ችግኝን የት መትከል አለብን?

0
960

ዓለማችን የአየር ንብረት ነገር በእጅጉ የሚያሳስባት ደረጃ ላይ ደርሳለች። የደን ሀብት እየተመናመነ፣ ተፈጥሮም በብዙ እየተጎዳና ለሰው ልጅ ምቹ መኖሪያ የተባለችው ምድር በብዙ እየተጎሳቆለች መሆኑ ይስተዋላል። ኢትዮጵያ በበኩሏ ተደራራቢ ችግሮች ያሉባት ቢሆንም፣ አንድም ይህን ዓለም ዐቀፍ ችግር ታሳቢ በማድረግ ችግኞችን በመትከል የደን ልማት ላይ ከመሥራት አልቦዘነችም። ታድያ ችግኞቹ አድገው የታለመው ግብ እንዲሳካ የሚተከሉበት ቦታም ወሳኝ ነው መባሉን በማንሳት አለቃ ዮሐንስ ተከታዩን ጽሑፍ አሰናድተዋል።

የሰው ልጅ ለመኖር ከሚያስፈልጉት መሠረታዊ ፍላጎቶች መካከል ያልተበከለ አየር እና ጤናማ አካባቢ ወሳኞቹ ናቸው። የሚበላ ሁሉ ለሰውነታችን እንደማይጠቅመው፣ ጎጂውን አየርም ሆነ አካባቢን ለይተን ካላወቅን ከጥቅሙ ጉዳቱ እንደሚያመዝን እሙን ነው።

ለመኖር ከሚያስፈልጉን መካከል በቀዳሚነት የሚጠቀሰው አየር ለሰውነታችን ተስማሚ እንዲሆን ራሱ ተፈጥሮ የሚያስተካክል ቢሆንም፣ የእኛ የሰዎች አጋዥነት ከሌለው እንደተግባራችን ለውጡን መቋቋም ስለመቻላችን አጠያያቂ ነው። የሚያስፈልገንን ንጹህ እና ጤናማ አየር ለማግኘት የምንተነፍሰውን አየር ተጠቅሞ መልሶ የሚያቀርብለን ተክል በበቂ ሁኔታ ያስፈልጋል።

የደን ሽፋን ብቻ ሳይሆን በባሕር የሚኖር የአልጌ ተክል ክምችትም በቂ ኦክስጅን እንድናገኝ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ቢኖረውም፣ በሰው ልጆች ጥፋት ምክንያት የሚወድመው ከሚበቅለው ተመጣጣኝነቱ እየበለጠ የዓለማችን ሙቀት መጠንም እየጨመረ መምጣቱን ባለሙያዎች ሲናገሩ ይሰማል።

የደን መኖር የካርቦን ልቀትን ለመቆጣጠር ብቻም ሳይሆን፣ የምናገኘውን ለመጠጥ የሚውል ውሃን መጠንም ለመወሰን እንዲሁም ድርቅን ለመቀነስ እጅግ ጠቃሚ መሆኑ ይታወቃል። በተፈጥሮ የበቀሉ ዛፎችን እንዳይቆረጡ መከላከል ያላዋጣ መንገድ በመሆኑ ዘላቂ ጥቅም በሚያስገኝ መልክ እየቆረጡ በመተካት ጥቅም ላይ ለማዋልም ይሞከራል።

በምድር ወገብ ዙሪያ ያሉ በደን ሀብታቸው የታወቁ አገራት፣ ‹‹እኛም በሀብታችን መጠቀም አለብን›› በሚል አስተሳሰብ የራሳቸውን ጨፍጭፈው አጥፍተው እንደቀሩት ላለመሆን፣ ችግኝ እየተከሉ በዛውም ፍጥነት የነበራቸውን እየቀነሱ መምጣታቸው ይነገራል። የደን ሽፋኑን በሰው ሠራሽ መንገድ እንደአጠፋፉ ፍጥነት መተካት ካለመቻሉ ባሻገር፣ በተፈጥሮ ለመድኃኒትነትም ሆነ ለፍጥረታት በመላ ከፍተኛ ጥቅም ያላቸው እጽዋት ገና ሳይታወቁና በቂ ጥናት ሳይደረግባቸው እንደሚጠፉም የዘርፉ ምሁራን ይናገራሉ።

