ባለፉት 20 ዓመታት የአዕምሯዊ ንብረት የምስክር ወረቀት ያገኙ የፈጠራ ሥራዎች 103 ብቻ እንደሆኑ ተነገረ

0
1313

ባለፉት 20 ዓመታት ዓለም ዐቀፍ የማጣራት ሂደትን አልፈው የአዕምሯዊ ንብረት (ፓተንት) የምስክር ወረቀት ያገኙ የቴክኖሎጂ የፈጠራ ሥራዎች 103 ብቻ መሆናቸውን የኢትዮጵያ አዕምሯዊ ንብረት ባለሥልጣን ለአዲስ ማለዳ አስታወቀ።

በ20 ዓመታት ውስጥ በባለሙያዎች ልየታ መሠረት የአዕምሯዊ ንብረት ሰርተፍኬት እንዲያገኙ ማመልከቻ ከቀረበባቸው 671 የፈጠራ ሥራዎች መካከል እስካሁን ዓለም ዐቀፍ የማጣራት ሂደቶችን ላለፉ 103 የፈጠራ ሥራዎች ብቻ የምስክር ወረቀት እንደተሰጠ የአዕምሯዊ ንብረት ባለሥልጣን የኮምዩኒኬሽን ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ታምሩ ታዬ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

እስካሁን የምስክር ወረቀቱ ካልተሰጣቸው 568 የፈጠራ ሥራዎች መካከልም ውድቅ የተደረጉ፣ የማጣራት ሂደታቸው በመካሄድ ላይ የሚገኙ እንዲሁም የማጣራት ሂደታቸው ተጠናቅቆ የምስክር ወረቀቱን ለመስጠት በሂደት ላይ የሚገኙ የፈጠራ ሥራዎች እንደሚገኙ የገለጹት ታምሩ፣ ዓለም ዐቀፍ የማጣራት ሂደቶች ጊዜ የሚወስዱ መሆናቸውንም ተናግረዋል።

በዚህ የምስክር ወረቀት የሚስተናገዱ የፈጠራ ሥራዎች በዓለም ዐቀፍ ደረጃ አዲስ መሆን የሚገባቸው ሲሆን፣ ሌሎች የፈጠራ ሥራዎችን የሚያስተናግዱና ከዚህኛው የምስክር ወረቀት በደረጃ የሚያንሱ ሌሎች ሦስት የምስክር ወረቀት ዓይነቶችም ተዘጋጅተዋል።

ከነዚህም መሀል የግልጋሎት ሞዴል በሚባለው ኹለተኛ የምስክር ወረቀት ዓይነት አዲስ ላልሆኑ ነገር ግን ማሻሻያን ላመጡ የፈጠራ ሥራዎች የምስክር ወረቀት የሚሰጥ ሲሆን፣ በዚህኛው ዘርፍም ባለፉት 20 ዓመታት ከቀረቡት ከ4 ሺሕ 148 ማመልከቻዎች ለ1 ሺሕ 76 የፈጠራ ሥራዎች የምስክር ወረቀት እንደተሰጠ ታምሩ ገልጸዋል።

የኢንዱስተሪያል ዲዛይን የምስክር ወረቀት በሚባለው ሦስተኛው ዘርፍ ደግሞ የኢንዱስትሪ ምርቶችን ለማኅበረሰቡ በማቅረብ ሂደት ውስጥ ለሚሠሩ የምርት ዲዛይን የፈጠራ ውጤቶች የሚሰጥ ሲሆን በዚህ ዘርፍም ማመልክቻ ከቀረበባቸው 3 ሺሕ 377 የፈጠራ ሥራዎች ለ975 የፈጠራ ሥራዎች የምስክር ወረቀት እንደተሰጠ ታምሩ ገልጸዋል።

በውጭ አገር የአዕምሯዊ ንብረት የምስክር ወረቀት ያገኙ ነገር ግን ወደ አገር ውስጥ ያልገቡ የፈጠራ ሥራዎች በሚስተናገዱበት አራተኛው የአስገቢ አዕምሯዊ ንብረት የምስክር ወረቀት ዘርፍም አስገቢዎች ማመልከቻ ካቀረቡባቸው 358 የፈጠራ ሥራዎች ለ253 የምስክር ወረቀት እንደተሰጠ ተነግሯል።

ባለሥልጣኑ በተጨማሪ በሚሰጣቸው የንግድ ምልክት የምስክር ወረቀት እና የቅጂ መብት የምስክር ወረቀት ደግሞ ባለፉት 20 ዓመታት ለ19 ሺሕ 266 የአገር ውስጥና የውጭ አገር የንግድ ምልክቶች እንዲሁም ለ6 ሺሕ 477 የቅጂ መብት ለጠየቁ የፈጠራ ሥራዎች የምስክር ወረቀት እንደሰጠ ታውቋል።

በአጠቃላይ የአዕምሯዊ ንብረት የምስክር ወረቀት ለማግኘት ወደ ተቋማቸው የሚመጡ ሰዎች ቁጥርም አናሳ እንደሆነ የተናገሩት ታምሩ፣ ባለሥልጣኑ የግንዛቤ ማስጨበጫዎችን ለኅብረተሰቡ በማድረስ ላይ እንደሚገኝ ገልጸው፣ የፈጠራ ሥራ ያላቸው ግለሰቦችም ሆኑ ተቋማት ሥራዎቻቸውን በማስመዝገብ የፈጠራ ባለቤትነታቸውን እንዲያስከብሩ ጥሪ አቅርበዋል።

በተሰጡ የምስክር ወረቀቶች ላይ የሚቀርቡ የይገባኛል ክሶችም በባለሥልጣኑ ውስጥ በተቋቋመው የአዕምሯዊ ንብረት ‹ትሪቡናል› የሚስተናገዱ ሲሆን፣ ይህ ትሪቡናል በሚቀርብለት ጥያቄ መሠረት የተሰጠውን የምስክር ወረቀት የማጽደቅም ሆነ የመሻር ሥልጣን እንዳለው ዳይሬክተሩ ገልጸዋል። ይሁንና ትሪቡናሉ በሚሰጠው ውሳኔ ቅር የተሰኘ አካል ወደ መደበኛ ፍርድ ቤት በመሄድ ይግባኝ ማለት እንደሚችልም አያይዘው ተናግረዋል።


ቅጽ 5 ቁጥር 210 ኅዳር 3 2015

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here