የውጭ ባንኮች ለኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ተስፋ ወይስ ስጋት?

0
1813

በኢትዮጵያ የግል ባንክ ለመመሥረት ኢትዮጵያዊ ዜግነት የግድ ሆኖ የተደነገገው በ1991 መሆኑን የሕግ መዛግብት ይጠቁማሉ። ከአራት ዐስርት ዓመታት በላይ ለውጭ ባንኮች ዝግ ሆኖ የቆየው የኢትዮጵያ የባንክ ዘርፍ በቅርቡ ልክ እንደቴሌኮም ዘርፉ ለውጭ ገበያ ክፍት ተደርጓል።

ይህን ተከትሎም የውጭ ባንኮች ወደ ኢትዮጵያ መግባት፣ በብዙዎች ዘንድ እንደ መልካም አጋጣሚ የታየ ሲሆን፣ ቀላል የማይባሉ ሰዎችም ዘርፉን ለውጭ ገበያ ክፍት ማድረግ ቀላል የማይባል ስጋት እንዳለው ያምናሉ።

በአገሪቱ ምጣኔ ሀብት ላይ የጎላ አዎንታዊ አስተዋጽኦ ይኖረዋል ብለው የሚናገሩ አካላት፣ የውጭ ምንዛሬ ችግርን በመፍታት በኩል የውጭ ባንኮች መግባት ዓይነተኛ ሚና አለው ነው የሚሉት። የውጭ ባንኮቹ መግባት ከፍ ያለ የቁጠባ ወለድ እንዲሁም ዝቅተኛ የብድር ወለድ ምጣኔ ለሚሹ ተጠቃሚዎች የተሻለ አማራጭ እንደሆነም ይነሳል።

ይህም የበጀት አቅርቦትን (የብድር አገልግሎትን) በማሳደግ የኢንቨስትመንት ሥራዎች ይበልጥ እንዲነቃቁ እና የአገሪቱ ምጣኔ ሀብትም እድገት እንዲኖረው ያግዛል የሚል ሐሳብም ይቀርባል። የአገር ውስጥ ባንኮችን ውድድር ውስጥ እንዲገቡ በማድረግ ከእስካሁኑ የተሻለ የባንክ ተደራሽነትና ዕድገት እንዲኖር ያስችላል የሚሉ የምጣኔ ሀብት ባለሙያዎች አሉ።

የተሻለ የሥራ ባህል ከመፍጠር እንዲሁም ከእውቀትና ከቴክኖሎጂ ሽግግር አንጻርም ቢሆን የባንኮቹ መግባት መልካም እንደሆነ ይነሳል። ይሁን እንጂ፣ የአገር ውስጥ ተቋማትን ከማዳከም እና እነሱን ከመቆጣጠር አቅም ጋር ተያይዞ የውጭ ባንኮች መግባት ለምጣኔ ሀብቱ ሥጋቱ የላቀ ነው የሚሉ አካላትም በርካታ ናቸው።

አሁን ባለው የማይክሮ ኢኮኖሚ ቀውስ የውጭ ባንኮች መግባት ያልተዋጠላቸው አካላት፣ ሊያደርሱት የሚችሉት ቀውስ ቢኖር እንኳን ሊቋቋም የሚችል ምጣኔ ሀብታዊ አቅምም ሊኖር ይገባል ይላሉ።

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የምጣኔ ሀብት መምህር አጥላው ዓለሙ (ዶ/ር) ጉዳዩን አስመልክቶ ከአዲስ ማለዳ ጋር በነበራቸው ቆይታ፣ የኢትዮጵያ መንግሥት አገሪቱን ለማሳደግ የረዥም ጊዜ ዕቅድ ቢኖረው ኖሮ፣ የራሱን ተቋማት (ባንኮች) ያሳድጋል እንጂ የውጭ ባንኮችን አያስገባም ነበር የሚል ሐሳባቸውን ሰንዝረዋል።

አንድ የረዥም ጊዜ እቅድ ይዞ አገሬን አሳድጋለሁ የሚል እና የሚቃወሙኝ ይቃወሙኝ በማለት ዋጋ ከፍሎ አገሩ በረዥም ጊዜ ማግኘት ያለባትን እንድታገኝ ወገቡን ታጥቆ የሚተጋ ራዕይ ያለው መንግሥት የአገሩን ተቋማት ነው የሚያጠናክረው ሲሉ ያነሳሉ።