የበቀሉ ዛፎችም ሆኑ እፅዋት በምንም መልኩ አይነኩ ማለት የሚቻልበት ዘመን ላይ ባለመሆናችን አጠቃቀማችን ዘላቂ ጉዳት በማያመጣና ችግሩን በሚቀንስ መልኩ ለማድረግ ጥረት ይደረጋል። ባለፉት ጥቂት ዐስርት ዓመታት ብቻ የወደሙትን ተክሎች ለመተካት እጅግ ብዙ ተግባር ቢጠበቅም፣ አገራት በተናጥልም ሆነ በቡድን የተቻላቸውን ለውጥ ለማምጣት ሲሞክሩም ይስተዋላል።

አገራችን ኢትዮጵያም የደን መመናመን የሚያመጣውን ችግር እንደሌላው ስለተረዳች ባህርዛፍን ካስመጣችበት ጊዜ አንስቶ በስፋት ደን የማልማትን ጉዳይ ሥራዬ ብላ ይዛዋለች። በቀደሙት ዘመናት በሃይማኖት ተቋማት ዙሪያ ብቻ ተገድቦ የኖረውን ችግኝ የመትከል ልማድ እና ተግባርን፣ ለማገዶ በሚል በማስፋፋት ቀስ በቀስ ለአየር ጠባይ መቀየር የሚረዱ የደን ሽፋንን ለማሻሻል የሚያግዙትንም መትከል ተጀምሯል።

‹ደነ ልማት› በሚል መጠሪያ ከደርግ ዘመነ መንግሥት ይደረግ ከነበረው እንቅስቃሴ ጀምሮ እስከ ቅርቡ በቢሊዮን የሚቆጠር ችግኝን አፍልቶ በዘመቻ መልክም መትከል መጀመሩ የሚያስመሰግን ነው። ይህ ጅምር ግን ዘላቂነት ባለው መልኩ ካልቀጠለና ራሱን የቻለ መመሪያና ሕግ ወጥቶለት እንዲዘልቅ ካልተደረገ ብሎም በአንድ ሰው ትከሻ ላይ ብቻ ተመሥርቶ የሚደረግ ከሆነ እንደማያዛልቅ የሚናገሩ አሉ።

ዛፍ በዝቶ ጫካ እንዲሆን ብቻ ሳይሆን የተፈጥሮ ደኖች እየተስፋፉ እንዲሄዱ ማድረጉ ከማንም ዜጋ የሚጠበቅ ኃላፊነት ቢሆንም፣ ከአተካከሉ ጀምሮ መቆጣጠርና መምራት ያለበት አካልም መኖር አለበት። ችግኝን ተክል መሆኑ ብቻ በቂ ነው ብሎ አፍልቶ በየትም ቦታ መትከሉ ከመጥቀም ይልቅ ጉዳት ሊያስከትል እንደሚችልም መታሰብ ይኖርበታል።

አገር በቀል ዝርያዎችን መጠቀሙ ባህር ዛፍ ካመጣብን ተጽዕኖ እንድንላቀቅ ከማድረጉ ባሻገር፣ ለአካባቢው የሚስማማው የትኛው እንደሆነና የትኞቹ ተክሎች ለሚፈለገው ለውጥ በቶሎ ይጠቅማሉ የሚለው በጥናት ተለይቶ መቅረብ ይኖርበታል። ምንም ገቢ የማያስገኝና ምጣኔ ሀብታዊ ጥቅም የሌለውን ተክልን ከማብዛት ይልቅ፣ በቦታው መብቀል እስከቻለ ድረስ የሚበላ ፍሬን የሚያፈራም ይሁን ሌላ ግልጋሎትን በቁሙ ሊሰጥ የሚችል ዝርያን ቅድሚያ መስጠቱ እንደሚሻል ግልጽ ነው።

