በሩብ ዓመቱ 960 ሚሊዮን ዶላር ከኢንቨስትመንት ገቢ መገኘቱ ተገለጸ

0
1125

በ2015 በጀት ዓመት በአንደኛ ሩብ ዓመት ከኢንቨስትመት ፍሰት 960 ሚሊዮን ዶላር ማግኘት መቻሉን የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ገለጸ።

በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የንግድና ቱሪዝም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ከኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ጋር የ2015 በጀት ዓመት አንደኛ ሩብ ዓመት ዕቅድ አፈጻጸም ሪፖርት በገመገመበት ወቅት እንደተገለጸው፣ በሩብ ዓመቱ 1 ነጥብ 35 ቢሊዮን ዶላር ከኢንቨስትመንት ፍሰት ገቢ ለማግኘት ዕቅድ ተይዞ 960 ሚሊዮን ዶላር ገቢ ማግኘት ተችሏል።

ሆኖም የተገኘው ገቢ ከባለፈው በጀት ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር የ11 በመቶ ብልጫ አለው ተብሏል።

በሦስት ወራት ውስጥ በታየው የኢንቨስትመንት ፍሰት በተለይ በነሐሴ እና በመስከረም ወራት የተሻለ ነበር ያለው ኮሚሽኑ፣ የኢንቨስትመንት ፈቃድ ካወጡ ባለሀብቶች ውስጥ 70 በመቶ ያህሉ የውጭ አገር ባለሀብቶች መሆናቸውን ጠቅሷል።

ከአገር ውስጥ ባለሀብቶች ጋር ጥምረት የፈጠሩት 21 በመቶ ድርሻ ያላቸው ሲሆን፣ የአገር ውስጥ ባለሀብቶች ቀሪ ዘጠኝ በመቶ ድርሻ እንዳላቸው ነው የተገለጸው። ከዚህ ውስጥ የቻይና እና የሕንድ ባለሀብቶች የኢንቨስትመንት ፈቃድ በመውሰድ በቅደም ተከተል ቀዳሚዎች መሆናቸውም ተመላክቷል።

ኮሚሽኑ የኢንቨስትመንት ፍሰቱን ለመሳደግ በኦስሎ፣ ቶክዮና ሴኡል የመሳሰሉ ከተሞች የአገሪቱን የኢንቨስትመንት ዕድሎች የማስተዋወቅ ሥራዎችን ሲሠራ እንደነበርም ሳይጠቅስ አላለፈም።

ኮሚሽኑ በ2014 በጀት ዓመት ከ3.2 ቢሊዮን ዶላር በላይ ገቢ መገኘቱን ገልጾ፣ በተያዘው በበጀት ዓመት ደግሞ 6 ነጥብ 15 ቢሊዮን ዶላር ከኢንቨስትመንት ፍሰት ገቢ ለማገኘት ዕቅድ መያዙን ጠቅሷል።

በሌላ በኩል በሩብ ዓመቱ ከኢንዱስትሪ ፓርኮች ምርት ወደ ውጭ ገበያ በመላክ ከሚገኝ ገቢ 34 ሚሊዮን ዶላር ማግኘቱን የገለጸ ሲሆን፣ ይህም ከተያዘው ዕቅድ አንጻር አፈጻጸሙ 44 በመቶ ብቻ መሆኑን አመላክቷል።

የተገኘው ገቢ ከባለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸርም ቅናሽ አለው ያለው ኮሚሽኑ፣ ለዚህ እንደምክንያት ከሚጠቀሱ ነገሮች አንዱ የፓርኮቹ ገበያ 90 በመቶው ወደ አሜሪካ በመሆኑ ነው ሲል አብራርተቷል።

ስለሆነም እንደቀድሞው ገዥዎች ምርት አያዙም፣ በአጎዋ ገበያ መሰረዝ የተነሳም በተለይ የገበያ መሠረታቸውን አሜሪካ ያደረጉ ኩባንያዎች መዘጋት እየጨመረ ነው ተብሏል።

የኢትዮጵያ መንግሥት ኢንዱስትሪ ፓርኮች ከውጭ ገበያ ወደ አገር ውስጥ የሚገቡ ምርቶችን ለመተካት ትኩረት ሰጥተው እንዲሠሩ አቅጣጫ ማስቀመጡም፣ ሌላው የኢንዱስትሪ ፓርኮች የውጭ ገበያ እንዲቀንስ ያደረገ ምክንያት መሆኑ ተጠቅሷል።

የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን በዘርፉ ይስተዋላሉ ብሎ ከጠቀሳቸው ችግሮች መካከል፣ የውጭ ምንዛሬ እጥረት፣ የግብዓት እጥረትና ዋጋ መጨመር፣ የኤሌክትሪክ አቅርቦት ችግር እንዲሁም የመሬት አቅርቦት አለመኖር ቀዳሚዎቹ ናቸው። በተለይም ለኢንቨስተሮች መሬት ለማግኘት ረዥም ጊዜ የሚወስድ መሆኑ እና አሠራሩም ግልጽ አለመሆኑ ትልቅ ተግዳሮት ሆኖ ተነስቷል።

ቋሚ ኮሚቴው በበኩሉ በክልሎችና በከተሞች ቀልጣፋ አሠራር ባለመኖሩና ብልሹ አሠራር በመስፋፋቱ የኢንቨስትመነት ተነሳሽነቱን እየጎዳው ነው ሲል ሐሳብ ሰንዝሯል።


ቅጽ 5 ቁጥር 210 ኅዳር 3 2015

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here