ይህ ግን ትናንሽ የዶላር ምንጮችን ለማግኘት የአጭር ጊዜ ዕቅድ እንጂ የምጣኔ ሀብቱን ቀውስ ለማቃለል የተወሰደ የተጠና የረዥም ጊዜ ዕቅድ አካል አይደለም ይላሉ።

የውጭ ባንኮችን መግባት በተመለከተ በምን ዓይነት ሁኔታና አሠራር ነው የሚለው በግልጽ የታወቀ ነገር የለውም የሚሉት መምህሩ፣ አክለውም በጥቅሉ ግን አቅም ያላቸው የውጭ ባንኮች ከገቡና በፈለጋቸው ቦታ እንዲሠሩ ከተፈቀደላቸው የአገር ውስጥ ባንኮችን ይውጧቸዋል ነው ያሉት።

ይሁን እንጂ፣ አሁን አገር ውስጥ እንዳሉት ባንኮች ዝቅተኛ አቅም ያላቸው የውጭ ባንኮች ከመጡ ደግሞ ከመፎካከር ውጭ ሊያመጡት የሚችሉት ጉዳት እንደሌለ ሳይጠቅሱ አላለፉም። ‹‹ትላልቅ የውጭ ባንኮች ከገቡ ምንም ጥያቄ የለውም የእኛዎቹን ባንኮች ይውጧቸዋል›› ካሉ በኋላም፣ መዋጥ ብቻም ሳይሆን ጥለው በመጥፋት ትልቅ የምጣኔ ሀብት ሊፈጥሩ እንደሚችሉ ጠቁመዋል።

በፈረንጆች 1998 በእስያ የተነሳውን የምጣኔ ሀብት ቀውስ አንስተውም፣ ‹‹በዚህን ወቅት ትንሽ ችግር ሲያጋጥማቸው አገራቱን ጥለው ነው የወጡት። በዚህም አገራቱ የምጣኔ ሀብት ውድቀት ነው ያጋጠማቸው›› ሲሉ አውስተዋል።

እነሱ ከገንዘባቸው እንጂ አገራቸው ስላልሆነ ምንም ነገር እንደማይገዳቸው፣ ኢትዮጵያ ውስጥም የውጭ ባንኮችን በውጭ ምንዛሬ (ዶላር) ለማስተናገድ የአገሪቱ ምጣኔ ሀብት አቅም የሌለው በመሆኑ ጥለው ቢጠፉ የከፋ ቀውስ ሊፈጠር እንደሚችል ጠቅሰዋል።

ያለውን የዶላር ክምችት አንድ የውጭ ባንክ አሟጦ ቢወስደው፣ እሱን ለመተካት የአገሪቱ ምጣኔ ሀብት በጣም ደካማ ነው ይላሉ።

‹‹በሥራ ሳይሆን ከውጭ ገበያ በማስገባት የቆመ/የተቋቋመ ምጣኔ ሀብት ነው ያለን። የማምረት አቅማችን አላደገም፣ በጣም የተዛባ የወጪ ገቢ ንግድ ነው ያለው። ባንኮቹ ጥለው ቢጠፉ የሚከሰተውን ቀውስ ለማስተካከል ሊሠራ የሚችለው ግብርናው ላይ ነው።›› ሲሉ ገልጸው፣ ይህም ቀውሱን ለማስተካከል ፈታኝ እንደሚያደርገው አመላክተዋለል።

ስለሆነም፣ ቅድሚያ የአገር ውስጥ ምጣኔ ሀብትን ማሳደግ በተለይ የአምራች ዘርፉን እንዲሁም ግብርናውን ማዘመን የተሻለ እንደሚሆን ነው የጠቆሙት።

የአገሪቱን ምጣኔ ሀብት ከውጭው ጋር ተወዳዳሪ ማድረግ እንደሚያስፈልግ ከጠቀሱ በኋላም፣ ‹‹ኹሉን ነገር እያስመጣን ነው። አሁን ደግሞ የፋይናንስ ተቋማትንም እናስመጣ መባሉ ከተስፋው ይልቅ የሚያመጣው ስጋት የሚልቅ ነው።›› ሲሉ አስረድተዋል።