በባለሙያ ተለይቶ መመራት ያለበት የተክሉ ወይም የመትከያው ወቅት ብቻ ሳይሆን፣ የመትከያ ቦታውም እጅግ ወሳኙ ቁምነገር መሆኑን ባለሙያዎች ይናገራሉ። ገላጣና ድርቅ የሚያዘወትረው ቦታ ስለሆነ ብቻ ይጠቅማል ብሎ ማሰብ የተሳሳተ አመለካከት እንደሆነ ከሠሞኑ ይፋ የተደረገ ጥናት ጠቁሟል።

ይኸው ‹ኔቸር ጂኦ-ሳይንስ› ላይ የወጣ አዲስ ጥናት እንደጠቆመው፣ ችግኝ የሚተከልበት ቦታ ሲመረጥ የቦታው አቀማመጥና የንፋስ አቅጣጫው ከግምት መግባት እንዳለበት ነው። የደን መኖር የውሃ መጠንን ይጨምራል የሚባለው የደኑ ቦታና የነፋሱ አመጣጥ አስተዋጽኦ ሲኖረው ነው መባሉንም ኮስሞስ አስነብቧል።

የችግኝ ተከላ ፕሮግራሞች የነፋስ አቅጣጫንና የመትከያ ቦታ ምርጫን ከግምት ስለማያስገቡ የውሃ መጠንን ለመጨመር አስበው በተቃራኒው ድርቀትን ሊያስከትልባቸው እንደሚችል ተነግሯል። ለችግኝ ተከላ ተብሎ ውሃ ለማጠጣት በሚልም አላግባብ የሚባክን ውሃም ችግሩን እንደሚያባብሰው ዓለም ዐቀፍ አጥኚው ቡድን አሳውቋል።

እንደጥናቱ ከሆነ፣ ዛፍ ስለተተከለ ብቻ የውሃ መጠንን እንደማይጨምር ነው። እንደቦታው ሁኔታ ከነፋስ አቅጣጫ ጋር በተገናኘ የውሃ መጠኑን ሊጨምረው አልያም ይባሱኑ ሊቀንሰው እንደሚችል ነው።

ይህ ችግኝ የመትከያ ቦታን ከመምረጥ ጋር እንደሚገናኝ የተናገሩት ተመራማሪዎቹ፣ የአካባቢው የነፋስ አቅጣጫ ደኑን በሚያልፍበትና በሚርቅበት ሁኔታ ልዩነቱ እንደሚፈጠር ያብራራሉ። ይህ ሁኔታ እንደአገራቱና ንፍቀ ክበቡ የሚለያይ መሆኑንም በጥናታቸው አስቀምጠዋል።

ደን የአካባቢውን የውሃ ይዘት ከመለወጥ ባሻገር፣ ነፋስ ከተክሎቹ የሚተነውን እርጥበታማ አየር ይዞ ወደሚሄድበት አካባቢም መጠኑን ይለያየዋል። ነፋሱ የማይቆይባቸው ወይም የሚመጣባቸው ቦታዎች ከነበራቸው የውሃ መጠን ያነሰ ፍሰት ሊኖራቸው እንደሚችል ባለሙያዎቹ ጠቁመዋል።

ባለሙያዎቹ በፈረንጆቹ የዘመን አቆጣጠር ከ2001 እስከ 2018 ድረስ የተለያዩ ክፍለ ዓለም ያሉ የሳተላይት መረጃዎችን በማጥናት ከድምዳሜ መድረሳቸውን አሳውቀዋል። የደን ሽፋንን ከግምት በማስገባትና በየክፍለ አኅጉራቱ ያለውን እርጥበታማነት እና የውሃ ስርጭት በማጥናት ግኝታቸውን የደን አልሚዎችና ፖሊሲ አውጪዎች እንዲያውቁ አድርገዋል።

በዓለም ዐቀፍ ደረጃ የደን ሽፋን መጨመሩ በአማካይ የውሃ መጠኑን በዓመት በዜሮ ነጥብ 26 ሚሊሜትር እንደሚያሳድገው ታውቋል። ይህ ጭማሪ ግን በኹሉም የዓለማችን ክፍል በተመሳሳይ እንደማይሆን ልዩነቱን በማስቀመጥ አስረድተዋል።

