሥልጣናት ይኖራሉ አይኖሩም የሚለው ለበርካቶች ሙግት መነሻ ሆኗል። የፍቅር ዜማም ይሁን እዛው ለአድናቆት ይግጠሙት እስካሁን የተባለ ነገር ባይኖርም፣ እርጅናዬን ያሸብርቀው ያሉም ቀልዳቸውን ሰንዝረዋል።
ቅጽ 5 ቁጥር 210 ኅዳር 3 2015