በመሆኑም፣ የውጭ ባንኮች ወደ አገር ውስጥ ገብተው ሥራ ሲጀመሩ የመጀመሪያው ተጽእኖ ሊሆን የሚችለው የአገር ውስጥ ባንኮች መዋጥ ነው ብለዋል።

‹‹ትልልቅ ባንኮች ከመጡ መጀመሪያ ብዙ የውጭ ምንዛሬ ይዘው ይመጣሉ። ያመጡትን ገንዘብ ደግሞ ከነትርፉ መልሰው መውሰድ ይፈልጋሉ። በዚህ ጊዜ የሚፈልጉት የውጭ ምንዛሬ ከየት ነው የሚገኘው?›› በማለትም ይጠይቃሉ።

በእርሳቸው ዕይታ፣ የውጭ ባንኮቹ በውጭ ምንዛሬ ይዘውት የመጡትን ገንዘብ በውጭ ምንዛሬ ለመውሰድ የአገሪቱ ምጣኔ ሀብት የማያስችል ከሆነ፣ ያላቸው አማራጭ ጥሎ መውጣት ነው። ስለዚህም ነው የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ የተረጋጋ አይደለም የምንለው ካሉ በኋላም፣ መንግሥት ባንኮቹን ለመቆጣጠር ስላለው አቅም አንስተዋል።

የመንግሥት የቁጥጥር አቅም በጣም ደካማ ነው ሲሉ ጠቁመው፣ እንደማሳያም ከ18 ዓመት በላይ የዘለቀውን የምጣኔ ሀብት ግሽበት መቆጣጠር እንዳልቻለ አመላክተዋል።

‹‹የትም አገር ላይ የብሔራዊ ባንክ ዓላማ ኢንቨስትመንት አይደለም። ይልቅስ የገንዘብ አቅርቦትን፣ ግሽበትን እና የውጭ ምንዛሬን መቆጣጠር ነው። ስለሆነም ግሽበትን መቆጣጠር የማይችል ብሔራዊ ባንክ ነው ያለን›› ያሉት መምህሩ፣ በዚህ አቅም የውጭ ባንኮች ሊያስከትሉት የሚችለውን ቀውስ የመከላከልና የመቆጣጠር አቅም እንደሚያንሰው ጠቁመዋል።

ባንኮች የሚከፍቱትን ቅርንጫፍ ለመገደብ መታቀዱም አዋጭ የቁጥጥር ዘዴ ማለት እንዳልሆነ ጠቅሰው፣ ዋናው ጉዳይ ባንኩ የሚኖረው የቅርንጫፍ ብዛት ሳይሆን፣ በአንዱ ቅርንጫፍ ምን ያህል ሀብት ይንቀሳቀሳል የሚለው ይመስለኛል በማለት አክለዋል።

ለአብነትም የአገሪቱ ምጣኔ ሀብት ማዕከል በሆነችው አዲስ አበባ ላይ አምስት ቅርንጫፍ መክፈት የቻለ የውጭ ባንክ ሌላ ቅርንጫፍ መክፈት አይጠበቅበትም። በእነዚህ ብቻ ሌሎች የአገር ውስጥ ባንኮችን መቆጣጠር ይችላል ባይ ናቸው።

መምህሩ በመጨረሻም ‹‹እነሱ (መንግሥት ማለታቸው ነው) የሚያስቡበትን መንገድ አላውቅም፣ እስካሁን ግን የአገሪቱ ምጣኔ ሀብት በትክክል እየተመራ እንዳልሆነ ነው የሚገባኝ›› በማለት ሐሳባቸውን ቋጭተዋል።

ከሰሞኑ ይፋ የተደረገ መረጃ እንደሚጠቁመው፣ በሚገቡ የውጭ ባንኮች ላይ ገደብ ተጥሏል። ይህን ተከትሎ መንግሥት በሚቀጥሉት አምስት ዓመታት ለተመረጡ ውስን የውጭ ባንኮች ብቻ ነው ፈቃድ የሚሰጠው።