ከዓለማችን 45 በመቶውን በሚሸፍኑት አካባቢዎች የተተከሉ ወይም የበቀሉ ዛፎች በአካባቢው እንዲሁም ነፋስ ወደሚነፍስበት አቅጣጫ ባሉ ቦታዎች የውሃ መጠንን እንደሚጨምሩ ማወቅ ችለዋል። ይህ ሁኔታ በምሥራቅ ቻይና፣ በደቡብ ምሥራቅ እስያ፣ በምሥራቃዊ የአሜሪካ ግዛቶች፣ በአውሮፓና በምሥራቅ አፍሪካ የሚታይ እውነታ መሆኑን ጠቁመዋል።

በእንዲህ ዓይነት ነፋስ የሚነሳባቸው አካባቢዎች የሚተከሉ ዛፎች የካርቦን ልቀትን ከመቆጣጠር ባለፈ፣ በአካባቢያቸውም ሆነ ነፋሱ ወደሚሄድባቸው ቦታዎች እርጥበትን በመውሰድ ድርቅን በመከላከል የውሃ መጠንን ይጨምራሉ ተብሏል።

በተቃራኒው 34 በመቶ በሚሆነው የዓለማችን አካባቢ የሚተከሉ ዛፎችም ሆኑ ያሉት ደኖች በቦታቸው የውሃ መጠኑን በማመናመን ነፋስ ወደሚወስደው ቦታ የእርጥበት መጠኑን ይጨምራሉ። ደቡብ አውስትራሊያ፣ ደቡባዊ አፍሪካ፣ መካከለኛው ምሥራቅ እንዲሁም ሰሜን ምሥራቅ አሜሪካ አካባቢ ያሉት ናቸው የአካባቢያቸውን የውሃ መጠን የሚቀንሱት ሲሉ ተመራማሪዎቹ ተናግረዋል።

በተቀረው 8 በመቶ በሚሸፍኑት የዓለማችን ክፍሎች የሚበቅሉት ደግሞ የአካባቢያቸውንም ሆነ ነፋስ የሚሄድበት አካባቢን እርጥበታማነት እንዲያሽቆለቁል የሚያደርጉ ናቸው። ኒው ጊኒ፣ የቲቤት አምባ (Plateau)፣ እና ምዕራባዊ ካናዳ የሚበቅሉ ዛፎች ከጥቅማቸው ጉዳታቸው እንደሚያመዝን ባለሙያዎቹ በጥናት ተረጋግጧል ብለዋል።

በአጠቃላይ፣ የደን ሽፋን መጨመሩ ከከባቢ አየር አንጻር የካርቦን ልቀትን በመቆጣጠር ከፍተኛ አስተዋጽኦ ቢያበረክትም፣ የዓለማችንን ንጹህ ውሃ ከማብዛት አኳያም የሚተከልበትና የሚስፋፋበት ቦታ መመረጥ እንዳለበት ነው።

ከዓለማችን መሬት ውስጥ 31 በመቶው በደን የተሸፈነ እንደሆነ የ2020 የዓለም ምግብ ድርጅት (FAO) ሪፖርት ያመላክታል። ከዚህ መጠን ውስጥ በተፈጥሮ የበቀለው ሲሶ ገደማ መሆኑ ተጠቁሟል። ከአጠቃላይ 4 ነጥብ 06 ቢሊዮን ሄክታር የደን ሽፋን ውስጥ ግማሹ ማለት በሚቻል መልኩ በአምስት አገራት ውስጥ የሚገኝ ነው። ሩሲያ፣ ብራዚል፣ ካናዳ፣ አሜሪካና ቻይና ቀዳሚዎቹ ሲሆኑ፣ ኹለት ሦስተኛው ደን የሚገኘውም በ10 አገራት ብቻ ነው። የአፍሪካዋ ኮንጎ ከአውስትራሊያ በመቀጠል 3 ነጥብ 1 በመቶውን የደን ሽፋን በመያዝ በሰባተኛ ደረጃ ተቀምጣለች።


ቅጽ 5 ቁጥር 210 ኅዳር 3 2015

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here