በዚህም በሚቀጥሉት አምስት ዓመታት ከሦስት እስከ አምስት ለሚደርሱ የውጭ ባንኮች ፈቃድ ሊሰጥ እንደሚችል እና ቅርንጫፍ መክፈት ለሚፈልጉም እያንዳንዳቸው መክፈት የሚችሉት ከኹለት እስከ አራት ብቻ እንደሚሆን ነው የተጠቆመው። ነገር ግን ብሔራዊ ባንክ በልዩ ሁኔታ ጥናት አድርጎ የተጨማሪ ቅርንጫፍ ፈቃድ ሊሰጥ እንደሚችልም ተመላክቷል።

በርካታ የፋይናንስ ተቋማትና ባለሙያዎች የውጭ ባንኮች እንዴት ይግቡ በሚለው ጉዳይ ላይ ከአገር ውስጥ ባንኮች ጋር ተዋህደው እንዲሠሩ (ድርሻ ገዝተው) ይመክራሉ። ይሁን እንጂ ብሔራዊ ባንክ የአገር ውስጥ ባንኮች ስጋት ካደረባቸው መዋሃድ እንዳለባቸው ለዚሁ ማስፈጸሚያ ባዘጋጀው ረቂቅ ደንብ ጠቁሟል። የፋይናንስ ተቋማቱን ስጋት ተከትሎም ክፍተቶችን ለመሙላት እሠራለሁ ማለቱ ይታወሳል።

ከአፍሪካ እንደ ናይጄሪያ እና ደቡብ አፍሪካ ያሉ አገራትም የውጭ ባንኮችን በማስገባት የተሻለ የምጣኔ ሀብት መነቃቃት እንደፈጠሩ መረጃዎች ይጠቁማሉ። እስካሁንም የደቡብ አፍሪካ፣ የኬንያና የናይጄሪያ ባንኮች ወደ ኢትዮጵያ ገብቶ ለመሥራት ፍላጎት ማሳየታቸው ተመላክቷል።

የሥራ ዕድል

የውጭ ባንኮች ወደ አገር ውስጥ መግባታቸው ከሚያስገኘው ትሩፋት አንዱ የሥራ ዕድል መሆኑ ይታመናል። ምንም እንኳን በቁጥር አነስተኛ ሊሆኑ እንደሚችሉ ቢጠቆምም ቀላል ለማይባሉ ዜጎች አማራጭ የሥራ ዕድል ይዘው እንደሚመጡ ይጠቀሳል።

ከዚህ ባለፈ የውጭ ባንኮች ለአንድ የሥራ መደብ ተመሳሳይ የትምህርትና የሥራ ልምድ ያላቸው ኢትዮጵያውያን አለመኖራቸው ከተረጋገጠ (ብሔራዊ ባንክም ፈቃድ ሲሰጥ) የውጭ ዜግነት ያላቸው ባለሙያዎችን ቀጥረው ሊያሠሩ እንደሚችሉ ተመላክቷል። ሆኖም ባለሙያዎቹ የሚቀጠሩበትን ሁኔታ በተመለከት፣ የቅጥር ሁኔታውና የጊዜ ገደቡ በፖሊሲ የተወሰነ ነው ተብሏል።

በዚህም የውጭ ዜግነት ያላቸው ባለሙያዎች ሊቀጠሩ የሚችሉት በከፍተኛ የሥራ አመራር መደብና ለተወሰኑ ዓመታት ለማገልገል ብቻ እንደሚሆን ነው የተገለጸው።

ስለሆነም፣ አንድ ባንክ (የአገር ውስጥ ባንኮችንም ይጨምራል) ከሦስት ዓመት ላልበለጠ ጊዜ የውጭ ዜግነት ያላቸው የፋይናንስ ባለሙያዎችን በከፍተኛ የሥራ መደብ ወይም በልዩ ሙያ በኢትዮጵያ ቀጥሮ እንዲያሠራ ሊፈቀድለት ይችላል ሲል የማስፈጸሚያ የፖሊሲ ማዕቀፉ ይገልጻል።


ቅጽ 5 ቁጥር 210 ኅዳር 3 2015

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here